የመዲናዋን ሰላም ለማጽናት ሕዝቡ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል

አዲስ አበባ፦ የመዲናዋን ሰላምና ጸጥታ ለማጽናት ሕዝቡ እያደረገ ያለውን ያላሰለሰ ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የመዲናዋን ሰላም ማፅናት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ትናንት ውይይት አካሂዷል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ሕዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በተከናወኑ ተግባራት በከተማዋ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ተችሏል፡፡ አሁንም በመዲናዋ ሰላምና ጸጥታ ለማጽናት ሕዝቡ እያደረገ ያለውን ያላሰለሰ ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

ከሰላምና ጸጥታ ሥራው ጎን ለጎን በከተማዋ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ሕዝባዊ ውይይት መደረጉን የገለጹት ወይዘሮ ሊዲያ፤ በዚህም ከኅብረተሰቡ ጋር በተሰራው ጠንካራ የክትትልና ጥቆማ ሥራዎች በከተማዋ ያለው የወንጀል ምጣኔ አምስት በመቶ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማን ሰላምና ጸጥታ ለማድፈረስና ሕዝቡን ለማሸበር የሚጥሩ ጽንፈኛ አካላት ቢኖሩም በሕዝቡና በሰላም ሠራዊቱ ጥቆማና ክትትል እንዲሁም በጸጥታ መዋቅሩ ቅንጅት የሽብር ዓላማውን መቀልበስ ተችሏል ብለዋል።

ከሕዝብ ጋር እየተሠራ ባለው ሥራ መዲናዋን ሰላም የሰፈነባትና ለፅንፈኛ ኃይሎች የጥፋት ተልዕኮ የማትመች ማድረግ መቻሉን ገልጸው፤ ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠል አሁንም ዜጎች ከመንግሥት ጎን ሆነው ሰላምን ማፅናት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ሰላምን ለማስፈን ሕዝብን የሰላሙ ባለቤት የማድረግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን በመግለጽ፤ በከተማዋ የኮሪደር ልማትንና መሰል ፕሮጀክቶች በሰላምና ፀጥታ ችግር ሳይደናቀፉ ለማስቀጠል እየተሠራ ያለው ሰላምን የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

ኅብረተሰቡ ለከተማዋ ሰላም ዘብ በመቆም፣ደረቅ ወንጀልን በመከላከልና ጥቆማ መስጠት፣ በየአካባቢወረ የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በእርቅ ማእድ በመፍታት ለጸጥታ መዋቅሩ አጋዥ ድርሻውን መወጣት እንደሚጠበቅበት ወይዘሮ ሊዲያ ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ኤልያስ አበበ እንደገለጹት፤ እየተከናወኑ ያሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በማስቀጠል የመዲናይቱን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር በግንባር ቀደምትነት የሚተገብሩ አመራሮችና የሰላም ሠራዊቶች ተፈጥረዋል፡፡ በቀጣይም ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ አምሳሉ አራጌ በበኩላቸው፤ የማህበረሰብ ፖሊሶች በአንድ ስፍራ ላይ ረጅም ጊዜ ሲቆዩ ከመላመድ የተነሳ የሥነምግባር ብልሽት እያሳዩ እንደሆነና ወንጀሎችም ሲከሰቱ እያዩ የሚያልፉበት ሁኔታ እንደሚስተዋል በመግለጽ፤ እንደ ደንብ አስከባሪዎች በየስድስት ወሩም ቢሆን የሥራ ቦታቸው ሊቀያየር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የቢሮው የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ለኅብረተሰቡ ገለጻ ተደርጎ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ በቀጣይም በውይይቱ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በቂ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሠራበትም ተመላክቷል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You