ከውጭ የሚገባውን የእንስሳት መድኃኒት በሀገር ውስጥ ለመተካት ለአምራቾች ድጋፍ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፡– ከውጭ የሚገባውን የእንስሳት መድኃኒት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ለአምራች ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በባለስልጣኑ የእንስሳት መድኃኒት ሪጉላቶሪ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሰለሞን ከበደ (ዶ/ር) ለኢትየጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ከውጭ የሚገባውን የእንስሳት መድኃኒት በሀገር ውስጥ ለመተካት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለአምራች ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡

ባለስልጣኑ በውጭ ሀገር መድኃኒት ለሚያመርቱ አካላት የምልከታ ክፍያ ከአራት ሺህ እስከ ስድስት ሺህ ዶላር እንደሚያስከፍል ጠቁመው፤ ለሀገር ውስጥ አምራቾች ይህን ክፍያ እንደማይቀበልም አስረድተዋል፡፡

የግል ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ እንዲሰማሩ መንግሥት በለሚ ፓርክ የመሥሪያ ቦታዎችን ማመቻቸቱን ጠቁመው፤ የእንስሳት ክትባት ከዶሮ ውጪ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ በሚገኙ የእንስሳት መድኃኒት አምራቾች የሚሸፈን ሲሆን 95 በመቶ የሚሆነው የእንስሳት መድኃኒት አሁንም ከውጭ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ለሀገር ውስጥ አምራቾች ምርታቸውን በሚፈለገው ልክ እንዳያመርቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት እንቅፋት እንደሆነባቸው መሪ ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡

በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር የሚገባውን መድኃኒት ለማወቅ እንደ ሀገር ጥናት መደረጉን ጠቅሰው፤ ከጸጥታ ጋር በተገናኘ በድንበር አካባቢ የተወሰነ የመድኃኒት ዝውውር መኖሩን ማወቅ ተችሏል ብለዋል፡፡

በሀገር ውስጥ የሚሸፈነውን አምስት በመቶ የእንስሳት መድኃኒት አቅርቦት ለማሻሻል በዘርፉ ለሚሰማሩ የሀገር ውስጥ አምራቾች ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ሰለሞን (ዶ/ር) ገለጻ፤ የእንስሳት መድኃኒት አስመጪዎች ከአምራቹ በተሻለ ትርፋማ መሆናቸው አምራቾች ወደ ዘርፉ እንዳይቀላቀሉ አድርጓቸዋል፡፡

ለአምራቾች ቅድሚያ ያለመስጠት ሁኔታዎች መኖራቸው አምራቾች ውጤታማ እንዳይሆኑ እንዳደረገ ገልጸው፤ የክልል ግብርና ቢሮዎች የመድኃኒት ግዢ በሚፈጽሙ ጊዜ ለሀገር ውስጥ አምራቾች ቅድሚያ በመስጠት መደገፍ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ አምራቾች እንዲበረታቱ የሚታዩ ማነቆዎችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ አዳሚ ቱሉና ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት ከክትባት ባለፈ የእንስሳት መድኃኒት እያመረቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ኢስት አፍሪካ የመድኃኒት ፋብሪካ ወደ ማምረት እንደሚመለስ ጠቁመዋል፡፡

ባለስልጣኑ ቃሊቲ በሚገኘው መመርመሪያ ማዕከል ከውጭ የሚገቡና በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችን በመፈተሽ ወደ ገበያ እንዲገቡ እንደሚያደርግ አመላክተዋል፡፡

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You