“የኢትዮጵያ በፈተናዎች ያለመበገር ፅናት በመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራዎቿ ማሳያነት ይገለጣል” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ በፈተናዎች ያለመበገር ፅናት የምጣኔ ሀብት መረጋጋትንና ምርታማነትን ባስቀደሙት በመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራዎቿ ማሳያነት ይገለጣል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የልዑካን ቡድናቸው በኬንያ በተዘጋጀው የዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር (አይዲኤ) 21ኛ የማሟያ ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ በፈተናዎች ሁሉ የተሻገረ ያለመበገር ፅናት የምጣኔ ሀብት መረጋጋትንና ምርታማነትን ባስቀደሙት በመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራዎቿ ማሳያነት ይገለጣል ብለዋል።

በብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን በሚመራው ሥራ ምክክር እና የእርቅ ሰላም ፍላጎታችን እና ተምኔታችን ማጠንጠኛ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ትምህርትን ተደራሽ በማድረግ ብሎም ወጣቶችን በማብቃት ኢትዮጵያ ሁለት ሚሊዮን አዳዲስ ሥራዎችን ለመፍጠር ውጥን መያዟን ተናግረዋል።

አረንጓዴ አሻራን በመሰሉ ሰፊ ንቅናቄዎች እንዲሁም ከአካባቢ ጋር የተስማማ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለሁሉም በማዳረስ፣ የዲጂታል ሽግግር እና የተፈጥሮ ከባቢን የመንከባከብ ተግባራት ለመከወንም ትኩረት ሰጥታለች ሲሉ ተናግረዋል።

በመድረኩ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ለአህጉሩ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርባለች።

ጉባኤው ለአፍሪካ ልማት የገንዘብ ድጋፍና ቀዳሚ የትኩረት መስኮችን ለማመላከት እንዲሁም በጉዳዩ ላይ አፅንዖት ለመስጠት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የገንዘብ ድጋፍ አቅራቢዎች በ21ኛው የማኅበሩ ዘመን ድጋፋቸውን ለመጨመር በፅኑ እንዲያጤኑ የማሳሰብ አላማ ያነገበ መድረክ መሆኑም ተመላክቷል።

የሚቀርቡ ድጋፎች የአፍሪካን የልማት ተግዳሮቶችና መልካም እድሎች በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You