በጂኦተርማል ዘርፍ የሰው ኃይል አቅምን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፡- የጂኦተርማል ልማት የሚያስፈልገውን ቴክኖሎጂ ለማሟላት መንግሥት የአጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን በሀገርና በውጭ ሀገራት በማመቻቸት የሰው ኃይል አቅም እያሳደገ እንደሚገኝ የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ።

የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ የጂኦተርማል ልማት የሚፈልገውን ቴክኖሎጂ ለማሟላት መንግሥት የተለያዩ ስልጠናዎችን እያመቻቸ ነው።

የአካባቢ ማህበረሰብን በተለያዩ ሥራዎች በማሳተፍ ለወጣቶች ስልጠና እንዲያገኙ ድርጅቶቹ እየሠሩ ይገኛሉ ያሉት አቶ ሚሊዮን፤ የሀገር ውስጥ ልምድ ያለው ባለሙያ ባይኖር እንኳን ከውጭ ከሚመጡ ባለሙያዎች ጋር በማካተት ልምድ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ማዕድንና ጂኦተርማል ዘርፍ የምርመራና የጥልቅ ቁፋሮ ሥራ የሚከናወንበት በመሆኑ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ይፈልጋል ያሉት አቶ ሚሊዮን፤ በዚህም የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ሁኔታዎች እየተመቻቸ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ተወዳድረው ሥራውን እንዲያከናውኑ እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

አቶ ሚሊዮን አክለውም፤ ስድስት የተለያዩ ሀገራት ባለሀብቶች እንዲሁም አንድ የመንግሥት ተቋም በዘርፉ ተሰማርተዋል ያሉ ሲሆን፤ 11 የፍለጋና የማልማት ፈቃዶች በማውጣት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

እንደ አቶ ሚሊዮን ገለጻ፤ በኢትዮጵያ በተደረገ ጂኦሎጅካል ሰርቬ እስካሁን 27 የሚሆኑ ከፍተኛ ሙቀት ያላቸው የጂኦተርማል አለኝታ ቦታዎች ኤሌክትሪክ ማመንጨት ይችላሉ። ኢትዮጵያ ከዘርፉ በአጠቃላይ ከአስር ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የማመንጨት አቅም አላት።

በማዕድን ዘርፍ ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን አያይዘው የተናገሩት አቶ ሚሊዮን፤ በጂኦተርማል ዘርፍ ለ300 ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

የጂኦተርማል ዘርፍ ከፍተኛ ሀብት የሚጠይቅ በመሆኑ ሁለት የውጭ ኩባንዎች የኃይል ግዢ ስምምነትና የተግበራ ስምምነት ከመንግሥት ጋር በመፈራረም በሁለት ዙር እያንዳንዳቸው 150 ሜጋ ዋት ለማመንጨት ቁፋሮ እያከናወኑ መሆኑንም ነው አቶ ሚሊዮን ያብራሩት።

አቶ ሚሊዮን፤ በመንግሥት ኩባንያ በኩል 10 ጥልቅ የምርመራ ጉድጓዶች አጠቃላይ ጥልቀታቸው 27 ሺህ ሜትር በላይ መቆፈር የተቻለ ሲሆን ሁለት ተጨማሪ ጉድጓዶች በመቆፈር ላይ ናቸው።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You