የጨረር ሕክምናው መጀመር ሲጉላሉ ለነበሩ ታካሚዎች ዕረፍት የሚሰጥ ነው

አዲስ አበባ፦ የጨረር ሕክምናው መጀመር ሲጉላሉ ለነበሩ ታካሚዎች እረፍት እንደሚሰጥ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የካንሰር ህክምና ማዕከል አሳወቀ።

የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የካንሰር ሕክምና ማዕከል በቅርብ ቀናት የጨረር ሕክምና መስጠት ይጀምራል።

የኮሌጁ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር አለሙ ጣሚሶ (ተ/ፕሮፈሰር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ ቀድሞ እየሰጠ ከሚገኘው የካንሰር ሕክምና በተጨማሪ ዘመናዊ የጨረር ሕክምና መስጫ አስመርቆ ለማስጀመር ዝግጅቱን አጠናቋል። በዚህም ለመጀመሪያ ዙር ፈቃደኛ ሆነው በተገኙ 30 አካባቢ ታካሚዎች በመጪው ሰኞ የጨረር ሕክምና አገልግሎት መስጠት ይጀምራል።

በዳይሬክተሩ ንግግር መሠረት፤ የሀዋሳና አካባቢው ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም የጨረር ሕክምናውን ለማግኘት ጅማ ድረስ መጓዝ ይጠበቅባቸው ነበር። ሕክምናው እንደሚያስፈልጋቸው ከተረጋገጠ በኋላም እስከ አንድ ዓመት ድረስ ሲጠብቁ ቆይተዋል። የሕክምናው በከተማዋ መጀመር ይህን ድካምና መጉላላት የሚያስቆም ነው።

የጨረር ሕክምናው ለሀዋሳ ከተማ ብሎም ለደቡብ ኢትዮጵያና ለአጎራባች ታካሚዎች በሙሉ ማገልገል የሚያስችል መሆኑንም ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተሩ በንግግራቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ማሽኑ የተለያዩ የሙከራ ሂደቶችን ማለፉን ያመላከቱት ዳይሬክተሩ፤ ከጨረር ኤጀንሲና የውሃ ሙከራውን በማለፍም ለቀጣይ የሕክምና ሂደት ተዘጋጅቷል ብለዋል።

ማሽኑ በሆስፒታሉ በተያዘው በጀት ዓመት መተከሉን ያመላከቱት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተሩ፤ በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት ሳይሰጥ መክረሙን በመግለፅ አሁን ግን በሀገር ውስጥና ከደቡብ አፍሪካ በመጡ ባለሙያዎች አገልግሎት የመጀመር ሂደት ላይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ባለሙያዎችን የማሰልጠንና የማብቃት ሥራዎች ሲሠሩ መክረማቸውን የገለጹት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተሩ፤ በሕክምና አሰጣጥ ሥርዓቱ ላይም በስልጠናው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተግባራዊ የሚያደርጉበት አግባብ ስለመኖሩ አንስተዋል።

በዘርፉ ያለውን የማዕከላት ውስንነት ለመቅረፍ በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የቆየው የካንሰር ሕክምና ማዕከል በሐረር፣ ጅማ፣ ሀዋሳና ጎንደር በማዳረስ የሕክምናውን አድማስ ለማስፋት ሥራዎች መከናወናቸው ይታወቃል።

በዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You