ጽዱ አዲስ አበባ፤ ጽዱ ኢትዮጵያ

በንጽህና እና በድምጽ ብክለት ጉዳይ ላይ ስንት ጊዜ እንደጮህን የዚህ ጋዜጣ ሰነዶች ምስክር ናቸው:: በግሌ አሜሪካ ወይም አውሮፓ ሀገራት መኖር የምመኘው ፒዛና በርገር ለመብላት ወይም ፈጣን የቴክኖሎጂ አማራጮችን ለመጠቀም አይደለም:: ከዚህ በላይ የሚያጓጓኝ ንጹህ አየር መተንፈስ ነው:: የዓለም ምርጥ የአየር ንብረት ያላት ሀገር ውስጥ ሆኖ፣ ተፈጥሮ ያዳላላት የሚመስል ምቹ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሀገር ውስጥ ተቀምጦ፤ በሰው ሰራሽ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሀገራትን አየር መናፈቅ ምንኛ መረገም ይሆን?

በቅርቡ የጽዱ ኢትዮጵያ ዘመቻ ተጀምሯል:: አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ የሰሞኑ የአየር ሁኔታ ንፋስና ፀሐይ የበዛበት ነው፤ በኢትዮጵያ የአየር ሁኔታ ይህ የተለመደ የግንቦት ወር ባህሪ ነው:: ተፈጥሯዊ ክስተት ነው:: ሌላኛው አጋጣሚ በኮሪደሩ ልማት ምክንያት የግንባታ ሥራዎች ስላሉ መንገዶች አቧራ የበዛባቸው ናቸው:: ይህ ለጥቂት ጊዜ ስለሆነ በተስፋ እናልፈዋለን:: የግንቦት ወር ፀሐያማ መሆኑ ደግሞ የተፈጥሮ ፀጋ ነው::

አደገኛ የሆነው ግን ይህ ሳይሆን በሰው ሰራሽ መንገድ ያበላሸናቸው ነገሮች ናቸው:: ከተፈጥሯዊው የአየር ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ብዙ ሰዎች በተደጋጋሚ ጉንፋን እና መሰል በሽታዎች ይይዛቸዋል:: ጉንፋን ቀላሉ ነው፤ ብዙ ሰው የአስም ህመምተኛ ነው:: ይህ ሁሉ የሚሆነው በቆሻሻ በሚፈጠር መጥፎ ሽታ ነው::

አዲስ አበባ ውስጥ አፍንጫ ሳይያዝ የሚታለፉ ወንዞች የሉም:: ቱቦ ባለበት ቦታ ያለፈ ሁሉ ጉንፋን ተይዞ ወይም ከፍተኛ የራስ ምታት አጋጥሞት ነው የሚያልፈው:: ድልድዮች ባሉበት ሁሉ አጸያፊ ነገር እያዩ ማለፍ የተለመደ ነው:: በየቦታው ሽታ አለ:: በተለይ በእንዲህ አይነቱ የግንቦት ወር ከፍተኛ ነፋስና ፀሐይ ያለበት ስለሆነ ለብዙ በሽታዎች አጋላጭ ነው:: የዝናብ ወቅት ሲሆን ቢያንስ ዋና ዋናውን ዝናብ ሊያጥበው ይችላል፤ ሽታውም የከፋ አይሆንም::

ይሄ ሁሉ የሆነው እንግዲህ በግንዛቤ ማጣት ነው:: በሰው ሰራሽ መንገድ ነው እየታመምን ያለነው:: የጽዳት ባህላችን ደካማ ስለሆነ ነው:: የዕለት ከዕለት ሥራ መሆን የሚገባውን ጽዳት፣ በዘመቻ ነበር የምናጸዳው:: አሁን የተጀመረው የዘላቂ መፍትሔ ዘመቻ ይህን ችግር ሙሉ በሙሉ ባይቀርፍ እንኳን ይቀንሳል ማለት ነው:: አርዓያ ይሆናል ማለት ነው::

ብዙ ነገሮችን የምናደርገው ዓመት ጠብቀን ነው:: ለምሳሌ ዕቅድ የምናወጣው አዲስ ዓመት (መስከረም) ሲደርስ ነው:: መስከረም ካለፈ በኋላ፤ እንኳን አዲስ ዕቅድ ማውጣት የታቀደውም ይረሳል:: የበጎ አድራጎት ሥራዎችን (ለምሳሌ ህሙማንንና አቅመ ደካሞችን መርዳት) የምንሰራው እንደ እንቁጣጣሽ፣ ገና፣ ፋሲካ፣ መውሊድ ወይም አረፋ ያሉ በዓላት ሲመጡ ነው:: እነዚህ በዓላት ሲያልፉ ይረሳል::

ብዙ ነገሮችን የምናደርገው አሁንም ሁነት ጠብቀን ነው:: እስከ ዛሬ በነበረው ልማድ ከተሞች የሚጸዱት በከተማዋ ውስጥ የሆነ ዝግጅት የሚደረግ ከሆነ ነው:: ያ ዝግጅት ሲያልፍ ግን አይቀጥልም፤ እንዲያውም ይባስ ብሎ በዝግጅቱ ምክንያት የወዳደቁ ተረፈ ምርቶች የሚያቆሽሹት ይበልጣል::

በየዓመቱ ‹‹ህዳር ሲታጠን›› እየተባለ በየቦታው ቆሻሻ ይቃጠላል (ሌላ ቀን አይደረግም እንጂ)፤ ዋና ዓላማውም ቆሻሻን ማቃጠልና ጽዱ አካባቢ መፍጠር ነው::

እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች የማንቂያ ምክንያት ይሆኑናል:: ቢያንስ በእንዲህ አይነት አጋጣሚ እንኳን አስታውሰን መነቃቃት ቢፈጠር ማለት ነው:: ልቦና ቢሰጠን ደግሞ በዚያው ቢለምድብን ጥሩ ነበር፤ ግን አልሆነም:: ስለዚህ አሁን የሚሰሩት ቋሚ የሆኑ ግንባታዎች የተሻለ መነቃቃት ይፈጥራሉ ማለት ነው:: ሌሎችንም ለመሥራት ያነሳሳል::

በተሻለ ሁኔታ አዲስ አበባ ንጹህ የምትሆነው ግን በማጽዳት ብቻ ሳይሆን ባለማቆሸሽ ነው:: የከተማዋ ነዋሪ በነቂስ ወጥቶ ሁሉንም ቆሻሻ ጠራርጎና አጽድቶ ቢገባ የአስተሳሰብ ለውጥ ከሌለ በአንድ ቀን ማበላሸት ይቻላል:: በየቦታው መጸዳጃ ቤቶች ቢዘጋጁም የአዕምሮ ንቃቱ ከሌላ መጸዳጃ ቤት ላለመግባት ብሎ ብቻ መንገድ ላይ የሚሸና ሊኖር ይችላል:: የደረቅ ቆሻሻ ማስቀመጫዎች ቢዘጋጁም ህሊናው የማይሰራ ሰው ሜዳ ላይ ሊጥለው ይችላል::

የወንዝ ዳርቻዎች ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል:: በክረምት ጎርፍ ጠራርጎ ሲወስደው ወንዙ ንጹህ ይሆናል፤ ወዲያውኑ ግን ረፋድ እንኳን ሳይሆን አፍንጫ ተይዞ የሚታለፍበት ይሆናል:: በግንብ እና በአጥር ዙሪያ ያለው አፍንጫ የሚበረቅስ መጥፎ ሽታ አብሮ የተገነባ አልነበረም፤ በሰዎች ሽንት እና የቆሻሻ መጣያነት ነው እንደዚያ የሚሆነው:: ይህ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ስናየው የቆየነው ነው:: አሁንም እየተገነቡ ባልሆኑ ወንዞች አካባቢ አለ::

የሚያቆሽሸውን ያህል በዚያው መጠን ደግሞ ቶሎ ቶሎ የሚያጸዳ ቢኖር ችግሩ ይቀንሳል:: ልብ ብላችሁ ከሆነ ብዙ ጊዜ ሽንት የሚሸናው ከዚህ በፊት የተሸናበት ቦታ ላይ ነው፤ ቆሻሻ የሚጣለው ቆሽሾ የሚታይ ቦታ ላይ ነው:: የያዝነውን ሶፍት እንኳን ንጹህ ቦታ ላይ ለመጣል ይከብደናል:: ቆሻሻ ቦታ ከጠፋ ብዙ ሰው ሊጥለው ያሰበውን ነገር በኪሱ ይከተዋል፤ ቆሻሻ ያለበት ቦታ ለመጣል ማለት ነው:: እንግዲህ ከዚህ የምንረዳው ሁሉም አካባቢ ንጹህ ቢሆን ሁሉም ለንጽህና እንደሚበረታታ ነው::

የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ? ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቀረ ቢሆንም የፕላስቲክ ውሃ የታሸገበትን ወረቀት ለመጣል ዘወር ዘወር ብለው ያያሉ:: የተጣለ ካለ ሁሉም ይጥላል:: የተጣለ ከሌለ ግን ፕላስቲኩ ወገብ ላይ ካለው ሽፋን ውስጥ ያደርጉታል፤ ወይም ኪሳቸው ይከቱታል (እኔ ብዙ ቀን ኪሴ ከትቻለሁ):: መሬት ላይ በመጣል የሚጀምረው አንድ ሰው ነው ማለት ነው፤ ከዚያ በኋላ መቼም አንዴ ተጥሎበታል በሚል ሁሉም እየጣለ ወለሉ የፕላስቲክ ፋብሪካ ይመስላል:: ለምሳሌ አነሳሁት እንጂ የውሃ ፋብሪካዎች የክዳኑን መሸፈኛ አስቀርተውታል::

እነሆ ይህ በዘመቻ ብቻ የሚደረግ የጽዳት ባህላችን ለውጥ ሳያመጣ ቀርቶ በእንዲህ አይነቱ ነፋስና ፀሐይ በሚበዛበት የግንቦት ወር ጉንፋን በጉንፋን ስንሆን ቆይተናል:: በመንደሮች መካከል ባሉ የውስጥ ለውስጥ ቦዮች ሁሉ መጥፎ ሽታ አለ::

የሚያሳዝነው ግን የተማረ የሚባል ሰው ባለበት ሁሉ አስነዋሪ ነገር የሚታይ መሆኑ ነው:: ይሄ በትልልቅ የፌዴራል ተቋማት ውስጥ ሳይቀር የታዘብኩት ነው:: በእንደዚያ አይነት ተቋም ውስጥ ቢያንስ መጻፍና ማንበብ የማይችል የለም፤ በብዛት ደግሞ ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ነው:: ምንም እንኳን ጥፋቱን የሚፈጽመው ጥቂት ሰው ሊሆን ቢችልም መጸዳጃ ቤት ውስጥ የሚታየው ነገር ከላይ እስከ ታች ምን ያህል ኋላቀር እንደሆንን ያሳያል::

በቅርቡ በመንግሥት የተጀመረው የጽዱ ኢትዮጵያ ዘመቻ ከምንም በላይ የሚጠቅመው አርዓያነቱ ነው:: የሚሰሩት መጸዳጃ ቤቶች ሁሉንም ያዳርሳሉ ማለት አይደለም፤ ግን ሌሎች እንዲሰሩ ያነሳሳሉ:: መጸዳጃ ቤቶች ተሰሩ ማለት ችግሩ የመጸዳጃ ቤት ብቻ ነበር ማለት አይደለም:: አጠቃላይ የንፁህነትን መንፈስ ይፈጥራል:: የህሊና መነቃቃትንም ይፈጥራል:: በአግባቡ ካልያዝነው የተፈለገውን ውጤት አያመጣምና የጽዱ ኢትዮጵያ ግንባታዎች ሲሰሩ አስተሳሰባችንም ጽዱ ይሁን!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You