ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት በ‘ኦንላይን’ ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፡- በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት በኦንላይን መሰጠቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ታደሰ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታል በማድረግ በኩል የሀገሪቱን ንግድን ለመጀመርና ለመስራት ያለውን የአመችነት ደረጃ ለማሻሻል በከፍተኛ ትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ 2 ሚሊዮን 638 ሺህ 83 የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቶችን በኦንላይን ለመስጠት ታቅዶ አንድ ሚሊዮን 816 ሺህ 41 የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቶችን በኦንላይን መስጠት ተችሏል ብለዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን በተሠሩ ሥራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ የኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ሽፋኑን 90 በመቶ ማድረስ የተቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

በኦንላይን ከተሰጡት አገልግሎቶች ውስጥም አዲስ የንግድ ምዝገባ፣ አዲስ የንግድ ፈቃድ፣ የንግድ ፍቃድ እድሳት እና ማሻሻያ እንዲሁም የንግድ ስምና የንግድ ፈቃድ ስረዛ የመሳሱትን ጨምሮ በሚኒስቴሩ የሚሰጡ አስራ ዘጠኝ የተለያዩ አገልግሎቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የንግዱ ማህበረብ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ባለበት ቦታ ሆኖ እንዴት አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችል የግንዛቤ እና የክህሎት ስልጠና መሰጠቱን ገልጸው፤ ኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ከወረዳ ኔት ጋር የማስተሳሰር ሥራ በመሥራት ሽፋኑን ከፍ ለማድረግ አስችሏል ሲሉ ተናግረዋል።

ኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ሽፋኑን ለማሳደግ በተለይም አገልግሎቱ ባልተጀመረባቸው አካባቢዎች ላሉ የንግድ ዘርፍ አገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎች የተግባር ስልጠናዎችን በመስጠትና አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ የማብቃት ሥራም ተሠርቷል ብለዋል።

ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ የሚሰጠውን የንግድ ምዝገባ እና ፍቃድ የአገልግሎት ሥርዓትን በመተግበርና በማዘመን እየተሠራ ነው የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ ይህም ለደንበኞች የሚሰጠውን አገልግሎት በማቀላጠፍ ከአላስፈላጊ እንግልት የሚያስቀር ነው ብለዋል።

አቶ ተስፋዬ እንደሚገልጹት፤ የተደረገውን የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ተከትሎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባካሄደው የተገልጋዮች አስተያየት ጥናት የተገልጋዮች እርካታ 93 በመቶ ማድረስ መቻሉን ማረጋገጥ ተችሏል።

በዘርፉ የሚስተዋለውን ብልሹ አሠራርና ሕገ ወጥነት በማላቀቅና ሕጋዊ የአሠራር ሥርዓትና የሕግ ማእቀፍ ለመዘርጋት በትኩረት የሚሠራ መሆኑንም አቶ ተስፋዬ ጠቅሰዋል።

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You