‘ፐብሊክ ዲፕሎማሲ’ በኢትዮጵያ ላይ ሊጣሉ የነበሩ ማዕቀቦች እንዲከሽፉ አድርጓል

አዲስ አበባ፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ በተሠራ ጠንካራ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ በኢትዮጵያ ሊጣሉ የነበሩ ማዕቀቦች መክሸፋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር አብዱ ያሲን አስታወቁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር አብዱ ያሲን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 15 ጊዜ አጀንዳ ሆና ቀርባለች ያሉት አምባሳደር አብዱ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ በመሠራቱ በኢትዮጵያ ሊጣሉ የታሰቡ ማዕቀቦች ማክሸፍ ተችሏል ብለዋል።

ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ስለ ኢትዮጵያ እውነቱን እንዲያውቅ የተሰሩ የሕዝብ ለሕዝብ መድረኮች ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው አመልክተዋል።

የፐብሊክ ዲፕሎማሲውን አዎታዊ ተጽዕኖ ለማሳደግ ኢትዮጵያ ከበርካታ የዓለም አቀፍ ከተሞች ጋር የእህትማማች ስምምነት መፈረሟን ገልጸው፤ የተፈረሙ ስምምነቶችም ለሀገራዊ አንድነት፣ ለቀጣናው ትስስርና ለሁለትዮሽ ግንኙነት ማደግ እገዛ እያበረከቱ መሆኑን አስታውቀዋል።

ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስለ ሀገር ለዓለም ማሳወቅ መሆኑን በመጥቀስ፤ የተጀመሩ የከተማ ማስዋብ ሥራዎች ሲጠናቀቁ ለኢትዮጵያ የገጽታ ግንባታ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል አምባሳደር አብዱ።

የተጀመሩ ከተማን የማስዋብ ሥራዎች ሲጠናቀቁ በርካታ ቱሪስቶችን በመሳብ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያስተላልፉት መልዕክት ትልቅ መሆኑን ጠቁመ፤ ከተማዋን ለማስዋብ የሚሰሩ ሥራዎች ለፐብሊክ ዲፕሎማሲው አጋዥ መሆኑንም ተናግረዋል።

ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በአንድ ሀገር ውስጥ የሁሉም ዜጋ ሥራ ነው ያሉት አምባሳደር አብዱ፤ የተለያዩ የማህበረሰብ አባላትና ተወካዮች ሀገራቸውን በሚገባና በሚችሉት ልክ ማስተዋወቅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በትምህርት ዘርፍም ከሌሎች ሀገራት ጋር ጥሩ ትስስር እየተፈጠረ በመሆኑ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ውጤት እያመጡ ነው። አማርኛ በቻይና ዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ ነው። በቀጣይም ሌሎች ቋንቋዎችን እንዲያስተምሩ እየተመካከርን በመሆኑ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ በትልቁ የማስተዋወቅ አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

ኢትዮጵያም ለጎረቤት ሀገራት በርካታ የትምህርት እድል ሰጥታለች ያሉት አብዱ፤ በያዝነው ዓመት ለጎረቤት ሀገራት ከ850 በላይ የትምህርት እድል መስጠቷን አንስተዋል። ይህም የትምህርት ዕድል ያገኙት የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ስለኢትዮጵያ መልካም አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል።

በቀጣይ ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንዲፈጠር በማድረግ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You