“ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት ታሪክንና ዓሉታዊ ትርክትን ለይቶ መሥራት ያስፈልጋል” – ባህሩ ዘውዴ (ኢሜሬትስ ፕ/ር) የታሪክ ምሁርና ተመራማሪ

አዲስ አበባ፡- ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት ታሪክንና ዓሉታዊ የሆኑ ትርክቶችን በመለየት አስፈላጊውን ሥራ መሥራት ተገቢ ነው ሲሉ የታሪክ ምሁርና ተመራማሪው ባህሩ ዘውዴ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡

ኢሜሬትስ ፕሮፌሰር ባህሩ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅ እንደገለጹት፤ ያለፉ ታሪኮችን በተገቢው መንገድ በማጤን ከዓሉታዊ ትርክቶች ለይቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡

በታሪክ ከትናንት በመማር ዛሬን ማሻገር ተገቢ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ባህሩ፤ የታሪክ ባለሙያዎችም ትክክለኛውን ታሪክ ለሕዝቡ ከማድረስ አኳያ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የተለያዩ ልዩነት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን ከስሩ በማጥራት ለምክክር እንዲቀርቡ ማስቻል ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

እንደ ፕሮፌሰር ባህሩ ገለጻ፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ዓላማ ልዩነቶችን በመፍታት ወደ አንድ ሀገራዊ እሳቤ ማምጣት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ታሪክን በአግባቡ መገንዘብ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡

ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ‹‹ትስስርና መስተጋብር በኢትዮጵያ ታሪክ›› በሚል ርዕስ ላይ የተካሄደ የጥናት ሰነድ ለምክክር ኮሚሽኑ ማቅረቡን ጠቁመዋል፡፡

ሰነዱ የታሪክ ተመራማሪዎች የደረሱበት ድምዳሜ የሚዳስስ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ባህሩ፤ ይህም ትክክለኛውን ታሪክ ለመለየት የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ተጋንነው ከሚወሩት ውስጥ አብዛኞቹ ከእውነት የራቁ ናቸው ያሉት ኢምሬትስ ፕሮፌሰር ባህሩ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚከፋፍለው ይልቅ በአብዛኛው አንድ የሚያደርግ ታሪክ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ጋር በቅርበት እየሠራ እንደሚገኝም ነው ፕሮፌሰር ባህሩ ያስታወቁት፡፡

የምክክር ኮሚሽኑ በየጊዜው የሚያማክር አማካሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ማህበሩም የተዛቡ የታሪክ አረዳዶች ለመቀልበስ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢሚሬትስ ፕሮፌሰር ባህሩ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመፈራረጅ ይልቅ ትክክለኛውን ታሪክ መገንዘብ ይኖርበታል፡፡ እንዲሁም ከተዛባ ትርክት ሊወጣ ይገባዋል፡፡ ሀገሪቱ አሁን ላይ ላለችበት ውስብስብ ችግር መንስኤው ታሪክን በአግባቡ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You