ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ- የደኅንነት ስጋት መንስኤ

ትንታኔ

በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ በፀጥታ መዋቅሩ አማካኝነት በቁጥጥር ስር ሲውል ይስተዋላል፡፡ በየጊዜው በዘመቻም ይሁን በመደበኛ የፀጥታ ማስከበር ሥራ በሚደረጉ ፍተሻዎች ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር ዛሬም የቀጠለ ነው፡፡ ይህ ቢሆንም ግን፣ ሕገ ወጥ የመሣሪያ ዝውውር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ እንደመጣ ይነገራል፡፡ የመሳሪያ ዝውውሩ መስፋፋት ለሀገር ሰላም ብሎም ለማኅበረሰብ ደኅንነት አስጊ መሆኑ ላይ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ በተለያዩ ዘርፎች የሚገኙ ምሁራን ለሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መበራከት ምክንያቶችን ይዘረዝራሉ፤ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት መፍትሔ ያሏቸውን ጉዳዮችም ያስረዳሉ።

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት መምህሩ ዶ/ር ተመስገን ቶማስ፣ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለሀገር ሰላም ማጣት ትልቁ መንስዔ ነው ይላሉ፡፡ የጦር መሳሪያ ፍላጎት ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዲጨምር ዋነኛው ምክንያት እንደሆነም ያነሳሉ፡፡

እርሳቸው እንዳሉት፣ የአፍሪካ ቀንድ ተብሎ በሚጠራው የአህጉሪቱ ክፍል በሚገኙ ሀገራት የሚከሰቱ፣ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ያሉ ግጭቶች ለጦር መሳሪያ ፍላጎት መጨመር ምክንያት ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡

ዶክተር ተመስገን እንደሚሉት በፖለቲካም ሆነ በአካባቢያዊ አጀንዳ ነፍጥ ያነገቡ እና ጦርነትን አማራጭ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ኢ -መደበኛ አደረጃጀቶች ሁሉ የጦር መሳሪያ ፍላጎት ይኖራቸዋል፡፡ የጦር መሳሪያ ፍላጎት ሲኖር መሳሪያ ሸጦ ትርፍ ማጋበስ የሚፈልግ ይፈጠራል፡፡ የጦር መሳሪያ ፈላጊና አቅራቢ ሲገናኙ የጦር መሳሪያ ልክ እንደ ሌሎች መደበኛ የግብይት እቃዎች ሁሉ በግብይት ሥርዓት ውስጥ ይገባል፤ የጦር መሳሪያ ደግሞ፣ የፈለገ አካል ሁሉ የግሉ ሊያደርገው የሚገባ አይደለም፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ የጦር መሣሪያ ፈላጊ፣ ደላላና አቅራቢ ሰንሰለትን መበጠስ ያስፈልጋልም የሚሉት ዶክተር ተመስገን፤ ለዚህም ጠንካራ መዋቅራዊ ሥርዓት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ይህ ልውውጥ ከየት መስመር ነው የሚመጣው የሚለውን የግንባር ላይ ቁጥጥር ማጠናከር እና በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያስችላቸውን ተቋማዊ ጥንካሬ መፍጠር ይገባል። ሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር ላይ በሚሳተፉ አካላትም ላይ እንዲሁ ጠንከር ያለና አስተማሪ እርምጃ መውሰድም ያስፈልጋል፡፡

ዶክተር ተመስገን ከጠቀሷቸው መፍትሔዎች በተጨማሪ በሀገር ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ የመሳሪያ ፍላጎት እንዲቀንስ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ያስረዳሉ፡፡ እንደ እርሳቸው ሃሳብ፣ ፖለቲካዊ ለሆኑ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ እየተሰጣቸው ሲሄዱ ግለሰቦችና ቡድኖች ለመሳሪያ ያላቸው ፍላጎት እየቀነሰ ይሄዳል፤ በተመሳሳይም ሁከት፣ ጽንፈኝነት፣ ግጭቶች እየቀነሱ ይሄዳሉ፡፡

ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ፍላጎት እርስ በእርስ የሚታኮስ ቡድን ስላለ ብቻ የሚጨምር አይደለም ያሉት ዶ/ር ተመስገን፤ ዜጎች የደህንነት ስጋት ሲሰማቸውም ጭምር ራሳቸውን ለመጠበቅ ህጋዊ ባልሆነ መልኩ መሳሪያን መታጠቅ ምርጫቸው ያደርጋሉ ብለዋል፡፡ መንግሥት ዜጎች የሚተማመኑበት የሕዝብን ደህንነት መጠበቅ የሚችል ከሆነ የግለሰቦች መሳሪያን የመታጠቅ ፍላጎትን በከፍተኛ መጠን መቀነስ እንደሚያስችለው ገልጸዋል፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶ/ር ደጉ አስረስ በበኩላቸው እንደሚሉት፣ አንድ መንግሥት ሲቋቋም ከሌሎች አደረጃጀቶች ለየት የሚያደርገው መሳሪያን በቁጥጥሩ ስር ማዋል መቻሉ ነው፡፡ የመሳሪያ ዝውውር፣ ትጥቅ እና መሳሪያን ጥቅም ላይ የማዋል ተግባር በመንግሥት ቁጥጥር ስር ካልዋለ የሀገርን ሰላም በዘላቂነት ለማስፈን በሚደረገው ጥረት እንቅፋት ከመሆኑም ባሻገር፣ የመንግሥት ህልውናም ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል ይላሉ፡፡

እንደ ዶ/ር ደጉ ማብራሪያ፣ ከመንግሥት ኃይል ውጪ ያለ አካል መሳሪያ ሲይዝ ወንጀሎች ይበራከታሉ፣ መንግሥትም ዜጎቹን የመጠበቅ አቅሙ ይዳከማል፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ላሉ አደረጃጀቶችም ዋስትና መስጠት አይችልም፡፡ መንግሥት ይህንን መከላከል የሚችል ጠንካራ ሥርዓት ሲኖረው የመሳሪያ ዝውውሩን መግታት ብሎም ጠንካራ አገልግሎት ለሕዝቡ መስጠት ያስችለዋል፡፡

ጠንካራ የሚባሉ ሀገራት ጥንካሬያቸው የሚለካው በቀዳሚነት መሳሪያን በማምረት ሁለተኛው ደግሞ ያመረቱትን መሳሪያ በመቆጣጠር ነው ያሉት ዶ/ር ደጉ፣ በእነዚህ ሀገራትም ቢሆን አልፎ አልፎ ችግሮች ባይጠፉም መሳሪያን መቆጣጠር ካልቻሉ ሀገራት የተሻለ ሰላም የሰፈነባቸው ሊሆኑ እንደማይችሉ ይጠቅሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶ/ር መብራቱ አለሙ ደግሞ መሳሪያን ሕጋዊ ማድረጉ በራሱ በሚገባ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ እንደ እርሳቸው እይታ፣ ከፀጥታ አካላት (ከሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ፖሊስ፣ የመንግሥት ኃላፊዎች አጃቢዎች)፣ ከፍተኛ የሀብት መጠን ካላቸው ባለሀብቶች ውጪ መሳሪያ በማንም ሰው እጅ መግባት የለበትም፡፡ በግለሰቦች ዘንድ መሳሪያን በቀላሉ ሕጋዊ የማድረጉ ልምድ መገታት አለበት፡፡ ይህን ልምድ ከማስቀረትም ባሻገር መንግሥት በማኅበረሰቡ ውስጥ ተበትነው የሚገኙ መሳሪያዎች የመሰብሰብ ሥራ መስራት አለበት፡፡

በሀገራችን ያለው ግጭት እንዲባባስ ከሚያደርጉ ሰበቦች መካከል አንደኛው የሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውር እንደሆነ ያነሱት ዶ/ር መብራቱ፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት በተለይ ከኬንያና ሱዳን ጋር ረጅም ድንበር የምትዋሰን መሆኗን ጠቅሰው፣ ከጎረቤት ሀገራት ወደ ሀገራችን የጦር መሳሪያ ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡

ዶ/ር መብራቱ ወደ መፍትሔው ሲሻገሩ በዋናነት ሀገራችን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጠንካራ መሆን እንደሚገባውም አስተያየት ይሰጣሉ፡፡

የፀጥታ አካላት ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን ለመቅረፍ የሚያስችሉና አቅምን ለማጎልበት የሚጠቅሙ ልምዶችና ቴክኖሎጂዎችን ከሌሎች ሀገራት እንዲወስዱ ቢደረግ መልካም እንደሆነም ይመክራሉ፡፡

ኅብረተሰቡን የሀገር ሰላም ግንባታው አካል በማድረግ ሕገ ወጥ የመሳሪያ ንግድ ላይ የተሰማሩ አካላትን ሲመለከት እንዲጠቁም ማድረግ፤ ጥቆማ ለሚሰጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች መንግሥት የሕግ ከለላና ማበረታቻ ቢሰጥ ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን መግታት ይቻላል የሚል አስተያየትም ሰጥተዋል፡፡

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You