የወዳደቁ ፕላስቲክ ኮዳዎችን ወደ ሀብትነት የቀየሩት ብርቱዎች

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙዎች ተምረው ሥራ ከመጠበቅ ይልቅ ውስጣቸውን አድምጠው፤ አካባቢያቸውን አስተውለው፤ አዳዲስ የቢዝነስ ሃሳቦችን ለመፍጠር ሲጣጣሩ ይስተዋላል። የቢዝነስ ሃሳብ ከመፍጠርም አልፈው በፈጠሩት ቢዝነስ ራሳቸውን ከማሸነፍ አልፈው ሀብት ያካበቱ እንዲሁም ለሌሎች መትረፍ የቻሉ መመልከት እየቻልንም ነው።

በተለይ አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅና ለመሞከር ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር በብዙ ይጥራሉ። እነዚህ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ሥራቸውን በዕውቀትና ከልብ በመነጨ ከፍተኛ ተነሳሽነት ጀምረው ካሳቡት ሲደርሱ መመልከት ተለምዷል። ረጅሙ የስኬት ጉዟቸውም የነገ ተስፋቸውን ይበልጡኑ ብሩህ ያደርግላቸዋል።

እነዚህ ወጣቶች የስኬትን ቁልፍ በእጃቸው ማስገባት በመቻላቸው የሕይወት ውጣውረድ አያስፈራቸውም፤ ይልቁንም መኖር ያጓጓቸዋል። ጉጉታቸውም ይበልጡኑ ለማደግ፣ ለመለወጥ፣ ለመሻሻልና ለብዙዎች ፋና ወጊ ለመሆን ነው። መንግሥት እንዲህ ላሉ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች የሚያደርገው ድጋፍ እጅግ የሚያበረታታ እንደሆነም ብዙዎች ይስማማሉ። በተለይም አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማበረታታት መንግሥት የተለያዩ ድጋፍና ክትትሎችን በማድረግ ሰፋፊ ሥራዎችን እየሠራ ነው። በዚህም በርካታ አምራች እጆች ተፈጥረዋል፤ ኢንዱስትሪዎችም ተስፋፍተዋል።

እኛም በዕለቱ የስኬት አምዳችን እንግዳ ለማድረግ የወደድነው በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት›› የሚለውን መሪ ሃሳብ ተግባራዊ እያደረጉ ካሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል አንዱን ነው። ድርጅቱ በዋናነት የወዳደቁ ፕላስቲክ ኮዳዎችን ሰብስቦ ለተለያየ አገልግሎት የሚውለውን የፕላስቲክ ገመድ በተለያየ ቀለምና የውፍረት መጠን ያመርታል። የፕላስቲክ ገመዱም ገበያ ውስጥ እጅግ ተፈላጊ እንደመሆኑ ሰፊ ተደራሽነት አለው። ተራ፣ ቀላልና አልባሌ ቆሻሻ ሆኖ በየመንገዱ የሚጣለውን ፕላስቲክ ኮዳ በመሰብሰብ ቆሻሻውን አራግፎ ወደ ምርት መቀየር የቻለው ይህ ድርጅት አሁን ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው።

ማህበሩ በአራት ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ሃሳብ የተመሠረተ ሲሆን፤ ከማህበሩ መሥራቾች አንዱ ተቀጥሮ በሚሠራበት ድርጅት መሰል ሥራዎችን ማለትም ጥቅም ላይ ከዋሉ ፕላስቲክ ኮዳዎች የተለያዩ ምርቶች እንደሚመረቱ መረዳት መቻሉ ለፋብሪካው መቋቋም ምክንያት ሆኗል።

የተረዳውን እውነት ወደ ውስጡ ለማስገባት ሁለት ጊዜ ያላሰበው ወጣት፣ ጓደኞቹን አስተባብሮ አሁን ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን ዕውን አድርጓል። ወጣትነት አዳዲስ ነገሮችን የማወቅና የመሞከር ጉጉት እንደመሆኑ ወጣቶቹ የተረዱትን እውነት በተግባር በሥራ ለመቀየር ሙሉ አቅማቸውን አሰባስበው የአዋጭነት ጥናት አድርገው ወደ ማምረት ሥራ ገብተዋል።

አሁን ኢንዱስትሪያልን የመሠረቱት ወጣቶች በተለያየ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው በቅጥር ይሰሩ የነበሩ ወጣቶች ናቸው። ወጣት አፈወርቅ ኃይሉ የአሁን ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ ሲሆን፤ ወደዚህ ሥራ ከመግባቱ አስቀድሞ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ተቀጥሮ ሠርቷል። ከአራቱ ወጣቶች አንዱ እንደመሆኑ ከፋብሪካ ምስረታ ጀምሮ የነበረና አሁንም ፋብሪካውን በሥራ አስኪያጅነት እየመራ ያለ ወጣት ነው። ወጣቱ የጓደኞቹን የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ተቀብሎ ወደ ሥራው ሲገባ በሙሉ እምነትና በከፍተኛ ተነሳሽነት ነው።

ወጣት አፈወርቅ እንደሚለው፤ ፋብሪካው በዋናነት የሚያስፈልጉት ጥሬ እቃዎች የወዳደቁ ፕላስቲክ ኮዳዎች ናቸው፣ የፕላስቲክ ገመድ በሀገሪቱ ሰፊ ፍላጎት ያለው መሆኑን በጥናት በማረጋገጥም ነው ወደ ሥራው የገቡት።በወቅቱ ሥራው አዋጭና ተመራጭ ስለመሆኑ ጥናት ሲያደርጉም ለሚያመርቱት የፕላስቲክ ገመድ ዋናው ግብዓት የወዳደቁ ፕላስቲክ ኮዳዎች መሆናቸው ሥራቸውን ቀላል አድርጎላቸዋል። ምክንያቱም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የውሃ ፋብሪካዎች በመኖራቸው ፕላስቲክ ኮዳዎቹን ማግኘት ከባድ አይሆንም። በመሆኑም የወዳደቁ ፕላስቲክ ኮዳዎች ተሰብስበውና በሚፈለገው ጥራት ተዘጋጅተው የፕላስቲክ ገመድ መሆን ችለዋል።

‹‹በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት ፕላስቲክ ኮዳዎች በዋናነት ጥሬ እቃ ሆነው እያገለገሉ ነው›› የሚለው ወጣት አፈወርቅ፤ አሁን ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እያመረታቸው ካሉ የፕላስቲክ ገመዶች በተጨማሪ ካልሲ፣ ጅንስና ጥጥ ይሠራበታል ይላል።

እሱ እንደሚለው፤ ከፕላስቲክ ኮዳዎች የሚሠራው ጥጥ መልሶ ኮንፈርቶችን ትራሶችንና በብርድ ጊዜ የሚለበሱ ፈር ያላቸው ጃኬቶችን ለማምረት ጭምር ያገለግላል። እነዚህን አይነት አልባሳት በማምረቱ ሥራ በስፋት የተሰማሩት የቻይና ባለሀብቶች መሆናቸውን ወጣት አፈወርቅ ጠቅሶ፣ ለተለያዩ ምርቶች ጥሬ ዕቃነት እያገለገሉ ያሉት ፕላስቲክ ኮዳዎች ወደፊት ተጥለው የመታየት ዕድላቸው እጅግ ጠባብ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁሟል።

ፕላስቲክ ገመዶችን እያመረተ ለገበያ የሚያቀርበው አሁን ኢንዱስትሪያልም በዋናነት ዓላማ አድርጎ የተነሳው ከወዳደቁ ፕላስቲክ ኮዳዎች የፕላስቲክ ገመድ ማምረት መሆኑን ገልጾ፣ የወዳደቁ ፕላስቲክ ኮዳዎችን መሰብሰብ በራሱ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው በተጨማሪ ለአካባቢ ንጽህና ጉልህ አበርክቶ እንዳለውም ነው ያመለከተው።

ወጣት አፈወርቅ እንዳብራራው፤ እጅግ በጣም አደገኛ የሆኑና ለመበስበስ ከ500 ዓመት በላይ የሚወስድባቸውን ፕላስቲክ ኮዳዎች ሰብስቦ ጥቅም ላይ ማዋል በራሱ ከፍተኛ ፋይዳ አለው፤ ፋብሪካው ፕላስቲክ ኮዳዎችን የሚያገኘው የክልል ከተሞችን ጨምሮ ፕላስቲክ ኮዳዎቹን ከሚሰበስቡ በክፍለ ከተማና በወረዳ ከተደራጁ አካላት ነው። ፋብሪካው ከእነዚህ አስር ከሚደርሱ ማህበራት ለመፈጨት ዝግጁ የሆነውን ፕላስቲክ ኮዳ ገዝቶ ይጠቀማል።

ወጣት አፈወርቅ እንዳብራራው፤ ‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› ከሚሉትም በላይ ፋብሪካው አካባቢን የሚበክሉ የወዳደቁ የፕላስቲክ ኮዳዎችን በመጠቀም ፕላስቲክ ገመዶችን አምርቶ ለገበያ ያቀርባል፤ ለ60 ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል፣ ከዚህ ባለፈም ፕላስቲክ ኮዳዎቹን ሰብስበው ከሚያቀርቡ በክፍለ ከተማና በወረዳ ከተደራጁ አስር ማህበራት ጋር በመሥራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል።ታጥበው ለመፈጨት ከተዘጋጁትና በቀጥታ ወደ ማሽን መግባት ከሚችሉት ፕላስቲክ ኮዳዎቹ በተጨማሪ ፋብሪካው ማንኛውንም ፕላስቲክ ኮዳ ከሰብሳቢዎች በመግዛት አጥቦና አዘጋጅቶ ይጠቀማል ።

ፕላስቲክ ገመዱ ምንም አይነት ጥሬ ዕቃ ከውጭ ሳይመጣ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የወዳደቁ የፕላስቲክ ኮዳዎች ብቻ በተለያየ ቀለምና የውፍረት መጠን ይመረታል። ቀይ፣ አረንጓዴ፣ ቢጫና ሰማያዊ ቀለም ያላቸው ገመዶች በገበያው ላይ በእጅጉ ተፈላጊ ናቸው። በውፍረት መጠንም እንዲሁ ባለ ሶስት፣ ባለ ስድስት፣ ባለ ስምንት፣ ባላ አስርና ባለ አስራ ሁለት ተብለው ይመረታሉ። አንዱ እሽግ ከ 10 እስከ 100 ሜትር የሚደርስ ጥቅል አለው። ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ፕላስቲክ ገመዱን ደንበኞች በሚፈልጉት መጠንና ቀለም እያመረተ በሀገሪቷ በሚገኙ በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።

ፋብሪካው ያመረታቸውን ፕላስቲክ ገመዶች በዋናነት የሚያቀርበው መርካቶ ለሚገኙ እንዲሁም ከሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ለሚመጡ ጅምላና ችርቻሮ ነጋዴዎች በማቅረብ ምርቱ በመላው ሀገሪቷ እንዲደርስ እያደረገ እንደሆነና በዚህም ውጤታማ መሆኑን ገልጿል።

እነዚህ ገመዶች በስፋት አገልግሎት የሚሰጡት በክልል ከተሞችና ገጠራማ በሆኑ አካባቢዎች ቢሆንም በከተሞች አካባቢም ለተለያዩ አገልግሎቶች ይውላሉ። ለአብነትም መኪኖች ጭነት ማሰሪያነት ያገለግላል፤ ለተለያዩ ጥቃቅን ለሆኑ ማሰሪያዎችና ሌሎች አገልግሎቶች ጭምር ፕላስቲክ ገመዱ ይፈለጋል።

‹‹በተለይም በገጠር አካባቢዎች እህል ደርሶ በሚሰበሰብበት ወቅት ፕላስቲክ ገመዶቹ በጣም ይፈለጋሉ።›› የሚለው ወጣት አፈወርቅ፤ አዝመራ በሚሰበሰብበት ወቅት እንደ ሀገር የፕላስቲክ ገመድ ፍላጎቱ በከፍተኛ መጠን ይጨምራል ብሏል።ከዚህ ባለፈም የውፍረት መጠናቸው ቀጠን ያሉት የፕላስቲክ ገመዶች የጠፍር አልጋ፣ ወንበርና ሌሎች የቤት ውስጥ ቁሳቁስን ለመሥራት የሚጠቀሙበት እንደሆነና ሰፊ የገበያ ፍላጎት እንዳለው አጫውቶናል።

በሶስት ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ሥራ የጀመረው አሁን ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ወደ ምርት ከገባ አጭር ጊዜ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ከ16 ሚሊዮን ብር ካፒታል በላይ ማስመዝገብ ችሏል ሲልም አስታውቋል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከፍተኛ እገዛ እንዳደረገላቸው ጠቅሶ፣ መጠነኛ በሆነ ወለድ ያለኮላተራል ባገኙት በዚህ ብድር በሊዝ ፋይናንሲንግ ማሽነሪዎቹን በመግዛት ወደ ሥራ እንደገቡ አስታውቋል።

አፈወርቅ እንደሚለው በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ ነው። በተለይም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እያደረገ ባለው እገዛ በርካቶች ህልማቸውን ዕውን ማድረግ ችለዋል። አሁን ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርም ይዞ የመጣውን ሃሳብ ተግባራዊ ማድረግ እንዲችል ባንኩ ያደረገው ድጋፍም ትልቅ ነው። ከዚህ ቀደም ወጣቶች በውስጣቸው ያለውን ሃሳብ ወደ ሥራ ለመቀየር ብድር ሲጠይቁ ባንኮች የሚጠይቁት ወለድ እንዲሁም የሚጠየቀው ማስያዣም የማይሞከር በመሆኑ ሃሳብ ያለውን ሰው የሚያበረታታ አልነበረም። የአሁኑ እነዚህን ችግሮች በማስወገድ ምቹና ቀልጣፋ አሠራር ተዘርግቷል። ይህም ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ በእጅጉ ያበረታታል ብሏል።

አሁን ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ፋብሪካ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ቃሊቲ መናኸሪያ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በወር እስከ ሃምሳ ሺህ ኪሎ የሚደርስ ምርት እያመረተ ይገኛል። ምርቱ ከገበያ በከፍተኛ ደረጃ ይፈለጋል። ፋብሪካው አሁን ካለበት የቦታ ጥበት የተነሳ ገበያው በሚፈልገው ልክ እያመረተ አይደለም፤ በቀጣይ ሥራውን ለማስፋፋት ጥያቄ እያቀረበ ይገኛል። እስከዚያው ድረስ ግን ገበያውን ተደራሽ ለማድረግ ማሽነሪዎችን ጨምረው በስፋት እንደሚሠሩ ተናግሯል።

በሀገሪቱ እየተበራከቱ የመጡት የውሃ ፋብሪካዎች አገልግሎት የሰጡ የፕላስቲክ ውሃ ኮዳዎችን ለማግኘት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩም ተናግሯል። ፋብሪካው ፕላስቲክ ኮዳዎቹ ተፈጭተው በውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የተለያዩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ለሀገር እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም ብሏል።

በአሁኑ ወቅትም ፋብሪካው አንድ ኪሎ ታጥቦ የተዘጋጀና ጥራቱን የጠበቀ ፕላስቲክ ጠርሙስ ከ40 እስከ 50 ብር እንደሚገዛም ይናገራል፤ ፋብሪካው በቀጣይ ማስፋፋያ በማድረግ ጥሬ ዕቃውን በራሱ የማዘጋጀት ዕቅድ እንዳለውም ገልጿል። ይህም 50 በመቶ ያህል የማምረቻ ወጪን እንደሚቀንስልት ተናግሯል።

ድርጅቱ ፕላስቲክ ኮዳውን ጥራቱን በጠበቀ መንገድ ፈጭቶ በማዘጋጀት ለፋብሪካው ግብዓት ከመጠቀም በተጨማሪ ለውጭ ገበያም የማቅረብ ዕቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑንም ጠቁሟል። በዚህም ከራሱ አልፎ ሀገርን በውጭ ምንዛሪ ግኝት ለመደገፍ እንደሚሰራ ተናግሯል።

ለሥራ በተፈጠሩ እጆች በተቋቋመው አሁን ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ውስጥ የሚሠሩት ወጣቶች ናቸው። ወጣቶቹም በፋብሪካው መሥራት የሚያስችላቸውን ሙያና ክህሎት ከድርጅቱ አግኝተዋል ሲል ጠቅሶ፣ ወቅቱ ሃሳብና የሥራ ፍላጎት ላለው ወጣት ምቹ መሆኑን አስታውቋል። ወጣቶች ይህን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ሃሳባቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You