‹‹በአፍሪካ ጠንካራ የባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ለመፍጠር ይሠራል›› -አምባሳደር መስፍን ቸርነት

የባሕል ስፖርት ዓለም አሁን ለደረሰችበት የስፖርት እድገት መሠረት በመሆን ጉልህ ሚናን ተጫውቷል። ይህም የሆነው በጠንካራ ብሔራዊ ፌዴሬሽንና የሕዝብ ጠንካራ ተሳትፎ ውጤት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ኢትዮጵያ በባሕል ስፖርቶች የታደለች ብትሆንም በጥናት ተለይተው እና ሕግ ወጥቶላቸው እየተዘወተሩ የሚገኙት በጣት የሚቆጠሩት ብቻ ናቸው። ለዚህም የተደራጀና ጠንካራ ብሔራዊ ፌዴሬሽን አለመኖሩ ስፖርቶቹ በብዛት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳይገቡና የሚፈለገውን እድገት እንዳያሳዩ አድርጎ ቆይቷል።

ለስፖርቱ እድገት የተቋሙ ማደግ አስፈላጊ በመሆኑ የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽንና የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር በጋራ ለመሥራት ወጥነዋል።

የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ አልፎ በምሥራቅ አፍሪካ ብሎም በአፍሪካ ትልቅ እና ጠንካራ ለማድረግ በፌዴሬሽኑና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። የባሕል ስፖርት የተቋቋመበት ራዕዩ ሕዝባዊ መሠረት ለማስያዝ፣ ስፖርቱን ማሳደግና ማጎልበት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ አድጎ ማየት ቢሆንም ያለ ጠንካራ ተቋም ሊታሰብ አይችልም።

የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን በባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱ ፌዴሬሽኖች አንዱ ሲሆን ስፖርቶቹን በጥናትና ምርምር በማሳደግና አልምቶ ወደ ዘመናዊ ደረጃ ለማሸጋገር ታስቧል።

የስፖርት ዘርፍ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካና በአፍሪካ የባሕል ስፖርት መነሻና ትልቅ ፌዴሬሽን ፈጥራ እንድትወጣ የመንግሥት ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል። በመሆኑም የሀገሪቱን የባሕል ስፖርት ፌዴሬሽን የማጠናከርና በምሥራቅ አፍሪካና በአፍሪካ ጠንካራ የባሕል ስፖርት ፌዴሬሽን ለማድረግ ጥረት ይደረጋል ብለዋል። ለዚህም ከሚመለከታቸው አጋሮች ጋር በጥናትና በተለያዩ እውቀቶች በማስደገፍ ኢትዮጵያ የባሕል ስፖርት ማዕከል እንድትሆን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የስፖርት ፖሊሲ በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሠረት ስፖርቱ ጠንካራ ሆኖ በአሕጉርና ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲወጣ የሚቻለውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አምባሳደሩ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በባሕል ስፖርት የአፍሪካ ጽሕፈት ቤት ብትመሠርትና ውድድሮችን ብታዘጋጅ ለስፖርቱ እድገት እገዛ ይኖረዋል የሚል እምነት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዘንድ እንዳለ በመጠቆምም ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ በእቅድ እንደተያዘ አስረድተዋል።

እንደ አምባሳደር መስፍን ገለፃ፣ ለስፖርቱ ዕድገት የሚያግዙትን ሰነዶች በማዘጋጀት እና ከአጋር አካላት ጋር በምሥራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ በባሕል ስፖርት ዕድገት ላይ ለመሥራት መንግሥት ጠንካራ አቋም አለው። የመጀመሪያው ሥራ የሚሆነውም በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ የባሕል ስፖርት አጥንቶ መለየት ይሆናል። ይህም ስፖርቱ በሌላው ዓለም ለሀገራዊ ጥቅል ምርቱ የሚያበረክተውን አስተዋፅዖ ለማሳደግ ይረዳል።

የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሕይወት መሐመድ በበኩላቸው፣ ስፖርቱን ለማሳደግና ወጣቶችን በቴክኖሎጂ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር በማቀድ የተለያዩ ጥረቶች እንዳሉ ተናግረዋል። በትምህርት ቤቶች የታዳጊ ፕሮጀክቶች ጅምር ሥራዎችን በሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል። በተለያዩ ሀገራት የሚገኙትን ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የሀገራቸውን የባሕል ስፖርት እንዲያውቁ የሚደረግበት ሁኔታም ይፈጠራል ብለዋል።

ስፖርቱ አድጎ እና ኢትዮጵያ የባሕል ስፖርቶች ማዕከል እንድትሆን የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት የጠቆሙት ፕሬዚዳንት፣ ፌዴሬሽኑ አሁን ያለበትን የበጀት ውስንነት ለመቅረፍ ስፖርቱን ሕዝባዊ መሠረት ለማስያዝ የሚሠራ ቢሆንም በገንዘብ ሊደገፍ እንደሚገባው አብራርተዋል። ውድድር የሚደረግባቸው አስራ አንዱን የባሕል ስፖርት ዓይነቶችን ለማሳደግና በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸውና ተዘውታሪ እንዲሆኑ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል። በዚህም መሠረት በቀጣይ የአፍሪካ ሆኪይ ፌዴሬሽን አባል ለመሆን እንደሚሠራ ጠቁመዋል። ከአፍሪካ አንዱና ጠንካራ ፌዴሬሽን ለማድረግ አባል ለመሆንም የገና ጨዋታን የማዘመን ሥራም በትኩረት ይሠራል። የኦሊምፒክ ስፖርቶች የሆኑትን ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በመተባበር ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግም ገልፀዋል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You