ትዕግስት አሰፋ በለንደን ማራቶን ክብረወሰን ለማሻሻል ተዘጋጅታለች

በየዓመቱ በአለም ከሚካሄዱ ታላላቅ ማራቶን ውድድሮች አንዱ የሆነው የለንደን ማራቶን ዛሬ ሲካሄድ ኢትዮጵያዊት አትሌት ትዕግስት አሰፋ የውድድሩን ክብረወሰን ለመስበር ትሮጣለች፡፡ ውድድሩ ለ44 ጊዜ ሲካሄድ የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷ ትዕግስት አሰፋ፣ አልማዝ አያና፣ ትዕግስት ከተማ፣ መገርቱ ዓለሙ እና የዓለም ዘርፍ የኋላው ከኬንያዊያን አትሌቶች ጋር የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል፡፡

በወንዶቹ አንጋፋው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ ሞስነት ገረመው፣ ታምራት ቶላ፣ ዳዊት ወልዴ፣ ልዑል ገብረስላሴ፣ ሴይፉ ቱራ እና ሚልኬሳ መንገሻን የመሳሰሉ ታላላቅ አትሌቶች የሚያደርጉት ፉክክርም በጉጉት ይጠበቃል፡፡

በዛሬው ውድድር በእንግሊዛዊቷ አትሌት ፓውላ ራድክሊፍ 2፡15፡25 ተይዞ የቆየውን የውድድሩን ክብረወሰን ለመስበር ከሚሮጡት አትሌቶች መካከል ትዕግስት አሰፋ እና ኬንያዊት ብሪጊድ ኮስጌ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ውድድሩን የማሸነፍ ቅድመ ግምት የተሰጣት ትዕግስት አሰፋ ባለፈው መስከረም ወር በተካሄደው የበርሊን ማራቶን በአስደናቂ ሁኔታ የዓለም ክብረወሰን በመጨበጥ ስታጠናቅቅ፤ ቀደም ሲል ኬንያዊቷ ብሪጊድ ኮስጌይ ያስመዘገበችውን ክብረወሰን በመስበር ነበር፡፡

እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ በሚጠበቅበት የዛሬው የለንደን ማራቶን የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን የጨበጠችው ትዕግስት ከተሳካላት ውድድሩን 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ በመጨረስ የራሷን ዓለም ክብረወሰን ለመስበር ዝግጅት ማድረጓን ተናግራለች፡፡ አትሌቷ በርሊን ላይ ክብረወሰኑን የጨበጠችው 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ53 ማይክሮ ሰከንድ በመሮጥ ነበር፡፡ በጀርመን ዋና ከተማ ይህን ስትሮጥ በብሪጊድ ኮስጊ ያስመዘገበችውን የአለም ክብረወሰንን በሚያስደንቅ ሁኔታ በመስበርም ጭምር ነው።

ትዕግስት ለውድድሩ ያደረገችው ዝግጅት እና ክብረወሰኑን ለመስበር ያላትን ዕቅድ አስመልክታ ሃሳቧን እንዲህ በማለት ገልጻለች፡፡ “ወደ ፊት ከሁለት ሰአት ከአስር ደቂቃ በታች መሮጥ እፈልጋለሁ”። “ያንን ለማድረግ የሚያስችለኝን ልምምድ ማድረግ ከቻልኩ ዋናው ነገር ያ ይሆናል። እግዚአብሔር ቢፈቅድ በዛ መንገድ መሄድ እችላለሁ ብዬ አስባለሁ። ለንደን ውስጥ ውድድር ለማድረግ በጣም ጓጉቻለሁ። ባለፈው አመት ማራቶንን እዚህ ለመሮጥ አስቤ ነበር፣ ነገር ግን ተጎድቻለሁ። ይህ ደግሞ በዚህ ጊዜ የበለጠ እንድወስን አድርጎኛል” በማለት ተናግራለች፡፡

ባጋጠማት የጅማት ጉዳት ምክንያት “ከትራክ ሯጭነት ወደ ማራቶን መቀየሩ ቀላል አልነበረም” ትላለች። ብዙ ጠንክሮ መሥራት ይፈልግ ነበር እናም ወዲያውኑ አልሰራም ግን አሁን በጣም ቀላል እና የበለጠ ተፈጥሯዊ ስሜት ይሰማኛል፡፡” ስትልም ተናግራለች፡፡

ትዕግስትና እና ኮስጌ በለንደን የሚፋለሙት ከ2019 የአለም ቻምፒዮና ሩት ቼፕጎቲች፣ የኦሊምፒክ ቻምፒዮን ፔሬስ ጄፕቺርቺር እና የ2022 የለንደን ማራቶን አሸናፊዋ ያለምዘርፍ የኋላው ጋር ሲሆን፤ ይህም በታሪክ ከአራቱ ፈጣን ሴቶች መካከል ሦስቱ በውድድሩ ውስጥ ይገኛሉ ማለት ነው። ውድድሩ በአትሌቶች ምርጫ ስኬታማ በመሆኑ የዓለም ክብረወሰን ይመዘገብበታል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በውድድሩ ክብረወሰን እንዲሰበር አሯሯጮች ትልቅ የቤት ስራም ይጠብቃቸዋል፡፡

የለንደን ማራቶን ዳይሬክተር ሂዩ ብራሸር ከውድድሩ መጀመር አስቀድመው በሰጡት አስተያየት “በሴቶች የማራቶን ሩጫ ወርቃማ ዘመን ላይ ነን። በበርሊን ባለፈው አመት ባሳየችው አስደናቂ ሩጫ የአለም ክብረወሰንን በላቀ ደረጃ ያሳደገችው ትዕግስት አሰፋን ጨምሮ ሌሎች አራት ሴቶች ይሳተፋሉ። ሆኖም ትዕግስት፣ ኮስጌ እና እንደ ሩት ቼፕጌቲች፣ ፔሬስ ጄፕቺርቺር እና ያለምዘርፍ የኋላው በአጠቃላይ አስር ሴቶች ከ2 ሰአት ከ17 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ በታች የሮጡበት እንደሚሆን አልጠራጠርም” በማለት ገልጸዋል።

በወንዶች ውድድር በታሪክ ሶስተኛው ፈጣኑ የማራቶን ሰዓት ባለቤት፣ የኦሊምፒክ፣ የዓለም ቻምፒዮና እና የሀገር አቋራጭ ንጉስ ቀነኒሳ በቀለ አሸንፎ በፓሪስ ኦሊምፒክ ለመጨረሻ ጊዜ ሀገሩን የሚወክልበት እድል ለመፍጠር ይሮጣል፡፡ አንጋፋው አትሌት ፊቱን ከመም ወደ ጎዳና ውድድሮች ካዞረ በኋላ በርካታ ጊዜ ድል ማድረግ ችሏል፡፡ ቀነኒሳ ከወራት በፊት አትሌት ሲሳይ ለማ ፈጣን ሰዓት አስመዝግቦ ባሸነፈበት የቫሌንሲያ ማራቶን ተሳትፎ በማድረግ በአንጋፋ አትሌቶች ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን በእጁ አስገብቷል፡፡

“በማራቶን አሁንም የተሻለ መስራት እንደሚችል አእምሮዬ ይነግረኛል፣ በጣም ብዙ ግቦች አሉኝ። ኦሊምፒክ ከፊታችን ነው፡፡ ምናልባት ፓሪስ የመጨረሻ ኦሊምፒክ ሊሆን ይችላል” በማለት ለአሸናፊነቱ ያለውን ተስፋ ገልጿል።

የቀድሞ የርቀቱ የዓለም ቻምፒዮንና የኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊ ታምራት ቶላ፣ በታሪክ ሰባተኛ ፈጣን ሰዓት ባለቤት የሆነው ሞስነት ገረመውና ዳዊት ወልዴን ጨምሮ ስድስት ጥሩ ሰዓት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ወንድ አትሌቶች ይሮጣሉ፡፡

አለማየሁ ግዛው

 

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You