አሁንም አሁንም እናቱ እንዳጣ ህጻን በጉጉት ዓይናችንን ታክሲዎቹ ወደሚመጡበት አቅጣጫ እንልካለን፤ የሚመጡት ግን አልፎ አልፎ በመሆኑ ተስፋ አስቆራጭ ነው። ማለዳ የተነሳሁት በጊዜ ካሰብኩበት ለመድረስ ነበር፤ ሰልፍ የተባለ መሰናክል ባይገጥመኝ። እንደ እኔ ማልደው የተነሱ መንገደኞች ታክሲ ለመሳፈር ቀድመውኝ ረጅም ሰልፍ ይዘዋል።
አማራጭ ስለላልነበረኝ ተቀላቀልኳቸው፤ ለሰዓት የቀረቡ ደቂቃዎች ቢቆጠሩም ለውጥ ግን አልነበረም። እኔም እድሌን ለመሞከር ቆምኩ እንጂ ከመሄጃዬ ዘግይቻለሁ። የሌሎች ሰልፈኞች ገጽ ላይ እንደእኔ ብስጭት ይነበባል፤ ከፊት ለፊቴ የተሰለፉት አንዲት ባልቴትና ልጅ እግር ሴት ግን ወሬ ስለያዙ ይህ የተሰማቸው አይመስልም።
የሚያወሩት ስለሚሰማኝ አልፎ አልፎ ጆሮዬን ወደ እነርሱ እየላኩ አደምጣለሁ። ከእነርሱ ጋር የሌለችውን ሌላ ሴት እያነሱ ሲጥሉ ቆይተው፤ ልጅ እግሯ «እኔስ ክፉ አይወጣኝም፤ ትዝብት ነው ትርፉ» ስትል ወሬዋን አሳረገች። ያን ሁሉ ክፉ ደግ ከዘረዘሩ በኋላ «ታዘብናት» ሲሉ ማቅለላቸው አስደነቀኝ።
እናንተስ ሳይፈቀድልኝ ከወሬያቸው በመታደሜ «ታዘብንሽ» አላላችሁኝ ይሆን? ሁላችንም ታዛቢዎች ሆንን እኮ ወገን። እኔን ጨምሮ አብዛኛዎቻችን በመገናኛ ብዙሃን፣ በተገናኘንባቸው ስፍራዎች፣ ባገኘናቸው መድረኮች እንዲሁም በማህበራዊ ድረገጾች መታዘብን ልምድ አድርገናል።
በውሃ በተከበበ ደረቅ መሬት ቆሞ የመናገርን ያህል ሁሉም ሰው ከደሙ ንጹህ ነኝ ዓይነት እሳቤ ይዞ መታዘብ አንዱ የዘመናችን ባህሪ ሆኗል። በትልልቅ የመገናኛ አውታሮች ስራቸውን መታዘብ ብቻ ያደረጉ ሙያተኞች አሉ። ተቋማትም «እንወያይ» በሚል ባዘጋጁት መድረክ ታዳሚው እንደታዘባቸው ይነግራቸዋል።
እግር በጣለንና ባልተሳካልን አጋጣሚ ሁሉ ድክመቱን ከእኛ አርቀን፤ እርስ በእርሳችን ስለመተዛዘባችን እንወያያለን። ወደ ማህበራዊ ድረገጾች ጎራ ከተባለማ የትዝብቱም ታዛቢውም ዓይነትም ቁጥርም ይበዛል። በድረገጾች አውድ ከግለሰብ እስከ መንግስት ትዝብት ላይ ያልወደቀ ማን አለ¡
ኧረ እንዲያውም ለመታዘብ ምክንያት እና አጋጣሚ መጠበቅ ተጀምሯል። ይህንን ትዝብቴን ያጠናክርልኝ ዘንድ ከታዘብኩት ላካፍላችሁ (ከታዛቢው ትውልድም አይደል የተገኘሁት¡)። የመብራት መቆራረጥን አስመልክቶ «ግድቦቹ ውሃ አጥሯቸዋል» የሚል ምክንያት «ፈረቃ» ከተባለ መፍትሄ ጋር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እንደተሰጠን አይዘነጋም።
ታዲያ ወቅቱ የክረምት መግቢያ በመሆኑ፤ መዝነብ ከመጀመሩ «የዛሬው ዝናብ ግድብ መሙላት ያቅተዋል?» ስንባባል ቆየን። ዝናቡ መጠንከር ሲጀምርም የኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ አካባቢ ያለው መንገድ በውሃ መጥለቅለቁን ያዩ በቅድሚያ ፎቶ አነሱት።
ከዚያማ «ዝናቡ ከግድቡም አልፎ መስሪያ ቤቱን እንዲህ አጥለቅልቆታል…» ሲሉ ትዝብት ጠቀስ ፌዛቸውን ከማህበራዊ ድረገጻቸው ግድግዳ ለጠፉ። ሌላውም ይህንን ሲቀባበል ነው የቆየው።
እኔም ይህንን ትዝብት ስመለከት ታዛቢዎችን ታዘብኳቸው¡ ምክንያቱም የሆነውን በትክክል ሳናጣራ የሚሆነውንም መጠበቅ አቅቶን ነዋ ለትዝብት የተነሳነው። የሰው ፍጹም እንደሌለው ስናውቅ፣ ሰው ከሰዎች፣ ሰዎችም ከህዝብ መሃል እንደሚፈለቀቁ ረስተን ራሳችንን ታዛቢ ብለን እንሰይማለን።
እኔን ሲመስለኝ የታዛቢ ትርጉሙ ከምኑም የማይነካካ ገለልተኛ አካል ነው። የሆነውን መመስከር የሚችል መሆን ያለበትንም ለማንም ሳያዳላ የሚጠቁም እማኝም ነው። እኛ ግን የነገሩ አንድ አካል ሆነን ስናበቃ «የለሁበትም» በሚል ስሜት ሌላውን እንኮንናለን።
አብነት እናንሳ አንዱ ተነስቶ «አንድን ታዋቂ ሰው ከመጠጥ ቤት አገኘሁት» ይላችኋል። በጄ ካላችሁት ይቀጥላል «… ስንት ሲጠበቅበት፣ ለኛ አርዓያ መሆን ሲገባው…» እያለ። ቆይ ግን ይህ ታዛቢ ከመጠጥ ቤት አሊያም በአልባሌነት ከፈረጀው ስፍራ የተገኘው ለምን ይሆን?
ተቋማትም የትዝብት ሰለባ ናቸው፤ ክረምት ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ መንገዶችን እንታዘባለን። ዝናብ መንገዱን አጥለቅልቆት አላሳልፍ ሲለን ባገኘነው አጋጣሚ «መንገዶች ባለስልጣን፤ መንገዶችን ባለማደሱ፣ ቦይ ባለማውጣቱ እንዲሁም በጥንቃቄ ጉድለት በሰራው ስራ…» እያልን ትዝብታችንን እናዥጎደጉዳለን።
በእኛ አያያዝና ግድየለሽነት ስንት ነገር አበላሽተናል? እነርሱማ ሙያቸው ነውና «ተገቢ» ባሉት መንገድ ሰርተው አስረክበውናል። እኛም በጋውን በፍሳሽ መውረጃዎች ደረቅ ቆሻሻ እየጣልን፣ በግንባታ መሳሪያና ቁሳቁስ መንገድ እየዘጋን፣ መንገዳችንን የሚያበላሹትን እንዳላየን እያለፍን፣ … እንቆይና ጣታችንን ወደሌላ እንጠቁማለን።
መንግስትም አይቀርለትም «ይህንን አመጣለሁ፣ እንዲህ እፈጥራለሁ፣ ያንን አሟላለሁ፣… ቢልም…» እንላለን። «እኛን ሳያማክር፣ ቃል የተገባልን ተረስቶ፣… » ማለታችንም በየስፍራው የሚታይም የሚሰማም ነው። ወደ ቁም ነገሩ ስንመለስ ግን መንግስት ማነው? ከእኛስ ምን ይጠበቃል?… የሚሉትን መመለስ አንችልም።
ትዝብት ለመማማሪያ ካልሆነ ከሃሜት ያለፈ ቁም ነገር አይኖረውም። እከሌ ይህንን አደረገ፣ ያንን ከወነ ስንልም በእኛ በኩል የሚጠበቅብንን መወጣታችንን ማረጋገጥ ይገባናል። ትዝብታችን በትክክል ለተጠቆመው አካል ደርሶ ለውጥ ማስከተሉንም መመዘን ያስፈልጋል። «ታዘብናችሁ» የተባሉት አካላትም፤ ስማቸው እንደጠፋ ሳይሆን ለሰሩት ግብረመልስ እንደተሰጣቸው አምነው በሚሻለው መንገድ መጓዝን ምርጫቸው ሊያደርጉ ይገባል፤ መልዕክታችን ነው::
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2011
ብርሃን ፈይሳ