ከ‹‹ቅንጡዎቹ›› ዝርዝር የሚመደቡት የቆዳ አልባሳት

ሰዎች ከቆዳ የተሠራ ልብስን ምርጫቸው የሚያደርጉት ረጅም ጊዜ የሚቆይና ጠንካራ በመሆኑ፣ አልያም ቅንጡ ልብስ የምንለው አይነት ተደርጎ በመወሰዱ መሆኑን ብዙዎች ሲያነሱ ይደመጣል። በቀደሙት ዓመታት የቆዳ አልባሳት እንደ ፋሽን በስፋት ተመራጭ ነበሩ። ይህ ልምድ በመሐከል ደብዘዝ ብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ከቆዳ የተሰሩ አልባሳትን ምርጫቸው የሚያደርጉ ሰዎችን እየተመለከትን ነው።

አቶ አየለ ፈይሳ ይባላል፤ የብዙአየሁ እና አየለ የቆዳ ውጤቶች የኅብረት ሥራ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ነው። በቆዳ አልባሳት ሥራ ላይ ያለውን የሥራ ሂደት ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ የመሥራት ልምድ፣ አቅም እና ችሎታን ያጣመረ ሙያ እንዳለው ይናገራል። በስሩ ሁለት ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ በተለምዶ ሌዘር የምንውን ከቆዳ የተሠራ ጃኬት ለገበያ ያቀርባል። ከቆዳ በተለያየ ሞዴል ከሚሠራቸው ልብሶች በተጨማሪም ቦርሳና ቀበቶዎችንም ያመርታል ።

ሙያውን ያገኘው በቆዳ ሥራ ኢንስቲትዩት ወይንም የሌዘር ቴክኖሎጂ ውስጥ ገብቶ በመማር ነው። ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላም የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ላይ ተዘዋውሮ ሠርቷል። አየለ ተቀጥሮ በሠራባቸው ጊዜያት የራሱን ልምድ ካዳበረ በኋላ ከሙያ አጋሮቹ ጋር በመደራጀት ወደዚህ ሥራ ገብቶ ለአምስት ዓመት ሠርቷል።

በኢትዮጵያ የተሠሩ የቆዳ ውጤት ጃኬቶችን የውጭ ሀገር ዜጎች እንደሚወዱ የሚናገረው አየለ፣ እነዚህ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝትም ሆነ ለተለያዩ ጉዳዮች በመጡበት ወቅት ገዝተው እንደሚሄዱ ይናገራል።

የቆዳ ውጤት የሆኑ ጃኬቶችን የሚጠቀሙ ሰዎች እና የሌዘር ልብስ ወዳጆችም በየጊዜው ፋሽኑ እና ወደገበያ የሚወጣው ቀለም በተቀየረ ቁጥር የመግዛት ፍላጎታቸው ይጨምራል ሲል ጠቅሶ፣ ሁሌም ቢሆን ግን ከቆዳ የተሠሩ ልብሶችን እንዲጠቀሙት የሚያደርገው ጥራቱ መሆኑን ይገልፃል ።

እንደ አየለ ገለጻ፤ የሀገር ውስጥ ቆዳ አልባሳት ሙለሙሉ ከቆዳ ውጤት ብቻ የተሠሩ ሲሆኑ፣ ከውጭ ሀገር የሚመጣው ደግሞ ቆዳው ተፈጭቶ በጨርቅ ላይ እንደ ቀለም እንዲፈስ ተደርጎ ትክክለኛውን ቆዳ እንዲመስል በማድረግ በፋብሪካ ውስጥ የሚመረት ነው መሆኑን ይገልፃል።

‹‹ቆዳውን የምናገኘው ከፋብሪካዎች ሲሆን ፋብሪካዎቹ ኤክስፖርት ከሚያደርጉት ውጪ ለሀገር ውስጥ ነጋዴዎችና አምራቾች ልብስ፣ ቦርሳና ጫማ ሥራ የሚያመች ሂደትን በፋብሪካ ያለፈ ቆዳ ተረክበን እንሰራለን›› ሲል ያብራራል። መሰል አምራቾች ዋናውን ግብዓት ቆዳ ከእነዚህ ፋብሪካዎች እና አቅራቢዎች በተመሳሳይ እንደሚረከቡ ይናገራል። ቆዳው ለአልባሳት አገልግሎት የሚውል ከሆነ የበግ ቆዳ፤ ለቀበቶ፣ ቦርሳዎች፣ ጫማ ከሆነ ደግሞ የበሬ ቆዳ እንደ ግብዓት ጥቅም ላይ እንደሚውልም ይገልጻል።

ቆዳው ከፋብሪካ በሚገዛበት ወቅት ልብስ ለመሥራት የሚያገለግል ጨርቅ በሜትር ተለክቶና ዋጋ ወጥቶለት እንደሚሠራው ሁሉ ከፋብሪካ ለአምራቾች የሚቀርበው ቆዳም የሚሸጥበት የመጠን ስፋት ‹‹በስኩዌር ፊት›› ተለክቶ መሆኑን ባለሙያው ይናገራል። ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የወጣላቸው የቆዳ አይነቶች እንዳሉም ይገልፃል። አንድ ስኩዌር ፊት ቆዳ በ55 ብር ሲገዛ ለአንድ ጃኬት የሚፈጀው ከ28 እስከ 32 ስኩዌር ፊት ቆዳ ወይንም ከሰባት እስከ ስምንት የበግ ቆዳ መሆኑን ያስረዳል።

ጊዜው ሰዎች የተለያዩ መረጃዎችን በበይነ መረብ የሚያገኙበት በመሆኑ ደንበኞቹ ከተለያዩ ድረገጾች ላይ የተመለከቱትን ዲዛይንና ሞዴል ይዘው ለማሠራት ወደ እርሱ እንደሚሄዱ ጠቅሶ፣ እሱም ያመጡትን ዲዛይን ተመልክቶ ካማከራቸው በኋላ እንደየምርጫቸው ለማዘጋጀት ወደ ሥራ እንደሚገባ ይገልፃል።

እሱ እንደሚለው፤ ከቆዳ ውጤቶች የሚሠሩ ልብሶችን፣ ጃኬቶችን ለመሥራት የሚያገለግሉት ተጨማሪ ግብዓቶች ገበር ማስቲሽ ዚፕ እና ቁልፍ የመሳሰሉት ናቸው። አሁን ላይ እነዚህ ምርቶች አቅርቦት ከቀደመው ጊዜ በተሻሻለ መልኩ ይገኛሉ። ነገር ግን የሚሸጡበት ዋጋ ላይ አለመረጋጋት ይታያል ።

አንድ ደንበኛ እንዲሠራለት የሚፈልገውን የቆዳ ጃኬት ዲዛይን ይዞ ሲመጣ የደንበኛውን ልኬት ባለሙያው ከወሰደ በኋላ በዲዛይኑ መሠረት ወረቀት ላይ እንዲሰፍር ይደረጋል። ንድፉ ከወጣ በኋላም በተመረጠው ቆዳ ላይ ይቆረጣል፤ ከተቆረጠ በኋላ ማድረቂያ ተለጥፎበት ወደ ስፌት ይገባል፤ አብሮትም ገበር ይደረግለታል። በዚህ ሁኔታ የሚያልፍን አንድ ጃኬት ሠርቶ ለማጠናቀቅ የአንድ ቀን ጊዜ ይወስዳል።

ከዚህ ቀደም ከቆዳ የተሠሩ ጃኬቶች ጥቁር እና ቡኒ ውስን የቀለም ምርጫዎች ነበሩ የሚለው አየለ፣ አሁን ግን በገበያ ላይ ከ10 በላይ የቀለም አማራጮች አሉ ሲል ጠቁሟል። ጥቁር ቀለም ግን የሁልጊዜ የሰዎች ምርጫ ሆኖ መቆየቱን ጠቅሶ፣ በሞዴል ደረጃም ሸሚዝ ሞዴል፣ ጃኬት ሞዴል፣ ቦዲ ጃኬት እና ኮት የምንላቸው ሌሎችም ዲዛይኖች ቢኖሩም በተለምዶው ግን ጃኬት ተብለው ይወሰዳሉ ሲል ያብራራል።

አቶ አየለ እንደገለጸው፤ በፋብሪካ ውስጥ የተለያዩ ሂደቶችን አልፎ የሚመጣው ቆዳ ለስላሳ አልያም ጠንካራ ባሕሪ ሊኖረው ይችላል። እነ አቶ አየለ በዚህ ጊዜ ጠንከር ያለውን ብዙውን ጊዜ ወደ ምንደገፍበት ቶሎ ሊጎዱ ወደሚችሉ የሰውነታችን ክፍሎች የመሳሳት ባሕሪ ያለውን ደግሞ ጉዳት ወደማይደርስበት የሰውነት ክፍል ላይ ተጠቅመው ይሠራሉ ።

‹‹ከቆዳ የተሠሩ ምርቶች ዋጋቸው የማይቀመስ ነው›› የሚለው የብዙዎች ሀሳብ ይመስላል። አየለም አቅም ያለው ሰው ሁሉ ሊለብሰው የሚወደው መሆኑን ጠቅሷል። አየለ ሠርቶ የሚያጠናቅቀውን ልብስ ዋጋ ለማውጣት የተጠቀመው ቆዳ፣ ገበር ዚፕ እና ቁልፍ የሚጠቀመው የሰው ጉልበት በዋጋው ላይ የራሳቸው አስተዋፅዖ አላቸው። አንዳንድ ጊዜ የሚሠራው ዲዛይን ለየት ያለ በሆነ ቁጥር የሚወስደው ጊዜም ዋጋው እንዲጨምር ያደርጋል።

ከገበያ አኳያም አቶ አየለ የቆዳ ሥራዎቹን ለራሱ ደንበኞች በመሸጥ እና የተለያዩ ባዛሮች ላይ ሥራዎችን ይዞ በመቅረብም ይሸጣል። ከዚህም ባለፈ ለተለያዩ ሱቆች በብዛት ያስረክባል ።

የሚሸጣቸውን ልብሶች ከሦስት ሺህ ብር ጀምሮ ለገበያ እንደሚያቀርብ ጠቅሶ፣ ከፍ ያሉ ካቦርቶችን እስከ አምስት ሺህ ብር ዋጋ ለገበያ ያቀርባል። በአብዛኛው ከቆዳ የተሠሩ አልባሳት በክረምት ወቅት እንደሚፈለጉም ተናግሯል። አንድ ከቆዳ የተሠራ ልብስ መልበስ የፈለገ ሰው እንዳይጨማደድ በመስቀያ አድርጎ ማስቀመጥ፣ ውሀ በነካው ጊዜ በጨርቅ በመወልወል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርበትም ያስገነዝባል።

የቆዳ አልባሳት ተመራጭ የሚያደርጋቸው ሌላኛው ጉዳይ ረጅም ጊዜ መቆየታቸው መሆኑን ጠቅሶ፣ በጊዜ ሂደት ቀለማቸው ሊደበዝዝ፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሊጎዱ እንደሚችሉም ይገልጻል። በዚህ ጊዜ ቀለም በመቀባት የተጎዳውን ቦታ በማደስ እና አንዳንዴም መቀየር በሚችሉ ሞዴሎች መቀየር እንደሚቻልም ጠቁሟል። የቆዳ ልብስ ሙሉ ለሙሉ እድሳት ከተደረገለት እስከ አራት ዓመት እንደሚቆይ አስታውቆ፣ ጥንካሬ እንዳለው ባለሙያው ነግሮናል።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You