ይህችን ምድር በ1946 ዓ∙ም በቀድሞው ጎጃም ክፍለ ሀገር፣ አነደድ ወረዳ፣ ዳማ ኪዳነ ምህረት መንደር ሲቀላቀል ሀገር፣ መንደር፣ ቀዬው፣ ቤቱም ሰላም ነው፡፡ የሚያምር ልጅነት ነበረው፤ አባቱ ቄስ ታምር ጥሩነህ ልጃቸው እንደሳቸው መንፈሳዊ እንዲሆን በማሰብ ይመስላል ዘወትር ወደ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ ከመዝሙረ ዳዊታቸው ጋር ከእጃቸው የማይነጥሉት ተወዳጅ ልጃቸው ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል መጠነኛም ቢሆን አቋቋሙንም ሆነ ከበሮ አመታቱን ቀስሟል፡፡ ከቤቱ አራት እህትና ሦስት ወንድሞች አሉት፣ ዓለሙ ሙሉ ናት፡፡
የሥሙ ነገር ጂጂ “ሥም የለኝም በቤቴ” እንዳለችው ነው፡፡ ዋና መጠሪያ ሆኖ ከሕዝብ ጋር የተዋወቀበትን “ሙሉቀን” ያወጣችለት እህቱ ስትሆን፣ ወላጅ እናቱ ወይዘሮ እናትነሽ ጌታሁን ደግሞ “ሙሉሰው” ትለው ነበር፡፡ የዚህ ምክንያቱ እሱን ከመውለዳቸው በፊት አስወርዷቸው ስለነበር፤ እንዲሁም፣ ከሱ በላይ ያሉት አራት ታላላቆቹን ሲወልዱ በከባድ ምጥ ስለነበርና ሙሉቀን ሲወለድ በቀላል ምጥ መገላገላቸውን ተከትሎ ሙሉሰው አሉት፡፡ አባት በሌላ ወገን ቀይ፣ ድንቡሽቡሽ ልጃቸውን “ሥማቸው” ይሉታል፤ በመሬት የተነሳ ሙግት ቢጤ ገጥሞ ነበርና ከሳሾችህን ሥማቸው ሲሉት ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ ስያሜ የእህቱ ስያሜ ጎልቶ ሙሉቀን የሚለው ገኖ ዋና መጠሪያው ሆኖ ጸደቀ፡፡
በልጅነት እድሜው ከምንም በላይ የሚወዳቸው እናቱ ወይዘሮ እናትነሽ በለጋ እድሜው መሞታቸውን ተከትሎ ሕይወት በእነ ሙሉቀን ቤት እንደቀድሞ በሰላም ልትቀጥል አልቻለችም፡፡ በዚህ መከፋት ውስጥ እንዳለ አጎቱ መለሰ ገሰሰ ሊጠይቋቸው መኖሪያቸውን ካደረጉበት አዲስ አበባ ወደ እነ ሙሉቀን መንደር ዘለቁ፡፡ በወቅቱ ከገጠር ልጅ ላሳደግ ብሎ መውሰድ የተለመደ ነበርና አጎቱ በቤቱ ካሉት ስምንት ልጆች ሙሉቀንን መርጠው “እኔ አሳድገዋለሁ” ብለው ወደ ከተማ ወሰዱት፡፡ መኖሪያው አዲስ አበባ፣ ኮልፌ ሰፈር ሆነ። እንደመንደሩ ሕፃናትም ትምህርት ቤት ተመዘገበ። ታዲያ አጎቱ እንዲማርበት በገዙለት ደብተር ላይ “ሙሉቀን መለሰ” ብለው አጎትየው ጻፉ። ከዛን ጊዜ ጀምሮ ሙሉቀን መለሰ በሚለው ፀና።
ከአጎቱ ጋር ኑሮውን ቢገፋም የአጎቱ ቤት ኑሮ ብዙም የሚያወላዳ አልሆነለትም፡፡ በተለይ ከአጎቱ ሚስት ጋር መስማማት ከብዶታል፡፡ በዚህ መከፋት ውስጥ እያለ ኮልፌ አጠና ተራ የአባት ጡረተኞችና ወላጅ ያጡ ሕፃናትን የሚቀበል ድርጅት መኖሩን ሰማ፡፡ አላንገራገረም፤ ሄዶ ይቀበሉት ዘንድ ጠየቀ። ጥያቄው ተቀባይነት አገኘ። በተለይ የማሳደጊያው አስተዳዳሪ ተወዳጅ ልጅ ነበር፤ ኤልቪስ የሚል ቅጽል ስም አውጥተውለት ነበር፡፡ ወጣ ሲሉ ልብስ ይዘውለት ይመጡ ነበር፡፡ ወደፊትም ወደውጭ ሀገር ልከው እንደሚያስተምሩት ቃል ገብተውለት ነበር። እዛው ማሳደጊያ ውስጥ የሙዚቃ ትምህርት ቤት መከፈቱን ተከትሎ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ሙዚቃ መማር ጀመረ።ለስድስት ወር ያህል እንደተማረ የእህቱን መታመም ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት አቀና፡፡
ከጎጃም መልስ የሙዚቃ ትምህርቱን አልቀ ጠለበትም። ይልቁንስ በሻይ ቤት ተቀጥሮ እራሱ ለእራሱ ለመኖር መፍጨርጨር ቀጠለ፡፡ አንድ ቀን የጎረምሶች አብሮ ማምሸት የተለመደ ነውና ሙሉቀን ከእኩያ ጓደኞቹ ጋር ሳይታወቃቸው በጨዋታ መሃል የሰዓቱን መምሸት ልብ ሳይሉት ይቆያሉ፡፡ ሳያስቡት ሰዓቱ ሄዶ ነበርና አንዱ ጓደኛቸውን ለመሸኘት ወደ ዳጃች ውቤ ያቀናሉ፤ በዚህ የምሽት ጉዞ የውቤ በረሃ መብራቶች ማርከውታል፡፡ በተለይ ለጓደኛሞቹ የአንደኛው ቤት ውበት ከሌሎቹ የተለየ የውቦች ውብ ሆኖባቸዋል፡፡ “ምንድነው?” ብለው ሲያጣሩ ፈጣን ኦርኬስትራዎች የሚጫወቱበት ፓትሪስ ሉሙምባ የምሽት ክበብ መሆኑ ይነገራቸዋል፡፡ ሲያጣሩ የቤቱ ባለቤት ወይዘሮ አሰገደች አላምረው መሆናቸውን ይደርሱበታል፡፡ “ሥራ ይስጡኝ ብል እሺ ይሉኛል?” ሲል በቅርብ ያለን ባለሱቅ ቢጠይቅ “ጻፍና ጠይቃቸው” ሲል ወረቀትና እስክሪብቶ ሰጠው፡፡ ከጓደኞቹ ጋር ወደ ውስጥ ገብቶ የጻፈውን ደብዳቤ ለኦርኬስትራ መሪው ሰጠ፡፡
የኦርኬስትራው መሪ ከትንሽዬ ልጅ የተሰጠው ደብዳቤ ያሳቀው ከመሆኑም በላይ ነገሩን ብዙም ከቁም ነገር አልወሰደውም ነበር፡፡ ሁኔታውን ከርቀት የተከታተሉት የቤቱ ባለቤት “ምንድነው?” ሲሉ ጠየቁ። የባንዱ አስተባባሪ በሳቅ ታጅቦ ባለ ደብዳቤው ትንሽዬ ልጅ ፈተና ፈትነውት ካለፈ እንዲቀጥሩት መጠየቁን በሳቅ ታጅቦ ነገራቸው፡፡ ወይዘሮ አሰለፈች “ፈትነውና እየው፤ ካለፈ ይገባል፤ ካልሆነ ሌላ ሥራ እሰጠዋለሁ” አሉ፡፡ በወቅቱ ሙሉቀን በኋላ እንደሚገልጸው በሁሉ ነገሩ ጥላሁንን ለማስመሰል የሚሞክርበት ዘመን ነውና በባዶ እግሩና በቁምጣ ሆኖ “ለእውነት እሞታለሁ፣ አልሳሳም ለነፍሴ” እና “እንክርዳድ እንክርድድ” የተሰኙትን የጥላሁንን ዘፈኖች አቀነቀነ፡፡ በብቃቱ የተማረኩት የምሽት ቤቱ ሠራተኞች የዛኑ ማታ መዋጮ አዋጡለት፡፡ በነጋታው ካኪ ልብስ ተገዛለት። ሱፍ ተለካ፣ ጫማ ተገዝቶለት ተጫማ፡፡ በቤቱ ባለቤት ወይዘሮ አሰለፈችና በሕፃኑ ሙሉቀን መሃል ውል ታሰረ፡፡ ውሉ ሙሉቀን ማታ ማታ በቤታቸው ሊዘፍን፤ እሳቸው በወር 90 ብር ደመወዝ ሊከፍሉት ነው፡፡ በወቅቱ 90 ብር ብዙ ነበርና እሱም “ሚልየነር የሆንኩ መሰለኝ” በማለት በአንድ ወቅት በ1973 ዓ.ም ከደራሲ ስብሀት ገብረእግዚአብሔር ጋር በጸደይ መጽሔት ላይ በነበረው ቃለመጠይቅ ተናግሮ ነበር፡፡
ውብ መልኩ፣ ማራኪ ድምጹ፣ ቅልጥፍናው ታክሎበት የምሽት ቤቱን ሕይወት ለመደ፡፡ በለጋ እድሜው በምሽት ክበቡ አድማጭ የሚይዝ ሆነ፡፡ ያም ቢሆን ብዙ አልዘለቀም፡፡ የፖሊስ ኦርኬስትራ አባላት ዓይናቸውን ጣሉበት፡፡ ገና በቅጡ 16 ዓመት ሳይሞላው ፓትሪስ ሉሙምባ ምሽት ክበብ ውስጥ ከሚጫወትበት ፈጣን ኦርኬስትራ አስኮብልለው የፖሊስ ኦርኬስትራን ተቀላቀለ፡፡ በወቅቱ የኦርኬስትራው ትንሹ ሙዚቀኛ ነበርና በሁሉም ዘንድ ተወዳጅ ነበር፡፡ ኦርኬስትራውን በተቀላቀለበት ወቅት ተወዳጆቹ ደራሲዎች ሰለሞን ተሰማ “የዘላለም እንቅልፍ” የተሰኘ ሥራ፤ ጋሽ ተስፋዬ አበበ “ያ ልጅነት”፣ “እናቴ ስትወልደኝ መች አማካረችኝ”፣ “እምቧይ ሎሚ መስሎ” የተሰኙና ሌሎች ሥራዎችን ለሱ አስበው፤ ግጥምና ዜማ ሠርተውለት በግሩም ሁኔታ ተጫወታቸው፡፡
ምንም እንኳን የራሱን ሙዚቃ መጫወቱና ከኦርኬስትራው ጋር በርካታ ቦታዎች ተዘዋውሮ በመሥራቱ ዝናው ቢናኝም ከፖሊስ ኦርኬስትራ በገዛ ፈቃዱ በመልቀቅ በግል ባንዶች ተዘዋውሮ ሠርቷል። ከዚህ ውስጥ ረዥም ጊዜ በዳህላክ ባንድ ቆይታ ቢያደርግም ከኢትዮ ስታር ባንድ፣ ከኢኪዌተርስ ባንድ፣ ከሮሃ ባንድ፣ እንዲሁም ከሙላቱ አስታጥቄ ጋር ሠርቷል፡፡ ከኦርኬስትራው ከተለያየ በኋላ “የዘላለም እንቅልፍ” እና “ያላየነው የለም” የሚሉ ዘፈኖቹን በሸክላ አስቀርጾ ለአድማጭ በመድረሳቸው ዝናው ይበልጥ ናኘ፡፡ ሙሉቀን ከሠራቸው ተወዳጅ ዘፈኖች መሃል “ሆዴ ነው ጠላትሽ”፣ “ሰውነቷ”፣ “መውደዴን ወደድኩት”፣ “ይረገም ይህ ልቤ”፣ “ውቢት”፣ “ወተቴ ማሬ”፣ “ምነው ከረፈደ”፣ “ናኑ ናኑ ነይ”፣ “ተነሽ ከልቤ ላይ”፣ “ውሃ ወላዋይ” የሚሉት ሥራዎቹ ከሌሎቹ በተለየ በበርካታ አድማጮች ዘንድ የሚታወሱ ሥራዎቹ ናቸው፡፡
ከሠራቸው በርካታ ሙዚቃዎች ውስጥ በሙዚቃ ጥራት ሰውነቷና ሆዴ ነው ጠላትሽ በአሰራር ደግሞ ሙላቱ አስታጥቄ ያቀናበራቸውና ከዳህላክ ባንድ ጋር የዘፈናቸው ቼ በለውና ውቢት የተሰኙት ሥራዎች ከሌሎች ሥራዎች ይልቁበታል፡፡ ለሙሉቀን ዘፈኖች አሁን ድረስ መወደድ በተፈጥሮ የታደለው ተሰጥኦ እንዳለ ሆኖ፤ ዜማና ግጥም ሲመርጥ የሚያደርገው ጥንቃቄ፣ ለሙዚቃ ቅንብር የሚሰጠው ትኩረትና ከባለሙያዎቹ ጋር ተናቦ መሥራቱ የሥራው ጥራት ላይ ይታያሉ፡፡ (በነገራችን ላይ ሙሉቀን ድራምን ጨምሮ ሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎችን አሳምሮ ይጫወታል፣ በብዙ ድምፃውያን ሥራ ላይም ድራመር ሆኖ ሰርቷል)። እሱ ሙዚቃን በቃሽኝ ካላት 37 ዓመታትን ቢሻገርም አሁን ድረስ በበርካታ የሀገራችን የሙዚቃ ወዳጆች ዘንድ የድምጻዊያን ቁንጮ ቦታነትን እንደተቆናጠጠ ዘልቋል፡፡ እሱ ሙዚቃን ከተሰናበተ በኋላ የተወለዱ በርካቶች የሚሰሙት ደግሞም የሚያዜሙት ተወዳጅ ድምጻዊ ነው፡፡
እሱ ጋ ሙዚቃን ለመሥራት ጥድፊያ የለም። ከተለያዩ ደራሲዎች የሚሰጠውን ግጥምና ዜማ ለመምረጥ ጊዜ ይወስዳል፤ በየሄደበት ሰዓት ሰጥቶ ይሰማል፤ በዚህ ሂደት የማይሆነውን ይጥላል፤ ማሻሻል የሚፈልገውን ዜማና ግጥም ያሻሽላል፡፡ አንዱን ከአንዱ ቀላቅሎ የተሻለ ግጥምና ዜማ ያዘጋጃል፡፡ በዚህ የተነሳ የሱ ሥራዎች አሁን ድረስ በልዩነት ይወደዳሉ፡፡ በአንድ ወቅት ሁለገብ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ የሆነችውና ለሙሉቀንም በርካታ ግጥሞችን የሰጠችው ዓለምፀሐይ ወዳጆ በሙዚቃው ዘርፍ በሀገራችን በግጥምና ዜማ ረገድ ይፈጸም የነበረውን አነስተኛ ክፍያ ያሻሻለና የግጥምና ዜማ ደራሲዎች የተሻለ ክፍያ እንዲያገኙ ያስደረገ ድምጻዊ መሆኑን መስክራለች፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ሙዚቃን ወደፊት ያራመደ በመሆኑ በበርካታ የሙዚቃ ባለሙያዎች ‹‹የኢትዮጵያ ሙዚቃ አብዮተኛ›› ተደርጎ እንዲታይ አድርጎታል፡፡
ሙሉቀን በተወዳጅ የሙዚቃ ሥራዎቹ አሁን ድረስ ሥሙ ቢነሳም ዓለማዊ ሙዚቃን የሠራው ግን ለ17 ዓመታት ብቻ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ዓለማዊ ሙዚቃ በቃኝ ብሎ የመንፈሳዊውን ዓለም ተቀላቅሎ በዝማሬ ከ37 ዓመታት በላይ አገልግሏል፡፡ ሆኖም አሁንም ሙዚቃዎቹ እንደ አዲስ የሚያጣጥሙ ትውልዶች መፈጠራቸውን አላቆሙም፡፡ ሙሉቀን ከሙዚቃው ዓለም የተለየበት ወቅት በዝና ማማ ጫፍ የነካበት፣ የተሻለ ተከፋይ የሆነበትና በየቦታው ፈላጊው የበዛበት ወቅት በመሆኑ ማንም ይህ ይመጣል ብሎ ስላልጠበቀም በሙዚቃ ሥራው የሚወዱት በርካቶችን ያሳዘነ ውሳኔ ነበር፡፡
በበፊት ሕይወቱ ብዙም አማኝ አልነበረም፡፡ ለዚህም አንዱ ምክንያቱን ሲያስረዳ ከችግሩ ያመልጥና በአቋራጭ ሀብታም ይሆን ዘንድ ፈጣሪውን ተማምኖ ሎተሪ ይገዛል፤ ለፈጣሪውም ሎተሪው እንዲደርሰው አደራ ይለዋል፡፡ ግን ሎተሪው ሳይደርሰው ይቀራል። ያኔ ታዲያ ፈጣሪን ተማምኖ ከመማጸን “ፈጣሪ የለም” ወደ ማለት ይሸጋገራል፡፡ ሎተሪውም ሳይደርሰው፤ እሱም ከፈጣሪው ጋር እንደተኳረፈ ኑሮ ይቀጥላል፡፡ ሙሉቀንም በሙዚቃ ሥራው የተሻለ ዝናም፣ ብርም ያገኛል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ከሙዚቃ ልምምድ መልስ የተወሰኑ የባንዱ አባላት ወደ “ቸርች” ሲሄዱ አብሬያችሁ እሄዳለሁ በማለት ያቀናል፡፡ በወቅቱ ፈጣሪ የለም ብሎ ይከራከራቸው ስለነበር ግር ቢሰኙም፤ ከፈለገ ይምጣ በማለት አብሮአቸው ይጓዝ ዘንድ ፈቀዱ፡፡ ወደ ቸርች የጀመረው ምልልስ ዘፈን እየሠራ፣ ያለማቋረጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና በጸሎት ፕሮግራሞች መካፈሉን ቀጠለ፡፡ በሂደትም ከመጠጥና ከሲጋራ ጋር የነበረው ቁርኝት ተፋታ፡፡
የዘመኑ ተወዳጅ ድምጻዊ ነውና በርካታ ታዋቂ ሰዎችና ባለሥልጣናት የሱን ቤት ለመዝናናት ይመርጡት ነበር። እሱም እንግዳ ለማስተናገድ ይሆነው ዘንድ የእንግዶቹን ምርጫ ታሳቢ ያደረጉ የመጠጥ ዓይነቶች በቤቱ አዘጋጅቶ እንግዶቹን ይጠብቅ ነበር፡፡ ያኔ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት ይበልጥ ሲጠጋ እንግዶችን በመጠጥ ከማስተናገድ መቆጠብ ጀመረ፡፡ በዚህ ዓይነት ሂደት ከሙዚቃ ሳይለያይ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት ተስቦና ከሱስ ነፃ ሆኖ ወደ ስድስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ቆይቷል፡፡ በዚህ መሃል ለሙዚቃ ሥራ ወደ አሜሪካ አቀና፡፡ በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች ተዘዋውሮ የሙዚቃ ሥራውን አቀረበ፡፡ ከአንድ ዓመት ከግማሽ የአሜሪካ የሙዚቃ ሥራ ቆይታ በኋላ “ከዛሬ ጀምሮ ከሙዚቃ ሥራ አሰናብቼሃለሁ” የሚል ድምጽ መስማቱንና ይህን ቀን ሲጠብቀው የነበረ በመሆኑ በርካቶች ማመንና መስማት ባይፈልጉም “ሙዚቃ በቃኝ” ብሎ ለመለየት መወሰኑን በአንድ ወቅት ከኢቢኤስ ቴሌቪዥን የ“እንጫወት” ፕሮግራም አዘጋጆች ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል፡፡
ያለፉትን 37 ዓመታት መኖሪያውን በሀገረ አሜሪካ ቨርጂኒያ አድርጎ የቆየ ሲሆን፤ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ሳይመለስ ቆይቷል፡፡ ለረዥም ጊዜ በሕክምና ሲረዳ ቢቆይም፣ በተወለደ በ70 ዓመቱ ሚያዝያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ሕይወቱ አልፏል፡፡ የቀብር ሥነ-ሥርዓቱም ሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም የሕይወቱን ረዥም እድሜ በኖረባት አሜሪካ ተፈጽሟል፡፡ ለወዳጅ ዘመዶቹ እንዲሁም አድናቂዎቹ መጽናናትን በመመኘት አበቃን።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም