‹‹በማንዴላ ዋንጫ›› የቦክስ ፍልሚያ ለውጤት የሚያበቃ ዝግጅት ተደርጓል

በነፃነት ታጋዩና በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ መታሰቢያነት የሚካሄደው ‹‹የማንዴላ ዋንጫ›› የቦክስ ውድድር እአአ ከሚያዝያ 15-21 በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ ይካሄዳል። የኢትዮጵያ ቦክስ ብሔራዊ ቡድንም በዚህ ውድድር ተሳታፊ ነው። ብሔራዊ ቡድኑ ለዚህ ውድድር ተሰባስቦ ዝግጅት ከጀመረ 15 ቀን ሆኖታል። እያደረገ የሚገኘው ዝግጅትም ጠንካራና ለውጤት የሚያበቃ መሆኑን የቡድኑ አሰልጣኝና ቦክሰኞቹ ገልጸዋል።

የቦክስ ብሔራዊ ቡድኑ የሀገር ቤት ዝግጅቱን አጠናቆ ዛሬ ጉዞውን ወደ ውድድሩ ስፍራ ያደርጋል። ቡድኑ ከመጋቢት 24 ጀምሮ መቀመጫውን ቱሊፕ ሆቴል በማድረግ በጃንግል ቦንግ፣ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ በራስ ሀይሉ እና በፕላቲኒየም ጂምናዚየሞች የውድድሩን ስፍራ ባማከለ ሁኔታ በቀን ሁለቴ ልምምዱን ሲሰራ ቆይተል። ቡድኑ በአፍሪካ ጨዋታዎች ተሳትፎው ሜዳሊያ ያመጡ ቦክሰኞች እና በአንደኛው ዙር የቦክስ ቻምፒዮና ተጫውተው ውጤት ያስመዘገቡ የቡጢ ተፋላሚዎችን አካቶ ዝግጅቱን በማድረጉ በደርባኑ ውድድር ውጤት እንደሚጠብቁ ዋና አሰልጣኙ ዋና ኢንስፔክተር ቴዎድሮስ ጥላሁን ተናግረዋል።

አብዛኞቹ ቦክሰኞች ልምድ ባይኖራቸውም በክለቦቻቸው ጠንካራ ተፎካካሪዎች መሆናቸውን የገለጹት አሰልጣኙ፤ የቡድኑ የአካል ብቃት፣ ቴክኒክና የታክቲክ ስልጠናዎችን በማሳደግ ክፍተቶችን ተለይቶ መስራቱን አስረድቷል። በዚህም መሰረት አዳዲስ የሆኑትን እና በዓለም አቀፉ ቦክስ ፌዴሬሽን አማካኝነት የሚወጡትን ሕጎች በመለየት ዝግጅቱ እንደተደረገ ገልጸዋል። ስፖርተኞቹ በታክቲክ፣ ቴክኒክና በአካል ብቃቱ ረገድ ጥሩ የሚባሉና ውጤት ማምጣት የሚችሉ ወጣቶች በመሆናቸው ውድድሮችን ለማሸነፍ ያላቸው ጉጉትም ከፍተኛ እንደሆነ አሰልጣኙ ተናግረዋል።

የቡድኑን የአሸናፊነት ስነልቦና ለመገንባት በባለሙያ እና ልምድ ባላቸው ስፖርተኞች እና አሰልጣኞች በመታገዝ ስልጠና አግኝተዋል። ዝግጅታቸውን በትልቅ ሞራልና ተነሳሽነት ማድረጋቸውንም አክለዋል። በዝግጅቱ ወቅት በሚደረገው ልምምድ ሴቶችና ወንዶች እኩል በሆነ ደረጃ በትጋት እየሰሩ ለውጤት የሚያበቃ ዝግጅትን እንዳደረጉም አስረድተዋል።

ስፖርቱ በአፍሪካ ጨዋታዎች ውጤት እንደሚመዘገብበት በተግባር ታይቷል። ባለሀብቱና መንግሥት ትኩረት ቢሰጡት ከዚህ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይችላል። ለሚደረገው ዝግጅት ፌዴሬሽኑ ጥሩ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፤ አመርቂ ውጤት ለማምጣት የሁሉም ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን አሰልጣኙ ጠቁመዋል።

የብሔራዊ ቡድን አምበል አብረሃም አለም፣ ቡድኑ ከጋናው ውድድር መልስ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነና ሰፊ የመዘጋጃ ጊዜን እንዳገኘ ይናገራል። የቦክስ ስፖርት በመነቃቃት ላይ እንደሆነ የሚናገረው አብረሃም በጥሩ ሁኔታ እንደተዘጋጁና የተሻለ ውጤት እንደሚመጣም ተስፋ አድርጓል። አሰልጣኞቹ በቂ ልምድ ያላቸው በመሆኑ ለቡድኑ የሚያስፈልጉ ስልጠናዎችን እንደሰጡ እና ከስልጠና መልስ ስፖርተኞቹ የሚያገኙት አገልግሎትም ዝግጅቱን የሚመጥን እንደሆነ አስረድተዋል። ሀገርን በተለያዩ ውድድሮች በመወከል የብር ሜዳሊያ ማምጣት የቻለው ይህ ቦክሰኛ፤ ከዚህ በፊት በነበሩ ውድድሮች በጥቂት ስህተት ቢሸነፍም፣ ይሄንን በማረም ወርቅ ይዞ ለመምጣት ተዘጋጅቷል። የቡድን መንፈስ ላይ የተሰራው ሥራ ትልቅ መሆኑን የተናገረው አብረሃም፤ እሱና የቡድኑ አባላት 11 ወርቅ ሜዳሊያዎችን ለማምጣት እንዳሰቡም ገልጿል።

ሌላዋ የብሔራዊ ቡድኑ አባል ምክትል ሳጅን ሮማ አሰፋ በበኩሏ የተደረገው ዝግጅት በቡድን መንፈስ የመወዳደር ስሜትና ከሚሰጠው ስልጠና አኳያ ጥሩ መሆኑን ገልጻለች። ለውድድር የሚያበቃ ዝግጅት በመደረጉ ሜዳሊያውን በሙሉ የመውሰድ አቅም እንዳላቸውም ተስፋ አላት።

በዚህ ውድድር ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ41 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ 360 ቦክሰኞች በ12 የሴቶችና በ13 የወንዶች ሚዛን ለአህጉሪቱ ክብር ይፋለማሉ።

የኢትዮጵያ ቡድን በአንድ ዋና እና ምክትል አሰልጣኝ ዝግጅቱ እየተመራ ውድድሩ የሚያካድ ሲሆን፤ በተለያዩ ኪሎ ግራሞች 4 ሴትና 7 ወንድ በድምሩ 11 ቦክሰኞችን በመያዝ ይፎካከራል። በወንዶች 51 ኪሎ ግራም ፍትሐዊ ጥሙይ፣ በ54 ኪሎ ግራም ሱራፌል አላዩ፣ በ57 ኪሎ ግራም አብዱሰላም አቡበከር፣ በ60 ኪሎ ግራም አቡበከር ሰፋን፣ በ63 ኪሎ ግራም አብረሃም አለም፣ በ67 ኪሎ ግራም ኤርሚያስ መስፍን እና በ75 ኪሎ ግራም ተመስገን ምትኩ ኢትዮጵያን ይወክላሉ። በሴቶች ደግሞ በ52 ኪሎ ግራም ቤቴልሔም ገዛኸኝ፣ በ54 ኪሎ ግራም ሮማን አሰፋ፣ በ60 ኪሎ ግራም ሚሊዮን ጨፌ እና በ66 ኪሎ ግራም ቤቴል ወልዴ ተካተዋል።

ዓለማሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You