የፀጥታው ምክር ቤት ፍልስጤም ባቀረበችው ጥያቄ ላይ ሳይስማማ ቀረ

የፀጥታው ምክር ቤት ፍልስጤም ባቀረበችው ጥያቄ ላይ ሳይስማማ ቀረ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት አባላት የፍልስጤም አስተዳደር ባለስልጣን ባቀረበው ሙሉ የተመድ አባልነት ጥያቄ ላይ አልተስማሙም።

ጥያቄውን አዲስ አባል ለሚቀበለው የተመድ ኮሚቴ ያቀረቡት የሚያዝያ ወር የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የማልታዋ አምባሳደር ቫኔሳ ፍራዚየር በተደረገው ዝግ ስብሰባ “ስምምነት የለም” ብለዋል።

አምባሳደሯ አክለውም እንዳሉት “ነገርግን አብዛኞቹ የአባልነት ጥያቄውን ደግፈውታል።”

አባል ሀገራቱ በጥያቄው አስፈላጊነት ላይ ተስማምተው ቢሆን ኖሮ ለምርጫ ወደ ምክር ቤቱ ይቀርብ ነበር።

በተመድ የፍልስጤም ተወካይ ርያድ መንሱር የፀጥታ ምክር ቤት የሙሉ አባልነት ጥያቄያችንን በመቀበል ዓለም አቀፍ መግባባት የተደረሰበትን የ’ቱ ስቴት ሶሉሽንን’ ለመፈጸም ቁርጠኛ ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረው ነበር።

ፍልስጤም ከ12 ዓመታት በፊት በመተድ የታዛቢነት ቦታ ተሰጥቷታል።

የፍልስጤም አስተዳደር ሙሉ የተመድ አባል ለመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ጥያቄ ያቀረበው በ2011 ነበር።

በተመድ የእስራኤል አምባሳደር ጊላድ ኢርዳን ፍልስጤም ለእስራኤል የደህንነት ስጋት ነች ሲሉ ጥያቄውን አስቀድመው ተቃውመዋል።

አምባሳደሩ ለእስራኤል የሀገርነት እውቅና መስጠት የተመድን ቻርተር የሚጥስ እና በድርድር ዘላቂ መፍትሔ እንዳይመጣ የሚያደርግ ነው ሲሉ ተቃውመዋል።

የአረብ ሀገራት ከእስራኤል ጎን የፍልስጤም ሀገር ማቋቋም የሚያስችለው ‘የቱ ስቴት ሶሉሽን’ ተግባራዊ ካልሆነ በመካከለኛው ምሥራቅ ዘላቂ ሰላም አይመጣም የሚል አቋም ይዘዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You