ፊክ መጨናነቅ የፈተነው የመንገድ ግንባታ በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ሰፋፊ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል፡፡ መንገዶቹ ማሳለጫዎች፣ ትላልቅ ድልድዮች፣ ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች የተገነባላቸው መሆናቸው ለተሽከርካሪ የትራፊክ አንቅስቃሴም ሆነ ለእግረኞች ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ እንደዚህ አይነቶቹ የመንገድ ግንባታዎች አሁንም በኮርደር ልማቱና በሌሎች ፕሮጀክቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
ከተማዋ በሁሉም መውጫ በሮቿ በኩልም ተመሳሳይ ግንባታዎችን ስታካሂድ ቆይታለች፤ እያካሄደችም ትገኛለች፡፡ በከተማዋ መውጫ በሮች ከተገነቡት የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል የቃሊቲ ቱሉዲምቱ መንገድ ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳል፡፡ ይህ መንገድ ምን ያህል የትራፊክ አንቅስቃሴውን እንዳሳለጠው ይታወቃል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ አሁንም በከተማዋ መውጫ ላይ አንድ የመንገድ ፕሮጀክት መገንባት ጀምሯል፡፡ ይህ መንገድ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ የሚታይበት ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደጠቆሙት፤ ይህ መንገድ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ይታይበታል፤ የእግረኛና የተሽከርካሪ መንገዶቹ በአግባቡ ፍሰቶቹን በሚመጥን መልኩ ያልተገነቡ በመሆናቸው ሁሌም አደጋዎች ይደርሳሉ፡፡ ይህን ተከትሎም የሰው ሕይወት ያልፋል፤ የንብረት ውድመት ይደርሳል፤ በትራፊክ መዘጋጋት ሳቢያም በሕዝብ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል ሲደርስ ይስተዋላል፡፡
በተለምዶ የጅማ በር በመባል የሚታወቀው የዚህ አየር ጤና ወለቴ መንገድ ግንባታም ተጀምሯል፡፡ መንገድ መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ በመንገዱ ሳቢያ የሚታዩ የትራፊክ መጨናነቅና የመሳሰሉትን ችግሮች ለማስቀረት የመንገዱ ግንባታ ሊካሄድ ውል ከተገባ ከዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ይሁንናም ወደ ግንባታ የተገባው በቅርቡ ነው። የአካባቢው ማኅበረሰብ በጉጉት የሚጠብቀው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት አሁንም በሚፈለገው ፍጥነት እየሄደ እንዳልሆነ እየተጠቆመ ነው።
ለእዚህ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት መፋጠን የወሰን ማስከበር እንዲሁም የውኃ፣ የመብራት እና የመብራት ተቋማት ቅንጅታዊ ሥራ ወሳኝ መሆኑ ይታመናል፡፡ ይሁንና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ከአንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይዞ እያስገነባ የሚገኘው የአየር ጤና፣ ካራ፣ ወለቴ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት የግንባታ ሥራ በተለይ በወሰን ማስከበር እና ተያያዥ ምክንያቶች ዘግይቶ ነው የተጀመረው፡፡ አሁን የሚገኝበት የግንባታ ደረጃም ዝቅተኛ መሆኑ እየተጠቆመ ነው። ግንባታው በትራፊክ እንቅስቃሴው የተጨናነቀ መሆን፣ አማራጭ የትራንስፖርት መንገድ በአካባቢው ባለመኖሩ ምክንያት በሚፈለገው ፍጥነት እየተሠራ ላለመሆኑ ይገለጻል።
አቶ ለሜቻ ቶላ ተወልደው ያደጉት ከአየር ጤና ወደ ወለቴ በሚወስደው ቀደም ሲል ረጲ ጉለሌ አሁን ደግሞ ግራር በተባለው በዚሁ አካባቢ ነው። በዚሁ አካባቢም ለረጅም ጊዜ ኖረዋል፡፡ በአካባቢው በጣም አስከፊ አደጋዎችን መመልከታቸውን ጠቅሰው፣ በዚህ መንገድ ጥበት የተነሳ አባታቸውንና የአባታቸውን ወንድም በትራፊክ አደጋ ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ እግረኛውና ተሽከርካሪው በመንገዱ እየተጋፉ ነው የሚሄዱት፡፡ የዚህ መንገድ ግንባታ ሥራ መጀመር መልካም ቢሆንም፣ ወደፊትም እንዳይጠብ ከዚህ በበለጠ ስፋት መሠራት አለበት ሲሉ ያስገነዝባሉ። መንገዱ ለእግረኛው ሰፋ ብሎ እግረኛውን ከተሽከርካሪው ራቅ በማድረግ መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
መንገድ አንድን አካባቢ ለመለወጥ ወሳኝ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ለሜቻ፣ በጀሞ አካባቢ ጨፌ ፉሪ ሜዳ በሚባል አካባቢ እየሄዱ እግር ኳስ ይጫወቱ የነበረበት አካባቢ በአካባቢው የተሻለ መንገድ መገንባቱን ተከትሎ አካባቢው እድገት ማሳየቱን ተናግረዋል፤ የአየር ጤና ወለቴ መንገድ ሥራም በፍጥነት ተጠናቅቆ ለማየት ጉጉት እንዳደረባቸው አመላክተዋል።
አቶ ብሥራት ጥላሁን በአካባቢው ለረጅም ዓመታት ኖረዋል፤ ይህ ብቻም አይደለም፤ ለረጅም ዓመታትም በተለያዩ አካባቢዎች አሽከርካሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ አቶ ብሥራት መንገድ ለአንድ አካባቢ እድገት እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው ይላሉ። የተሻለ መንገድ ሲኖር ርቀት ያለው አካባቢ ቢሆንም እንኳን በፍጥነት ማሽከርከር እና ካሰቡበት ደርሶ በፍጥነት መመለስ ይቻላል ሲሉ አብራርተው፣ ጅማ መንገድ ተብሎ የሚታወቀውና የከተማዋ መውጫ ከሆኑት አንዱ የሆነው ይህ የአየር ጤና ወለቴ መንገድ የትራፊክ መጨናነቅ በእጅጉ ሲያሳስባቸው መኖሩን ይናገራሉ፡፡
በዚህ መንገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሽከርካሪውና የነዋሪው ቁጥር እየበዛ ሲመጣ መንገዱ እየጠበበ መምጣቱን ይገልጻሉ፡፡ የትራፊክ ፍሰቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጨናነቀ ያለበት ይህ መንገድ ቅድሚያ ተሰጥቶት ቀደም ብሎ ሊሠራ ይገባውም አንደነበር ተናግረዋል። የመንገዱ ሥራ ሲጠናቀቅ የትራፊክ መጨናነቁ መቅረቱ አንድ ነገር ሆኖ አካባቢውም የተሻለ እድገት እንዲኖረው እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡
ለመንገድ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ በተለይ የውሃ፣ የመብራት፣ እና የቴሌ ተቋማት ተቀናጅተው መሥራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። የእነዚህ መሠረተ ልማቶች ባለቤቶች መንግሥታዊ ተቋማት መሆናቸውን ተናግረው.፣ ተቋማቱ ተቀናጅተው በወሰን ማስከበሩ እና ምሰሶዎችን ኬብሎችን፣ እና የመሳሰሉት ማንሳት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ እነዚህ ሥራዎች በፍጥነት እንዲፈጸሙም ጠበቅ ያለ መመሪያ መሰጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
የትራንስፖርት ችግር አንዱ የሚመጣው ከተሽከርካሪ ቁጥር ማነስ ብቻ ሳይሆን ከመንገድ ጥበት ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ ለምሳሌ ከካራ ተነስቶ ሜክሲኮ ለመድረስ ብዙ ጊዜ የሚወስደውና የሰዓት ብክነት የሚከሰተው በትራፊክ መጨናነቅ እና በመንገድ ጥበት ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የከተማዋ መውጫ መግቢያ ጭምር የሆነው የዚህ መንገድ ግንባታ በፍጥነት ተጠናቅቆ ለኅብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
መንገዱ ሰፋ ካለ ፈጣን ምልልስ እንዲኖር ያስችላል፤ ለአካባቢው ኢኮኖሚያዊ አንቅስቃሴ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፤ አካባቢው ውበት እንዲጎናጸፍ በማድረግ ተፈላጊ አንዲሆን ያደርገዋል ሲሉ አብራርተው፣ ግንባታው በፍጥነት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በዚህ መንገድ ፕሮጀክት ሥራ ከወለቴ አካባቢ እየተሠራ ወደ አየር ጤና የሚደረገውን ጉዞ አድንቀው፣ ቱቦዎች ወዲያው አለመሸፈናቸው ጎርፍ በሚያመጣው ቆሻሻ እንዲደፈኑና ሌላ ችግር እንዲሰከት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡ ከሁለት ወራት በሁዋላ ክረምት እንደሚገባም ጠቅሰው፣ በመንገዱ ላይ መጨናነቅ ከመፈጠሩ በፊት ግንባታውን ማፋጠን እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
የወለቴ አየር ጤና መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ተቋራጭ ይርጋዓለም ኮንስትራክሽን ድርጅት የሳይት መሐንዲስ የሆነው ይዲዲያ ብርሃኑ እንዳለው፤ መንገዱ የስትራክቸራል እንቅስቃሴ እየተሠራ ሲሆን፣ የመሬት ላይ ሥራውን በሚፈለገው ፍጥነት ለመሥራት የትራፊክ እንቅስቃሴው ተግዳሮት እየሆነ ነው። አካባቢው ትራፊክ እንቅስቃሴ የሚበዛበት በመሆኑ እና አንዳንድ ጊዜም ሙሉ ሙሉ የሚዘጋጋ መሆኑ በፕሮጀክቱ ግንባታ ሥራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ ይገኛል፡፡
መንገዱንም ለማስፋት የተፈለገበት አንዱ ዓላማ የትራፊክ ጭንቅንቁን ለመፍታት መሆኑን ተናግራል፡፡ መንገዱ የከተማዋ መውጫና መግቢያ መንገድ መሆኑን ጠቅሶ፣ ከትላልቅ እስከ አነስተኛ ተሽከርካሪዎች ድረስ በብዛት አንደሚንቀሳቀሱበት ገልጸል፡፡ በተለይ በሥራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት የሚታየው የትራፊክ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑን ተናግሯል።
የሳይት መሐንዲሱ እንዳለው፤ በዚህ ወር የተሻለ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በግራ በኩል ከአየር ጤና ካራ ድረስ የስትራክቸር ሥራው ተሠርቷል፤ ከከተማ ሲወጣ በቀኝ በኩል ደግሞ አብነት ከሚባል እስከ ወለቴ አንድ ኪሎሜትር ያህል ስትራክቸሩም የመሬት ላይ ሥራውም ተሠርቷል።
ቀጣይ ሥራዎችን ለማከናወንም የትራፊክ መጨናነቁ ማስተጓጎል ሊያደርስ እንደሚችል ስጋቱን ጠቅሶ፣ አሁን ላይ መንገዱን ከትራፊክ እንቅስቃሴ ዝግ አድርጎ ለመሥራት እንዳልተቻለም ነው ያመለከተው፡፡ ማሽኖችም ተሽከርካሪዎችም አብረው እየተንቀሳቀሱ ባለበት ሁኔታ ሥራው እየተሠራ መሆኑን ጠቁሟል።
መንገድ ሲዘጋጋ በግንባታ ሥራው የሚሳተፈው መኪናም ተደርቦ ለመቆም ይገደዳል ሲል ይዲዲያ ገልጸዋል፡፡ አካባቢው ተለዋጭ መንገድ የሌለው መሆኑን ተናግሮ፣ አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገድ እንዲጠቀሙ ለማስገደድ አልተቻለም፤ የትራፊክ ኃይሉ ግን ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል ብሏል። ከአየር ጤና እስከ ካራ ድረስ የወሰን ማስከበር ሥራ ተሠርቶ ዝግጁ መደረጉንም ተናግሯል፡፡
የሳይት መሐንዲሱ የአየር ጤና ወለቴ መንገድ ፕሮጀክት እያከናወነ የሚገኘውና ሀገር በቀል የሆነው ይርጋዓለም ኮንስትራክሽን ረጅም ዓመት ልምድ ያለው መሆኑን ጠቅሶ፣ የራሱ ማሸነሪዎች ያሉት እና ከዚህ በፊትም በጅግጂጋና ሀዋሳ በመሳሰሉት በርካታ የመንገድ ሥራዎች ላይ መሥራቱን ጠቅሷል።
በአየር ጤና አካባቢ ባለው ሳይትም በቋሚነት ከኮንስትራክሽን ስራው ጋር የሚንቀሳቀሱ እና በቅንጅት የሚሠሩ ከውሃ እና ከቴሌ፣ እና ከመብራት ኃይል ተቋማት ባለሙያዎች ጋር እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል። ለእያንዳንዱ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ምላሽ እያገኘን ነው ሲል ነው የተናገረው።
የሳይት መሐንዲሱ፤ በግንባታው የ24 ሰዓት ሥራን ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር አምሽቶ መሥራት በምሽት በፈረቃ የሚሠራባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ጠቅሶ፣ ይህ ሥራ ከትራፊክ መጨናነቁ አንፃር ሥራ ላይ እየዋለ መሆኑን አስታውቋል።
ግብዓት የማምጣት፣ ማሽነሪዎችን የማንቀሳቀስ ሥራዎች በምሽት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት የኮንስትራከሸን ሥራው በጣም እንደሚስተጓጎል ጠቁሞ፣ እርጥበቱንና ፍሳሾችን በማድረቅ የሚሠራበት ሁኔታ እንዳለም ተናግሯል።
እሱ እንዳብራራው፤ የኮንስትራክሽን ድርጅቱ ከበቂ በላይ ማሽነሪዎች አቅርቧል፡፡ በየቦታው የተከፋፈሉ ሳይቶች ሰፊ ስለሆኑ በተለያዩ ቦታዎች ላይ እንቅስቃሴዎች ባሉባቸው ቦታዎች ሁሉ ፎርማኖች፣ ጀነራል ፎርማኖች፣ ረዳት ፎርማን፣ የሰዓት ተቆጣጣሪዎች መኖራቸው እና ሌሎች ባለሙያዎች በተዋረድ የሥራ ክትትል እና ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።
አብዛኛዎቹ በፕሮጀክቱ ሥራ እየተሳተፉ የሚገኙ ባለሙያዎችም ልምድ ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ሥራውን ለማፋጠን ተጨማሪ ባለሙያዎችን ወደ ሳይቱ የማምጣት ሥራ እየተሠራ መሆኑን የሳይት መሐንዲሱ ጨምሮ አብራርቷል።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ ሰለሞን እንዳስታወቁት፤ የዚህ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አምስት ነጥብ 67 ኪ.ሜ ርዝመት ይሸፍናል፤ ከ30 እስከ 42 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት ይኖረዋል። የመንገድ ፕሮጀክቱን ሥራም ይርጋዓለም ኮንስትራክሽን የተባለ ሀገር በቀል ድርጅት የሚያከናውነው ሲሆን፣ ተቋራጩ ግንባታውን በሁለት ዓመት ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ የኮንትራት ውል ፈርሞ ነው ወደ ሥራው የገባው፡፡ በአሁኑ ወቅትም የግንባታ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡
የወሰን ማስከበር ችግሮች በወቅቱ ተጠናቀው ባለመነሳታቸው ግንባታው ከሚጀመርበት ጊዜ አንድ ዓመት ያህል ዘግይቶ መጀመሩን አቶ ኢያሱ ጠቅሰው፣ እሰካሁንም ድረስ የመብራት፣ የቴሌ ምሰሶዎች አለመነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህ የተነሳም የግንባታ ሥራው በሚፈለገው ፍጥነት እየተከናወነ አለመሆኑን ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ የሆኑ የኤሌክትሪክ መስመሮች፣ በመሬት ውስጥ የተቀበሩ የቴሌ ፋይበሮች እና የውሀ መስመሮች ባለመነሳታቸው የግንባታ ሥራውን በሙሉ አቅም ለማከናወን አዳጋች ሆኗል። ከእነዚህ ጋር የተያያዙ ሥራዎች አሁንም ገና መፍትሔ አላገኙም፤ በመሆኑም በሙሉ አቅም እና በሚፈለገው ደረጃ እና ፍጥነት ሥራዎችን ለመሥራት፣ የግንባታ ሥራዎቹንም ለማከናወን አልተቻለም።
አሁን የወሰን ማስከበሩ ሥራ በተከናወነበት በሁለት ነጥብ ሦስት ኪሎ ሜትር ውስጥ የድሬይኔጅ መስመር ዝርጋታ፣ የድጋፍ ግንብ ሥራዎች፣ የአፈር ቆረጣ፣ የገረጋንቲ አፈር ሙሌት እና መሰል ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። አጠቃላይ አፈፃፀሙም አምስት ነጥብ 59 በመቶ ላይ ደርሷል።
መንገዱ የከተማዋ ምዕራብ አቅጣጫ መውጫ መሆኑን ጠቅሰው፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ የትራፊከ ፍሰቱን በማሳለጥ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለግንባታው መፋጠን በወሰን ማስከበር ሥራዎች ላይ ያለው መተጋገዝ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ መሠረተ ልማቶቹ በፍጥነት ከተነሱ በተያዘው የጊዜ ገደብ ውስጥ የግንባታ ሥራዎቹን ለማከናወን እንደሚቻል ይናገራሉ።
አቶ እያሱ የአየር ጤና ወለቴ መንገድ ፕሮጀክት አጠቃላይ የአየር ጤና ወለቴ መንገድ አፈጻጸም ደረጃም አራት ነጥብ 73 በመቶ አካባቢ ላይ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
በአካባቢው ተለዋጭ መስመር አለመኖሩና የግንባታው መጓተት በነዋሪዎች እና በአጠቃላይ የትራፊክ እንቅሰቃሴዎቹ ላይ ትልቅ ጫና መፍጠሩን አቶ እያሱ ጠቅሰው፣ ይሄንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን የወሰን ማስከበር ሥራ በፍጥነት መፈፀም እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2016 ዓ.ም