“በተደጋጋሚ ወተት የምወስደው ከአንድ ሰው ቤት ነው። እንደልማዴ አንድ ቀን ጠዋት ሁለት ሊትር ወተት ወስጄ፤ አንዱን ሊትር ለራሴ ሌላውን ደግሞ ነፍሰጡር ለሆነች ጎረቤቴ ሰጠሁ። ከቆይታ በኋላ ግን የተፈጠረው ነገር ምነው እጄን በሰበረው ያሰኘ ነበር። ወተቱን የጠጡት ልጆቼ ባጋጠማቸው የጤና ችግር ታመው ለሆስፒታል በቁ ፤ ልጆቼን አሳክሜ ከመጣሁ በኋላ በፍጥነት ያመራሁት ወተቱን ወደ ሰጠኋት ጎረቤቴ ነው።
እሷም ’ወደላይ ወደታች‘ ሲላት ውላ በመጨረሻ ህክምና ተቋም በመሄድ የተወሰነ እፎይታ ማግኘቷን ነገረችኝ። እኔም ያጋጠመኝን ነግሬያት ያመራሁት ወተት ወደምገዛበት ቤት ነበር። በንዴትና በደምፍላት ’ምን አይነት ወተት ነው የሰጠሽኝ?‘ ስል ጠየቅኳት። ጥያቄዬ ምንም አልመሰላትም ‘እኔም ሁልጊዜ ከማመጣበት አምጥቼ ነው ያከፋፈልኩት‘ የሚል ነበር መልሷ። ያጋጠመኝን ችግር ነገርኳት ‘ ከአንቺ በቀር ሌላ ሰው በእዚህ መልኩ የመጣ የለም ’ ስትል ከደሙ ንጹህ መሆኗን ለራሷ መሰከረች…” እኔም ምንም ሳልመልስላት ወጣሁ፡፡
ጠዋት ይህንኑ ወተት ላመጣ ስወጣ የሰማሁት ለቅሶ ሰለነበር ልደርስ ሄድኩኝ። ያው እንደምታውቁት ለቅሶ ቤት ከማስተዛዘን ባሻገር ትላልቅ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ጉዳዮች የሚነገሩበት መድረክም አይደል! እኔም የገጠመኝን ለገበያ አዋልኩት፡፡ ኧረ ጉድ እኮ ነው ምን ያልሆንነው ነገር አለ! ጨዋታ በዚህ በተጀመረው አጀንዳ ሞቅ ብሎ ቀጠለ ፤ ቤቱ ሰዎች ሀዘንተኞችን ለማስተዛዘን የተሰባሰቡበት ነበርና ከወ ዲያ ከወዲህ ሀሳቦች መውጣታቸው ለጨ ዋታው ድምቀት ሆኗል።
አንደኛው ከወዲህ ጥግ “በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ከጀሶ ጋር የተቀላቀለው እንጀራ እና ስምንት በርሜል ሊጥ ለኤግዚቢት ተይዞ በወረዳው ጽህፈት ቤት አይተናዋል። ይሄንንም ድርጊት ሲፈጽሙ ነበር የተባሉት 3 ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአካባቢው ህብረተሰብ አይቷል ፤ ታዝቧል።
ይሄ የህግ አካላት እርምጃ እና ቅጣት ግን ከሳምንት በላይ የዘለለ አልነበረም ማለት ይቻላል። ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባሉት ግለሰቦችም የቅጣት ዜና ሳይሆን የመለ ቀቃቸው ዜና ሳምንት ባልሞላው ጊዜ እውን ሆነ። ፍትህ የት ነህ ልበል? ወይስ …” ሌላኛው ከወዲያኛው ጥግ “የሚገርም እኮ ነው! በቀደም ዕለት አንድ የህጻናት አልሚ ምግብ የሚያስመጣ ድርጅት እንዲሁ ባዕድ ነገር በመቀላቀል መያዙን ሰምቻለው፤ በፍራቻ እና በስጋት ቦዝዞ….”
እንዲያ በደራው ጨዋታው መሀል እኔም ባልደረባዬ የነገረችኝ ትዝ አለኝ። “ከአገር ውስጥ አልፎ ተርፎም የጀሶ እንጀራ አሜሪካ ገባ “ ስትለኝ ማመኑ ቢከብደኝ እንኳን አይሆንም ብሎ ለመሟገት ድፍረቱ አልነበረኝም። ምክን ያቱም ወንጀሉን የሚሰሩት፣ የሚያ ቀናባብሩት፣ የሚያሰራጩት የእኛው እህትና ወንድም አይደሉም።
ባህር ማዶ ይሄንን አይልኩም ብሎ ለማለት ምን ይከብዳል ። ደግሞ እኮ “ ነጋዴ” ብር ያግኝ እንጂ አይን የለውም፤ ገንዘብ እንጂ ሰብአዊነት አልፈ ጠረበት ለማለት አሰብኩና ደግሞ እነዛን ንጹህ ነጋዴዎች አስቤ ከአንደበቴ ቆጠብ አልኩ ። ልጽፈው ግን ግድ ሆነ። መረጃ እንደ መረጃ ማገልገሉ ያው ከጉዳት ማዳኑ አይቀርማ። ከተዳፈርኩ ይቅር በሉኝ!
እንዲያ በደራው ጨዋታው መሀል እኔም ባልደረባዬ የነገረችኝ ትዝ አለኝ። “ከአገር ውስጥ አልፎ ተርፎም የጀሶ እንጀራ አሜሪካ ገባ “ ስትለኝ ማመኑ ቢከብደኝ እንኳን አይሆንም ብሎ ለመሟገት ድፍረቱ አልነበረኝም። ምክን ያቱም ወንጀሉን የሚሰሩት፣ የሚያ ቀናባብሩት፣ የሚያሰራጩት የእኛው እህትና ወንድም አይደሉም። ባህር ማዶ ይሄንን አይልኩም ብሎ ለማለት ምን ይከብዳል ።
ደግሞ እኮ “ ነጋዴ” ብር ያግኝ እንጂ አይን የለውም፤ ገንዘብ እንጂ ሰብአዊነት አልፈ ጠረበት ለማለት አሰብኩና ደግሞ እነዛን ንጹህ ነጋዴዎች አስቤ ከአንደበቴ ቆጠብ አልኩ ። ልጽፈው ግን ግድ ሆነ። መረጃ እንደ መረጃ ማገልገሉ ያው ከጉዳት ማዳኑ አይቀርማ። ከተዳፈርኩ ይቅር በሉኝ!
ለወንጀለኛ ከዚህ ተመለስ ማለት እኮ አይቻልም። የትም መድረስ ይችላል። በማንም ላይ ምንም ነገር ማሰብና መስ ራትም ይችላል። ሁሉም በእነሱ እጅና በእነሱ አእምሮ የሚታሰብ አይደል? በቃ የሚፈለገው ገንዘብ ብቻ ነው። ግን ግን ገንዘብ ህሊና ይሆናል? ማለቴ ከምንም በላይ እኮ ህሊና የሚባለው ይሄ ሰዎችን የሚጎዳ ህጻናትን የሚገድል የእድሜ ልክ በሽተኛ የሚያደርግ ስራ ሰርቶ ገንዘብ አግኝቶ ጥሩ ኑሮ እየኖርኩ ነው ማለት ይቻላል? አይቻልም! እንዳልል እማ ተችሎ አየነው አይደል ? ይሄ ነው እንግዲህ ለዜጋው የማያስብ የንግድ ህብረተሰብ፣ የእሱ ተባባሪ። እንዳው በንዴት ብዙ ክፉ ክፉ ነገር ወጣኝ እንዴ? ህጋዊውን ፣ለወገንና ለአገሩ የሚቆረቆረውን የንግድ ህብረተሰብ ማለቴ እንዳልሆነ ይያዝልኝ! እነሱን ስማቸው ያስከብራቸዋል፤ እጃቸው ያሸልማቸዋል፤ ያሾማቸዋል።
ለምን ብትሉ የሁሉም ነገር ፈራጁ ስራ ነዋ። በሀቅ መስራት በታማኝነት ማገልገል የልፋት ውጤት የሆነውን ሀብት ብቻ ሳይሆን ስም፣ ዝና ሁሉ ያስከትላል። ስም ደግሞ ከመቃብርም በላይ ነው።
ምን ያልሆንነው ነገር አለ ? ያለው አንድ የህግ ምሁር ለፅሁፌ ርዕስ መነሻ ሆነኝ እና እኔም ምን ያልሆነው ነገር አለ! ብዬ ይሄን አልኩ። እውነት እኮ ነው ምን ያልሆነው ነገር አለ። እንጀራን ከጀሶ፣ እንጀራን ከሰጋቱራ ተቀየጠ ምግብ ሆኖ በላነው ፤ወተት ከሳሙና አረፋ ተቀየጠ ጠጣነው፣ ቅቤ ከሙዝ፣ ከድንች፣ ከረጋ ዘይት፣ ከውሀ ተቀላቅሎ ተከሸነ ሸመትነው፤ በርበሬ ከሸክላ አፈር ፣ ከቀይ ስር ተቀየጠ በተመሳሳይ ጥቅም ላይ አዋልነው፤ … ሌላም ሌላም ባዕድ ነገሮች ተቀይጠው ወደ ገበያ ገቡ ሸመትናቸው።
ግን እኮ ይሄ ሁሉ ሰው ወገቤን፣ እግ ሬን፣ ጨጓራዬን… የሚለው ምናልባት የእነዚህ የባዕድ ነገሮች ቅይጥ የረጅም ጊዜ ውጤት ይሆን? መጠርጠር ደግ ነገር ነው ብዬ ነው ፡፡ይህን ማለቴ እውነቱን ግን የሚያውቀው የደረሰበት ብቻ ነው።
አሁን ደግሞ ከውስኪ ጋር የተቀየጠ አደገኛ ነገር መያዙን እንዲሁ ከጨዋታው መሀል ወደ ጆሮዬ ገባ፤ ይሄ ግን ብዙም የተጫዋቹን ቀልብ የገዛ አልነበ ረም፤ “እስከዛሬው በደሀው ወገን ላይ ነበር፤ አሁን ወደ ሀብታሙም ሊዘመት ነው“ ከሚል ያለፈ አልነበረም። ምንም ቢሆን ውስኪ የቅንጦት መጠጥ ነው ሊቀር ይችላል፤ ዳቦ እና እንጀራ ገዝቶ የሚበላው ግን ሌላ አማራጭ የለውም! ለእነዚሁ አረመኔ ነጋዴዎች ተላልፎ የተሰጠ ሚስኪኑ ነው የሚለው ጨዋታ ጎላ ብሎ ወጣ ።
ውስኪ አቅራቢውም ሆነ ጠጪው ምን እንደሚሉ ባላውቅም ለረጅም ጊዜ ግን ”የተወጋ ውስኪ“ ገበያውን እንደያዘው መስማቴን አስታውሳለሁ። አሁን ግን ኧረ ውስኪ ጠጪዎች ከመወጋት ከፍ ያለ ችግር ውስኪም አረገዘች የሚለው ጥቆምታ ሊያነቃቸው ይገባል። አይደል? ሁሉም ወገን ነዋ! ነጋዴ ወገን አያውቅም፤ የነጋዴ ወገኑ ገንዘብ ብቻ ነው ብላችሁ ግን አትጠይቁኝ ንጹህ ነጋዴዎችን ማስቀየም ይሆንብኛል።
ግን እስኪ አስቡት ማን ማንን ነው የሚያጠቃው ፤ በማን ላይ ነው ሀብት የሚሰበስበው? ወንጀል ሰርቶስ ምን አይነት ህሊና ነው የሚኖረው ? ይሄንን ሰርቶ እንቅልፍ የሚተኛውስ ምን አይነት አእምሮ ቢኖረው ነው ? ብቻ ምላሹን ለአንባቢው ልተው።
ይህን ሳነሳ ህጉስ? የፍትህ አካላትስ ምን እየሰሩ ናቸው ? የሚል ጠያቂ አይጠፋም። አዎ! አሁን ዲሞክራሲ ፣ነፃነት፣ ገለመሌ … እያልን የምናወራበት ነው። መጠየቅ የሚገባንን ብቻ ሳይሆን ማንሳት የሌለብንን ወይም ደግሞ አሁን ወቅቱ ያልሆነውን ጥያቄ የምናነሳበት ሰዓት አይደል? ። ጠያቂ ትውልድም አፍርተናል ። ይሄንን ጥያቄ ቢያነሳ ይገባል። ኧረ እንዳውም ተገቢ ነው።
ከመስመሬ ወጣሁ መሰለኝ ልመለስ። አንዳንዱ ነጋዴ በፍጥነት ሀብታም መሆን በመሻት፣ በአቋራጭ ለመክበር የማይወጣው ዳገት፣ የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም። የፍትህ አካሉንም ሆነ የጸጥታ ሀይሉን ሲችል አጭበርብሮ ካልሆነም በእግሩ ሳይሆን በእጁ ብሎ የራሱ ያደርገዋል። ዓላማውን ቃልኪዳኑን ሁሉ ያስተወዋል።
ስለዚህ በወገኑ ፣ በሀገሩ ላይ ምንም የከፋ ነገር አይሰራም ብሎ ማለት አይቻልም ፤ ምክያቱም ግቡ ሀገር ወገን አይደለም። ግቡ ገንዘብ ነው፤ ገንዘቡ ከተገኘ ሌላው የእሱ ጉዳዩ አይደለም። አሁን አሁን ተባብሰው አይነታቸውን አስፍተው የምናያቸው የወንጀል ድርጊቶች የሚያሳዩት ለገንዘብ ተብሎ ምንም ክፉ ነገር እንደሚሰራ ነው። ህጉም አስተማሪ ቀጪ ሳይሆን ልል፤ ፈፃሚና አስፈፃሚው በእዛው መስመር መጓዛቸው ችግሩን አገዘፈው መሰለኝ። እኔ እንዲህ ተሰማኝ የእናንተን ግን እንጃ! ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2011
አልማዝ አያሌው