በጋና በተካሄደው 13ኛ የአፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ አብዛኛውን ውጤት ያስመዘገበችበት የአትሌቲክስ ውድድር እንደነበር ይታወሳል።በእርምጃ ውድድር አንድ ወርቅና አንድ የብር ሜዳሊያ ማስመዝገብ ተችሏል።ኢትዮጵያ በውጤታማነት በማትታወቅበት የርምጃ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀው ደግሞ አትሌት ምስጋናው ዋቁማ ነው።አትሌቱ ወጣት፣ በብዙ ውጣ ውረዶች ለድል የበቃና አሁንም የድል ረሀብ የሚንፀባረቅበት ስፖርተኛ ነው፡፡
አትሌት ምስጋናው ተወልዶ ያደገው በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወንጪ ወረዳ ሲሆን የእርምጃ ውድድርን የተቀላቀለው በ2013 ዓ.ም ነው።ከዛ በፊት በ 5 እና 10 ሺ ሜትር ርቀቶች ላይ ለመስራት ሞክሯል።በረጅም ርቀት እራሱን ኮከብ አትሌት አድርጎ ህልሙን ለመኖር፣ በመታተር ላይ የነበረው አትሌት በሰዎች ምክር ፊቱን ወደ እርምጃ ውድድር በማዞር ልምምዱን በትጋት ቀጠለ። ባገኘው የሙከራ እድል ዘርፉን ተቀላቅሎም ዛሬ ላይ በውጤት ጎዳና መጓዝ ጀም ራል፡፡
በ20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር ኢትዮጵያን በአፍሪካ ደረጃ በመወከል ወርቅ ያጠለቀው ይህ አትሌት፣ ልምምዶቹን በብዙ መሰናክሎች ውስጥ ሆኖ በማከናወን ያገኘውን እድል በአግባቡ ተጠቅሟል።
በአካዳሚም ይሁን በሌሎች የስልጠና ሂደቶች የማለፍ ዕድሎች ያላገኘው አትሌት ምስጋናው በትውልድ ስፍራው በሚኖርበት ወቅት በሚማርበት ትምህርት ቤት ለስፖርት በነበረው ፍቅር ከሚያደርገው እንቅስቃሴ በስተቀር ያገኘው የስልጠና እድል የለም።የእንጀራ ነገር አስገድዶት የትውልድ ቀዬውን ለቆ ወደ አዲስ አበባ በመጣበት ወቅት ከኑሮ ጋር በሚያደርገው ግብ ግብ በስፖርት ውስጥ ማለፍ ለሱ የሚታሰብ አልነበረም። አትሌቱ የስፖርቱ ፍቅር በውስጡ ስለነበር ከብዙ ዓመታት በኋላ ወደ ስፖርት ተመልሶ ለድል መብቃቱን ይናገራል።
አሰለፈች መርጊያን የመሳሰሉ ታዋቂ አትሌቶች ከትውልድ ስፍራው መውጣታቸው፣ እንደነሱ ለመሆን በልጅነቱ ህልም ሰንቆ በትጋት ፈተናዎችን እየተጋፈጠ መስራቱን ቀጠለ።ከዘመድ ጋር እየኖረ በሆቴል የመስተንግዶ ስራን ከዛም የጽዳት ስራን እየሰራ ህይወትን ለማሸነፍ ከሚያደርገው ግብ ግብ ጎን ለጎን ልምምዱን እየሰራ ቆይቷል። የመስተንግዶ ስራ ከስልጠናው ጋር ሊጣጣምለት ባለመቻሉ የጽዳት ስራን መስራት ጀመረ።በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጽዳት ስራውንና ልምምዱን ጎን ለጎን ለአራት ዓመት ከግማሽ ሰርቷል።
በድርጅቱ በሳምንት ሶስት ቀን ስራ እና ልምምዱን እንዲሰራ ፍቃድ ቢሰጠውም ያ በቂ ባለመሆኑ ስራውን ትቶ ሙሉ ጊዜውን ለአንድ ዓመት ልምምድ ማድረጉን መረጠ።ለአንድ ዓመት ያለስራና ዘመድ ላይ ጥገኛ ሆኖ ጠንክሮ ልምምዱን በመስራት በአዲስ አበባ ክለቦች ቻምፒዮና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለሙከራ ወክሎ በመወዳደር ሶስተኛ ሆኖ ማጠናቀቁ ለክለቡ እንዲፈርም አስቻለው።በአንድ ወቅት ውድድር ሊያደርግ ዋዜማው ላይ እያለም ልብ ሰባሪ የእህቱ ህይወት ማለፉን የሰማበት ዕለትና ወንድሙን በካንሰር በሽታ ያጣበት ቅጽበት ፈታኙ ጊዜ እንደነበር ያስታውሳል።
በእርምጃ ውድድር በሀገርና በአህጉር አቀፍ ደረጃ ክለብ ከተቀላቀለ በኋላ አሰልጣኖች የሰጡት ስልጠና እና ከልጅነቱ ጀምሮ አብሮት ያደገው የስፖርት ፍቅር በውጤት ለመታጀቡ ዋናው መንስኤ እንደሆነ ያስታውሳል።ፊቱን ወደ እርምጃ በማዞር ክለብ ከገባ በኋላ ጥሩ አሰልጣኝ በማግኘቱ ጠንክሮ እየሰራ የአሸናፊነት ስነልቦናን ተጎናጽፏል።ለዚህ ሁሉ ድልና ውጤታማነቱ አንዲት አሰልጣኝ ስሟ በልዩ ሁኔታ ይጠቀሳል።የእርምጃ አሰልጣኝ አምሳለ ያዕቆብ ወደ እርምጃ ውድድር እንዲገባ አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ ትልቅ ሚና አላት።አሰልጣኙ ሻለቃ ባዬ አሰፋ እንዲሁ በሚሰጡት ስልጠና ጠንክሮ በመስራቱ ውጤታማ እንደሆነም ያስረዳል።
የመጀመሪያ ሀገር አቀፍ ውድድሩን በ2013 ዓ.ም አሰላ በተካሄደው የኢትዮጵያ ወጣቶች ቻምፒዮና በ10 ኪሎ ሜትር የመም ውድድር አንደኛ መውጣት ችሏል።በተመሳሳይ ዓመት በሀዋሳ በተካሄደው የኢትዮጵያ ቻምፒዮና 20 ኪሎ ሜትር እርምጃ ክለቡን ወክሎ በመወዳደር ሁለተኛ ወጥቷል።ከዛ በኋላ በተካሄዱ ሀገር አቀፍ ውድድሮች በሙሉ አንደኝነቱን የነጠቀው የለም።ባካሄዳቸው ውድድሮች 11 የወርቅ፣ 1 ብርና 1 የነሐስ ሜዳሊያዎች አሉት፡፡
ሀገርን መወከል የቻለው በአህጉር አቀፍ ውድድሮች ሲሆን 2014 ዓ.ም ሞሪሺዬስ ላይ በተካሄደው 22ኛ የአፍሪካ ቻምፒዮና ሀገሩን ለመጀመሪያ ጊዜ ወክሎ በመሳተፍ የዲፕሎማ ተሸላሚ መሆን ችሏል።በ2015 ዓ.ም በዛምቢያ በተካሄደው መላው የአፍሪካ ጨዋታዎች ሀገሩን ወክሎ የወርቅ ሜዳሊያን አጥልቋል።ዘንድሮ በጋና በተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች እንዲሁ በ20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር አንደኛ በመውጣት ወርቁን ወስዷል።
ይህ ውድድሩ ለአንድ ተጨማሪ ዓመት በመራዘሙ እና ከ33 ዓመት በፊት ወርቅ መመዝገቡ በመስማቱ የረጅም ጊዜ ዝግጅት በማድረግ ለውጤት እንደበቃ ይናገራል።ኢትዮጵያ በሶስት ወንድና በሶስት ሴት ተወዳዳሪዎች በተወከለችበት ውድድር የኬንያና የአልጄሪያ አትሌቶችን ፉክክር ተቋቁሞ አሸንፏል።ከተፎካካሪዎች መብዛትም በላይ የአየር ንብረቱ አስቸጋሪ መሆኑ ከድል አላስቀረውም፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2016 ዓ.ም