ሁለት ክለቦች የደመቁበት የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ቻምፒዮና

የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ክለቦች ቻምፒዮና በአንደኛና ሁለተኛ ዲቪዚዮን ክለቦች መካከል ከፍተኛ ፉክክሮችን አስተናግዶ ፍጻሜውን አግኝቷል። በ1ኛ ዲቪዚዮን 7 ክለቦችን፣ በ2ኛ ዲቪዚን 9 በአጠቃላይ 16 ክለቦችን ከመጋቢት 23-27 በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲያፋልም የቆየው ቻምፒዮና በሁለት ክለቦች የበላይነት ተጠናቋል።

መቻልና አራዳ ክፍለ ከተማ አትሌቲክስ ክለቦች ለውድድሩ ከተዘጋጁት 8 ዋንጫዎች 7ቱን በመውሰድ በበላይነት አጠናቀዋል። ቻምፒዮናው በአንደኛ ዲቪዚዮን ከውድድሩ መጀመሪያ ቀን ጀምሮ በመቻል፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ኢኮስኮና ፌደራል ማረሚያ ቤቶች መካካል አጓጊ ፉክክሮችን አስተናግዷል።እነዚህ ክለቦች ከአጭር ርቀት እስከ 10 ሺ ሜትር እና የሜዳ ተግባራት ውድድሮችን ጨምሮ ጠንካራ ፉክክር ያደረጉ ሲሆን፣ መቻል በበርካቶቹ ውድድሮች ስኬታማ መሆን ችሏል፡፡

ለሰባት ተከታታይ ቀናት በተካሄዱ ውድድሮች መቻል በሰበሰባቸው በርካታ ሜዳሊያዎችና ነጥቦች በሁለቱም ፆታ አጠቃላይ አሸናፊ መሆን ችሏል። መቻል በውድድሩ አራት ዋንጫዎችን በማንሳት ቀዳሚ ሲሆን፣ በሴቶች መካከል በተደረገው የቡድን ፉክክር 263 ነጥቦችን በመያዝ የቡድን ዋንጫው ባለቤት ሆኗል።በዱላ ቅብብል ኢትዮ ኤሌክትሪክ የብር ሜዳሊያውን ሲወስድ መቻል ወርቁን ወስዷል።ሌላኛው ውጤታማ ክለብና ጠንካራ ተፎካካሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ206 ነጥብ ሁለተኛ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ157 ነጥቦች ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።

በወንዶች የቡድን ሽልማትም መቻል፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ቀዳሚዎቹን ደረጃዎች የያዙ ሲሆን መቻል አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን ዋንጫውን ወስዷል።በዱላ ቅብብል ደግሞ መቻል ወርቅ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ብርና ኢኮስኮ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችለዋል።በዚህም መሰረት መቻል 222 ነጥቦችን በመሰብሰብ 1ኛ እና የዋንጫ ተሸላሚ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ191 ነጥብ 2ኛ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ185 ነጥብ ውድድሩን በሶስተኝነት አጠቋል። መቻል በሴቶችና በወንዶች ድምር ውጤት 485 ነጥቦችን ሰብስቦ የአጠቃላይ አሸናፊና የዋንጫ ተሸላሚም ነው።የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ397 ነጥብ 2ኛ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ342 ነጥብ 3ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል፡፡

መቻል ውድድሩን በፉክክር እንዲታጀብ፣ አጓጊ እንዲሆን ከመክፈቻው እስከ መዝጊያው ቀን ድምቀት በመሆኑ የሽብርቅ ዋንጫውንም በ85 ነጥቦች ማሸነፍ ችሏል።ኢኮስኮ በ70 ነጥብ፣ ፌደራል ፖሊስ 60 ነጥብ በመያዝ የሽብርቁን ቀሪ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል፡፡

በሁለተኛ ዲቪዚዮን አራዳ ክፍለ ከተማ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ አይሸዓና ለሚ ኩራ ክለቦች ጠንካራ ፉክክር አድርገውበታል።በዚህም በወንዶች አራዳ ክፍለ ከተማ 234 ነጥቦችን በመሰብሰብ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊና የዋንጫ ተሸላሚ ሆኖ በበላይነት አጠናቋል። አዲስ አበባ ፖሊስ በ110 ነጥቦች 2ኛ፣ አይሸዓ ስፖርት ክለብ በ60 ነጥቦች ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን መጨረስ ችለዋል። በወንዶች የዱላ ቅብብል አራዳ ክፍለ ከተማ ወርቅ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ ብርና ኤልሚ አላንዶ ነሐስ ሜዳሊያን ወስደዋል፡፡

በሴቶች 2ኛ ዲቪዚዮን እንዲሁ አራዳ ክፍለ ከተማ 210 ጥቦችን በመሰብሰብ የዋንጫ ተሸላሚ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።አዲስ አበባ ፖሊስ 88 ነጥቦችን ሰብስቦ 2ኛ በመሆን የውድድሩን ሲጨርስ ለሚኩራ ክፍለ ከተማ ሶስተኛ መሆን ችሏል።በሴቶች ዱላ ቅብብል ውድድር አራዳ ክፍለ ከተማ ወርቅ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ ብር፣ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የነሐስ ሜዳሊያውን ተሸልሟል።

በውድድሩ 2ኛ ዲቪዚዮን ጥሩ ፉክክር በማስ መልከት በሰበሰባቸው ሜዳሊያዎች፣ በወንዶችና ሴቶች የሁለት የዋንጫ ባለቤት መሆን የቻለው አራዳ ክፍለ ከተማ 450 ነጥቦችን በመሰብሰብ ነው የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ የሆነው። አዲስ አበባ ፖሊስ በ198 ነጥቦች 2ኛ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በ120 ነጥቦች 3ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።አዲስ አበባ ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብ 65 ነጥቦችን በመያዝ የሽብርቅ ዋንጫው አሸናፊ መሆን ችሏል። አራዳ ክፍለ ከተማ በ60 ነጥብ 2ኛ፣ ለሚኩራ 50 ነጥብ 3ኛ በመሆን የተሸለሙ ክለቦች ናቸው፡፡

በውድድሩ ለአሸናፊዎች በየዲቪዚዮኑ እንደየ ደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት የተበረከተ ሲሆን፣ ሶስትና ከዚያ በላይ የወርቅ ሜዳሊያ ያመጡ፣ በየዘርፉ የውድድሩን ክብረወሰን ያሻሻሉ እና የውድድሩ ኮከብ ሆነው ለተመረጡ አትሌች የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በተጨማሪም የውድድሩ ኮከብ አሰልጣኝና ውድድሩ እንዲሳለጥ ጉልህ ሚና ያበረከቱ ዳኞች ተሸልመዋል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You