ብዙ ግዜ ደጋግመን የምንሰማቸውን ጉዳዮች ጆሯችን በለመዳቸው ቁጥር መገረም፣ መደንገጥ ይሉትን እየተውነው ይመስላል:: ምንአልባት እኮ የሰማነው አልያም ያየነው ጉዳይ የሕይወት ዋጋ የሚያስከፍልና ፈጽሞ ከአዕምሮ የማይጠፋ ሊሆን ይችላል:: ይህ አይነቱን ሐቅ መላመድ ስንጀምር ግን እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ፈጽሞ ብርቃችን አይሆንም:: ሰምተን እንዳልሰማን፣ አይተን እንዳላየን በዋዛ እናልፈዋለን::
የትራፊክ አደጋ ነገርም እንዲህ እየሆነ መምጣቱን መታዘብ ይቻላል:: በየቀኑ የምንሰማቸው ከባድና አሰቃቂ አደጋዎች ውስጣችንን ቢያስደነግጡን ምናልባትም ለደቂቃዎች ብቻ ይሆናል:: ችግሩ ሁሌም በሌሎች እንጂ በእኛ ዘንድ ይደርስ አይመስለንምና ዝንጉነታችን እየበዛ ነው::
በቅርቡ በተለያዩ ስፍራዎች በርከት ያሉ አደጋዎች ማጋጠማቸውን እየሰማን ነው:: እነዚህ አደጋዎች በውስጣቸው ሞትና ጉዳት ብቻ አልያዙም:: ከእያንዳንዱ ክስተት በስተጀርባ እጅግ አሳዛኝና ልብ ሰባሪ ታሪኮችም አሏቸው:: ብዙዎቻችን ይህን ሐቅ ስንጋራ ውስጣችን በእኩል ያዝናል፣ ካለቀሱት ጋር አልቅሰን እንዳዘኑት የቅርብ ሰዎች ልባችን ይሰበራል:: ዛሬ አልፎ ነገ ሲተካ ግን ዋጋ የሚያስከፍለን ዝንጉነት መልሶ ይወዳጀናል:: ስናሽከረክር ደንታ ቢሶች እንሆናለን፣ አስፓልት ስናቋርጥ ኃላፊነቱን ለአሽከርካሪው ብቻ እንተዋለን:: ‹‹ዜብራ›› ይሉት መስመር ደግሞ የግል ሀብታችን የሚመስለን በርካቶች ነን::
ይህ ሁሉ ያልተገባ ድፍረት ግን በንብረትና በቀላል የአካል ጉዳት ብቻ አይታለፍም:: እንደዋዛ ውድ የሚባለውን የሰው ልጅ ክቡር ሕይወት ይነጥቃል:: ከአዕምሮ የማይጠፋ ጥቁር ታሪክን ያትማል:: የትራፊክ አደጋ ክፉና ድንገቴ ነው:: የጀመሩትን ሳይጨርሱ፣ የወጠኑትን ሳይቋጩ፣ የከፈቱትን ሳይዘጉ በወጡበት ያስቀራል::
እስከዛሬ በሀገራችን ብዙ አሳዛኝ ታሪክ ያላቸው የትራፊክ አደጋዎችን ሰምተናል:: የሚገርመው ግን አሁንም ድረስ በዚህ ጉዳይ ዝንጉ መሆናችን ነው:: በየግዜው የትራፊክ አደጋ ሲያጋጥም ከበስተጀርባ የሚወቀስ የሚከሰሰው ብዙ ነው:: የሾፌሩ ያልተገባ ፍጥነት ይነሳል፣ የእግረኞች ግዴለሽነት ይጠቀሳል:: የመንገዶች ምቹ አለመሆን ሰበብ ይደረጋል:: ጉዳዩን አስመልክቶ ከፖሊስ የሚቀርበው ሪፖርትም ከዚሁ የዘለለ አይደለም:: ፍጥነት፣ ለእግረኞች ቅድሚያ አለመስጠት፣ ደንብ መተላለፍ ወዘተ ..እያለ ይቀጥላል::
በየአጋጣሚው ሕግ ጥሰው ተገኝተዋል በተባሉ አሽርካሪዎች ላይ የሚጣለው ቅጣትም ተፅዕኖ አሳድሮ ችግሩን ሲቀርፈው አልተስተዋለም:: በየግዜው ችግሩን አስመልክቶ የሚተላለፉ መልዕክቶች፣ የአደጋ ሪፖርቶች፣ የጋዜጣ፣ የሬዲዮና የቴሌቪዢን ዘገባዎች ሁሉ ለሚከሰቱ ችግሮች የታሰበውን ያህል ዋስትና መሆን አልቻሉም:: ዛሬም በየአፍታው ከባድ አደጋዎች እየተከሰቱ የሰው ልጆች ክቡር ሕይወት ይነጠቃል::
ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ አስተማሪ መሆን ካልቻለ የአንድ ወገን ጥረት ብቻውን ለማንም አይጠቅምም:: በርካቶች ይህን እውነታ እየሰሙና እያወቁ እንኳን ስህተት በሞላቸው ገጠመኞች ሕይወታቸውን እያጡ ነው:: የሌሎችን ዓለም ነጥቀውም ጥቂት የማይባሉ ተስፈኞችን ከመንገድ አስቀርተዋል::
ለትራፊክ አደጋ መንስኤዎቹ ብዙ ናቸውና ከዚህም በላይ መጥቀስ ይቻላል:: አንዳንዴ ግን በመዘናጋትና በቸልተኝነት የሚፈጠሩ አጋጣሚዎች ዋጋ ማስከፈላቸው ሲታሰብ ከልብ ያስቆጫል:: እኔ ይህን ሀሳብ መምዘዜ ያለምክንያት አይደለም:: በከተማችን አንድ ስፍራ ያስተዋልኩት እውነት ከበዛ ስጋት ቢጥለኝ እንጂ::
በቅርቡ በተለምዶ ‹‹ጀርመን አደባባይ›› እየተባለ የሚጠራው ስፍራ ለትራፊክ ፍሰቱ በሚበጅ መልኩ ማሻሻያ ተደርጎለታል:: ይህ ስፍራ ከዚህ ቀድሞ በአደባባይ የተከበበ ነበርና የመንገድ መጨናነቅ ሲስተዋልበት ነበር:: ቦታው መጋቢ መንገድ እንደመሆኑ ከየአቅጣጫው የሚመጡ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተላልፍ ነው::
ይህ ለዓመታት የዘለቀ ሂደት ከነችግሩም ቢሆን በርካታ መኪኖችንና እግረኞችን ሲያመላልስና ሲያገለግል ቆይቷል:: በከተማዋ ለትራፊኩ ፍሰት ማሻሻያ መደረጉ አንድም አሳሳቢ አደጋዎችን ለመቀነስ ሌላም ደግሞ የተሻለ የመንገድ እንቅስቃሴ እንዲኖር ያግዛል::
ይህ እውነታ በታወቀ ግዜም ክፍተት አለባቸው ተብለው በሚገመቱ አካባቢዎች ችግር ፈቺ ማሻሻያዎች በማድረግ ሁኔታውን በዘላቂነት ለመቅረፍ ተግባራዊ ርምጃዎች ለመውሰድ ያስችላል:: በጀርመን አደባባይ ላይ የተደረገው ሂደትም ይህን መሰሉን ተግባር የያዘ ነው::
በዚህ ስፍራ መሐል አደባባዩን በማፍረስ መንገዶች እንዲሰፉና የትራፊክ መብራቶች እንዲተከሉ ተደርጓል:: ይህ እውነታ ቅርጽ ከመለወጥ ባሻገር ለበርካቶች እፎይታን አቀብሏል:: መንገዱ በተለያዩ አቅጣጫዎች መኪኖችን የሚያስተናግድ ነውና መፍትሔ ማስከተሉ አያጠራጥርም::
አሁን ላይ በዚህ ስፍራ የተካሄደው የትራፊክ ማሳለጥ ሂደት በወጉ ተጠናቋል:: አደባባዩ ፈርሶም ተገቢ መብራቶች ተተክለዋል:: ቀድሞ የነበረው አይነት ገጽታ የለምና እግረኞችና ተሽከርካሪዎች የመንገዱን አጠቃቀም ለመልመድ እየሞከሩ ነው:: ይህ ሲባል ግን ጉዳዩ ስጋት ካለው ሙከራ የዘለለ ነው ማለት አይደለም:: አደባባዩ ተወግዶ የተተከሉት መብራቶች ሥራ አለመጀመራቸው ከተለመደው አቅጣጫ ውጭ ብዙኃንን እያደናበረ ይገኛል:: ይህን ችግር በተባለው ልክ አይቶ ለማረጋገጥ ከጀሞ አቅጣጫ ወደ ቀድሞው አደባባይ የሚተሙትን መኪኖች ማየቱ ብቻ በቂ ነው::
ይህ መንገድ በተለይ ማለዳው ላይ ከሁሉም መጋቢ መንገዶች ወደ መሐል አቅጣጫ የሚከንፉትን ተሽከርካሪዎች በአንድ ያገናኛል:: እንደውም አንዳንዴ ድንገት ግንባር ለግንባር የገጠሙ ያህል በድንጋጤ ቀልብ የሚያስቱበት አጋጣሚ አይጠፋም:: በተለይ ትናንሽ መኪኖች ከአውቶቡስና ከባድ ተሸከርካሪዎች ጋር ሲሽቀዳደሙ በእጅጉ ያስደነግጣል::
ይህ መንገድ የትራፊክ እንቅስቃሴውን ጤናማ ለማድረግ ታስቦ የተሠራ መሆኑ ግልጽ ነው:: እንዲህ መደረጉ የቀድሞ ችግሩን ከመቅረፍ አኳያ የሚኖረውን ድርሻ የላቀ ያደርገዋል:: ሥራው በታሰበው መልኩ ከመጠናቀቁ የዘለለ በሕግና ሥርዓት የሚመራው ስልት አለመከተሉ ግን ስጋቶች እንዲቀጥሉ አስገድዷል::
አሁን ላይ ሁሉም ተሽከርካሪዎች ወደ ዋናው መንገድ ለመግባት ‹‹እኔ ልቅደም፣ እኔ›› በሚል ሩጫ ውድድር ላይ ናቸው:: ሁሉም ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ አንድ መስመር ተሰባስበው እንዲገናኙ በሚያስችላቸው አጋጣሚዎችም እያለፉ ነው::
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በየአቅጣጫው የሚመጡ መኪኖችን በአንድ ሕግ የሚያስቆማቸው የትራፊክ መብራት ሥራ አለመጀመሩ ነው:: በእርግጥ የተጀመረው እንቅስቃሴ በታለመለት ዓላማ ተጠናቆ ጤናማ ስምሪት በቅርቡ እንደሚጀመር ጥርጥር የለውም:: አሁን ላይ ያለው ማሳለጥ ግን ሥርዓት የተበጀለት አለመሆኑ ለከፍተኛ አደጋ የመጋለጥ አጋጣሚውን ያሰፋል::
በአንድ አፍታና ባልተጠበቀ አጋጣሚ ለሚደርሱ አደጋዎች እንዲህ አይነቶቹ ክፍተቶች የሚኖራቸው ድርሻ ቀላል አይሆንም:: ሁኔታው በፍጥነት ሳይስተካከል ቀርቶ ለሚከሰት የከፋ ችግርም የሚሰጥ ሰበብና ምክንያት መፍትሔ ሊሆን አይችልም:: አንድ ሥራ ተከናውኖ በፍጥነት ወደተግባር መግባት ካልተቻለ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝንበት አጋጣሚ ይኖራል::
የዚህ መንገድ ችግር በመኪኖች መተራመስ የሚስተዋለው ስጋት ብቻ አይደለም:: ለመሻገር ግራ የገባቸው እግረኞች ጭምር ከወዲያ ወዲህ ሲሯሯጡ የሚታይበት ነው:: ለጤናማ እንቅስቃሴ የሚወሰዱ ፈጣን እርምጃዎች ሁሌም ቢሆን የምስጋናን ዋጋ ሊነፍጉ አይገባም:: ትኩረት ተደርጎ፣ በጀት ተይዞ፣ ጊዜ ተወስኖ መፍትሔውን ማሳየት ቀላል ባለመሆኑ::
ሥራዎችን ጀምሮ ውጤቱን በወጉ ሳያጠናቅቁ መተው ግን ጥረቱን ሙሉ አያደርገውም:: ይህ አይነቱ ቀላል የሚመስል መዘናጋት ደግሞ ውሎ አድሮ ዋጋ ማስከፈሉ አይቀሬ ነው:: ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ‹‹እንዲህ ስለነበር ነው›› እያሉ ማሳበብ ከወደቁ በኋላ ለማንሳት መሯሯጥ ትርጉም አይሰጥም:: እናም እኔ በትዝብቴ እንዲህ እላለሁ ‹‹የጀመርነውን እንጨርስ ፣ የጨረስነውን እንጀምር››::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2016 ዓ.ም