ወዲያ ወዲህ

በህይወቴ የምቆጭባቸው ሁለት ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው በነሶቅራጠስ ዘመን አለመወለዴ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በእኔ ዘመን ሶቅራጠስን መሳይ ሰው አለመፈጠሩ ነው። የኦሾና የሶቅራጠስ ስለህይወት ያላቸው እይታ ይማርከኛል። ከእየሱስ ጋር አብረው ህይወትን የፈጠሩ ይመስል ህይወት ማለት እንዲህ ናት፣ መኖር ማለት ይሄ ነው ሲሉ በሰሚ ልቦና ውስጥ ጉጉት ይፈጥራሉ። ግን እንዴት ህይወት ገብቶኝ ሱሰኛ ሆንኩ? ግን እንዴት ራሴን ማፍቀር አቃተኝ? ያልመለስኩት ጥያቄዬ ነው።

አሁን አሁን ቁጭቴ ወደሶስት ከፍ እያለ መጥቷል። እየሱስ ምድር ላይ ሳለ ብኖር እላለው። በከብቶች በረት ሲወለድ፣ ውሀ ቀድቶና እንጨት ለቅሞ እናቱ ማርያምን ሲያገለግል፣ በጭቃ ህያው ወፍ ሲሰራ ባየሁት እላለው። ወደ ገሊላ ሲያቀና፣ በዶኪማስ ቤት ውሀውን ወደ ወይን ሲቀይር ብታደም እላለው። የቢታኒያ ድንጋዮች ሲያመሰግኑት፣ በበርሀ ውሀ ሲያፈልቅ፣ በደብረታቦር በብርሀን ባየው እመኛለው። መካኗን ሳራን ሲያስቅ፣ ፈርኦንን ሲቀጣ፣ ለአብረሀም ቃል ሲገባ፣ ኖህን ከጥፋት ውሀ ሲያድን ጎኑ ብሆን እላለው። በጌቴሴማንያ በአትክልቱ ስፍራ፣ በጥብሪያዶስ በባህሩ ዳር፣ በዳናው ጥላ በጌርጌሴኖን አብሬው ቆሜ ቢሆን፣ ጣሊታን ከሞት ሲያስነሳ፣ መቅደላዊት በእንባዋ እግሩን ስታጥብ፣ የሳምራዊቷ ሴት ሲያነጋግር ሰምቼ ቢሆን። በአህያ ውርንጭላ ሲጓዝ፣ የማርያም እህት ማርታ መልካም እድልን መርጣ እግሩ ስር ስታርፍ፣ ዘኪዮስ ሊያየው ዛፍ ላይ ሲወጣ፣ ከተከተሉት ከአምስት የገበያ ህዝብ አንዱን ብሆን። በእለተ አርብ አሳ ካበላቸው አምስት ሺ እንግዶች አንዱን ሆኘ ብሆን ያምረኛል። እንደዛች ለአስራ ሁለት አመት ደም እንደሚፈሳት ሴት ቀሚሱን ዳስሼው ቢሆን፣ እንደጰርጠሚዮስ የናዝሬቱ እየሱስ ሆይ ብለው፣ እንደ ሀር ሻጪዋ ሊዲያ በድምጹ ልቦናዬ ቢከፈት አስባለው።

እያሱ ጸሀይን ሲያቆም፣ ኤሊያስ ዝናብን ሲገስጽ፣ ሙሴ ባህር ሲከፍል፣ ዳዊት ጎልያድን ሲጥል፣ ደሊላ ሳምሶምን ስትረታ፣ ቤርሳቤህ ከኦርዮን ስትሸሽ፣ ሄሮዲያዳ አንገት ስታስቆርጥ፣ አስቴር ሀማስን ስትሰቅል፣ ሜልኮል ስትዘባበት፣ ኦዚያ ሲቀሰፍ፣ ሩት ስትቃርም፣ ሶስና ከእደረበና ስትድን፣ አፎሚያ ሲከብር፣ እስቂያስ ሲያነባ፣ አጋር ስትሰደድ፣ አናኒያና ሰጲራ ሲዋሹ፣ አክአብ ሲዝት፣ ኤልዛቤል ሲያቅራራ፣ ዮሴፍ ሲሸጥ፣ አዳም ሲያንቀላፋ ሰው ሆኘ ኖሮ ስል እመኛለው። ቃየል በወንድሙ ላይ ሲነሳ፣ ሄዋን ሉድ እና ቅሌማን ስትወልድ፣ ታራ ጣኦት ሲያመልክ፣ ስምኦን አይኑን በወስፌ ሲያፈስ፣ ፌቨን ወደቆረንቶስ ስትላክ፣ ሀናና ፍናና ሲነቋቆሩ ባይና ብሰማ። ጴጥሮስ ሲክድ፣ ይሁዳ ሲያስመስል፣ በርባን ሲፈታ፣ ቬሮኒካ የጌታን ደም ስትጠርግ ህይወት ኖሮኝ ቢሆን እላለው።

ጴጥሮስን ከቀራጭነት፣ ስሞንን ከአሳ አጥማጅነት፣ ማቲያስን ከውንብድና ወዳጁ እንዳደረገ እኔንም ከሱሰኝኔ አውጥቶ ደቀመዛሙሩ ቢያደርገኝ ስል ይሆኑ እመኛለው። በዚህ አለም ላይ እየሱስን እንደመከተል ምን ጥበብ አለ? ግን እኮ በራሴ ዘመን ላይም እየሱስን መፍጠር እችላለው። ያን ማድረግ ለምን አቃተኝ? ያኔ ብቻ አይደለም እየሱስ ዛሬም ጌታ ነው። ለምን በራሴ ውስጥ እሱን መፍጠር ተሳነኝ? ሰው ከምኞት ወጥቶ ላመል ፈቀቅ እስካላለ ድረስ የትናንት ምርኮኛ ነው። ቅርቡ እየሱስ ርቆኝ በማይሞትበት አለም ላይ እየኖርኩ የተወለደበትን ዘመን እናፍቃለው። እሱ እኮ ዛሬም አዲስ ..ዛሬም ስለእኛ ጎለጎታ ነው ብሎ የሚነግረኝ አማኝ አጣሁ። ለነገሩ ቢነግሩኝስ መች ሰምቼ። ክርስትና የተነሳሁበት የአርባ ቀን አጥቢያዬ አጠገቤ አይደል። ቄሱን ሳልሰማቸው መቼ ቀርቼ አውቅና። ያን በስብከቱ ጉድ የተባለለት ሰው ጆሮ ግንዴ ላይ አይደል? መች ከእውነቴ አራቁኝ። መች ከምኞቴ አሸሹኝ። መች ወደእየሱስ አደረሱኝ። አውቆ የተኛን አሉ..

መርፌ ሲለግም መች ቅቤ ይወጋና?

እንደልማዴ የማጨሰውን ሲጋራ በመሀል ጣቴ ሰክቼ፣ እንደእኔ ግራ የገባት የምትመስለውን የከሰዓት ጀምበር ተከትዬ እግሬ ወደወሰደኝ ወደሆነ ቦታ ተራመድኩ። ሰው ግን ሀሳብ ይጠፋዋል? ድንገት መጥቶ ሀሳብ ይጠፋኛል። ሃሳብ ቢኖረኝ ኖሮ እግሬ እንደመራኝ አልሄድም ነበር። እየሱስን ያልደረስኩበት ያለሀሳብ እግሬ እንደመራኝ እየተጓዝኩ ይሆን? አዎ እንደዛ ቢሆን ነው። እንደዚ ካልሆነ ሌላ ምንም አይሆንም። አንዳንድ ልማዶች የአለመርባት አዲስ ዓመቶች ናቸው። ሰው በሀሳብ እግሮቹን ካልመተረ መድረሻው የለውም አልኩ።

ብቻ እግሬን ተከትዬ ራቅ ብዬ ሄድኩ። የሲጋራዬ እድሜ አልቆ የመጨረሻ ጭሴን ወደሆዴ ስቤ ሌላ አቀጣጠልኩ። እየሱስን በእንደእኔ አይነቱ ወንበዴ ውስጥ ፈልጎ ማግኘት ፓስፊክ ውቅያኖስን በማንኪያ ጨልፎ ማጉደል መስሎ ታየኝ። ማን ነበር ያ በትንሽ ጽድቅ ከማንም ቀድሞ ገነት የገባው? ማን ነበረች ያቺ ስትዘሙት ኖራ በእግዜር ጻድቅ አይኖች የታየችው? ገድለ ኦሪት..ገድለ ሀዲሴን እንዳላበላሽ በሀሳቤ መሀል እየተሰነቀረ..አንተ እኮ ማለት እያለ ያመጻድቀኝ ጀመር።

ያለሀሳብ መጓዝ በመኖር ውስጥ ያለ የሰው ልጅ ያልደረሰበት ምቹ የነጻነት ስፍራ መስሎ ታየኝ። ግን አይደለም እንደማሰብ ጉልበታምና ሞገሳም ነጻ አለም አላየሁም። ገብቶኝ እንኳን ልወዳጀው አቅም አጣሁ። አለማሰብ አለማወቅ ነው። ዝም ብሎ መኖር..ዝም ብሎ መሞት። ህይወትን የምናምርባት በማሰብ ውስጥ ነው። ሞትን የምንንቀው በስልሳሌ ውስጥ ነው።

ባለማሰብ ብዙ ተጉዤ መድረሻዬን አንድ ስፍራ አደረኩ። ሰፊ ግቢ ውስጥ በቅለው የግቢውን ውጪ አውራ ጎዳናውን ባጠሉ ዛፎች ስር። ጥላው ያምራል..በተደራረቡና በተቃቀፉ ረጃጅም ዛፎች የተሰራ ጥላ ነው። የአስፓልቱ ግማሽ ድረስ ተወርውረው ጥላማ አድርገውታል። የግንቡን አጥር ተደግፋ አንዲት ሴት ቆማለች። አለማሰቤ ሀሳብ ጀመረ። ምንም እንኳን ተጉዤ ባልደርስበትም ከክርስቶስ ምክረ ሀሳብ ማፈንገጥ አልወድም። እንዲህ ስል ጻድቅ ነኝ እያልኩ ሳይሆን ቢሆንለት ለእውነት ቅድሚያ የሚሰጥ ሰው ነበርኩ እያልኩ ነው። ከጎለጎታ በፊትም ሆነ በኋላ የእየሱስ ህገ ሥርዓት መነሻ ያደረገው ፍቅርን ነው። አቅም ኖሮኝ ብችል እንደእየሱስ ጠላቶቹን ሁሉ በፍቅር የረታ መሆን እፈልግ ነበር። ግን አልቻልኩም..የምችለው አንድ ነገር ነው አቅም አጥቼ እንዳልጠላ መሆን።

ፊት ለፊቴ አንዲት ጉብል የቆመችበት ጥላ..ጥላው አማረኝ። ከጸሀይ ወደጥላ ልብ ላይ የሚያርፍ የሆነ መንፈስ አለው..። ያ መንፈስ አረፈብኝ። ሲጋራዬን እያቦነንኩ ከወጣቷ አጠገብ ሄጄ ቆምኩ። ለትዝብት በሰሉ አይኖች ፊትለፊት ጎዳናውን ትቃኛለች። ሀሳብ ብትዘራብኝ ስል ተደናብሬ ሄጄ ከሀሳቧ ላደናቅፋት ፈለኩ።

ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም ስል ከሲጋራዬ አንድ ጊዜ ስቤ ‹እንኪ! ስል ዘረጋሁላት።

እንደዛ ቀን አልተገላመጥኩም። ለምላሹ ብዙ መልካም ነገሮች ነበሯት። እሷ ግን ግልምጫን አስቀድማ እንዳልነበረ አደረገችኝ።

አልተከፋሁም። ‹ከሌሎች ጋር ለመኖር ብዙ አማማራጮች አሉን። እንደመልካም አንደበት ግን ጥሩ አማራጭ የለንም› ስል ምንም እንዳልመሰለኝ እንድታውቅ በዛውም እንድትማር ቃል ወረርኩላት።

‹የሰጠኸው እንደሚሰጥህ አታውቅም?

‹የሰጠውሽ መጥፎ መሆኑን በምን አወቅሽ?

‹የሚረቡ ወንዶች ጣታቸው መሀል እስክሪፕቶ እንጂ ሲጋራ አይዙም› ብላ ወደትዝብቷ ተመለሰች።

ኩምሽሽ አልኩ። ‹እኔ ያለኝን ነው የሰጠሁሽ› ስል ድንጋጤዬን ለመደበቅ ሞከርኩ።

‹ያሉን ነገሮች ሁሉ የማይጠቅሙን እንደሆኑ አታውቅም?

‹አልስማማም። ካጣናቸው እና ከሌሉን ነገሮች እንደሚበልጡ ነው የማውቀው።

‹እንደዛም ማሰብ ትችላለህ። ከሁሉም የሚበልጠው መልካም አንደበት ነው ስትል የሰማሁ መሰለኝ..?

‹አዎ ሰምተሻል..!

‹እንግዲያውስ ከሁሉም የሚበልጥ ሌላ ነጻ አውጪ እውቀት እንዳለም ጨምርበት› ብላኝ ትታኝ ሄደች። ከጥላው ወጥታ ጸሀዩዋ ላይ ስትማገድ የሆነ ነገር ቅር ቅር አለኝ። በወጣችበት ቅጽበት ተሲያቷን ትታ ጀምበር እንደጌታ የስቅለት ቀን ጨላለመች።

ወደእየሱስ ታደርሰኝ እንደሁ ስል ተከተልኳት። አስወጣችን እንጂ ከመች ጀምሮ ነው ሴት ወደገነት የምታስገባው? አንዱ ልቤ እንዲህ ይለኛል። ቢሆንም መራመዴን አላቆምኩም።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You