ጥበብ እና ቶኔቶር… ቶኔቶርና ሀገር ፍቅር… የርዕሰ ጉዳያችን መዘውረ ማዕዘናት ናቸው። የሃሳባችን ማጠንጠኛ ናቸው። በአንደኛው ገብተን በሌላኛው ተሿልከን ሦስቱንም ካገናኘው ድልድይ ላይ እኛም እንገናኝ። “ጥበብ ወዴት ነሽ?” እንበል። ጥበብም ጆሮዎቿ በዘመን ርቀት በቆይታ ብዛት ያላረጁና ያልጃጁ ስል ናቸው። ታዲያ ከመስማት አይቦዝኑምና እሷም ሰምታ ገና “አቤት!” ከማለቷ በድምጽዋ እንደ ሰሊሆም ወንዝ ልብን ታረሰርሳለች።
ሦስቱን ስብጥሮች ያገናኛቸው ድልድይም ይሄው የጥበብ ጥም ነው። እናም ቶኔቶር ኢትኤል ከሀገር ፍቅር ማማ ላይ ቆሞ ከማዶ አሻግሮ “ጥበብ ወዴት ነሽ?” ሲል ጥሪውን አስተጋባ። ጥሪውም ለአንድ የጥበብ ድግስ ነበር። ታዲያ ስለ ጥበብ ሲሉ ደግሰውና ጥበብን ጠርተው፤ እሷም ከድግሱ ካልተገኘችማ፤ አጃቢዎች ቆመው ከሠርጉ መሃል ሙሽሮቹን እንደማጣት ይሆናል። ጥበብ ግን አልቀረችም።
በርከት ያሉ ስጦታዎቿን ይዛ ከቤተ ተውኔቱ ቅጥር ግቢ፤ አልፋም ከአዳራሹ ዘልቃ ገባች። ቶኔቶር ኢትኤል መልቲ ሚዲያና ጥበብ፤ መጋቢት 16 አመሻሽ፤ በሀገር ፍቅር የቲያትር አዳራሽ ተገናኙ። በዚያም በድጉስ ጥበብ ላይ፤ ትኩስ የኪነት ወጥ ከያይነቱ ተወጥውጦ፤ የጥበበ ማዕዱ ለታዳሚያኑ ቀርቧል። “ጥበብ ወዴት ነሽ?” ሲል የመጣውም አጣጥሞ “ለፌ ወለፌ… ጥበብ ትስጥልኝ!” ሲል ተመልሷል። “ለፌ ወለፌ” ማለት አዘጋጁ ቶኔቶር ኢትኤል መልቲሚዲያ ለጥቅል ጥበባት ዝግጅቱ የሰየመው ስያሜ ሲሆን በግእዙ ወዲያ ወዲህ እንደማለት ነው። ስያሜው እንደሚነግረንም ቶኔቶር፤ በ“ለፌ ወለፌ” ጥቅል የጥበብ ማዕድ፤ የጥበብ አፍቃሪውን የጥበብ ረሃብ ለማስታገስ ሲል ባተሌ ስለመሆኑ ይነግረናል። ይህ ዝግጅት ቀደም ሲል በባህር ዳርና በአዳማ ከተሞች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጥምረት ፈጥሮ ያካሄደው ነበር። አሁን ታዲያ፤ የዚህ ግዙፍ ዓላማ ገመድ መበጠስ የለበትም ብሎ ስላሰበ፤ የለፌ ወለፌን የመቀመጫ ዙፋን ከአዲስ አበባ በማድረግ ከ30 ዓመታት በፊት የጣልናቸውን የጥቅል ጥበባት ስንቅ ይዞ፤ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ወዲያ ወዲህ ለማለት በመንገድ ላይ ነው።
ባሳለፍነው ሳምንት በሀገር ፍቅር “ጥበብ የት ነሽ?” ሲል ያሰናዳው መሰናዶም ከዚሁ እሳቤ በመነሳት ነበር። ይህም፤ በአዲስ አበባ ከተማ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
ታዲያ ቶኔቶር ኢትኤል፤ ዳግም ከሞት ሊቀሰቅሰው የሚፈልገው ይህ ጥቅል ኪነ ጥበብ ምንድነው? ብዙውን ጊዜ ከቲያትር ቤቶች ውስጥ ገብተን ቲያትር ተመልክተን እንወጣ ይሆናል። ከሲኒማ ቤቶችም ጎራ ብለን ፊልማችን ኮምኩመን ወጥተንም ይሆናል። ከሙዚቃ ኮንሰርቱም እንዲሁ፤ በሙዚቃው ዘና ፍንትው ብለን። ከአንድ የሥነ ጽሑፍ ምሽት ላይ ተገኝተን፤ በተመስጦ በምናብ ስልብ ብለን፤ በደስታ አጨብጭበን ወጥተንም ይሆናል። ታዲያ ሁሉንም ግን ያገኘናቸው በተለያየ ጊዜና ቦታ ብዙ ዞረን፤ ለእያንዳንዱ መግቢያ ከኪስ መዘን ነውና የቱንም ያህል ቢሆን፤ እንደ ጥቅል ጥበብ ሁሉንም ከአንድ የመድረክ ድግስ፤ ከአንድ ማዕድ ላይ ጥቅልል አድርጎ ጎርሶ እንደመውጣት አያረካንም።
ጥቅል ጥበባት ሲባል፤ ለአንድ የሙዚቃ ኮንሰርት ገብተን አንድ ግጥም እንደሚመረቅልን ዓይነትም አይደለም። ይልቁንስ በአንድ ጠጠር ሁሉንም… እንደማርገፍ ነው። ከሁሉም የጥበብ ዓይነት እኩል በእኩል በውህደት ይቀርባል። ነገሩ… አሁን ወደኋላ ሳይስበን አልቀረም። የቀደመውን፤ ደጉን የጥበብ ዘመን እናስታውስ። ታዲያ በዚያ ደጉ ዘመን በጥበብ መድረክ ላይ ስስት አልነበረም። በገፍ ሞልቶ ከአዳራሹ ለሚፈሰው ተመልካች፤ የሚቀርበው የኪነ ጥበብ ማዕድም በገፍ ነበር።
ሥነ ጽሑፉ..ሙዚቃው… ቲያትሩ… አጫጭር ድራማው… ሥዕሉ… ቀልድና ልዩ ልዩ ጨዋታው…ኧረ ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቅና… ብቻ ግን ከቡናው ጀበናና ሲኒ አጠገብ እንደሚጤሰው እጣን ሁሉም ይንቦለቦል ነበር፡፡
እነርሱም ልክ እንደኛው፤ እንደዛሬው በተናጠል መብረቅረቅን ሳይመርጡና ሳያምራቸው በፊት አንድ ላይ ሲቀርቡ የነበራቸውን ውበት የነበረ ይናገረው። ለደጉ ዘመን ደግነት አንድም ከዚሁ ህብር ውበት የተቀዳ ነው። ጥቅል ጥበባት በአንድ ሲሆኑ ሙያው ከሙያው ጥበበኛውም ከጥበበኛው አንዱ ከአንዱ ጋር ከመደጋገፉም፤ የጥበብ አፍቃሪው ተመልካችም ቁጥሩ ከፍ ያለ ይሆናል። የሙዚቃ አፍቃሪው ሙዚቃውን ብሎ መጥቶ፤ ልቡ በሁሉም ተለክፎ ይሄዳል፡፡
አንዱ አንዱን ፍለጋ ገብቶ ከዚያ ወዲያ እየዋለ እያደረ የድፍን ጥበብ አፍቃሪ ያደርገዋል። እንዲህ እንዲያ እያለ የታዳሚው ቁጥር ሲያይል፤ የኪነ ጥበብ ድግስ በተዘጋጀ ቁጥር ሁሉ ግፊያና ለመግባት የሚደረግ ሽሚያው ሌላ ነው። በእውነቱ እንደዚያ፤ የኪነት ቡድኖችና ጥቅል ኪነ ጥበባት እንደነበሩበት ጊዜ ያለ ተመልካችና የተመልካች ቁጥር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፤ አንዴ እንኳን ተመልክተናል ካልን ቅጥፈት ነው።
አሁን ላይ የመነመነው ተመልካቹ ብቻም ሳይሆን፤ ጥበብም ጭምር ናት። በፊት የነበሩ እጅግ በርካታ የጥበብ ዓይነቶች፤ በየጊዜው ከአካሏ ላይ እየረገፉ ቀጥና ከስታለች። ግራና ቀኙ እንዳለሆኖ፤ የቶኔቶር ኢትኤል ግዙፉ ዓላማ ግን እኚህኑ ወርቃማ ጥበባትና ተመልካች ዳግም መመለስ ነው፡፡
ቶኔቶር ኢትኤል ማነው? መልክና ግብሩስ ይሄው ብቻ ነው? አይደለም፤ ወዲህ ወዲያ የሚልባቸው ሌሎች በርካታ ነገሮችም አሉ። ህጋዊነቱን በማወጅ የጥበብን በር ከፍቶ የገባው በመስከረም 14/2014 ዓ.ም ነበር። ይህ ማለት የ2 ዓመት ባለዕድሜ ነው። ታዲያ ዕድሜው ድክ ድክ ለማለት እንጂ ለመሮጥ የማይሆን ዕድሜ ላይ ያለ ቢመስልም፤ ቆሞ ለመሄድ ካለው ጉጉት የተነሳ መሮጡን ግን ጀምሯል።
“የሚበስል እንጀራ ከምጣዱ… የሚያድግ ጥጃ ከገመዱ” እንዲሉ ባለችው አቅም እየተፍጨረጨረ ከወዲሁ የጀመራቸው አዳዲስና የቀደመውን ወርቃማ ዘመን የመመለስ ጽኑ ፍላጎቱ ያሳብቃል። “ስምን መልዓክ ያወጣዋል” ብሎም እንደ ስያሜው ለመሆን አሰበና፤ ኢትዮጵያ በታሪክ እንደምትጠብቀው እንደ ሕፃኑ “ኢትኤል” ያለ ይመስላል።
እንግዲህ ብዙ የካብን ቢመስልም፤ ሙገሳን ካወቁበት መቆሚያ፤ ከሳቱትም መሰበሪያ ነውና… ቶኔቶር በፊልሙ ዘርፍ፤ የሙሉ ጊዜ፣ አጫጭር እና ዘጋቢ ፊልሞችን ያቀርባል። እንዲሁም ተከታታይ የቴሌቪዥን ሚኒ ሲርየስ፣ ሲትኮምና ሲርየስ ድራማዎችንም ያዘጋጃል። የአየር ሰዓት በመውሰድም በሬዲዮ ሞገድ በልዩ ልዩ ሥራዎች ይንቀሳቀሳል። ሌላው ጥሩ ልንለው የምንችለው ነገር፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ከአራት ቤተ ተውኔቶች ማለትም፤ ከሀገር ፍቅር፣ ከብሔራዊ ቲያትር፣ ከአዲስ አበባ ቲያትርና ባህል አዳራሽ እንዲሁም ከራስ ቲያትር ጋር ህብረት በመፍጠር በቲያትር ቤቶቹ አዳራሽ በተለያዩ ጊዜያት ሥራዎቹን ያቀርባል።
በ“ወፌ ወለፌ” “ጥበብ ወዴት ነሽ?” ሲል የጥበብን ድምጽ ፍለጋ የሚወጣውም በዚሁ እንቅስቃሴው ነው። የሚያቀርባቸው ሥራዎችም አብዛኛዎቹ ከዛሬ ሠላሳ ዓመታት በፊት በቲያትር ቤቶቹ ውስጥ ይቀርቡ የነበሩ ይዘቶች ናቸው። ለአብነትም እንደ “በላ ልበልሃ” እና የ“አዝማሪ ቅብብል” ያሉ ይገኙበታል። በሌሎች ግብሮቹ፤ ሕትመትን ጨምሮ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ድራማዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ዝግጅቶች፣ ልቦለዳዊ እና ዘጋቢ ፊልሞች፣ ቲያትሮችና የኪነ-ጥበብ ፕሮግራሞችንም ይሠራል፡፡
የዓላማውን ዳርቻ ለማስፋት በሚያደርገው ጥረት ደግሞ፤ ትውልዱን በሰላ ጥበብ ለመቅረጽ የራሱን ትምህርት ቤት ከፍቶ በተለያዩ ዘርፎች ያስተምራል። በአጭር ጊዜ የሚሰጣቸው ስልጠናዎች እንዳሉ ሆነው በመደበኛነት፤ ከሙዚቃና ፊልም አንስቶ እስከ ቅርጻ ቅርጽና ሞዴሊንግ፤ በሌሎችም በማስተማር ላይ ይገኛል።
የጽንሰ ሃሳባችን ጥለት የተቋጨው ከቶኔቶር ኢትኤል መልቲ ሚዲያ ጋር እንደመሆኑ እኛ ካልነው ባሻገር እነርሱስ ስለራሳቸው ምን ይላሉ? ያየን የሰማነውን ይዘን፤ በጥያቄ ዘልቀንባቸዋል። እዩኤል ወርቁ፤ በመልቲ ሚዲያው ውስጥ የፊልምና ቲያትር ክፍል ኃላፊ፤ እንዲሁም የ“ለፌ ወለፌ” ኪነ ጥበብ ረዳት አዘጋጅ ነው። ካወጋን ብዙ ነገሮች መካከል በጥቂቱ እንቀንጭበው።
እዩኤል እንዲህ ይላል “…የሀገራችን የኪነ-ጥበብ እንቅስቃሴ በየዘመናቱ ልዩነት የራሱን መልክ እየያዘ፣ የራሱን ዕድገት እያሳየ የመጣ ቢሆንም፤ አሁንም ድረስ ወንዝ መሻገር እንዳቃተው መደምደም ይቻላል። ቶኔቶር ኢትኤል መልቲ ሚዲያ ከዚህ አንፃር የሚታየውን ክፍተት በመሙላት የሀገራችን የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ከኢትዮጵያም አልፈው በሌሎች የዓለም ሀገራት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻል እና የሀገራችን የዘመናት ታሪክ፣ ለረጅም ዘመናት ፀንቶ የኖረ ድንቅ ባህል፣ ሃይማኖታዊ እሴት በዓለም የኪነ-ጥበብ መድረክ እንዲታዩ እና እንዲታወቁ ማድረግ ትልቁ አላማው ነው”።
ከድሮ ዘንድሮ ላይ ከጎደሉና ከረገፉ የጥበብ ሰበዞች መሃከል ቶኔቶር፤ “የአዝማሪ ቅብብሎሽ” እና “በላ ልበልሃ” የመሳሰሉትን ዳግም ለመመለስ በመፍጨርጨር ላይ ይገኛል። ይህን ሲያስብ ከማዝናናቱ ባሻገር ዓላማው ምንድነው? መባሉ አይቀርም። እዩኤል ለዚህ መልስ አለው፣ “በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ የምንኖራቸው እና ቀደም ባለው ጊዜ የነበረው የሀገራችን ማህበረሰብ ይኖራቸው የነበሩ ባህላዊ የአኗኗር ዘይቤዎች እና ባህሎች ራሳቸውን ችለው ጥበብ ናቸው ብሎ ያምናል። ይህ ብቻ ሳይሆን በተለይም የሀገራችን ክውን ጥበባት ቅርፅን እና የአቀራረብ ፍልስፍናን በቀጥታ ከውጭው ዓለም የቀዱ ናቸው። ሆኖም ግን ለዘመናት ማህበረሰባችን በዕለት ተዕለት ሕይወቱ ውስጥ የሚከውናቸው የአኗኗር ዘይቤዎች ራሳቸውን ችለው ሌላ አዲስ ቅርፅ እና ፍልስፍና ይዘው ለመነሳት በቂ መደላድል ናቸው፣ ከፍ ሲልም ራሳቸውን ችለው አንድ የድረካ ስልት ናቸው ብለን እናምናለን። ለምሳሌ የአዝማሪ ጨዋታን እና በላ ልበልሃን ብቻ ብንወስድ ምንም ሳይጨመርባቸው እና ሳይቀነስባቸው ራሳቸውን የቻሉ የመድረክ ጥበባት መሆን የሚችሉ ናቸው። በተለይም አሁን የምንኖርበትን ማህበረ-ፖለቲካዊ ሕይወት ለመፈተሽ ስንጠቀምባቸው ደግሞ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖራቸዋል”፡፡
ሌላው፤ ከአንጋፋዎቹ የኪነ-ጥበብ ሰዎች መካከል እውቁ የቲያትርና የሬዲዮ ድራማ ደራሲ እና አዘጋጅ ኃይሉ ፀጋዬ፤ ደራሲ፣ ተዋናይ፣ መምህር እና አዘጋጅ ንጉሱ ጌታቸው፣ ድምፃዊት ሄራን ጌዲዮን፣ ታዋቂው የፊልም ዳይሬክተር ሄኖክ አየለ፣ ተዋናይ እና አዘጋጅ ሰለሞን ተስፋዬ (የጉዝጉዝ ልጅ) ከዚህ ግዙፍ ዓላማ በስተጀርባ ከመልቲሚዲያው ጋር ስለመሆናቸውና ሌሎች በአጋርነት የሚሰሩ በርካታ አካላት ስለመኖራቸው፤ ኢዩኤል ተናግሯል።
ባሳለፍነው ሳምንትም በሀገር ፍቅር በነበረው ዝግጅት ላይ አንጋፋዎቹም ታድመውበት ነበር። ሺመላሽ ለጋስ ከድፍን 50 ዓመታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ከቆመባት መድረክ ላይ ቆሞ ትውስታውን ለታዳሚው አካፍሏል። የባህልና ቋንቋ መልኩ ያልደበዘዘበት ሺመላሽ፤ ቲያትሩን ጨምሮ በብዙ ፊልምና ድራማዎች ላይ መስሎ ሳይሆን ሆኖ ከመተወኑም፤ የባላገርነትን ገጸ ሰብ ወክሎ በብዛት በመጫወት ደረጃ ምናልባትም ወሰኑን ሳይሰብር አይቀርም ብዬ አሰብኩ… ከባለ ሀምሳው ሺመላሽ ለጋስ ቀጥሎ፤ በኢትዮጵያ ተውኔት ውስጥ በተለይ ደግሞ በሬዲዮ ድራማ ፀሐፊነቱ ግንባር ቀደም የሆነውና ሌላኛው የ40 ዓመታት የጥበብ ተጓዥ፤ ፀሐፊ ተውኔት ኃይሉ ጸጋዬም ከንጉስ ጌታቸው ጋር የመድረክ ቆይታ አድርገዋል። የሞጋቾች የቴሌቪዥን ድራማ ፀሐፊው ኃይሉ ጸጋዬ፤ በኢትዮጵያ የቲያትር ታሪክ ውስጥ በሁለት ዓይነት የአጻጻፍ ስልት ከሚታወቁት ከእውቆቹ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን እና ከመንግሥቱ ለማ መሀከል በመሆንና የሁለቱንም ዓይነት ስልት ቀይጦ በመጠቀም ሦስተኛው ተጠቃሽ ፀሐፊ ተውኔት ልንለው እንችላለን።
በእለቱ ከነበሩት መካከል ሌላኛው፤ የኢትዮጵያ የፊልም ጥበባት ማህበር ፕሬዚዳንት፤ አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ ነበር። “እንደ ምክር ያዙት እንደ ዲስኩርም ስሙት” ሲል ለጥበብ ታዳሚው ወጣት እራሱን ቀይሮ እንዴት ሀገሩን ለመቀየር እንደሚችል ምክረ ጥበብ ጣል አደረገ። አይ…እኔን ሞት ይርሳኝ! አልረሳሁትም፤ የገጣሚ ደምሰው በሻው ግጥሞችና የወሎ እስክስታ፤ የባህል ውዝዋዜውም የማይረሳ ነው። የ“በላ ልበልሃ” ጨዋታና ተውኔቱም እንዲሁ…
በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ውስጥ ቶኔቶር ኢትኤል አለ። በቶኔቶር ኢትኤል ውስጥ ደግሞ “ለፌ ወለፌ” አለ። “ለፌ ወለፌ”ም “ጥበብ ወዴት ነሽ?” ይላል። በዚህ ጥሪና የጥበብ ጉዞ ውስጥ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ፤ መንገዱም ሁሉ የወርቅ ንጣፍ አይደለም። የሄደን ነገር መልሶ በማምጣት ውስጥ ከፊት እንደ ጅብራ የሚቆሙ ጋሬጣዎች ብዙ ናቸው። ለመሆኑ እጅግ ፈታኙ አቀበት የትኛው ይሆን? በዚህቹ ጥያቄና የእዩኤል ወርቁ ምላሽ እናሳርግ፡፡
“ለፌ ወለፌ መድረክ እጅግ ፈታኝ የነበረው ሁኔታ ፕሮግራሙን ለጥበብ አፍቃሪያን ተደራሽ የማድረግ፣ በቂ ተመልካች የማግኘት ችግር ነው። በርግጥ ይህ ችግር አሁን በመጠኑ የተፈታና ለፌ ወለፌም ወደፊት እንዲቀጥል ለማድረግ የማያግደው ቢሆንም አሁንም ይህ ሰፊ ማህበራዊ ፋይዳ ያለው መድረክ ቀጣይነት እንዲኖረው የበርካታ አካላትንና ተቋማትን ድጋፍ እና አጋርነት ይጠይቃል” ብሏል።
በስተመጨረሻም “ለፌ ወለፌ”፤ ይህን መሰሉ የጥበብ ድግስ እንኳንስ በነፃ ተገኝቶና ተገዝቶም ቢሆን ይላሳል እንጂ አይራከስም። ዝግጅቶቹ በሚኖሩበት ወቅት “ጥበብ ወዴት ነሽ?” ሲል ለመጣው ሁሉ ያለምንም ቆም በሉ፤ በር አሳላፊ በሩ ወለል ብሎ ይከፈታልና በ“ዘመን ጥበብ” ስም ግብዣው ለእናንተ አንባቢያን ይሁን፡፡
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም