ወላጆቹ አርሶ አደር ናቸው። እርሱም አርሶ የመብላቱን ጉዳይ ቢያውቀውም ቅሉ የህይወት መንገድ ወደሌላ ሙያ መርታዋለች። በልጅነቱ የቅስና ትምህርትን በአግባቡ ቢወስድም ከወጣትነት ዕድሜው ባለፈ ግን አልገፋበትም። በየሰው እጅ እና አንገት ላይ አልፎ ተርፎም በሴቶች ፀጉር ላይ የሚንጠለጠሉ የብር እና የወርቅ ጌጣጌጦችን እያዘጋጁ የመሸጥን ጥበብ ተምሯል። ለሥራ ካለው ፍቅር የተነሳ በሚሰራበት ቦታ እያደረ ህይወቱን መለወጥ ችሏል።
ፒያሳ ካሉ ወርቅ ቤቶች በአንዱ መኖሪያውን አድርጎ ባገኘው ዕውቀት እስከ አስመራ የደረሰ ንግድ አካሂዷል። አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ወርቅ እና ብር መሸጫ ቤት ከፍቶ እየሰራ ይገኛል። ሙሉ ስሙ በርሄ ኃይሌ ይባላል። ተወልዶ ያደገው በትግራይ ክልል አክሱም ማይወይኒ አካባቢ ነው። በልጅነቱ ከአባቱ ጋር ወደ እርሻ መውጣት የጀመረው በርሄ በሬዎቹን እየነዳ አባቱን ያግዝ እንደነበር ያስታውሳል።
አቅሙ ጠንከር ሲል ደግሞ እርሻውን በእራሱ ብቻ እየከወነ በየዓመቱ በቆሎ፣ ገብስ እና ጤፍ ያመርት ነበር። ከእርሻ ሥራው በተጓዳኝ ደግሞ የቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ ፊደል መቁጠር ጀመረ። የቄስ ትምህርቱ ግን ወደቤተክህነት ትምህርት አድጎ በአካባቢያቸው በሚገኝ ቤተክርስቲያን ድቁናን እስከመማር አድርሶታል። ከሥራ ቀናት በቤተክርስቲያን ተገኝቶ ሲቀድስ በሥራ ቀናት ደግሞ በቤተሰብ መሬት ላይ እርሻውን ሲከውን ይውላል። እንዲህ እንዲህ እያለ ሲኖር ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንዳለበት ያሰበው ወጣት ወደአክሱም እየሄደ መስራት እንዳለበት ይወስናል።
በእግሩ አቅራቢያው ወደምትገኘው ታሪካዊቷ አክሱም ከተማ እየተጓዘ የሸክም ሥራ እና የተለያዩ የቀን ሥራዎችን ሰርቶ አመሻሽ ላይ ወደቤቱ ይመለሳል። ሁለት ዓመታትን በአክሱም እየተመላለሰ ከሰራ በኋላ ግን ቤተሰቡ አንዲት እንስት አጭተውለት እንዲያገባ ጥያቄ ያቀርቡለታል። በሁኔታው ብዙም ያልተደሰተው በርሄ ጭንቅ ይለዋል። ምክንያቱም ቤተሰብ የሚያስተዳድርበት በቂ ገቢ እንደሌለው ስለሚያውቅ ትዳር በቶሎ መመስረቱን አልወደደውም። እናም ጥቂት ዓመት ሰርቶ እራሱን ከለወጠ በኋላ ትዳር ለመያዝ በማሰብ በ1984 ዓ.ም ከማይወይኒ ተነስቶ አዲግራትን መዳረሻው አደረገ።
ወደአዲግራት ሲያቀና ደግሞ በኪሱ የያዛት አንድ መቶ ብር እንደነበረች ያስታውሳል። በዚያም ሶስት ቀናትን ሥራ እያፈላለገ የአልጋ እና የምግብ ወጪ እየከፈለ ቆይቷል። በእንዲህ አይነት ሁኔታ ጊዜውን እየገፋ ያለመውን የተሻለ ህይወት እንደማያገኝ በመረዳቱ ፊቱን ወደሌላ ከተማ አዙሯል። ከወጪ ቀሪ እጁ ላይ ያለችውን 70 ብር ይዞ አዲስ አበባ የሚሄድ መኪና ውስጥ ለመሳፈር ወስኗል።
ስለአዲስ አበባ ከወሬ ውጪ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። በወቅቱም ከተማዋ ላይ አንድም ዘመዴ የሚለው ሰው ባይኖርም የአካባቢው ሰዎች ግን ተክለሃይማኖት የተባለው አካባቢ ይኖሩ እንደነበር መረጃ ነበረው። እናም የማያውቀው ከተማ ለመሄድ ቢሳፈርም ተሽከርካሪው ውስጥ ግን አንድ የማይወይኒ ጓደኛውን ያገኛል። ሁለቱም ግን አዲስ አበባን በውል አያውቋትም። ጓደኛው መሄድ የፈለገው ጅማ ወደሚገኘው ወንድሙ ጋር ቢሆንም መዲናዋ ላይ ግን የባለቤቱ እህት እንደምትኖር ያውቃል።
አይደርስ የለ ከሁለት ቀናት ጉዞ በኋላ ወጣቶቹ አዲስ አበባ ገቡ። ቀኑ ደግሞ የፋሲካ በዓል እለት ነበር። በዚህ ወቅት ጓደኛው <<ወደ ጅማ እንሂድ ወንድሜ ጋር>> ቢለው <<አልሄድም>> በማለቱ <<እንደዚያ ከሆነማ እኔም ብቻዬን አልሄድም ብሎ>> ጓደኛውም አብሮት ቀረ። በርሄ የቤተክህነት ትምህርት በመውሰዱ ከጓደኛው በተሻለ የተወሰነ አማርኛ ቋንቋ መናገር ይችላል። እናም የተሰባበረ አማርኛውን ተጠቅሞ ተክለሃይማኖት የተባለውን ሰፈር አቅጣጫ ማጠያየቅ ጀመረ።
በሰዓታት ልዩነት ከአውቶቡስ ተራ ተነስተው የሚፈልጉት ሰፈር ደረሱ። ቀኑ በዓል በመሆኑ ደግሞ በተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ለነዳያን የተዘጋጀውን ምግብ ተቋድሰው ድካማቸውን ማስታገሳቸውን ያስታውሳል። ከዚህ በኋላ በርሄና ጓደኛው መዳረሻቸውን ያደረጉት በአካባቢው የሚገኘው አሰብ ሆቴል በረንዳ ላይ ነው። በዚያ ተቀምጠው የሚያውቁትን የቀያቸውን አካባቢ ሰው ሲያማትሩ አንዴ አንገታቸው ወደላይ አንዴ ወደታች ሲል ዋለ።
ሳይደግስ አይጣላም ነውና ነገሩ በዚያው የፋሲካ እለት ተሳካላቸውና በርሄ ማይወይኒ እያሉ የሚያውቃቸውን አንድ አዛውንት ያገኛል። እናም ቤተሰቡን ነግሮ ሲተዋወቃቸው ለምን እንደመጣ እና እዛ ቢቆይ ግብርናው እንደ ተሻለው ይነግሩታል። አንዴ መጥቻለሁና ሥራ ፈልጉልኝ ብሎ እርሱም ሙጭጭ አለባቸው። ወዲያውም ጓደኛውን የባለቤቱ እህት ጋር አገናኝተው በርሄን መሿለኪያ አካባቢ ወደሚገኝ አንዲት ባለሃብት ቤት ይወስዱታል።
ሥራው ደግሞ የገስት ሃውስ ጥበቃ ነው። እናም የቤቱ ባለቤት የሆኑት እንስት በርሄን በ30 ብር ቀጥረው ማሰራት ጀመሩ። በዚያም የጥበቃ ሥራውን እየከወነ ጊዜ ሲያገኝ ደግሞ ወጣ ገባ እያለ ከተማውን ተላመደ። በዚህ ወቅት ግን አለማየሁ ስለሚባል የአክሱም ሰው ፒያሳ አካባቢ ወርቅ እንደሚሰራ ቀደም ብሎ ሰምቷልና እርሱን ማፈላለጉን ተያያዘው። በእግሩ ከመሿለኪያ እየተነሳ ፒያሳ እየሄደ በተደጋጋሚ ቢፈልገውም ሊያገኘው ግን አልቻለም። አንድ ቀን የአለማየሁን ወንድም እዚያው ፒያሳ ላይ ሲያየው ተደስቶ የአለማየሁን ሱቅ እንዲያሳየው ያደርጋል።
ጠዋት የወጣው በርሄ አስር ሰዓት ድረስ ጠብቆ የወርቅ ቤት ባለቤቱን አለማየሁን ያገኘዋል። ከዚያም ሥራ እንዲፈልግለት እና የማን ልጅ እንደሆነ አስረድቶ ይተዋወቀዋል። የወርቅ ቤቱ ባለቤትም ሥራ እስኪገኝ እየተመላለሰ እንዲጠይቅ እና እስከዚያው በጥበቃ ሥራው ላይ እንዲቆይ ነግሮ ያሰናብተዋል። አራት ወራትን በጥበቃ ሥራው ላይ እንደቆየ ግን ወርቅ ቤቷ ውስጥ ይሰራ የነበረ ባለሙያ ተጣልቶ እንደወጣ እና ለእርሱ የሚሆን ሥራ እንዳለ እየተመላለሰ ሲጠይቅ ተረድቷል።
እናም የገስት ሃውሱን ጥበቃ ሥራ አስረክቦ ፒያሳ ገባ። የወርቅ ቤቱ ሥራ ሲቀጠር ግን ምንም ደመወዝ አልነበረውም። ሙያ ለመልመድ ነበርና በርሄ ፍላጎቱ የመጀመሪያ ቀን ከሥራ በኋላ የሚያድርበት ቦታ ያፈላልግ ጀመር። የነበረችውን ነጭ አንሶላ ይዞ በረንዳ ሊተኛ ሲል አንድ ሰው ያየውና ልብሱን ሌሊት ሊወስዱበት ስለሚችሉ አሜሪካን ግቢ የተባለው አካባቢ በአነስተኛ ክፍያ ማደሪያ ማግኘት እንደሚችል ነግሮ ያሳየዋል።
በዚያች እለትም ከበረንዳ ተነስቶ ከብዙዎች ጋር በቆጥ ላይ በተሰራ መኝታ አንድ ብር ከፍሎ አደረ። በዚህ ሁኔታ ለአንድ ወር ማደሩን ያስታውሳል። አንድ ቀን ወደሥራ ሲገባ ግን የወርቅ ቤቱ ባለቤት ማደሪያ እንደሌለው ጠይቆ በመረዳቱ ወርቅ መሸጫው አጠገብ አንዲት ውሃ የምታስገባ ቤትን ጠራርጎ እንዲተኛ ይፈቅድለታል። በሚቀጥለው ቀን ደግሞ ያደረበት ቤት ቀዝቃዛ በመሆኑ ወርቅ መሸጫ ሱቋ ውስጥ በጊዜ እየገባ እነርሱ ቆልፈውበት እንዲሄዱ ተደረገ። በመሆኑም በርሄ ቀን የሰራባት ሱቅ ውስጥ ሰራተኞች ሲወጡ በጊዜ እራቱን በልቶ እና ሽንት ቤት ተጠቅሞ ውስጥ ተቆልፎበት ያድራል።
እንዲህ እንዲህ እያለ ሙያ እየለመደ ለሶስት ወራት በሱቋ ውስጥ ኖሯል። ከዚህ በኋላ ደግሞ ሱቋ ልትታደስ በመሆኑ በምድር ቤቱ በሚገኝ የወቅር ማንጠሪያ ስፍራ ላይ ከሱቋ ባለቤት ጋር ለስምንት ወራት እንዲያድር ተፈቀደለት። በነዚህ ጊዜያት ግን የብር እና የወርቅ ማዕድናትን የቀለበት እና የአንገት ሃብሎች አሰራር በተቻለው መጠን እየቀሰመ ነበር። ከየት እንደሚመጡ እና ለማን ማቅረብ እንዳለበት በቂ መረጃ ይዟል። አሁን ባለቤቱም በበርሄ ላይ እምነት ስላደረበት በሳምንት 30 ብር ሊከፍለው ስምምነት አደረገ። ለ2 ዓመታት እንደሰራ ደግሞ ደመወዙ በሳምንት 90 ብር ደረሰ።
በወርቅ ቤቷ እያለም ከአሮጌ ተራ አነስተኛ የወርቅና ብር ማቅለጫ እና መቆንጠጫ መሳሪያዎችን እየገዛ ማደራጀቱን ተያይዞታል። አሁን የማይ ወይኒው ወጣት የእራሱን ሥራ መጀመር እንዳለበት ልቡ ይነግረው ጀምሯል። ተክለ ሃይማኖት አካባቢ አነስተኛ ቤት ተከራይቶ የእራሱን የብር ጌጣጌጦች ማምረት ሥራ ጀመረ። ጠገራ ብር እያዘጋጀ እስከ መቀሌ እና አስመራ ድረስ እየሸጠ ጥቂት ገቢ መሰብሰብ ችሏል። በርካታ የብር ጌጣጌጦችን በእጁ አዘጋጅቶ ለብዙ ሰዎች ማጌጫነት አውሏል። ወርቅ እየገዛ እየሰራ ፒያሳ አካባቢ ያስረክባል።
የእራሱን ሥራ በጀመረ ጥቂት ዓመታት ትዳር መስርቶም ቤተሰብ መምራት ጀመረ። ከትዳር መልስ ሩዋንዳ አካባቢ ጉሊት በ100 ብር ተከራይቶ ያዘጋጀውን ብር እየሸጠ 2 ዓመት መስራቱን ያስታውሳል። ከዚያ በኋላም ገርጂ፣ ቦሌ መድኃኒዓለም እና ሾላ አካባቢ ብር ቤቶችን ከፍቶ ሲሰራ ቆይቷል። አሁን የሩዋንዳውን መሸጫ ለወንድሙ ሰጥቶ እየሰራበት ይገኛል። የሾላውን ደግሞ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ እየሰራበት ሲሆን ከሌሎች አስር ካላነሱ የብር አምራቾች ላይ ጌጣጌጦችን እየገዛ ለተጠቃሚው ያቀርብበታል። አሁን በርሄ ኑሮው ደህና ነው። አራት ልጆቹን ጥሩ ትምህርት ቤት እያስተማረ ደስተኛ ቤተሰብ ይመራል።
በሥራው ባገኘው ገቢም አንድ የቤት መኪና ሲገዛ፣ ትልቅ ቪላ ቤት ደግሞ በአዲስ አበባ አያት አካባቢ ገንብቷል። ለበርሄ ከሸክም ሥራ ተነስቶ እዚህ ደረጃ መድረስ ሙያ ለመልመድ እና አላማ ያለው ሕይወት መምራቱን እንደ ቁልፍ መንገድ አድርጎ ይወስደዋል። ማንኛውም የተሻለ ኑሮ ማግኘት የሚፈልግ ሰው ጥረህ ግረህ ብላ የሚለውን የአምላክ ቃል መሰረት አድርጎ ፍላጎቱን መሰረት ያደረገ ዘርፍ ላይ መሰማራት እንዳለበት ይገልጻል። ንግድ ደግሞ የተሻለ ተግባቦት እና ጥራት ያለው ምርት ይፈልጋልና እነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል የሚለው ደግሞ ምክሩ ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ 8/2011
ጌትነት ተስፋማርያም