እንደምን ሰነበታችሁ … ክረምቱም “መጣሁ መጣሁ” እያለ ነው … እናንተስ ክረምቱን እንዴት ለመቀበል ተዘጋጅታችኋል? … መቼም ክረምት ሲመጣ አብረው ከሚነሱ ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው መጻሕፍት/ ንባብ ነው።እናም ክረምቱን በማንበብ እንደምታሳልፉት ባለሙሉ ተስፋ ነኝ።
ወሩ ሰኔ ነውና አንድ ነገር አስታወሰኝ … መቼም ስለ ደቡብ አፍሪካዊው የነፃነት ታጋይና ፕሬዚደንት ኔልሰን ማንዴላ መረጃ አላችሁ ብዬ እገምታለሁ።የደቡብ አፍሪካው የፀረ-አፓርታይድ ትግል መሪ ኔልሰን ማንዴላ እስራት ተፈርዶባቸው ወደ ወህኒ የወረዱት በሰኔ ወር 1956 ዓ.ም ነበር።
“ታዲያ የማንዴላ ታሪክ ምን ይፈይድልናል?” የሚል ሰው አይጠፋም ብዬ አስባለሁ።ሰውየው ለፍትሕና ለእኩልነት ሲሉ የታገሉ የነፃነት ታጋይ መሆናቸው ለብዙ ሰው ትርጉም አለው።ከዚህ በተጨማሪም ማንዴላ “በእኔ ሃሳብ ውስጥ ልዩ ቦታ አላት” ብለው ወዳሞካሿት ኢትዮጵያ በመምጣት ወታደራዊ ስልጠና መውሰዳቸው ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውን ጋር ልዩ ቁርኝት እንዲኖራቸው ምክንያት ሆኗል።እኔም ማንዴላ ወደኢትዮጵያ በመምጣት ስለወሰዱት ስልጠና ከተለያዩ ምንጮች ያገኘኋቸውን ጽሑፎች አሰናድቼ ላካፍላችሁ ወደድኩ።
ጊዜው በ1954፤ ኢትዮጵያዊው ኮሎኔል ፍቃዱ ዋኬኔ ከደቡብ አፍሪካ ለመጣ አንድ ግለሰብ ወታደራዊ ሥልጠና በመስጠት ላይ ናቸው። ድምፅ ሳያሰሙ ወደ ጠላት ቀጣና በመግባት ፈንጂ መቅበር የሥልጠናው አካል ነበር። ሰውየው ‘ኡምኮንቶ ዌ ሲዝዌ’ በመባል የሚታወቀው የደቡብ አፍሪካ ሽምቅ ተዋጊ ቡድን የበላይ አዛዥ ነው።
ቡድኑ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚገኙ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰጪ ጣቢያዎች ላይ የፍንዳታ ጥቃት ፈፀመ፤ ይህን ተከትሎም የጊዜው የአፓርታይድ አገዛዝ አዛዡን ማፈላለግ ጀመረ። ሰውየው ግን ማንም ሳያይና ሳይሰማ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው ኖሯል። ከዚህ አልፎም በአፍሪካ ሃገራት እየተዘዋወሩ ለተዋጊ ቡድኑ እርዳታ ማሰባሰብን ሥራዬ ብለው ተያይዘውት ነበር።
የዚህ ሰው ስም ኔልሰን ሮሊህላህላ ማንዴላ ይባላል።በኢትዮጵያ የተገኙበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ራሳቸውን በወታደራዊ ስብዕና ለማነፅ ነበር። ለማንዴላ ስልጠና እንዲሰጡ የተመደቡትና በወቅቱ ኮልፌ የሚገኘው አድማ በታኝ ባታሊዮን ልዩ ኃይል አባል የነበሩት ኮሎኔል ፍቃዱ ዋኬኔ “ማንዴላ በጣም ጠንካራና ምንም የማይበግራቸው ሰው ነበሩ፤ አመራር ሲከተሉ ደግሞ ለጉድ ነው።
ደስተኛና ለመማር ዝግጁ የሆነ አንድ ደቡብ አፍሪካዊ ሲመጣ አስታውሳለሁ፤ በዚያ ላይ እጅግ ትሁትና ታጋሽ ነበሩ።በትንሽ ነገር ይስቃሉ፤ በሌሎችም ላይ ፈገግታ የሚያጭር ነገር ከማድረግ አይቆጠቡም። በዚያ ላይ ደግሞ እጅግ ተወዳጅ ሰው ናቸው” ብለዋል።
የኮሎኔል ፍቃዱ ድርሻ ለማንዴላ ፈንጂ ማፈንዳት፤ እንዲሁም ድንገተኛ አደጋ መጣል የመሳሰሉ ወታደራዊ ሥልጠናዎች መስጠት ነበር። “አካለ-ጠንካራ ሰው ነበሩ፤ አንዳንድ ጊዜ እንደውም ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር ሲያደርጉ አስተውላለሁ። ይህን ስመለከት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እመክራቸው ነበር፤ አንዳንድ ጊዜም አግዳቸው ነበር” በማለት ስለማንዴላ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ማንዴላን የማሰልጠኑን ግዳጅ ለኮሎኔል ፍቃዱ የሰጡት የኮሎኔሉ አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ታደሰ ብሩ ነበሩ። በ1953 ዓ.ም በነብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ የተመራውንና በንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ላይ የተቃጣውን የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ ካከሸፉ ወታደራዊ መኮንኖች መካከል አንዱ የነበሩት ጀኔራል ታደሰ ብሩ፤ በኋላ ላይ በደርግ እንደተገደሉ ይታወሳል።
ለማንዴላ ስልጠና እንዲሰጡ ትዕዛዙ የደረሳቸው ኮሎኔል ፍቃዱ፣ በስልጠናዎቹ የመጀመሪያ ቀናት ላይ የደቡብ አፍሪካዊው ሰው ጸባይ ብዙም ሊገባቸው አልቻለም ነበር። ኮሎኔሉ ስለጉዳዩ ሲናገሩ፣ «እኔ የማውቀው አንድ ከደቡብ አፍሪካ የመጣ እንግዳ እንዳለና ከእኛ ጋር የተወሰነ ጊዜ እንደሚያሳልፍ ብቻ ነበር ። ሁሉም ነገር ምስጢር ነበር፤ ማንም እንዲያውቀው አልተፈለገም» ብለዋል።
ማንዴላ ወደኢትዮጵያ እንዲገቡ የፈቀዱት አህጉረ አፍሪቃ ከቅኝ አገዛዝ በፍጥነት እንድትላቀቅ ፅኑ ፍላጎት የነበራቸው ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው። በጊዜው ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል የነበራት ሉዓላዊት አገር ነበረች። ጦርነት የተነሳባቸውን የአህጉሪቱን ክፍሎች ለማረጋጋት “ማን እንደ ኢትዮጵያ ኃይል!” የተባለለት ወታደራዊ ኃይል! ንጉሠ ነገሥቱ “ነፃነት ለማምጣት የሚታገሉ የአፍሪካ ወንድሞቻችን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ወታደራዊ ሥልጠና መውሰድ ይችላሉ” ሲሉ በይፋ አውጀው ነበር።
መሣሪያ መታጠቅ፤ ወታደራዊ ሳይንስ እና ጦር መምራት የመሳሰሉት ሥልጠናዎች የማንዴላ መዝገብ ውስጥ ተካትተዋል። ከከተማዋ ወጣ ብለውም የበርካታ ሰዓታት የእግር ጉዞ የመሳሰሉ ፈታኝ ሥልጠናዎችን መውሰድ ተያያዙ።
ማንዴላ “ሎንግ ዎክ ቱ ፍሪደም” (Long Walk to Freedom) ወይም በግርድፍ ትርጉሙ “ወደ ነፃነት የተደረገ ረዥም ጉዞ” ብለው በሰየሙት መፅሐፋቸው ላይ “ረዥም ጉዞ ማድረግ በጣም እወድ ነበር፤ መልክዐ- ምድሩ ግሩም ነበር። ሰዎች ከፍርግርግ እንጨት በተሰራ ቤት ውስጥ ሕይወት ሲመሩ ሳይ፤ ቀለል ያለ ምግብ ቤት ውስጥ በተጠመቀ ቢራ ሲያወራርዱ ስመለከት፤ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የማውቀውን ሕይወት ያስታውሰኛል” ሲሉ ጠቅሰዋል።
ማንዴላ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበራቸው ቆይታና ስልጠና በድብቅ እንዲያዝ የተፈለገ ቢሆንም እሳቸው ግን ዓይን በዛባቸው። አብረዋቸው ሥልጠና ከሚወስዱ ሰዎች መካከል ረዘም እና ገዘፍ ያሉ መሆናቸው ለዓይን አጋለጣቸው።
የክብር ዶክተር ተስፋዬ አበበ (“ፋዘር”) በወቅቱ የኮልፌው ባታሊዮን ሙዚቃ እና ድራማ ክፍል ኃላፊ ነበሩ። “ትዝ ይለኛል፤ ግቢው ውስጥ የነበረውን ሰፊ ሜዳ ሮጠው አይጠግቡም ነበር፤ ይዘላሉ፣ ቁጭ ብድግ ይሰራሉ፤ በዚያ ላይ አንድ ቀን እንኳን ሳይሰሩ አይውሉም” ሲሉ ማንዴላን ያስታውሳሉ።
አንድ ቀን ታዲያ ማንዴላ ከአሠልጣኛቸው ጋር ሆነው ማሰልጠኛው ውስጥ ባለ ምግብ ቤት ውስጥ ሲመገቡ ከክብር ዶክተር ተስፋዬ ጋር ተገናኙ። “በደህንነት ከመጠበቃቸው አንፃር፤ ከእሳቸው ጋር ተገናኝቶ ማውራት የማይታሰብ ነበር” ይላሉ።
የዚያን ቀን ግን አጋጣሚውን ያገኙት “ፋዘር” ከማንዴላ ጋር አወሩ።ስለ አፓርታይድ ነገሯቸው። የክብር ዶክተር ተስፋዬ፤ ማንዴላን “በጣም ሰው መቅረብ የሚወዱና ወሬ የሚያበዙ” ሲሉ ገልፀዋቸዋል።
ከዚያ በኋላ ታድያ የ“ፋዘር” የሙዚቃ እና ድራማ ክፍል በመኮንኖች ክለብ የሙዚቃ ትርዒት በሚያቀርብበት ወቅት ማንዴላ መገኘት ጀመሩ። “ፋዘር” እንደሚሉት፣ ማንዴላ ትርዒቱን በጣም ይዝናኑበት ነበር፤ ለእርሳቸው ሲዜምላቸው ደግሞ ይበልጥ ደስ ይላቸው ነበር፡፡
ማንዴላ በኢትዮጵያ እንዲቆዩ የታሰበው ለስድስት ወራት ቢሆንም፤ ፓርቲያቸው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (African National Congress – ANC) ከሁለት ሳምንታት ቆይታ በኋላ እንዲመለሱ ወሰነ። ታዲያ ማንዴላ ወደሃገራቸው ሲመለሱ ከጀኔራል ታደሰ ብሩ በርካታ የጦር መሣሪያ ሽልማት ተሰጣቸው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2011
አንተነህ ቸሬ