ኳታር ባላንጣዎቹ አሜሪካና ኢራን የገቡበትን ውዝግብ እንዲያረግቡና ለልዩነቶቻቸውም ሰላማዊ የመፍትሄ አማራጮችን እንዲመለከቱ ጥሪ አቅርባለች። የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሸህ መሐመድ ቢን አብዱራህማን አል ታሃኒ ሁለቱ ወገኖች ፊት ለፊት ተገናኝተው እንዲመካከሩና ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።ሚኒስትሩ ለንደን ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ “የአገራቱ ሁኔታ አሁን ባለበት መልኩ መቀጠል የለበትም፤ አንድ ቦታ ላይ እልባት ማግኘት አለበት ብለን እናምናለን። ሁለቱም ወገኖች ለድርድርና ለሰላማዊ መንገድ በሮቻቸውን ክፍት ማድረግ አለባቸው” ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም፤ ኳታርን ጨምሮ ሌሎች አገራት አሜሪካንንና ኢራንን ለማደራደር ጥረት አድርገው እንደነበርም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠቁመው፤ ውጥረቱ ማንንም እንደማይጠቅም ስለሚታወቅ ሁለቱ አገራት በሰላማዊ መንገድ መነጋገር የሚችሉበትን አማራጭ ለማመቻቸት ሙከራ ስለማድረጋቸውም ተናግረዋል።
የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር አሜሪካንን ከ2015ቱ የኢራን የኒውክሌር ስምምነት (Iran Nuclear Deal) ማስወጣቱን ተከትሎ አሜሪካ በኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ጥላለች።ለአብነት ያህል አገራትና ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከኢራን ነዳጅ እንዳይገዙ አስጠንቅቀዋል።ከዚህ በተጨማሪም የኢራንን አብዮታዊ ዘብ (Revolutionary Guard) ከአሸባሪዎች መዝገብ አስፍረውታል።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወትሮም ቢሆን በቋፍ ላይ የነበረውን የሁለቱን አገራት ግንኙነት ከድጡ ወደ ማጡ የሚወስድ ርምጃ ወስደዋል።በዚህም ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ኢራን ወደምትገኝበት ቀጣና ልከው አሰማርተዋል።
በዚህ ርምጃቸውም ሁለቱ አገራት ወደለየለት ጦርነት ሊገቡ ይችላል በማለት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስጋት ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሆኗል። በተለይ ደግሞ “ጦርነት ናፋቂ ናቸው” ተብለው በተደጋጋሚ የሚወቀሱትና ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር መስማማት አቅቷቸው “ከትራምፕ ጋር መስራት ይብቃኝ” ብለው የለቀቁትን ሌተናል ጀኔራል ኸርበርት ሬይሞንድ ማክማስተርን የተኩት ጆን ሮበርት ቦልተን፤ የፕሬዚዳንቱ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ መሆናቸው ሰውየው በኢራን ላይ ካላቸው የማያወላውል አቋም ጋር ተደምሮ አገራቱ ጦር እንዳይማዘዙ ያሰጋል።
ቦልተን ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ለመሆን የምታደርገውን ሙከራ ለማስቆም በማሰብ እስራኤል የኢራንን ወታደራዊ መሳሪያዎች እንድታወድም ሲገፋፉ ኖረዋል።ባለፈው ዓመት በኢራን ከተሞች ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ሲደረጉ “የኢራን ተቃዋሚዎች የውጭ መንግሥታትን ድጋፍ ከፈለጉና ለመቀበል ዝግጁ ከሆኑ አሜሪካ ድጋፍ ማድረግ አለባት” ብለው ነበር።በአጭሩ ቦልተን “ለኢራን የተሻለው አማራጭ ስምምነት ሳይሆን ወታደራዊ እርምጃ ነው” የሚል አቋም አላቸው።
እስላማዊቷን ሪፐብሊክ አጥብቀው በመኮነን የሚታወቁት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ኢራን ጦርነትን ከፈለገች መጥፊያዋን እንደመረጠች ትቁጠረው” የሚል የኢራንን ባለስልጣናት ክፉኛ ያበሳጨ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውም ሌላ ተጨማሪ ስጋት ተደርጎ ተቆጥሯል።“ኢራን የአሜሪካንን ጥቅሞች የምትጋፋ ከሆነ ሙሉ በሙሉ የሚያወድም ቅጣት ይጠብቃታል፤” በማለት የዛቱት ፕሬዚዳንቱ፤ በመካከለኛው ምስራቅ ዋነኛ አጋራቸው ከሆነችውና “ኢራን ዋና ጠላቴ ናት” ከምትለው ከእስራኤል ጋር ተባብረው በኢራን ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ኢራን በአንድ ወገን የባሕረ ሰላጤው አገራትና አሜሪካ ደግሞ በሌላ ወገን ሆነው የገቡበት አዲስ ፖለቲካዊ ፍጥጫ ወትሮውንም ቢሆን ሰላም ለራቀው የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ተጨማሪ ስጋት ሆኗል።ከባሕረ ሰላጤው አገራት መካከል በተለይ ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በየመን እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከኢራን ጋር ያላቸው ልዩነት የከረረ ነው።
ባለፈው ወር በሁለት የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ጣቢያዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ አዲስና የጋለ ውዝግብ ውስጥ የገቡት አገራቱ፤ ጦርነት ቀስቃሽ የሆነ ዛቻ እየተመላለሱ ነው።በነዳጅ ጣቢያዎቹ ላይ የተፈፀሙትን ጥቃቶች ኢራን የምትደግፋቸውና በየመን የእርስ በርስ ጦርነት ከሳዑዲ አረቢያና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር በተቃራኒ ተሰልፈው የሚዋጉት የሐውቲ ታጣቂዎች (Houthi) ፈፅመናቸዋል ብለው ኃላፊነት ቢወስዱም፤ ሳዑዲ አረቢያ ግን በነዳጅ ጣቢያዎቼ ላይ ለተፈፀሙት ጥቃቶች ከኢራን ራስ አልወርድም ብላለች።
ሳዑዲ አረቢያና ኢራን በቀጣናው ተፅዕኖ ለመፍጠር ይፎካከራሉ።ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙ ወዲህ ደግሞ ለወትሮውም ቢሆን በድርበቡ የነበረው የአሜሪካና የኢራን ግንኙነት ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል።ይህ የአገራቱ ውዝግብም በመካከለኛው ምስራቅ ብቻ ሳይወሰን ለመላው ዓለም ሰላም የስጋት ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።ታዲያ በዚህ መሐል ለአሜሪካም ለኢራንም ወዳጅ ናት የምትባለውና ከነሳዑዲ አረቢያ ጋር የከረረ ፍጥጫ ውስጥ ያለችው ኳታር ሁለቱን ወገኖች ለማሸማገል ያደረገችው ጥረት ፍሬ ያፈራላት አይመስልም።
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2011
አንተነህ ቸሬ