ዛሬ፣ ሰኔ 5 ቀን (June 12) “ዓለም አቀፍ የፀረ-ሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ቀን” (World Day Against Child Labor) ነው።የዓለም የሥራ ድርጅት ( International Labor Organization – ILO) በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕፃናት ላይ የሚደርሰው የጉልበት ብዝበዛ ትኩረት እንዲያገኝና ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ የመፍትሄ አማራጮችን ለመፈለግ እ.ኤ.አ በ2002 “ዓለም አቀፍ የፀረ-ሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ቀን” በየዓመቱ ሰኔ 5 ቀን (June 12) እንዲከበር ውሳኔ አሳልፏል።
በዕለቱም በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግሥታት፤ የሲቪክ ማኅበራት፤ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፤ ሰራተኞችና ሌሎች አካላት ዓለም አቀፋዊ ችግር በሆነው የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ጉዳይ ላይ እንዲመክሩና የመፍትሄ ሃሳቦችን እንዲያስቀምጡ ይጠበቃል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን የሚበልጡ ሕዝቦች በግጭቶች ምክንያት ቀውስ ውስጥ በገቡ አገራት ውስጥ ይኖራሉ።በሌላ በኩል ከ200 ሚሊዮን የሚልቀው የዓለም ሕዝብ ደግሞ በየዓመቱ ለልዩ ልዩ አደጋዎች የተጋለጠ ነው። ከዚህ መካከል አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ሕፃናት ናቸው።በዓለም ላይ ለጉልበት ብዝበዛ ተጋልጠው ከሚገኙ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ሕፃናት ውስጥ አብዛኞቹ የሚኖሩት ግጭት ባለባቸውና አደጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ነው።
ከዘላቂ የልማት ግቦች (Sustainable Development Goals – SDGs) መካከል አንዱ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ማስቀረት ላይ ያለመ ነው። ይህ ግብ እ.ኤ.አ በ2025 ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሕፃናትን ለውትድርና መመልመልን ጨምሮ በሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ የጉልበት ብዝበዛ ድርጊቶችን ሙሉ በሙሉ እንዲያስቆም እቅድ አስቀምጧል።
የዘንድሮው “ዓለም አቀፍ የፀረ-ሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ቀን” ከዓለም የሥራ ድርጅት 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ጋር ተያያዞ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።ድርጅቱ ባለፉት 100 ዓመታት የሕጻናት ከጉልበት ብዝበዛ እንዲላቀቁ ያከናወናቸውን ተግባራት እንደሚገመግምም ይጠበቃል።
የዓለም የስራ ድርጅት ከ20 ዓመታት በፊት ያጸደቀውን እጅግ አስከፊ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ኮንቬንሽን (ILO’s Worst Forms of Child Labour Convention) ያልፈረሙት አገራት ጥቂት ቢሆንም ኮንቬንሽኑ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተፈርሞ ዓለም አቀፍ ሕግ ለመሆን ከጫፍ ደርሷል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ኮንቬንሽኑን ያልፈረሙ አገራት እንዲፈርሙ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
የዓለም የሥራ ድርጅት በተለያዩ ጊዜያት
ባፀደቃቸው ደንቦችና ባስተላለፋቸው መልዕክቶች ውስጥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ከመጠየቅ ቦዝኖ አያውቅም።የመጀመሪያው የዓለም የሥራ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አልበርት ቶማስ ሕፃናትን ለጉልበት ብዝበዛ መዳረግ እጅግ ሰይጣናዊ ተግባር እንደሆነና ሁልጊዜም ቢሆን ለማኅበረሰብ የሚደረግ ጥበቃና ከለላ ከህፃናት መጀመር እንዳለበት ተናግረው ነበር።
ይሁን እንጂ፤ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ጉዳይ አሁንም ተገቢውን ትኩረት ያገኘ አይመስልም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአሁኑ ወቅት ከ152 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕፃናት ለጉልበት ብዝበዛ ተዳርገው ይገኛሉ።ምንም እንኳን ሕፃናት በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ቢገኙም ከአስር ሕፃናት መካከል ሰባቱ በግብርና ዘርፍ ላይ የተሰማሩ እንደሆኑም መረጃው ያሳያል።
የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፤ ድህነት የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ዋነኛ ምክንያት ነው። ችግሩን ለመፍታትም የመንግሥት፤ የኅብረተሰቡና የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር እጅግ አስፈላጊ ነው።ከሁሉም በላይ ፖሊሲ አውጪዎች የችግሩን ምንነት፣ መንስዔዎችና መፍትሄዎች የቃኘ የተደራጀ የፖሊሲ ሃሳብ ሊያቀርቡ እንደሚገባና ኅብረተሰቡ ስለጉዳዩ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ ተገቢ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2011
አንተነህ ቸሬ