የሠላም ዋጋ የሚታወቀው ሠላም ሲደፈርስ እና ወጥቶ መግባት ሲከብድ ነው። ሠላም በመገለጫው ካልሆነ በስተቀር የሚሰፈርበት ልኬት የለውም። እውነት ነው፤ ሠላም ልማት፤ ሠላም ዕድገት፤ ሠላም አንድነት ነው። ወልዶ መሳም፤ ወጥቶ መግባት፤ ሠርቶ መለወጥ እና ማደግ፤ ነግዶ ማትረፍ የሚቻለው ሠላም ሲኖር ነው።በአጭሩ ሠላም ለሁሉም ካስማ፤ የመልካም ነገሮች ሁሉ መሠረት ነው።
ኢትዮጵያውያን ለሠላም የሚሰጡት ዋጋም ሆነ ክብር እጅግ ከፍ ያለ ነው። ጠዋት ከቤታቸው ሲወጡ “ሠላም አውለኝ” ሲተኙም “ሠላም አሳድረኝ” በማለት ፈጣሪያቸውን ይማፀናሉ። ኢትዮጵያውያን ሠላም ምን እንዳስገኘላቸው፤ በአንጻሩም የሠላም መዛባት ምን እንዳሳጣቸው ከሌላ ሳይሆን ከራሳቸው ልምድ ጠንቅቀው ያውቁታል። ምክንያቱም በተለያዩ ዘመናት ተከስተው የነበሩ የሠላም መደፍረሶች ሞትን፣ የአካል መጉደልን፣ የንብረት መውደምን፣ ስደትን፣ ረሃብን፣ መታረዝን፣ ሥቃይን፣ ወዘተ በአጠቃላይ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ አስከትሎባቸዋል።
ሕዝብ ለሠላም ቅድሚያ ይሰጣል። ሠላሙን ለማደፍረስ የሚራወጡትን “ሃይ” የሚለው የችግሩ ሰለባ እና ቀጥተኛ ተጠቂ ስለሚሆን ነው። ስለሆነም በሠላም ጉዳይ ላይ አይደራደርም።
በሠላም መታጣት ጎጆ ፈርሷል። ቤተሰብ ተበትኗል። ባለመረጋጋት ሣቢያም ነዋሪው ከየቀዬው ተፈናቅሎ ሜዳ ላይ ወድቋል። በቅርቡም በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬያቸው ሲፈናቀሉ በስፋት ታይቷል። እርግጥ ነው፤ ተፈናቃይ ወገኖቻችንን መልሶ በማቋቋም ወደቀድሞው ሠላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ “ለወገን ደራሽ ወገን ነው” በማለት በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተንቀሳቅሰዋል።
ሠላም የሰው ልጅ በሕይወት ዘመኑ የሚኖረው ታላቅ ፀጋው እና ሀብቱ ነው።የሠላምን ታላቅነት ለመግለጽ ቃላቶች ሁሉ አቅም ያንሳቸዋል። የቤተሰብም ሆነ የግል ሕይወት፣ የእምነት ነፃነት፣ የአገር ብልፅግና እና ልማት፣ ዕድገት፣ ሥልጣኔ ከሠላም ውጭ አይታሰብም።የሠላም እጦት ወይም መደፍረስ ሥርዓት አልበኝነትን ያሰፍናል። በዚህም ሕይወት ይታወካል።በሠላም ወጥቶ በሠላም መመለስ አዳጋች ይሆናል።
የሠላም መኖር ክብር፣ ተደማጭነት፣ ተወዳጅነት እና ተመራጭነትን የሚያመጣውን ያህል አለመኖሩ ወጣቶች ትምህርታቸውን መማር፤ ሠራተኛው መደበኛ ሥራውን መከወን፣ ነጋዴው የቱንም ያህል ሀብት እና ወረት ቢኖረው ለተጠቃሚው ማቅረብም ሆነ መሸጥ አይሞከርም።
ስለዚህ ሠላም ከሌለ ነገን የተሻለ እናደርጋለን፣ ተምረን እንለወጣለን፣ ትልቅ ደረጃ ላይ እንደርሳለን የሚለው ሕልም እና ተስፋ አብሮ ይጨልማል።በሠላም መዘዋወር፣ ተንቀሳቅሶ መሥራት፣ መነገድ፣ መማር እንዲሁም በሕይወት መኖር ከቶ አይታሰብም። እናም ሠላም የሁሉም ዋነኛው የማዕዘን ድንጋይ ነው።ለዚህም ነው የሠላም ዋጋ በዓለማችን እጅጉን ውድ ነው የሚባለው፡፡
የአንድ አገር ሠላም እና መረጋጋት ዋነኛ ባለቤት ሕዝብ ነው።ሠላም እና መረጋጋት ለአገር ብልጽግና እና ዕድገት ያለው ድርሻም ከሁሉም የገዘፈ ነው። እዚህ ላይ ጥቂት ማሣያዎችን እንጠቃቅስ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሠላም እና መረጋጋት የጠፋባቸው አንዳንድ የዓለማችን አገሮች የቱን ያህል ለእልቂት፣ ለከፋ ትርምስ እና ቀውስ እንደተዳረጉ ማየት ይቻላል። በተለይ በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ሁኔታ መዳሰስ በቂ ማሣያ ይሆናል።
በሶሪያ፣ በሊቢያ፣ በየመን፣ በግብጽ፣ በሶማሊያ እና በሱዳን የተከሰቱትን ሁኔታዎች መመልከት ይበቃል። አገሮቹ ለዚህ ሁሉ ቀውስ የተዳረጉት በየአገሮቹ የሚንቀሳቀሱ አክራሪ እና ጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች የግል ጥቅማቸውን ለማግኘት እና ፍላጎታቸውንም በሕዝብ ጫንቃ ላይ ለመጫን ነው።
በተጠቀሱት አገሮች ሰዎች እንደዋዛ ሕይታቸው ይቀጠፋል። ባሉበት ሥፍራ መገኘታቸውን እንጂ የሚቀጥለው ሕይወታቸውን ተስፋ ማድረግ አይችሉም።በማንኛውም ሥፍራ እና ጊዜ ሞት አለና! ሠርቶ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት አይቻልም።
ሀብት ማፍራት ቅዠት ነው። አገሮቹ የተተረማመሱት ለፖለቲካዊ ነጻነቶች በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ነው ቢባልም፤ ፖለቲካዊ መብት እና ነጻነት ትርጉም አጥተዋል። አመለካከትን ማራመድ፣ መደራጀት፣ ሀሳብን መግለጽ፣ ምርጫ፣ የሥልጣን ውክልና፣ መንግሥት፣ የሕግ የበላይነት…ብሎ ነገር የለም።
በዚህ ዘመን ጥንታዊ ሥልጣኔ የነበራቸው በርካታ አገሮች በርስ በርስ ጦርነት ታምሰዋል፤ በመታመስም ላይ ይገኛሉ።በአሰቃቂ ሁኔታ የሰው ልጆች ሕይወት ጠፍቷል። ለዚህም ሶሪያን ዐቢይ ምሣሌ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። የቀደሙ ሥልጣኔዎቿ መገለጫ የነበሩት ታሪካዊ ሥፍራዎች፣ ሐውልቶች፣ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ መሠረተ ልማቶች፣ መኖሪያ ሕንጻዎች እንዳልነበሩ ሆነዋል።ወደ ፍርስራሽነት ተለውጠዋል።
በአንድ የታሪክ ዘመን ገናና የነበሩ አገሮች እና ሕዝቦች በአሳዛኝ ሁኔታ ለመበታተን ሲቃረቡ ተመልክተናል። የውስጥ ጉዳይን በሠላም እና በውይይት መፍታት ተስኗቸው በግትር እና ጽንፈኛ አቋም ተገፋፍተው በገዛ እጃቸው አገሮቻቸውን እንዳልነበሩ ለማድረግ ሲታትሩ አስተውለናል።ያልተቋጨው የሶሪያ ሰቅጣጭ የእለት ተእለት ጦርነት ቀጥሎ መገኘቱ ለዚህ ዐቢይ ምሣሌ ነው፡፡
የመጀመሪያው የተቃዋሚ ፖለቲከኞች አቋም በሽር አልአሣድን ከሥልጣን ማውረድ ነበር። ፖለቲከኞቹ በተከታታይ የጠሯቸው የመንገድ ላይ ምድር አንቀጥቅጥ ሰልፎች ጉድ የሚያሰኙ ነበሩ። በወቅቱ ሊከሰት የሚችለውን ጥፋት አርቆ ማሰብ ቢቻል ኖሮ ተነጋግሮ እና ተደራድሮ አገርን እና ሕዝብን ከጥፋት መታደግ ይቻል ነበር። ዘግናኝ ጥፋት እና ውድመት ባልተከሰተም ነበር፡፡
ተቃዋሚው ኃይል በምዕራባውያን የሎጂስቲክስ እና የጦር መሣሪያ ድጋፍ ይታገዛል። በሽር አልአሣድ ደግሞ በሩሲያ እና በኢራን ይረዳሉ። በዚህ ሁኔታ በየጎራቸው ተቧድነው ሲዋጉ ቆይተዋል። በመጨረሻ ላይ አክራሪውና እና አሸባሪው ቡድን የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅሞ ከሶሪያ እና ከኢራቅ ግዛት ሰፊ መሬት ተቆጣጥሯል። ወታደራዊ አቅሙ እና ብቃቱም እየጎለበተ ሄዷል። ትንቅንቁ እና ጦርነቱም ዛሬ ድረስ ቀጥሏል። ሶሪያም በአጭር ጊዜ ዳግም ለማንሰራራት በማትችልበት ደረጃ ወድማለች።
ሶሪያ መላ ከተሞቿ በአየር ድብደባ እና በከባድ መሣሪያዎች ጥቃት እንዳልነበሩ ሆነዋል። አሁንም ውጊያው ቀጥሏል። በተፈፀሙ እና አሁንም እየተፈፀሙ ባሉ ጥቃቶች የውጭ ኃይሎች በሰፊው ገብተውበታል። ሶሪያ አሁን ሙሉ በሙሉ ለመጥፋት ተቃርባለች።ይህን ሁሉ መዓት እና መቅሰፍት በአገራቸው እና በሕዝባቸው ላይ ያመጡት ዜጎቿ ናቸው።
በውስጥ ጉዳያቸው ላይ መምከር፤ የውጭ ኃይሎችም ጣልቃ እንዳይገቡባቸው በር መዝጋት እና መከላከል ስለተሳናቸው ነው። ነገር ግን በተፈጠረው ችግር ምክንያት ያለቁት፣ የተጎዱት፣ የተሰደዱት፤ አገራቸው የወደመችባቸው እና የጠፋችባቸው፤ ሁሉም ነገር እንዳልነበረ ሆኖ ወደ አቧራነት የተለወጠችባቸው እነሱ እና እነሱ ብቻ ናቸው።በዚህ ሊያዝኑ እና ሊፀፀቱ ይገባቸዋል።
ሌላው ዓለም ደግሞ ከበቂ በላይ ትምህርት ወስዶበታል።አገሩን እና ሠላሙን ከምንም በላይ ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት ተምሯል።ለአገሩ ሠላም እና ደህንነት ሌት ከቀን ፀንቶ መቆም እንደሚገባው ተረድቷል። የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህ ማጣት እና የሙስና ችግሮች በሰከነ ሁኔታ በምክክር ብቻ መፈታት እንዳለበት ተገንዝቧል።
ሠላምን የሚያጎለብቱ፣ ልማትን የሚያፋጥኑ፤ በአንፃሩ ንትርክን የሚያስቀሩ መንገዶችን መከተል አማራጭ የሌለው ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ፤ ሕዝቡ የጀመረውን የፀረ ድህነት ዘመቻ አጠናክሮ ባልቀጠለ ነበር። ከልማቱ በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ተፈላጊውን የዕድገት ራዕይ ሰንቆ ባልተጓዘም ነበር። በዚህ ደረጃ ላይ ሆኖ የተጀመረውን ብልጽግና እና ዕድገት ለማስቀጠል፤ በዚያውም ልክ ልማት እና ዴሞክራሲ አገር በቀል ፍላጎትን መሠረት ባደረገ መልኩ እንዲጎለብት በብርቱ መጣር ይኖርበታል።
ስለዚህ፤ ይህንን ታላቅ አገራዊ የለውጥ ጅምር ጉዞ ለማሰናከል አልፎ አልፎ በተለያዩ ቦታዎች የሚታዩት ግጭቶች መነሻ ምክንያት ምንድን ነው? በአገሪቱ ሠላም እንዳይኖር እየሰሩ ያሉት እነማን ናቸው? የሚሉትን ጉዳዮች ከሥር መሠረታቸው ተጣርተው ዘላቂ መፍትሔ ለማስገኘት በጋራ መረባረብ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። የሠላም እጦት የሕይወት አደጋ አለው። የሠላም እጦት የመሥራት፣ ሀብት የማፍራት እና የሀብት ባለቤት የመሆን መብቶች እንዳይረጋገጡ ያደርጋል። ልማት የሚባለው ጉዳይ ሥፍራ ያጣል። በሕይወት የመኖር መብት ዋስትና እንዲያጣ ምክንያት ይሆናል። ሠላም በሌለበት የሕግ የበላይነት እና ሥርዓት አይኖርም። ይህም የፈቀዱትን አመለካከት የመያዝ፣ የመደራጀት፣ አመለካከትን የማራመድ፣ ሀሳብን የመግለጽ…የተሰኙት ፖለቲካዊ መብቶች እና ዴሞክራሲያዊ ነጻነቶች የሚረጋገጡበትን ሁኔታ ያጠፋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2011
ጋሻው ጫኔ