የመናኸሪያዎቻችን መፀዳጃ ቤቶች

መናኸሪያ ሥራው ያው እንደ ስሙ ነው። ዘር፣ ቀለም፣ ፆታ፣ እድሜ ወዘተ ሳይለይ፤ ሁሉንም እኩል የሚያስተናግድ፤ እጅግ ሥራ የሚበዛበት ተቋም ቢኖር መናኸሪያ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም፣ ሁሉንም እኩል እንዲያስተናግድ በርካታ ጉዳዮች ይሟሉለት ዘንድ ግድ ይለዋል።

ልዩ ልዩ የሰውና የተሽከርካሪ ዓይነቶች በዓይነት በዓይነት የሚገኙበት መናኸሪያ በንግድ ሥፍራነትም ሆነ በምንተፋ ጠለፋነት ተወዳዳሪ የለውም የሚሉ በርካቶች ናቸው። ምንም እንኳን ሥፍራው በፀጥታ ኃይሎች ጥብቅና ቅርብ ክትትል የሚካሄድበት ነው ቢባልም፤ በጥብቅና ቅርብ ክትትል ስር እንዳለ አንድ ተቋም ሰላም የሰፈነበት ላለመሆኑ ምስክሮቹ ደንበኞቹ ናቸው።

ተዘረፍኩ፣ ተነጠቅሁ፣ እቃዬን መጫንም ሆነ ማስጫን፤ ማውረድም ሆነ ማስወረድ አልቻልኩም፣ ተሰደብኩ፣ ተገፈተርኩ ወዘተርፈ ብቻ ሳይሆን “መፀዳጃ ሥፍራ አጣሁ” እና የመሳሰሉት የዘወትር ጩኸት የሆኑበት የሀገራችን መናኸሪያ እንደ ሕዝብ መናኸሪያነቱ አረፍ ይባልበት ዘንድ ካፌ እንኳን የለውም። ምናልባት በአዲስ መልክ እየተገነባ ባለው፣ ከቃሊቲው መናኸሪያ እናይ እንደሆነ እንጂ፤ ከነባሮቹ የዚህን ዓይነት አገልግሎት መጠበቅ ማርን ከንቧ ሳይሆን ንብ ካልሆነችው እንደ መጠበቅ ይቆጠራል።

ይህን ስንል እንደ ደብረዘይቷ መናኸሪያ ዓይነት መዝናኛና መፀዳጃን (ከጀርባ ያለው ሳይሆን መግቢያው አካባቢ በስተቀኝ ያለችው) የያዙና ከውጭ ድርጅቶች ጋር በትብብር የተሰሩ እዚህም እዛም ሊኖሩ ይችላሉ። እንደዚህ ፀሐፊ ልምድ ከሆነ ግን “አሉ” በሚባሉበት ደረጃ ላይ ያሉ አይደሉምና አስተያየታችንን ከመቀጠል የሚያስተጓጉሉ አይሆኑም።

እርግጥ ነው፣ አንዳንድ መናኸሪያዎች ሆን ተብለው ሥርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን ለሥርዓት አልበኞች ሁነኛ ሥፍራዎችን ያመቻቹ እስኪመስሉ ድረስ ሥርዓት አልበኝነት ሲንሰራፋባቸው ይታያሉ። ብዙዎቹ ሰዎች እንዳይከበሩና እንዳይከባበሩ ሆን ተብሎ እየተሰራባቸው ያሉ እስኪመስል ድረስ ተግባራቱ ሲፈፀሙ ይታያሉ። አስተዳዳሪና ባለቤቱ መንገድ ትራንስፖርት ልክ እንደ ሌሎች ሚኒስትሪዎች ሁሉ ለምን በእነዚህ አካባቢዎች ሥርዓትን እንደማያስከብር ግልጽ አደለም።

በግልጽ እንደሚታወቀው መናኸሪያዎች በትራ ንስፖርት ሚኒስቴር ስር ናቸው። አስተዳዳሪያቸው እሱ ነው ማለት ነው። ታዲያ ለምን እንደ አንድ በሚኒስትር እንደሚመራ ግዙፍ ተቋም ዘመናዊነት አይስተዋልበትም፤ አሠራር አይዘረጋለትም፤ መዋቅር አይደራጅለትም በመዋቅር አይመራም? ይህ የሁሉም ጥያቄ ነውና ጊዜ መልስ እስኪሰጠው ድረስ መጠበቅ ግድ ይሆናል።

ይህ ዘመናትን ያስቆጠረው የመናኸሪያዎች አገልግሎትና ኋላቀርነት ከሰላምና ደህንነት፣ ጤና፣ ሥነ ምግባር፤ ዝርፍያና ቀማኛነት እና መሰል ጉዳዮች አኳያ ሲታይ ያለ መሻሻሉ ምክንያት ምን እንደሆነ እዚህ መልስ ለመስጠት ቢያስቸግርም፣ መልሱን የሚመለከታቸው አካላት አሳምረው ያውቁታልና ወደፊት ይነግሩናል፤ አሠራሩንም ያዘምኑታል ተብለው ይጠበቃሉ።

በመሠረቱ፣ ከላይ እንዳልነው፣ መናኸሪያዎች አካታች እንደ መሆናቸው መጠን ለሁሉም እኩል አገልግሎትን ይሰጡ ዘንድ ይጠበቃሉ። ያ ማለት በርካታ አገልግሎት መስጫ ሥፍራዎችንና ሙያዎችን ይዘው መገኘት አለባቸው፤ ሰላምና ፀጥታ፣ ማረፊያ ክበብ፣ ንፁህ ውሃ፣ ሱቆች፤ ከሁሉም በላይ ፅድት ያሉ መፀዳጃ ቤቶች ያስፈልጋሉ ማለት ነው። ይህ ደግሞ የሰዎች መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት እንጂ ችሮታ አይደለም።

መቼም ብዙዎቻችን ከቦታ ቦታ ከመዘዋወራችን አኳያ ከበርካታ መናኸሪያዎቻችን ጋር ትውውቅ ያለን መሆኑ ርግጥ ነው። በዛው ልክ ደግሞ ስለ መናኸሪያዎቻችን ገበና ማየትና ማወቃችን ደግሞ ሌላው ርግጥ የሆነ ምልከታችን ይሆናል።

ለምሳሌ ወደ ደቡብ የሀገራችን ክፍል ሄዶ፣ የአዲሱ ክልል (ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ) አካል በሆነውን የተርጫ ከተማ መናኸሪያ እየሆነ ያለውን የተመለከተ በመናኸሪያዎቻችን ምን ጉድ እየተሠራ እንደሆነ ይመለከታል። ጉዳዩ እንዲህ ነው።

ከተርጫ ከተማ ወደ ሌሎች ከተሞችም ሆነ ሥፍራዎች ለመሄድ የፈለገ ሰው ተርጫ ከተማ መናኸሪያ መድረስ ያለበት ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ነው። በቃ፣ ከዛ ሰዓት ጀምሮ ሰው በሰው ላይ ተደራርቦ ዋናው በርና አካባቢው እስኪጨናነቅ ድረስ ወከባ ይሆናል። የመናኸሪያው በር ልክ 12 ሰዓት ላይ ይከፈታል። የሚገርመው ነገር ቀድሞ የሚገባው 10 ሰዓት ላይ የመጣውና በብርድ ሲለበለብ ያነጋው ሳይሆን ለ12 ሩብ ጉዳይ የመጣው ወጠምሻ ነው።

በቃ፣ ልክ ሲከፈት ሁሉንም ገለባብጦ፣ ገፈታትሮ ከፊት ከች ይላል። ይህ ሁሉ ሲሆን የሚመለከተው አካል ያሰማራቸው “የፀጥታ ኃይሎች” በሥፍራው አሉ። በዚህ ግፍትሪያና ግልበጣ ወቅት የሚፈጠረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያየ ብቻ እንጂ ሌላ ሰው በፍፁም ሊረዳው አይችልምና እንለፈው። መፀዳጃ ቤቶችንም ከእንደ እነዚህ ዓይነት መናኸሪያዎች መጠበቅ የሚታሰብ አይደለምና እሱንም እንዝለለው።

አንድ ነገር ግን ብሎ ማለፍ ይገባል፤ ሁሉም እንደ አመጣጡ ቢሰለፍና በሰልፉ መሠረት እንዲገባ ቢደረግ ይህ ሁሉ፣ የእነዛ አቅመ ደካሞች፣ ሴቶችና ሕፃናት እንግልት ባልነበረም ነበር። ሌሎች መናኸሪያዎችንም በዚሁ ልክና መልክ ማየት ይቻላል። የጎንዮሽ ታሪኮችን ትተን፤ መፀዳጃ ቤቶች ላይ ብቻ አተኩረን ትንሽ እንጨዋወት።

በሀገራችን “የዓለም የመፀዳጃ ቤት ቀን” በየዓመቱ ሲከበር “በተሻሻሉ የመፀዳጃ ቤቶች በመጠቀም ተላላፊ በሽታዎች በህብረተሰቡ ላይ የሚያደርሱትን የጤና ችግር መከላከል እንደሚቻልና ለዚህም በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡” ከሚለው ዜና በስተቀር ስለ መፀዳጃ ቤቶች ሲነገር መስማት ብርቅ ነው። “የተሻሻሉ የመፀዳጃ ቤቶችን በመጠቀም እንደ አተት የመሳሰሉ የወረርሽኝ በሽታዎች የሚያደርሱትን የሞትና የሕመም ስቃይ ለመከላከል” ብዙ መሥራት እንደሚገባም እንደዚሁ።

በየዓመቱ በኅዳር ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለስድስተኛ ጊዜ፤ በሀገር ደረጃ ደግሞ ለሶስተኛ ጊዜ የተከበረውን የዓለም የመፀዳጃ ቤት ቀን በማስመልከት የጤና ሚኒስትር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች “ህብረተሰቡ የተሻሻለ የመፀዳጃ ቤት መገንባትን አስፈላጊነት፣ አያያዝ እና በአግባቡ መጠቀምን እንዲያጎለብት፤ በተጨማሪም በትምህርት ቤቶች፣ በገበያ ሥፍራዎች፣ በአውቶብስ መናኸሪያዎችና በመሳሰሉት የጋራ መፀዳጃ ቤቶችን መገንባትና ጥቅም ላይ ማዋል ያለውን ጠቀሜታ እንዲረዳ ማድረግ የበዓሉ መከበር ዋና ዓላማ” እንደሆነ የገለፁትን እዚህ ጋ እንደ አንድና በቂ ማስረጃ አድርጎ ማቅረብ ይቻላል።

ኃላፊዎቹ “በሀገር አቀፍ ደረጃ ስምንት የሚሆኑ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በጋራ በመቀናጀት በተለይ በከተሞች ያለውን የመፀዳጃ ቤት ችግር ለማቃለል አዲስ የአሠራር ቅንጅት በመንደፍ ወደ ሥራ” ገብተዋል ብለው የነበረ መሆኑንም አንስቶ መሞገት ያስኬዳል። ጥያቄው “በአውቶብስ መናኸሪያዎችና በመሳሰሉት የጋራ መፀዳጃ ቤቶችን መገንባትና ጥቅም ላይ ማዋል” የሚለው ካላከራከረ በስተቀር ማለታችን ነው።

በፈረንጆቹ 2018 ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ሀገር አቀፍ የመሠረታዊ የመፀዳጃ ቤት ሽፋን 72 በመቶ ደርሷል። “በኢትዮጵያ 93 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ መሠረታዊ መፀዳጃ ቤት በቤቱ እንደማያገኝ፤ ከሰሀራ በታች ብቻ 340 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝብ በቂና መሠረታዊ የመፀዳጃ አገልግሎት የሌለው መሆኑን የሚገልጸው፤ የወቅቱ የቢቢሲ ዘገባ ይህንን አይቀበልም) ይህ በእውነቱ ደስ የሚል አፈፃፀም ነው። ግን ደግሞ ምን ያህሎቹ በተገቢው መንገድ ስራ ላይ ውለዋል የሚለው ከታየ አፈፃፀሙን ጥያቄ ውስጥ ይከተዋልና ሊታሰብበት ይገባል።

ለሕዝብ ደህንነትና ጤና፤ ለከተሞች ፅዳትና ተዛማጅ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ ልቦናዊ ጉዳዮች የሚታሰብ ከሆነ “በተለይ ከመኖሪያ ቤት ውጭ በአብዛኛው የሚፀዳዱት የጎዳና ተዳዳሪዎች መሆናቸው አሌ አይባልም፡፡ ስለሆነም የጎዳና ተዳዳሪዎችም ሆኑ የመፀዳጃ አገልግሎት የማያገኙ ወገኖች በሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ሊጠቀሙ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት፤ የምክር አገልግሎትም መስጠት ያስፈልጋል” የሚሉ ጥናታዊ ዘገባዎች ትኩረትን ሊያገኙ የግድ ይሆናል።

በትኩረቱም ቀዳሚ ተተኳሪዎች የመናኸሪያ ዓይነት መፀዳጃ ቤቶች መሆናቸውንም ልብ ማለት ተገቢ ነው። የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ‹‹መንገድ ላይ ሲሸና የተገኘ 200 ብር ቅጣት ይጠብቀዋል›› (ደንብ ቁጥር 150/2015) የሚል መመሪያ ማውጣቱን ተከትሎ “ይሄ መፍትሔ አይሆንም” የሚሉ ሰዎችንም ማዳመጥ ያስፈልጋል። “መንግሥት ተንቀሳቃሽ የሆነ የመፀዳጃ ቤቶችን በየቦታው ማስቀመጥ” አለበት የሚለውም አስተያየት ገራገር ቢመስልም ፍሬ አያጣምና ልብ ሊባል ይገባል።

ቢቢሲ ለንባብ አብቅቶት እንደ ነበረው፣ ጆሴፍ የተባለ የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት (የካቲት 2020) ዜጎች መፀዳጃ ቤት ማግኘት ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸው መሆኑን በመጥቀስ የኬንያ መንግሥት ለዜጎቹ መፀዳጃ ቤቶችን እንዲገነባ ወስኗል፣ ለዚህ ውሳኔ ካበቁት ምክንያቶች መካከል፤

ኬንያ ውስጥ ክፍለ ሀገራትን በመኪና ማቋረጥ ከባድ የሚያደርገው የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ጉዳይ ነው። “የሕዝብ ማመለሻ ውስጥ ሆነው ሽንትዎ ቢመጣስ?” ሲል የሚጠይቀው ይህ ለውሳኔ የሚጋብዝ አስተያየት “ባለሥልጣናት መንገዶችን ሲያስገነቡ ስለ መፀዳጃ ቤቶች ጭራሽ አላሰቡም” ሲል ይወቅሳል። «የሕዝብ ማመለሻ አውቶብስ ሾፌሮች ድንገት ያሻቸው ቦታ ያቆማሉ። ከዚያ ሰው ወዳገኘው ጥሻ ጠጋ ብሎ ተንፈስ ይላል። እንደው ግድ ስለሆነ እንጂ ሴቶችም፣ ወንዶችም ሆኑ ሕፃናት በዚህ መልኩ ሲፀዳዱ ማየት» የተለመደ ነውና ይህ ሊወገድ፣ ችግሩም ሊቃለል ይገባል። የሚሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ።

ተቋሙ ለድምዳሜ ያመቸው ዘንድ ያነጋገራቸው ግለሰቦች “መንገድ በመገንባት እጃቸው ያለበት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መፀዳጃ ቤቶችን አልገነቡም፤ መፀዳጃ ቤቶችን ማግኘት ደግሞ የዜጎች ሕገ-መንግሥታዊ መብት ነው” ማለታቸውንም በመከራከሪያ ነጥቦቹ ላይ አስፍሯል። ተቋሙ “ሰዎች ያለ ፍላጎታቸው ሜዳ ለሜዳና ጥሻ ውስጥ ለመፀዳዳት መቀመጣቸው ሰብዓዊነታቸውን የሚያወርድ ነው። ሰዎች የተፈጥሮ ግዴታቸውን በጊዜው መወጣት ሲገባቸው መንግሥት ቦታ ባለማዘጋጀቱ ምክንያት እየተሰቃዩ ነው”በማለትም ክሱን ያጠናክራል። ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ካዳመጠ በኋላ ብይን የሰጠ ሲሆን፤ መንግሥት መፀዳጃ ቤቶችን በራሱ ወጪ ለዜጎች እንዲያመቻች አዟል። ይህ ለጠቅላላ እውቀት በመሆኑ እዚሁ ላይ እናቆመዋለን።

ማንም እንደሚያውቀው የመፀዳጃ ቤቶች ጉዳይ የቅንጦት ጉዳይ አይደለም። የመፀዳጃ ቤቶች ጉዳይ የምርጫ ጉዳይም አይደለም። የመፀዳጃ ቤቶች ጉዳይ የግዴታ ጉዳይ ነው። የመፀዳጃ ቤቶች ጉዳይ ከተፀዳጂው ቁጥጥር ውጭ የሆነ ጉዳይ ነው። የመፀዳጃ ቤቶች ጉዳይ መሠረታዊ የጤና ጉዳይ ነው። በአጠቃላይ፣ የመፀዳጃ ቤቶች ጉዳይ የሰዎች መሠረታዊ መብቶችና የዜጎችን ጤና የመጠበቅና አለመጠበቅ ጉዳይ ነው። በመሆኑም፣ ይገነቡ፣ በአግባቡም ይያዙ ዘንድ ሁሉም ነገር ያስገድዳል።

እኛ ሀገር ሆነ እንጂ እንደ አደጉት ሀገራት ቢሆን በመፀዳጃ ቤቶች ጉዳይ ብቻ ስንትና ስንት ሰዎችና ተቋማት ለፍርድ በቀረቡ፤ የሥራቸውን ዋጋም ባገኙ ነበር። እኛ ሀገር ሆነ እንጂ፣ መፀዳጃ ቤቶችን የተመለከቱ፤ ራሳቸውን የቻሉና ተገቢነት ያላቸው ስንትና ስንት አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ወጥተው ሥራ ላይ በዋሉ ነበር። ግና ምን ያደርጋል፤ እኛ ሀገር ሆነና ሁሉም እየሆነ ባለመሆኑ በየመንገድና ጥሻው መፀዳዳት ግድ ሆኗል።

የአሜሪካውን “ARA” (የአሜሪካ መፀዳጃ ቤቶች ማህበር – American Restroom Association) የመሳሰሉ መብትና ሕግ አስከባሪ ብሔራዊ ተቋማት ቢኖሩን ኖሮ በመፀዳጃ ቤቶች በኩል እነዚህ ሁሉ ጉድፎችና ድክመቶች ባልኖሩብንም ነበር።

“መናኸሪያዎቻችን መፀዳጃ ቤቶች አሏቸው ወይ?”ተብሎ ካልተጠየቀ በስተቀር በየመናኸሪያው ያሉ (እንደ ነገሩም ቢሆን) መፀዳጃ ቤቶች ድራማዊ በሆነ መልኩ አስቂኝ ናቸው። ባለቤታቸው ማን እንደሆነ እስከማይታወቁ ድረሰ እያደናገሩን ይገኛሉ። ግለሰቦችን በገንዘብ ለመደጎም ይሁን/አይሁን የተቋቋሙት መለየቱ ግር እስኪል ድረስ ያወናብዳሉ።

“ዜጎች ጤንነት የሚባል ነገር አያስፈልጋቸውም” የተባለ እስኪመስል ድረስ የንፅህና ጉድለታቸው ካገር ያስወጣል። ሱስ ልባቸው እስኪጠፋ ድረስ ጭውት ያለባቸው ጥቂቶች እንደ ፈለጋቸው የሚዘውሯቸው የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ሥፍራዎች ናቸው። (በላም በረቱ መናኸሪያ የተመለከትነው ይሄንን እንጂ ሌላ አይደለም።)

በዚህ መናኸሪያ መፀዳጃ ቤቶቹ (የሁለቱም ፆታዎች) በጥሩ ሁኔታ በሕዝብ ሀብት የተገነቡ ናቸው። ሰፋ፣ ለቀቅ ተደርገው የተሠሩ ሲሆን፣ እስከ ውስጥ – መቀመጫዎቹ ድረስ ፈታ ብለው ይቀመጡ ዘንድ ታስቦባቸው ስለ መገንባታቸው እራሳቸው ይናገራሉ። ታዲያ ምን ያደርጋል ∙ ∙ ∙

መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ∙ም ከሰዓት በኋላ ከደብረ ዘይት በመምጣት መውረጃዬን ላም በረቱ መናኸሪያ አደረኩ። የውሃ ሽንት አገልግሎት ማግኘት ፈለግሁና አንዱን ጠየኩት። በእጁ ጣት አመላከተኝ። ሄድኩ። በምስል ጭምር በተደገፈ መልኩ “የወንዶች” እና “የሴቶች” በበር ተለይቶ ተዘጋጅቷል። ቁጭ ብለው ገንዘብ የሚሰበስቡትን ሴትዮ አልፌ ወደ “የወንዶች” ገባሁ። ገንዳው ወረፋ ስለነበረና አብዛኞቹ የመፀዳጃ ክፍሎች ነፃ ቢሆኑም፣ በንፅህና እጥረት ተሰቃይተዋል። ሰው ገብቶ ይፀዳዳ ዘንድ አይደለም ዓይኑን እንኳን ወርወር ያደርግ ዘንድ አይጋብዙም። ግድ ነውና እንደ ምንም ተጠቅሜ ወጣሁ።

ስገባ አልፌ የገባኋቸውን ሴትዮ ስመለስም ማግኘት ግድ ነውና ተገናኘን። ለውሃ ሽንት 5 ብር ይፈልጉ ኖሯልና እጃቸውን ዘረጉ። እኔም ቦርሳዬን ከኋላ ኪሴ እያወጣሁ ሃሳብ መስጠቴን ቀጠልኩ። (እዚህ ላይ “መንግሥታዊ የሆኑት መናኸሪያዎች የሚያስከፍሉ ከሆነ፣ የግል ሆቴሎች ቢያስከፍሉ ምኑ ነው የሚገርመውና ነው አንድ ሰሞን ሲዋከቡ የነበረው?“ የሚል ሃሳብ ማንሳት ተገቢ ይሆናል።)

“ሽንት ቤቱ እኮ በጣም ቆሽሿል፤ ለምን አታፀዱትም?” ከማለቴ ያለ ምንም ዓይነት ደረሰኝ ገንዘብ የሚሰበስቡት እኚህ ሴትዮ የምንተዋወቅና የግል ቂም ያለን ሁሉ እስኪመስል ድረስ ጮሁብኝ። “ኑ ላሳይዎት” አልኳቸው። “በቃ ውጣ፤ እንደውም ያንተን ገንዘብ አልቀበልም” (አልተቀበሉኝም) አሉኝ። ወዲያው ምንም ሳይቆዩ ሱስ እያገላበጠ ልባቸው እስኪጠፋ የተጫወተባቸው የሚመስሉ ሁለት ጎረምሶች መጡና እንድወጣ ሊያስገድዱኝ ሞከሩ።

ከእነሱ ጋር ምንም ሃሳብ ሳልለዋወጥ ገንዘብ ተቀባይዋን ሴትዮ “እሺ ይህንን መናኸሪያ የሚያስተዳድረው ሰው ቢሮው የቱ ጋ ነው?” ስላቸው “ፓርላማ ነው፤ ሂድ ፓርላማ ጠይቅ” አሉኝ (ምናለ “የአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት ኤጀንሲ ሂድ” እንኳን ቢሉኝ፤ ወይም ወደ ከተማው ጤና ቢሮ)። ይሄ ሁሉ ሲሆን ከአንድ ተጠቃሚ ሰው በስተቀር ከጎኔ የቆመ ሰው አልነበረም። ይህ ሰው “ከዚህ ሁሉ ጭቅጭቅ እኮ እናፀዳዋለን ብትሉ ጥሩ ነበር። ማፅዳቱ አይሻልም?” በማለት ነበር ሃሳቤን የተጋራው።

ባጭሩ ገንዘብ መሰብሰቡ ብቻውን ምንም እንደማይፈይድ፤ መፀዳጃ ቤቱ በዚህ ከቀጠለ ከነጭራሹም ሊዘጋ እንደሚችልና የራሳቸውን ገቢ እንደሚያሳጣ፤ ለራሳቸውም ቢሆን የሚበጀው ከሸረሪት ድር ጀምሮ ያለውን ጉድ ማስወገድ መሆኑን ተናግሬ ወደ እምሄድበት ሄድኩኝ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዘመናዊ የመፀዳጃ ቤቶችን (ከመለስተኛ ካፌዎች ጋር) በተለያዩ ቦታዎች በማስቀመጥ ከዚህ በፊት የሠራው ሥራ የሚያስመሰግነው ነው። በእነዚህ መፀዳጃ ቤቶች ገንዘብ የማስከፈሉ ተግባር ያለ ሲሆን ለየት የሚያደርጋቸውና ተቃውሞ የማያስነሳባቸው ገንዘብ ተቀባዮቹ መፀዳጃ ቤቶቹን በሚገባ ማፅዳታቸው ነው። በተለይም ተግባሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘላቂ ልማት ስድስተኛው ግብ፣ ‹‹የውኃና የንፅህና አጠባበቅ አቅርቦትንና ዘላቂነትን ማረጋገጥ ለሁሉም›› ዓላማን ከመያዙ፤ እንዲሁም፣ ቀጣዩ ግብ፣ ‹‹በየቦታው መፀዳዳትን ማቆምና የንፅህና አጠባበቅ ተደራሽነትን ማረጋገጥ›› ማለቱ ሲታወስ ከላይ የተደረጉትን በአድናቆት ማንሳት ተገቢ ይሆናል። እዚህ ላይ አሁን በልማት ምክንያት እየፈረሱ ያሉትን በፍጥነት የመተካቱ ነገርም ሊታሰብበት የሚገባ መሠረታዊ ጉዳይ ነው።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You