በአሠራርና መመሪያ ሊመለስ ሲችል ዓመታትን የዘለቀ የመሬት ውዝግብ

የዛሬው «የፍረዱኝ ዓምድ» ዝግጅታችን በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአንድ አካባቢ የተፈጠረን የቦታ ውዝግብ ያስመለክተናል፡፡ ውዝግቡ የተፈጠረው በቀድሞው የመጠሪያ ስሙ ዞን 03 ወረዳ 17 ቀበሌ 20፣ በአሁኑ መጠሪያው ደግሞ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 በተለምዶ ቦሌ ሚካኤል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ ለጉዳዩ መነሻ የሆነን ደግሞ፡-

«የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማት እና አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም ባለሙያዎች መመሪያ እና አሠራርን ባልተከተለ መንገድ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ያለማሁትን ቦታ በመንጠቅ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ አድርገዋል፡፡ ሕዝብን እንዲያገለግሉ መንግሥት ያስቀመጣቸው ሹመኞች ያደረሱብኝን በደል ተመልክቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደኝ» ሲሉ፤ አቶ ተላይነህ አዱኛ፣ የተባሉ ግለሰብ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ዝግጅት ክፍል ቅሬታቸውን ይዘው መቅረባቸው ነበር። እኛም የግለሰቡን ቅሬታ ይዘን፣ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግረን የደረስንበትን የኢትዮጵያ ሕዝብ ግራና ቀኙን አይቶ መፍረድ ይችል ዘንድ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

አቤቱታ አቅራቢው፣

አቤቱታ አቅራቢው አቶ ተላይነህ አዱኛ ይባላሉ። በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ነዋሪ ናቸው፡፡ ውዝግብ የተነሳበትን ቦታ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ አጥረው ሲያለሙበት መቆየታቸውን ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪም ውዝግብ ከተነሳበት ቦታ ጎን በማህበር በመደራጀት ቦታ ተመርተው ቤት መሥራታቸውን ይናገራሉ፡፡

እንደ አቶ ተላይነህ ገለጻ፤ በቦታው በርካታ የልማት ሥራዎችን አከናውነውበታል፡፡ ዛፎችን ተክለው በማሳደግ እየሸጡ ሲጠቀሙ ኖረዋል፡፡ ዘመናዊ የዶሮ እና በግ እርባታ ሥራዎችን በማከናወንም ኑሯቸውን መደጎም ችለዋል፤ ቤተሰባቸውን አስተዳድረውበታል፡፡

በማህበር ተደራጅተው ቦታ ከመመራታቸው በፊት ውዝግብ የተነሳበትን ቦታ በሰነድ አልባ ሲያለሙት እንደቆዩ የሚናገሩት አቶ ተላይነህ፤ ቀንን ቀን ሲወልደው በማህበር ተደራጅተው ቦታ ካገኙት አጎራባች የሆኑት አቶ ይልቃል ወርቁ የተባሉ ግለሰብ ከተሰጣቸው ቦታ በተጨማሪ ከ400 ካሬ ሜትር በላይ ቦታ አስፋፍተው ያዙ፡፡ አስፋፍተው በያዙት ቦታ ላይ ወንድማቸው አቶ አብርሃም ወርቁ ተጠግቶ መኖር ጀመረ፡፡

በዚህ መልኩ ከወንድሙ ተጠግቶ የሚኖረው አቶ አብርሃም በቦታው ምንም መብት ሳይኖረው በአቶ ተላይነህ ይዞታ ላይ የመንገድ ይከፈትልኝ ጥያቄ ማንሳቱን የተናገሩት አቶ ተላይነህ፤ የመንገድ ይገባኛል ጥያቄ የተነሳበት ቦታ ለበርካታ ዓመታት በሰነድ አልባ ያለሙት እና የአፈር ግብር የገበሩበት ቦታ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡

አቶ አብርሃም አስፋፍቶ ለያዘው ቦታ መውጫ እና መግቢያ በመፈለግ በሀሰት በፈጠረው ክስ፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ እና በወረዳ አንድ መሬት ልማትና አስተዳደር አመራሮች ላይ ያልተገባ ጫና በመፍጠር እና በማስፈራራት ለበርካታ ዓመታት ያለሙትን ቦታ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ማደረጉንም ነው አቶ ተላይነህ የገለጹት፡፡

“የቦሌ ክፍለ ከተማ እና በወረዳ አንድ መሬት ልማትና አስተዳደር አመራሮች እውነታውን በደንብ ያውቁታል፡፡ ነገር ግን አቶ አብርሃም ባደረሰባቸው ጫና እውነትን እና መመሪያን ደፍጥጠው በሰነድ አልባ መካተት የሚችልን መሬት ወደ መሬት ባንክ ማስገባታቸው ከመንግሥት መመሪያ እና አሠራር የሚጣረስ ነው፤” በማለትም ነው ስለ ጉዳዩ በምሬት ያስረዱት፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ምላሽ፣

አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ ይባላሉ፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የመብትና የይዞታዎች ዘርፍ አገልግሎት አስተባባሪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚገልጹት፤ አቶ ተላይነህ ሰነድ አልባ መሬት እንዳላቸው እና ወረዳ አንድን በሰነድ አልባ መብት እንዲፈጠርላቸው ጠይቀው ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ የወረዳ አንድ አስተዳደር የፋይል ማደራጃ ክፍል የአቶ ተላይነህን ጥያቄ ተቀብሎ ፋይል አደራጅቶ ወደ ክፍለ ከተማው የመብትና የይዞታዎች ዘርፍ አገልግሎት ልኳል፡፡ የክፍለ ከተማው የመብትና የይዞታዎች ዘርፍ አገልግሎትም የ1988 ዓ.ም የአየር ካርታ የሚታይ ስለሆነ በመመሪያ ቁጥር 17 መሠረት ባለሙያ መሬቱን ለክቶ እና ጉዳዩን አጣርቶ ይስተናገዱ ተብሎ ፈቅዶ ተስተናግደዋል።

በመመሪያ ቁጥር 17 የሚስተናገዱት ደግሞ፣ በ1988 ዓ.ም አየር ክልል ውስጥ የገባውን ይዞታ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የአቶ ተላይነህ የፈለጉት በ1997 ዓ.ም ‹‹ላይን ማፕ›› የሚታየውን ይዞታ ጭምር ከ1988ቱ አየር ካርታ ጋር አብሮ እንዲሰራላቸው ነው፡፡ ሆኖም በአንድ ጊዜ በሁለት መመሪያ መስተናገድ አይቻልም፡፡

ይሄ አይቻልም ተብሎ ዝም እንዳልተባሉ የገለጹት አቶ አሸናፊ፤ ጥያቄያቸውን ለመመለስ ሲባል መጀመሪያ በመመሪያ ቁጥር 17 መብት ይፈጠርላቸው እና ከዚያ በኋላ የተረፈውን ይዞታ ደግሞ በመመሪያ ቁጥር 18 ይካተትላችኋል የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ተናግረዋል፡፡ በዚህም ለመኖሪያና ለድርጅት የሚውል ከ500 ካሬ ሜትር በላይ ቦታ እንደተሰጣቸው አስረድተዋል፡፡ የተረፈውን እና በ1997 ዓ.ም አየር ካርታ የሚታየውን ደግሞ በመመሪያው መሠረት በይካተትልኝ ለመስተናገድ የይዞታ ማስተካከል የሚባል ቡድን አገልግሎት እንዲጠይቁ እንደተነገራቸውም ነው የጠቆሙት፡፡

እንደ አቶ አሸናፊ ገለጻ፣ አንድ ሰው በካርታ ያልተካተተ ትርፍ ይዞታ አለኝ፣ በካርታ ይካተትልኝ ብሎ ሲጠይቅ፣ የይካተተልኝ አገልግሎት መመሪያ ስለሚፈቅድለት ያመለክታል፡፡ ነገር ግን የመሬት ልማት እና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ቅድሚያ የሚያየው ቦታው የመንግሥት ነው ወይስ አይደለም? መሬት ባንክ ገብቷል ወይስ አልገባም? የመንግሥት ፍላጎት አለበት ወይስ የለበትም? የሚሉትን እና መሰል ጥያቄዎችን ነው፡፡

በመሆኑም ቦታው የመንግሥት አይደለም፤ መሬት ባንክ አልገባም፤ የመንግሥት ፍላጎት የለበትም እና መስል ማረጋገጫዎች ሲሰጡ፣ መመሪያው በሚፈቅደው ልክ ለሰዎች መብት ይፈጠራል፡፡ ከዚህ አኳያ በመሬት ዝግጅት እና ዘርፍ ውስጥ የመሬት ባንክ መጠበቅ የሚባል ቡድን አለ፡፡

አቶ ተላይነህ የያዙትን ቦታ ለዚህ ቡድን ‹‹በኮርድኔት›› አካትተው መላካቸውን የሚናገሩት አቶ አሸናፊ፤ ሰነዶችን አደራጅተው የላኩትም በይካተትልኝ የተጠየቀው ቦታ ክርክር አለበት የለበትም? የመንግሥት ይዞታ ነው አይደለም? የሚለውን ለማወቅ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ በመጨረሻም የመሬት ባንክ መጠበቅ የሚባለው ቡድን ቦታው መሬት ባንክ ገብቷል የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ፡፡

ይህን ተከትሎ ክፍለ ከተማው የመብትና የይዞታዎች ዘርፍ አገልግሎት ቦታውን ማካተት አንችልም የሚል ምላሽ መስጠቱን ይገልጻሉ፡፡ በዚህም አቶ ተላይነህ እንዴት የእኔ ቦታ ባንክ ይገባል? የሚል ቅሬታ ይዘው ወደ ክፍለ ከተማው የመብትና የይዞታዎች ዘርፍ አገልግሎት መሄዳቸውን፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም አቶ ተላይነህ ለወረዳ አንድ አስተዳደር ሰነድ አልባ ይዞታ እንዳላቸው እና በመመሪያው መሠረት በሰነድ አልባ መብት ይፈጠርልኝ ብለው መጠየቃቸውን፤ በወረዳው ሰነድ አልባ ቦታዎችን የሚመለከተው ኮሚቴም ከ1988 ዓ.ም የአየር ካርታ የሚታይ ሰነድ አልባ ይዞታ አላቸው ብሎ ሰነድ አደራጅቶ፣ በቃለ ጉባኤም ተይዞ፣ የወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚም ደግፈውት መረጃቸው ወደ ክፍለ ከተማ መላኩን ነው ያብራሩት፡፡

በተላከው መረጃ መሠረትም ክፍለ ከተማው የመብትና የይዞታዎች ዘርፍ አገልግሎት እንዳስተናገዳቸው፤ ነገር ግን የምዝገባ ተቋሙ ሰነድ በሚጠይቅበት ወቅት በአቶ ተላይነህ ስም ሁለት ማህደር መገኘቱን፤ ይሄን ተከትሎም እንዴት ሁለት ማህደር ይኖራል? ተብሎ ምልከታ መደረጉን፤ በዚህ ምክንያት ፋይላቸው እንዲያዝ ማዘዛቸውን ይናገራሉ። ምክንያቱም የተሠራው ካርታ ወደ ምዝገባ ተቋም ተልኮ ዲጂታል ከሆነ አቶ ተላይነህ ሊሸጡና ሊለውጡ የሚችሉበት ዕድል መኖሩን ይናገራሉ።

አስተባባሪው እንዳብራሩልን፤ ካርታው መታገዱን ተከትሎ አቶ ተላይነህ ለክፍለ ከተማው መሬት ልማት ኃላፊ ለሆኑት ኢንጂነር ቸርነት ቅሬታ አቀረቡ፡፡ የክፍለ ከተማው መሬት ልማት ኃላፊም የደረሳቸውን አቤቱታ መነሻ በማድረግ ስለጉዳዩ ለማጣራት የመሬት ባንክ ባለሙያዎችን በመያዝ የክፍለ ከተማው የመብትና የይዞታዎች ዘርፍ አገልግሎት ኃላፊን ጠየቁ፡፡ የተጠየቁት ኃላፊም በሰነድ አልባ የተስተናገዱበት አግባብም ትክክል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቦታውን ያገኙት በሰነድ አልባ ሳይሆን በማህበር ነው የሚል ምላሽ ሰጡ፡፡

እንደ አቶ አሸናፊ ገለጻ፣ በማህበር ለተደራጁ ሰዎች መንግሥት የሚሰጠው መሬት በማህበሩ አባላት ልክ ሸንሽኖ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አቶ ተላይነህ በሽንሻኖ የሚደርሳቸው 175 ካሬ ሜትር ነው፡፡ ከማህበሩ ዳር ቦታ ላይ ያለ ሰው ደግሞ ትርፍ ቦታ ሊይዝ፤ ትርፍ የያዘ ሰውም በመመሪያው መሠረት ይካተትልኝ መጠየቅ ይችላል። ጥያቄውን ተከትሎም በቦታው ክርክር እስከሌለበት ድረስና መመሪያው እስከፈቀደ ድረስ ቦታው በሊዝ ይሰጣቸዋል፡፡ አቶ ተላይነህ ያሳሰባቸው ግን፣ ቦታው መሬት ባንክ እንዴት ይገባል? የሚለው ነው፡፡ ሆኖም ስካን ሲደረግ ወደ መሬት ባንክ የገባው መሬት ችግር የለውም፡፡

“የማህበሩ ቦታ እንዳለ ሆኖ፣ ከዛ ውጭ ያለውን ቦታ በይዞታ መልክ ከ1988 ዓ.ም በፊት ጀምሮ አቶ ተላይነህ እንደያዙት እና በቦታው የመሬት ግብር ይከፈሉበት እንደነበር የሚያሳይ ሰነድ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ቡድን በምርመራ አግኝቷል፡፡ በዚህ ላይ ምን ትላላችሁ?” ተብለው የተጠየቁት አቶ አሸናፊ፤ “እኔ እያልኩ ያለሁት ከሽንሻኖ በኋላ የተረፈውን መሬት የመንግሥት ክርክር እና መንግሥት ፍላጎት እስከሌለበት ድረስ ማካተት እንደሚችሉ መመሪያው ይፈቅድላቸዋል፡፡ ሆኖም መንግሥት መብት የፈጠረላቸውና እውቅና የሰጠው ለማህበር ስለሆነ መጀመሪያ የ175ቱን ካሬ ሜትር ቦታ መነሻ በማድረግ መብቱ ሊፈጠርላቸው ይገባል፡፡ ስለዚህ 175ቱን ይወስዱና ከዚህ ውጭ የይዞታ መሬት አለኝ በማለት ይካተትልኝ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ይህን ተከትሎ የፕላን ተቃርኖና የመንግሥት ፍላጎት እስከሌለበት ድረስ ይካተትላቸዋል ነው፡፡” በማለት አስረድተዋል፡፡

አቶ አሸናፊ አያይዘው እንዳስረዱትም፤ የይካተትልኝ ጥያቄ የሚቀርበው በመጀመሪያ ካርታ ከያዙ በኋላ ነው። ቀጥሎም በ175ቱ ላይ ሕጋዊ ካርታ እስከያዙ ድረስ ይካተትልኝ ጥያቄ ካቀረቡ ቦታው የማይካተትበት ሁኔታ የለም፡፡ ምክንያቱም መመሪያው ያዛል፡፡ ነገር ግን አቶ ተላይነህ ይህን ስንላቸው ፍላጎት የላቸውም፡፡ ምክንያቱም ያላግባብ ይዞታ ያስፋፉ በሚል የሚቀጡት ገንዘብ ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ በማህበር ተደራጅተው በያዙት ካርታ መሠረት የይካተትልኝ ጥያቄ ካመጡ በመመሪያው መሠረት የሚከለክላቸው ነገር የለም፡፡

ወደ መሬት ባንክ የገባበትን አካሄድ በተመለከተ ግን፣ ‹‹እኔ የመብት ፈጠራ ጋር በተያያዘ ያሉ ጉዳዮችን ብቻ ስለምሰራ ቅሬታ የተነሳበት መሬት ግን መቼ እና እንዴት እና መቼ ወደ መሬት ባንክ እንደገባ የማውቀው ጉዳይ የለም›› የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡

ዝግጅት ክፍላችን ባደረገው ማጣራት ደግሞ፣ ከሊዝ ጋር በተያያዘ አቶ ተላይነህ ሁለት ካርታ አላቸው። አንደኛው ‹‹እነ›› በሚል ሊዝ የከፈሉበት እና ‹‹በእነ›› የተሠራ 724 ካሬ ሜትር የሚለካ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ‹‹በእነ›› የሊዝ ክፍያ ተከፍሎበት በአቶ ተላይነህ ስም የተዘጋጀ 671 ካሬ የሚለካ ነው፡፡ እናም ይህ ለምን ሊሆን ቻለ? ተብለው የተጠየቁት አቶ አሸናፊ በምላሻቸው፤ አቶ ዳዊት ገብረማሪያም የተባሉ የቴክኒክ ባለሙያ የሠሩትን እና አቶ ተላይነህ ሊዝ የተዋዋሉበትን ሰነድ እንደ ሰነድ ቆጥረው የትም ሊወስዱት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሥራው የተቋረጠበት ምክንያት አዲስ በተሠራው መዋቅር የቴክኒክ ባለሙያው ዳዊት ገብረማሪያም ከመሥሪያ ቤቱ ወጣ፡፡ ቀደም ብሎ አንድን ሥራን የጀመሩ ባለሙያዎች ወጥተው አዳዲስ ባለሙያዎች በመጡ ጊዜ ቀደም ብሎ የነበረው ባለሙያ አዲሱን አይፈርምም፡፡ ለዚህም ያለው መፍትሔ ቀደም ብሎ የነበረው ባለሙያ የፈረመበትን ካርታ ማስወገድ (ቮይድ ማድረግ) ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የአቶ ተላይነህም ጉዳይ እንደገና ለአዲስ ባለሙያዎች ተመራ፡፡ በአዲስ ጉዳዩን የያዙት ባለሙያዎች ሲያጣሩም የካሬ ቁጥር ጨምሮ ተገኝቷል፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው ካርታ ተወግዷል፡፡ አሁን ላይ ያለው ሁለተኛው ካርታ ትክክለኛ ካርታ ነው፡፡ ሕጋዊ ሰነድ ነው፡፡ ስለዚህ መነጋገር የምንችለው ሕጋዊ በሆነ ሰነድ ነው፡፡ ያኛው ግን ጸድቆ ያልወጣ ካርታ ስለሆነ እንደ ሰነድ አይታይም፤ ብለዋል፡፡

አያይዘውም፣ መጀመሪያው የሊዝ ካርታ የተሠራው 1997 እና 1988 የአየር ካርታዎች አንድ ላይ ቀላቅሎ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ቦታ ሕጋዊ ለማድረግ ሁለት መመሪያዎችን ቀላቅሎ መጠቀም አይቻልም፡፡ በመመሪያ ቁጥር 17 ተስተናግደው የተረፈውን በመመሪያ ቁጥር 18 መሠረት ይካተትልኝ ብለው ጥያቄ አቅርበው ተግባብተን ነበር፡፡ ምክንያቱም የከፈሉበት ደረሰኝ ስላለ ይካተትልኝ ጥያቄው ሲስተናገድ ወደ ክፍያ ይዞራል፡፡ ስለዚህ በመመሪያ ቁጥር 18 መሠረት ሊያካትቱ ሲመጡ ማረጋገጫ ያስፈልጋል፡፡ ትልቁ ስህተት የሆነው መመሪያ ቁጥር 17 እና 18 መቀላቀሉ ነው፡፡

ይሁን እንጂ በክፍያ ላይ ከአቶ ተላይነህ ጋር መግባባት ላይ ደርሰው የነበረ ቢሆንም፣ በይካተትልኝ ለማስተናገድ በእንቅስቃሴ ላይ እያሉ መሃል ላይ መስተጓጎል እንደገጠማቸው የሚያስረዱት አቶ አሸናፊ፤ አሁንም ግን መሬት ባንክ ገባ ማለት የፈጣሪ ቃል ሆኖ የማይለወጥ አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ስለሆነም በሊዝ ወስደው ማልማት የሚችሉበት አግባብ ካለ ከመውሰድ የሚከለክላቸው አካል እንደማይኖር ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት ደግሞ በቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ዝግጅትና ማስተላለፍ ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አስራት መኮንን ናቸው፡፡ እንደ አቶ አስራት ገለጻ፤ ውዝግብ የተነሳበት ቦታ መሬት ባንክ ገባ ማለት ሙሉ በሙሉ የአቶ ተላይነህ አይደለም ማለት አይደለም፡፡ በቅሬታ ሰሚ ታይቶ ወደ እኛ ሲመጣ ጉዳዩ ታይቶ መሬቱ የመንግሥትን ጥቅም የሚያሳጣ ከሆነ፣ እና በትክክል መሬቱ የአቶ ተላይነህ ለመሆኑ ማስረጃ ካለ ወደ መሬት ባንክ ይገባና መረጃቸው ከታየ በኋላ ከመሬት ባንክ ወጥቶ ለአቶ ተላይነህ የሚሰጥበት አግባብ አለ፡፡ ስለዚህ ቅሬታ መምጣቱ ምንም ችግር የለውም፡፡ ይሁን እንጂ መጀመሪያ ቦታው መሬት ባንክ ከገባበት ከወረዳ ጋር በመሆን ወደ መሬት ባንክ የገባበት ሂደት ማጣራት ይጠይቃል፡፡ በሚደረገው ማጣራትም ቦታው በ1988 እና በ1997 የአየር ካርታ ላይ የሚታይ ከሆነ እና ህጋዊ መረጃዎች የተሟሉ ከሆነ በፕሮሰስ ካውንስል ታይቶ ላይሰጣቸው የሚችልበት አግባብ አይኖርም፡፡

የሰነድ ማስረጃዎች፣

ሰነድ አንድ፡- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዞን 03 ወረዳ 17 ቀበሌ 20 ፋይናንስ ጽሕፈት ቤት የቦታ ኪራይ እና የቤት ግብር ሂሳብ ማስታወቂያ ቅጽ 1991፣ በቀን 25/3/1993 ዓ.ም ከአቶ ተላይነህ አዱኛ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት እንዳመላከተው፤ አሁን ላይ ውዝግብ የተነሳበት ቦታ አቶ ተላይነህ የመኖሪያ ቤት ሰርተውበት እንደነበር፤ ቦታው ለአቶ ተላይነህ የተሰጠበት ቀን እንደማይታወቅ፤ የቦታው ጠቅላላ ስፋት 1019 ካሬ ሜትር እንደሆነ ፤ የቦታ ደረጃ ጋር በተያያዘ በቀድሞ ደረጃ አንድ በአዲሱ ደግሞ 22 ስለመሆኑ፤ የቤቱ የግንባታ ዘመን የማይታወቅ የተገመተ ዓመታዊ ኪራይ ተመን መጠን አንድ ሺ 974 እንዲከፍል የተወሰነ እና ከዚህም ዓመታዊ የቦታ ኪራይ 122 ነጥብ09 ብር ዓመታዊ የቤት ግብር ደግሞ 19 ነጥብ 74 ብር እንዲከፍሉ መወሰኑን የሚገልጽ ነው፡፡

ሌላው በዚህ ሰነድ የተመላከተው ደግሞ፣ 1981-1992 ዓ.ም ለቦታ እና የቤት የኪራይ ውዝፍ ክፍያ የተመለከተ ነው፡፡ በዚህም ለቦታ የኪራይ ውዝፍ ክፍያ 733 ነጥብ 91 ብር፤ 1992 ዓ.ም ለቦታ እና የቤት የኪራይ ውዝፍ ክፍያ ደግሞ 51 ነጥብ 30 ብር፤ በድምሩ 785 ነጥብ 21 ብር የከፈሉበት ሰነድ ነው፡፡

ሰነድ ሁለት፡- በዚህ የሰነድ ማስረጃ ማሳያ ስር ሁለት ሰነዶች ተካትተዋል፡፡ አንደኛው በ1993 ዓ.ም አቶ ተላይነህ አዱኛ ውዝግብ በተነሳበት ቦታ (በወቅቱ የቤት ቁጥር 2494) ተክለውበት የነበረን ዛፍ ለመሸጥ ለከፍተኛ 17 ቀበሌ 20 ያመለከቱበት፤ እና ማመልከቻቸውን ተከትሎ በቀን 27/03/1993 ዓ.ም በቁጥር 07/9/83/93 ፈቃድ ማግኘታቸውን እና በፈቃዱ መሠረት የደን ውጤት መጠቀሚያ ክፍያ 209 ነጥብ 58 ብር ለዞን 3 ግብርና መምሪያ በሞዴል 30 ቁጥር 32 የከፈሉበት ነው። ሁለተኛው ሰነድ ደግሞ ‹‹ኢትሐርሶ›› ለተባለ መገኛ አድራሻው ከፍተኛ 23 ቀበሌ 14 የቤት ቁጥር 1089 ለሆነ ድርጅት ውዝግብ ከተነሳበት ቦታ ላይ የነበሯቸውን ዛፎች ለመሸጥ የተዋዋሉበት ነው፡፡

ሰነድ ሶስት፡- ይህ ሰነድ በመሬት ልማትና ማኔጅመንት በ2001 ዓ.ም የተዘጋጀ ‹‹የስኬል ሪፖርት›› ነው፡፡ በዚህ ሪፖርት መሠረት ጂ.ኤይ.ስ ልኬቱ 760 ካሬ ሜትር መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ሰነድ አራት፡– አቶ አብርሃም ወርቁ የተባሉ ግለሰብ አሁን ላይ ውዝግብ በተነሳበት ቦታ ላይ መንገድ አለ ብለው ወረዳውን በተለያዩ ጊዜያት ሲያስተዳድሩ ለነበሩ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ አቶ ተላይነህ አዱኛን “ያለአግባብ የመንግሥትን ቦታ በወረራ ይዘዋል” በሚል ክስ ያቀረቡበት እና ሥራ አስፈጻሚዎች ምላሽ የሰጡበትን የያዘ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሁለት የወረዳው ሥራ አስፈጻሚዎች አቶ ተላይነህ የተባሉት ግለሰብ ምንም መሬት በወረራ እንዳልያዙ አመላክተዋል፡፡

ለምሳሌ፣ በአንድ ወቅት የወረዳ አንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩ ግለሰብ፣ በ17/03/2013 ዓ.ም አቶ ተላይነህ የመንግሥትን መሬት በወረራ ስለመያዛቸው እና ስላለመያዘቸው የወረዳው መሬት ማኔጅመንት እንዲሁም የግንባታ ፈቃድ ጽሕፈት ቤቶችን እንዲያጣሩ አዝዘው ነበር፡፡ የወረዳው መሬት ማኔጅመንት እና የግንባታ ፈቃድ ጽሕፈት ቤትም ጉዳዩን አጣርተው ለዋና ሥራ አስፈጻሚው ደብዳቤ ጻፉ፡፡ የተጻፉላቸውን ደብዳቤ መነሻ በማድረግም፣ አቶ አብርሃም የተባሉ ግለሰብ አቶ ተላይነህ በያዙት ቦታ ላይ መንገድ አለ ሲሉ የከሰሱት ትክክል ያልሆነ እና ስለመንገዱ የሚያመላክት ምንም ዓይነት ማስረጃ እንደሌለ፤ ተከሳሽ አቶ ተላይነህ አዱኛ በይዞታ የያዙት ቦታ ካርታ እንደሌለው ነገር ግን ቦታውን ለረጅም ጊዜ ሲያለሙት ነበር የሚል ሰነድ ነው፡፡

በተመሳሳይ፣ ወይዘሮ ዘቢባ ይመር የተባሉ የወረዳው አስተዳዳሪ፣ ከአቶ አብርሃም የቀረበላቸውን አቤቱታ ለመፍታት ባደረጉት ጥረት በቦታው መንገድ አለ የተባለው በአየር ካርታ መሠረት ምንም ዓይነት መንገድ የሌለ መሆኑን እና አቶ ተላይነህ አስፋፍቶ ይዞታል የተባለው ቦታ የመንግሥት ቦታ ሲሆን፤ በዚህ ቦታ ላይ ተከሳሹ ግለሰብ ችግኝ ተክለውበታል፡፡ ይህም የመሬት ወረራ ሊያስብል የሚያስችል እንዳልሆነ እና ግለሰቡ በአሁኑ ሰዓት የሰነድ አልባ ቤት ስለሆነ ያላቸው መስተንግዶውን ሲያገኙ ችግር የሚኖር ከሆነ ወደፊት የሚፈታ መሆኑን ያመላከቱበት ሰነድ ነው፡፡

ሰነድ አምስት፡- አቶ ተላይነህ አዱኛ ለመኖሪያ ከተፈቀደላቸው ቦታ በተጨማሪ የያዙትን ቦታ በሊዝ ለማካተት በእነ አቶ ተላይነህ የሚል የሊዝ ክፍያ በ27/10/2014 ዓ.ም 244ሺህ 422 ነጥብ 40 ብር የከፈሉበት፤ ይህን ተከትሎም ሁለት የተለያዩ ካርታዎች የተሠሩበት ነው፡፡ አንደኛው ካርታ በእነ አቶ ተላይነህ ስም 724 ካሬ ሜትር የሚለካ የነበረ ሲሆን፤ ምክንያቱ ባለተገለጠ አግብብ ካርታው ሳይጸድቅ መሻሩን እና ሁለተኛው ካርታ ደግሞ በሊዝ የተከፈለው በእነ አቶ ተላይነህ ሆኖ ሳለ በአቶ ተላይነህ ብቻ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ይህም 671 ካሬ ሜትር ይለካል፡፡

ሰነድ ስድስት፡– ይህ ሰነድ የእነ አቶ ተላይነህ አዱኛ ጎረቤት አቶ ይልቃል ወርቁ ወንድም አቶ አብርሃም ወርቁ የተባሉ ግለሰብ ከወንድማቸው ውክልና በመውሰድ አቶ ተላይነህን የመንግሥት ቦታ በወረራ ይዘዋል በሚል ለቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የሕዝብ ቅሬታ አቤቱታ ማስተናገጃ ጽሕፈት ቤት በተደጋገሚ አቤቱታ ያቀረቡበት ነው፡፡ ይህን ተከትሎ የክፍለ ከተማው አቤቱታ ሰሚ የክፍለ ከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት ኃላፊዎች ባላረጋገጡበት ሁኔታ እና ምክንያቱ በውል በማይታወቅ አግባብ አቶ ተላይነህ አዱኛ የመንግሥትን መሬት በወረራ ይዘዋል የሚል ውሳኔ ወሰነ፡፡ ይህን ውሳኔ ተከትሎ ቅሬታ ሰሚው በተደጋጋሚ ለክፍለ ከተማው እና ለወረዳ አንድ መሬት ልማትና አስተዳደር በሕገ ወጥ መንገድ የተያዘን መሬት አስለቅቁ ሲል በተደጋጋሚ ደብዳቤ ጻፈ፡፡ በዚህም የቦሌ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ ጫና ውስጥ በመግባቱ እና አቶ ተላይነህ ይዘውት የነበረውን መሬት ወደ መሬት ባንክ ማስገባቱን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡

የዘጋቢዎቹ እይታ

የክፍለ ከተማው ቅሬታ ሰሚ ያለ ምንም አሳማኝ ምክንያት በክፍለ ከተማው እና በወረዳው መሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ያልተገባ ጫና በማድረስ አቶ ተላይነህ አዱኛ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ በሰነድ አልባ የያዙትን ቦታ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ አድርጓል፡፡ እዚህ ላይ በምርመራ ቡድኑ ጋዜጠኞች ከተገኙ ግኝቶች መካከል ቅሬታ ሰሚው ውሳኔ ብሎ ውሳኔ የሰጠው በቅሬታ መመዝገቢያ ቅጽ 003 ነው፡፡

ነገር ግን ውሳኔ መስጠት እና የክፍለ ከተማውን መሬት ልማት እና አስተዳደር ማስገደድ የነበረበት በቅጽ 004 በተሞላ የውሳኔ ሃሳብ ነበር፡፡ ይህም የሆነው ቅሬታ ሰሚው በቅጽ 004 ውሳኔ ቢያቀርብ አቶ ተላይነህ በፍርድ ቤት ይጠይቁናል በሚል ፍራቻ መሆኑን ስማቸው እንዳይገለጽ ከጠየቁን በክፍለ ከተማው ቅሬታ ሰሚ ጽሕፈት ቤት የሚሰሩ አንድ ግለሰብ በድምጽ በተደገፈ ማስረጃ ነግረውናል፡፡

ሌላው በምርመራ ግኝቱ ማረጋገጥ የተቻለው ደግሞ፣ አቶ ተላይነህ በሰነድ አልባ የያዙት መሬት ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን፤ ነገር ግን በ1988 የአየር ካርታ የያዙት የመሬት ልክ 760 ፣ በ1997 የላይን ማፕ የተመላከተው ደግሞ 950 ካሬ ሜትር በላይ ነው፡፡ በ2003 ዓ.ም የአየር ካርታ ደግሞ ከ1200 ካሬ ሜትር በላይ ይታያል፡፡

ሙሉቀን ታደገ እና ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You