ሰዎች እድሜአቸው እየገፋ ሲሄድ ከሚከውኑት የእለት ተእለት ድርጊት እየራቁ ይሄዳሉ። አንዳንዶች ግን ፍቅር እስከ መቃብር በማለት በሚችሉት አቅም ሲሰሩ የኖሩትን ለመስራት ሲታትሩ ይስተዋላሉ።
እድሜ ቁጥር እንጂ የፈለጉትን ከማድረግ እንደማያግድ የፓላንዳዊቷ የ108 አመት የእድሜ ባለጸጋ ታሪክ ያስገነዝባል። ኦዲቱ ሴንትራል ከቀናት በፊት ያስነበበው ዘገባ እንዳመለከተው እኚህ ዋንዳ ዛርዚይካ የተባሉ የእድሜ ባለጸጋ ከምንም በላይ ፒያኖ መጫወት ይወዳሉ። ፒያኖ ሳይጫወቱ መዋል አይሆንላቸውም።
ስራቸውና ህይወታቸው ፒያኖ መጫወት ከሆነ መጫወታቸው ምን ያስደንቃል ሊባል ይችል ይሆናል። ከፒያኖ መጫወት ሊያፋቱ የሚችሉ የተለያዩ ፈተናዎች ገጥመዋቸውም እሳቸው ግን ፍቅራቸው ጨመረ እንጂ ሊቀንስ አልቻለም።
የ80 አመት ባልቴት በነበሩበት ወቅት እጃቸው ላይ ስብራት ቢገጥማቸውም እድሜው የገፋ ሰው ስብራት አይጠገንም ብለው አርፈው አልተቀመጡም፤ ሀኪሞች ከፒያኖ ጨዋታው እንዲታቀቡ ምክር ቢሰጧቸውም አልተገበሩትም፤ ፒያኖ መጫወታቸውን ቀጥለውበታል።
የዩሮ ኒወስን ዘገባ ዋቢ አርጎ ኤንዲቲቪ በድረ ገጹ እንዳስነበበው፤ ሚስ ዛርዚይካ በፒያኖ መጫወት ፍቅር ውስጥ የወደቁት በልጃገረድነታቸው በዩክሬን በስተምእራብ በምትገኘዋ ሊቪይቭ በሚኖሩበት ወቅት ነው። እኤአ በ1931 ከሊቪይቭ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ቢመረቁም በሁለተኛው የአለም ጦርነት ሳቢያ ፒያኖ መጫወትን ለማቋረጥ ተገደው ነበር። ይህም ቢሆን ፒያኖ መጫወታቸውን ተገዳደረባቸው እንጂ ጨርሶ አላስቆማቸውም።
እኤአ በ1944 ከአምስት አመት ቆይታ በኋላ ቤተሰባቸው ወደ ፓላንዷ ከተማ ክራኮው ሲመለስ ዛርዚይካ ፒያኖዋቸውን ያገኙታል። ከእናታቸው በስጦታ የተበረከተላቸው ይህ ፒያኖ ለዛርዘይካ ትልቁ ሀብት ነው። በፒያኖ በመጫወት ያላቸው ፍቅርም ከፓላንድ የእድሜ ባለጸጎችና ተዋቂ ዜጎች መካከል እንዲውሉ አርጓቸዋል።
አንድ የሀገሪቱ የቀድሞ የውዝዋዜ መምህር ለዛርዚይካ ጤነኛ መሆናቸው ለሙዚቃና ለፈጣሪያቸው ሙሉ ፍቅር እንዲያድርባቸው አድርጓል ሲሉ ይገልጻሉ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2011
ዘካርያስ