መንግሥታት /ገዥዎች/የፓለቲካ ለውጥ እንዲያደርጉ አልያም ስልጣን እንዲለቁ ለማድረግ በህዝብ ወይም በተቃዋሚዎች ዘንድ ጫና መፍጠሪያ ከሚባሉት መንገዶች አንዱ የረሃብ አድማ ነው። በዚህም እስር ቤት ውስጥ ያሉ የፓለቲካ ሰዎችን ጨምሮ የተለያዩ ወገኖች የረሃብ አድማ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ።
ሰሞኑን ከወደ ህንድ የወጣ የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ደግሞ የኮበለለን የፍቅረኛ ልብ ለመመለስ የረሃብ አድማ ያደረገ አንድ አስገራሚ ግለሰብ ታሪክን አስነብቧል። እንደ ዘገባው ከሆነ፤ የህንድ ምእራብ ቤንጋል ግዛት ነዋሪው አናንታ ቡረማን ሊፒካ ከተሰኘችው ፍቅረኛው ጋር ለስድስት ዓመታት ያህል ጊዜ ጣፋጭ ጊዜን ያሳልፋል።
ልጅት ግን ሳይታሰብ ቀስ በቀስ ገለል እያረገችው፤ ሁሉንም አይነት ግንኙነቷን ታቋርጣለች፤ ሲደውልላትም መልስ ትነፍገዋለች፤ ለሚልክላት አጭር የጽሁፍ መልእክትም ምላሽ ትነፍገዋለች፤ በየትኛውም የማህበራዊ ድረ ገጽ በኩል እንዳያገኛትም መንገዶችን ትዘጋበታለች።
ይህን ጊዜም አናንታ አንዳች ችግር እንደተፈጠረ ማሰብ ይጀምራል፤ ለምን ይህ ሊሆን እንደቻለም ማጣራት አለብኝ ሲል ይወስናል። በመጨረሻም የሊፒካ ቤተሰቦች ለሌላ ሰው ሊድሯት ማሰባቸውን ይደርስበታል። እስከወዲያኛው ሊያጣት ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ሲረዳም የመጨረሻ ያለውን እርምጃ ለመውሰድ ይወስናል።
በዚህም የቀድሞ ጓደኛውን መልሶ ለማግኘት ይረዳኛል ያለውን የረሃብ አድማ ለማድረግ መወሰኑን ያመላከተው ዘገባው፤ ይህም ብዙዎችን ስለማነጋገሩ አትቷል። በቀድሞ ጓደኛው ቤት በር አፍ ላይ ለቀናት መዋያ ማደሪያውን በማድረግ ምግብ ለምኔ ያለው ግለሰቡ፤ እንደምታገባኝ ቃሏን እስካልሰጠችኝ እህልም ሆነ ውሃ ወደ አፌ አይዞርም ይላል።
ከዚህ በተጓዳኝ፤ ‹‹ያለፉትን ስምንት ዓመቶቼን መልሽልኝ ››የሚል ጽሁፍ ጭምር ከፍ አርጎ መስቀሉ የበርካታ ተመልካቾቹን ትኩረት ይበልጥ እንዲስብ ያደረገው ሲሆን፤ ይህን ያስተዋሉ በሃዘንና በማፅናናት ተባብረውታል።
ይህ ግን የተመልካቹን እንጂ የልጅቷን ቤተሰቦችም ልብ ማራራት አልሆነለትም። ፍቅርህ ጥልቅ ስለመሆኑ ተረድተናልና ለልጃችንን ሰጥተንሃል ከማለት ይልቅ ለፖሊስ አሳልፈው ሊሰጡት ይወስናሉ።
በሊፒካ ፍቅር ክፉኛ የተለከፈው ግለሰብ ግን አሻፈረኝ በሎ በረሃብ አድማው የቀጠለ ሲሆን፤ ጊዜው እየጨመረ ሲመጣም ጤንነቱ ተጓድሎ ሆስፒታል እስከ መግባት ይደርሳል። እንዲያም ሆኖ ግን ፊቱን ወደ ምግብና መጠጥ ለመመለስ ፈቃዳኛ ሊሆን አልቻለም።
በዚህ ሁኔታ የግለሰቡ ህይወት እያደር አደጋ ላይ መውደቁ ያሳሰበው አላፊ አግዳሚዎች የልጅቷን ቤተሰቦች ቀርበው በማግባባት ከሌላ ሰው ጋር የታቀደው የጋብቻ ፕሮግራም እንዲሰረዝ ማድረግ መቻላቸውን ያመላከተው ዘገባው፤ በመጨረሻም አናንታ እና ሊፒካ በትዳር እንዲጣመሩ ተወስኗል ሲል አስነብቧል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2011
ዘካርያስ