ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት «ብትመርጡኝ እፈፅማቸዋለሁ» ያሏቸውን ተግባራት ስልጣኑን እንደተረከቡ ለመፈጸም ጊዜ አልፈጀባቸውም። ከፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት አገራቸውን ከመነጠል አንስቶ፤ በአገራቸው የንግድ ልውውጥ በተለይ ከቻይና በሚገቡ ሸቀጦች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ በመወሰን ቃል አባይ አለመሆናቸው አሳይተዋል።
ይሁንና ቃል ከገቧቸው ዋነኛ ተግባራት መካከል ስደተኞችን በመከላከል ረገድ አገራቸው ከሜክሲኮ ጋር የምትዋሰንበትን ድንበር በኮንክሪት ለመገንባት የነበራቸው ውጥን ግን ባቀለሉት ልክ አልቀለላቸውም። ህገ ወጥ ስደተኞችን በመግታት ከደህንነት ስጋት ያላቅቀናል ያሉትን እጥር ለመገንባት የፈለጉትን ገንዘብ ማግኘት አልሆነላቸውም።
ፕሬዚዳንቱ ዓላማቸውን ለማሳካት ያቀረቡት የገንዘብ ጥያቄ የኮንግረሱን ይሁንታ በቀላሉ ማግኘት ቢቸገርም፤ እሳቸው ግን የግንቡን ህልውና ለማረጋጋጥ ያደርሳሉ በሚሏቸው መንገዶች ሁሉ ሳይታክቱ በመመላለስና ተስፋ ሳይቆርጡ በመታገል በመጨረሻ ሙሉ በሙሉም ባይሆን በአመዛኙ የፍላጎታቸውን ማሳካት ችለዋል። አሁን የአሜሪካና ሜክሲኮን ድንበር የሚለያየውን የኮንክሪት አጥር መገንባት ጀምረዋል።
የትራምፕ አስተዳደር በዚህ ብቻ ሳይወሰን በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ሜክሲኮን አቋርጠው ወደ አሜሪካ በመግባት ላይ ስለመሆናቸው ከመካከላቸውም ወንጀለኞች ሊኖሩ እንደሚችሉ ደጋግሞ በማሳሰብ ስደተኞቹን ለመከላካል ከ5 ሺ 800 ያህል ድንበር ጠባቂዎችን አሰማርቷል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕም አገራቸው ህገ ወጥ ስደተኞችን ለመከላከል ሌት ተቀን እየደከመች ብትሆንም፤ ድካሟ የብቻ አንደመሆኑ የሚፈለገውን ለውጥ አላመጣችም፤ የስደተኞቹ መናህሪያ የሆነችው ሜክሲኮ ስደተኞቹን በመከላከል ረገድ በቂ ጥረት እያደረገች አይደለም» ሲሉ በተደጋጋሚ ነቅፈዋታል።
የፕሬዚዳንቱን ማሳሰቢያ ያደመጠችው ሜክሲኮም፤ባሳለፍነው ህዳር ወር ከመካከለኛው አሜሪካና ካሪቢያን አካባቢ የመጡ የአሜሪካ ድንበር በህገ ወጥ መንገድ አቋርጠው ለማለፍ የሞከሩ ናቸው ያለቻቸውን ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ወስና ታይታለች።
ይህም ቢሆን አሜሪካ ከሜክሲኮ በምትዋሰነው ደቡባዊ ክፍል ያለውን ህገ ወጥ ስደት ለመግታት ቀላል አልሆነም። ባሳለፍነው ወር ላይ ይፋ የሆነው መረጃ እንዳመላከተውም፤ 144ሺ ስደተኞች የአሜሪካን ድንበር በህገ ወጥ መንገድ አቋርጠው ለማለፍ ሲሞክሩ በፅጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ስደተኞች በቁጥጥር ስር ሲውሉም፤ በ13 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛው ሆኖ መመዝገቡ ተጠቁሟል።
ወትሮም በስደተኞች ላይ አይናቸው የሚቀላው ትራምፕም መሰል የቁጥር ማሻቀብን በመረጃነት በማስደገፍ የድንበሩን አካባቢ የሚመለከት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል። ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ ወደ አገራቸው በሚገቡ የሜክሲኮ ምርቶች ላይ የ5 በመቶ ቀረጥ አውጀዋል። ይህም ከሰኔ ወር መጀመሪያ አንስቶ ተግባራዊ እንደሚሆን በሂደትም ጭማሪ እንደሚደረግበት ይፋ አድርገዋል።
ይህ የዋሽንግተን ውሳኔ ቤጂንግ ላይ እንዳረገችው የፍትሃዊ ንግድ አጋርነት ጥያቄ አሊያም የበላይነት ለማስጠበቅና ለመንጠቅ የሚደረግ ግብግብና የባላንጣነት ሽኩቻ ሳይሆን፤ ሜክሲኮ ከድህነት፣ ግጭትና ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ከሆንዱራስ፣ ጓቲማላና ኤልሳልቫዶር ተነስተው ወደ አሜሪካ ድንበር የሚፈልሱ ስደተኞችን የመቆጣጠር ጥረቷን እንድታጠናክር ጫና ማሳደርን ታሳቢ ያደረገ መሆኑም ተመላክቷል።
የትራምፕን ውሳኔ የሰሙ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ምሁራን በአንፃሩ አሜሪካም የሜክሲኮ ምርቶች ዋነኛ ተገልጋይና ጥገኛ መሆኗን በመጥቀስ፣ መሰል ውሳኔ ወትሮም እያማረበት ለማይገኘው ኢኮኖሚ ተጨማሪ ራስ ምታት ሊያስከትል የሚችል ስለመሆኑ ለማስጠንቀቅ ጊዜ አላባከኑም።
አንዳንድ ሪፐብሊካን የህግ አርቃቂዎች ሳይቀሩ የተጨማሪ ቀረጡ ተፈፃሚነት ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ በሚገቡ የመኪና እና የምግብ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት ሊያስከትል እንደሚችል በመጠቆም ውሳኔው በድጋሚ ሊጤን እንደሚገባው እፅንኦት ሰጥተው ሲወተውቱ ተደምጠዋል።
ከፎክስ ኒውስ ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ ያደረጉት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአንፃሩ የሪፐብሊካኑ አባላት ውሳኔአቸውን ለመደገፍ አለመፈለጋቸው አሳፋሪ ተግባር መሆኑን በመጥቀስ፣ ማንም ይቃወማቸው ማን እርሳቸው ግን በውሳኔቸው ፀንተው እንደሚቆዩም አረጋግጠዋል።
ገና በመጀመሪያ ዓመት የስልጣን ቆይታቸው የአገራቸውን ኢኮኖሚ የሚያንገዳግድ ጫና መጋፋጥ ግድ የሆነባቸው የሜክሲኮ ፕሬዚዳንት ሎፔዝ ኦብራዶርም፤ቀደም ሲል ለትራምፕ እንደማያጎበድዱ ቢገልጹም፣ አሁን ግን ጉዳዩን በሰከነ መንገድ ማስኬድን ምርጫቸው አድርገዋል።
የአገራቸው የኢኮኖሚ ምህዋር ዋነኛ መሰረቱን በአሜሪካ ገበያ ላይ ያደረገ እንደመሆኑ መጪውን በመስጋት ከዋሽንግተን ጋር ያፋጠጣቸውን አብይ ጉዳይ ይበልጥ ለማጦዝ በሚል በአሜሪካ ምርቶች ላይ ተመሳሳይ የአፀፋ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ውሳኔ ለማሳለፍ አልፈጠኑም።
ይልቁኑስ ከፍተኛ ተደራዳሪ ልዑኮቻቸውን ወደ ዋሽንግተን ልከዋል፡፡ ቡድኑም በጉዳዩ ላይ በጤረጴዛ ዙሪያ ውይይት ካደረገ በኋላ በቀላሉም ባይሆን «የዋሽንግተን ስጋት ይገባናል» የሚል መልስ ይዞ ወደ አገሩ ተመልሷል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ «በድንበር በኩል ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞቹን በመከላከል ረገድ በቂ ጥረት እያደረገች አይደለም» ሲሉ የሚነቅፏት ሜክሲኮ፣ የአቋም ለውጥ በማድረግ ለትብብር እጇን ለመዘርጋት መወሰኗም በርካታ ወገኖችን አስገርሟል።
በአገራቱ መካካል በተካሄደው ውይይት የተገኘውን ውጤት ተከትሎ በሜክሲኮ አርገው የአሜሪካን ድንበር የሚሻገሩ ስደተኞችን የመቆጣጠር ጥረቴን አጠናክራለሁ ማለቷን ቢቢሲ አስንብቧል። ይህን ተከትሎም ትራምፕ የተጨማሪ ቀረጥ ውሳኔው እንዲነሳ አዘዋል።
ሜክሲኮ ስደተኞቹ በህገ ወጥ መንገድ የአሜሪካን ድንበር ጥሰው እንዳይገቡ በጓቲማላ በኩል በሚያዋስናት ድንበር ላይ 6 ሺህ ያህል አዲስ ድንበር ጠባቂዎችን የማሰማራትና በህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ከትትል ለማድረግ ወስናለችም ተብሏል። ከዚህ በተጓዳኝ ወደ አሜሪካ ጥገኝነት የሚጠይቁ ስደተኞች ጉዳያቸው እስኪጠናቀቅ በሜክሲኮ እንዲቆዩ የሚለውም የስምምነቱ አካል መሆኑ ታውቋል።
ምንም እንኳን ሁለቱ አገራት በጉዳዩ ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ መክረው ከዚህ መሰል መስማማት ላይ ቢደርሱም፤ ውይይቱ ግን በቀጣይ ሶስት ወራት ውስጥም ቀጣይነት እንደሚኖረውና አጠቃላይ ከመስማማት የተደረሱባቸው ውሳኔዎችም በይፋ እንደሚገለፁ ተመላክቷል።
የሜክሲኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርሴሎ አብራርዶም ስምምነቱ ለሁለቱ አገራት ተጠቃሚነት ፋይዳ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ በዋሽንግተንም በኩል ተመሳሳይ ሃሳብ ተላልፏል። ይሁንና አንዳንዶች በስምምነቱ ከሜክሲኮ ይልቅ አሜሪካ ጫና ፈጣሪ ሰለመሆኗና የፈለገችውን ስለማግኘቷ መረሳት የለበትም ሲሉ ተደምጠዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በዚህ መልክ ህገ ወጥ ስደተኞችን የመቆጣጠሩን ተግባር ከተናጠል ወደ አጋርነት ማሸጋገር በመቻላቸው በተለይ የሚፈልጉትን ለማግኘት የሄዱበት መንገድ የበርካቶችን አድናቆት አግኝቷል። የዚህ ሃሳብ አራማጆች ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው የገቡትን ቃል ለማስፈፀም በተለይ በንግድና በህገወጥ ስደተኞች ላይ የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎችና የሚወስዱት ጠንካራ አቋም በ2020 በሚካሄደው ምርጫ ዳግም እንዲያሸንፉ የማድረግ እቅሙ ግዙፍ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የፕሬዚዳንቱን እርምጃዎች አንዳንዶች አደገኛ ቁማር እየተጫወቱ ሰለመሆኑ ቢያስጠነቅቁም፣ የፕሬዚዳንቱ ውሳኔና ፈጣኑ ስኬት ግን በርካቶችን ማነጋገሩን ቀጥሏል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2011
ታምራት ተስፋዬ