“ያልገሩትን ፈረስ”

“ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም” ነበር ተረቱ…። ፈረስ ግን መዋጋት ጀምሯል፤ ፈረሱ ግን የፈረንጅ እንጂ የኛ አይደለም። ዛሬ ሁላችንም አንባቢያን ከእነዚህ ያልተገሩ ፈረሶች ላይ ለመቀመጥ እንገደዳለን። በየሰበብ አስባቡ እየደነበሩ ስንቱን ጀግና ፈረሰኛ ደመ ከልብ አድርገውታልና ጥንቃቄውም ይሻል። ቅሉ ያለመታደል ይሁን መታደል ሆኖ ለጊዜው የኛ ፈረስ የሚጋልበው ከሰማይ ላይ ሳይሆን ከምናብ ላይ ነውና ጥንቃቄውን ለሌሎቹ እንስጥ። እናም የእነዚህ ያልተገሩ ፈረሶች ጉዳይ ከሰሞኑ ከመጽሐፍት ዓለም ብቅ ብሏል።

“ያልገሩትን ፈረስ” የተሰኘ መጽሀፍ፤ ባሳለፍነው ቅዳሜ የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በዓለም ሲኒማ ተመርቆ ለንባብ በቅቷል። መጽሀፉን በዘመን ጥበብ ሙዳይ ውስጥ ያኖረችው ደራሲ ደግሞ ፋሲካ ሙሉ ናት። ይህ መጽሀፍ ለደራሲዋ የበኩር ሥራዋ ቢሆንም ብዙ የበኩር ታሪክና ክስተቶችን ይዞ የመጣ ትልቅ መጽሀፍ ነው።

በ395 ገጾች የተሰናሰነው የመጽሀፉን ታሪክና ዘውግ በግለ ታሪክ ሊመደብ የሚችል ይሁን እንጂ ታሪኩ ግን የመላው ኢትዮጵያዊ ታሪክ ነው። የሁሉም ታሪክ ነው ስንል፤ “ያልገሩት ፈረስ”ን ምንነት ማወቁ አስፈላጊ ነው። “ያልገሩትን ፈረስ” የኢትዮጵያ የዘመን ክስተቶች ነው። ይህም በየጊዜው፤ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ጥቁር ደመና እየዘረጉ፤ በድንገቴ የሞት ጎርፍ ምድሪቱን ያጨቀዩትን የቦይንግ አውሮፕላኖችን ለማመልከት ነው።

የአውሮፕላኖቹ በድንገት የመከስከስ መንስኤ ብዙዎች እንደሚሉትና የዛሬው መጽሀፋችን እንደሚነግረንም፤ ቀድሞውኑ በአምራች ድርጅቱ ያልተገሩ በመሆናቸው ነው። ታዲያ እነርሱ ያልገሩትን እኛ ተቀብለን ምን እናድርገው?

“ያልገሩትን ፈረስ” የመጀመሪያው ነገር፤ የዚህ መጽሀፍ ደራሲ ፋሲካ ሙሉ፤ ባልገሩት ፈረስ ምክንያት አለኝታና መከታዋን የተነጠቀች፤ ወጌሻ ለሌለው የልብ ስብራት ከተዳረጉት መሃከል አንዷ ናት። የሷ ታሪክ፤ በአንድ ሰሞን ሁላችንም ያለቀስንበትና ልባችን የተሰበረበት ታሪክ ነው። የሷ ግለ ታሪክ፤ የመላው ዓለም ገሀድ ነው። ጉዳዩ አምስት ዓመታትን ወደኋላ ያስጉዘናል። ከኢትዮጵያ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ናይሮቢ ለመሄድ ተነስቶ፤ ገና በስድስተኛው ደቂቃ ከአዲስ አበባ ብዙም ሳይርቅ፤ በአቼ የገበሬ መንደር ውስጥ ቁልቁል ሲምዘገዘግ ወርዶ ከመሬት የተላተመው አውሮፕላን የማይረሳ ነው። 157 ሰዎችን ይዞ ሁሉንም በሞት ቀጥፏቸዋል። ከእነዚህም መሀከል ለሀገራችን ብዙ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ዋና አብራሪው ካፒቴን ታምራት ሙሉ፤ የደራሲዋ ታናሽ ወንድምና የመጽሀፉ ዋናው ባለታሪክ ነው። የመጽሀፉ ሀቲት በብዛት የሚያጠነጥነው ስለ ካፒቴን ታምራት ሕይወትና ስለዚህ አደጋ ይሁን እንጂ፤ አብረውት ስለነበሩት ቀሪዎቹ አምስት ሰዎችን ጨምሮ፤ ግራና ቀኝ እያለ የማያነሳቸው ባለታሪኮችና የታሪክ ክስተቶች የሉም፡፡

በተለያዩ ጊዜያት፤ ባልገሩት ፈረስ ሳቢያ ሕይወታቸውን የተነጠቁ አብዛኛዎቹ በዚህ መጽሀፍ ተካተዋል። በሰጋሩ የሞት ፈረስ ላይመለስ የሄደን ከአፈር በላይ በድንጋይ ከበን የመታሰቢያ ሀውልት ብንሰራለት ከወዳጅ ዘመዱና ከተመልካቹ እይታ ያለፈ ለሟች የሚሰጠው አንዳችም ፋይዳ የለውም። ይህ እውነት ነው። የሞተ ሰው በጥበብ ሲታወስና የሌላኛውም እንባ ብዕር ሲያብስ፤ ያኔ ሟች አይሞትም። ነብሲያው ከአጸደ ገነት ማማ ላይ ሆና የደስታን ጩኸት ትጮሃለች። በሥራው ሕያው እንደሆነም ትውልድን አልፎ በትውልድ ይኖራል። በዚህም ካፒቴኑ ታምራትና መሰል የዚህ መጽሀፍ ባለታሪኮች ምንኛ ታድለዋል ያስብለናል።

“ያልገሩትን ፈረስ” ለታምራትና በአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸውን ለተነጠቁት በሙሉ በጥበብ የቆመ የመታሰቢያ ሀውልታቸው ነው። ለኛ ደግሞ በእነርሱ ውስጥ ትናትንና ዛሬን አልፎም ነገን የሚያሳየን መነጽራችን ነው። ከልጅነት እስከ ወጣትነት፤ ከትናንት እስከ ትናንት የነበረው የታምራት ሕይወት ለብዙዎቻችን፤ በጥበብ የሚስል ሞረድ ነው። የትዝታ ባህር፤ ያለፈና የወደፊት መነጽር ነው። ደራሲዋ ፋሲካስ ምን ትላለች? በምረቃው ወቅት፤ ካለቻቸው ብዙ ነገሮች፤ ጥቂቶቹ እኚህ ነበሩ፡-

“የብዙዎቻችሁ የልጅነት ታሪክ በታሜ ሕይወት ውስጥ ተቀምጧል። በተለይ ያኔ ኢትዮጵያ ቅደሚ…በሕብረተሰባዊነት አብቢ፤ ለምልሚ ብላችሁ የዘመራችሁ፤ ግራ እጃችሁን እያወራጫችሁ ኢትዮጵያ ትቅደም ስትሉ ያስተጋባችሁ…”ኸረ አምሳለ! ኸረ ሆይ!” እያላችሁ የተጫወታችሁ እራሳችሁን በአንደኛው ምዕራፍ ውስጥ ታገኙታላችሁ። የቡሄውን ሙልሙል ዳቦ እትየ ጌጤ ቤት ያደረሳችሁ…የጥምቀት በዓልን ለማክበር ከነ ሁሴን ከድርና ፋጡማ መሀመድ ጋር ወደ ጥምቀተ ባህሩ የሄዳችሁ ሁሉ እዚህ መጽሀፍ ውስጥ አላችሁ። ቆርኪ ደርድራችሁ እቃ እቃ የተጫወታችሁ፤ ወንዝ ወርዳችሁ ውሀ የቀዳችሁ፤ የታኘከ ማስቲካ የተጋራችሁ፤ ለጎረቤት የተላላካችሁ…እትዬ ማሚቴን ቡና የጠራችሁ ሁሉ እዚህ መጽሀፍ ውስጥ አላችሁ። በዘር፤ በቋንቋና በሀይማኖት ልዩነት ሳትደናበሩ በፍቅር ያደጋችሁ ሁሉ የታምራትን የልጅነት ሕይወት የሚገልጸው ምዕራፍ ላይ ራሳችሁን ታገኛላችሁ። በመጽሀፌ፤ ከታሜ ጋር አብረው የወደቁትን ሁሉ ለማነሳሳት ሞክሬያለሁ። ገና ሞታቸውን የሰማሁ እለት ከሕዝብ ጋር አንብቼላቸዋለሁ። ታሪካቸውን በመጽሀፌ ለማስፈር ቃለ መጠይቅ ሳደርግ ከቤተሰቦቻቸው ጋር አንብቼላቸዋለሁ። እየጻፍኩም ለብቻዬ ያለከልካይ አልቅሼላቸዋለሁ። እልህ አለ፤ ቁጭት አለ፤ ትዝብት አለ፤ ጥያቄ አለ… ብዙ መልስ ግን እንዳትጠብቁ፤ ምክንያቱም የኛ ዓለም ብዙ ጥያቄዎቻችንን ውጣ አስቀርታብናለችና ብዙዎችም ከጥያቄዎቻቸው ጋር አሸልበዋል…”

ደራሲ ፋሲካ ሙሉ፤ ይህን መጽሀፍ ለመጻፍ ስታስብ ለቁፋሮ ያልገባችባቸው ታሪካዊ የአውሮፕላን አደጋዎች የሉም። የሟቾቹን ቤተሰቦች ከያሉበት በማደን፤ ፈልጎም ለማግኘት የገባችው ውጣውረድ ብዙ እንደሆነ አውስታለች። ለመጽሀፏ የታሪክ አካል ካደረገቻቸው ብዙ የአውሮፕላን አደጋዎች መሀከል፤ ከፍተኛ የሰው ቁጥር ያለቀበትን የኢንዶኔዢያውን የአውሮፕላን አደጋም አካታበታለች። ቦይንግ 737 ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን በታሪኳ የማትረሳው ዘግናኝ አደጋ፤ 346 ንጹሀን ዜጎች ከአውሮፕላኑ ወደ ባህር ተረፍርፈዋል። እናት ልጇን እንደታቀፈች፤ ጓደኛማቾች፤ ወንድማማቾች፤ ከአንድ ሀገር፤ ከአንድ ቤተሰብ…ሰቆቃውን በአይነ ህሊናቸው ለደቂቃዎች እየተመለከቱ.. የ9 ወሯ ሩቢ፤ ከእናቷ ጋር ሆና ያሳለፈችውን የስድስት ደቂቃዎች ምጥ…ሁለቱ ጀግና አብራሪዎች፤ ዋና አብራሪ ካፒቴን ያሬድ ጌታቸውና ረዳት አብራሪው አህመድ ኑር ካልገሩት ፈረስ፤ ከቦይንግ 737 ማክስ ኤይት አውሮፕላን… ከጠላፊ ወንበዴዎች ጋር ለስድስት ደቂቃዎች ያህል ያደረጉት ትንቅንቅ…በአውሮፓውያኑ ኖቬምበር 23 ቀን 1996 ዓ.ም፤ ቦይንግ 767 ከአዲስ አበባ ወደ አቢጃን በበረራ ቁጥር 961 በመብረር ላይ እንዳለ፤ ወደ አውስትራሊያ ለመሄድ ከሚፈልጉ ሦስት የአውሮፕላን ጠላፊዎች በተደረገ ግብግብ ኮሞሮስ ደሴት ላይ የወደቀው አውሮፕላን ዘግናኝ አደጋና ዋና ካፒቴኑ ልዑል አባተ፤ በካፒቴን ሀብታሙ በንቲና በረዳት አብራሪው አሉላ ታምራት ጃንዋሪ 25 ቀን 2010 ዓ.ም፤ ከሊባኖስ ወደ አዲስ አበባ ሲበር የነበረውን የቦይንግ 337 አውሮፕላን አደጋ ጉዳይ፤ ዛሬም ድረስ በቂ ምላሽ ያልተገኘለት ጥያቄ እንደሆነ አለና እኚህንና ሌሎች ብዙ ጉዳዮችንም ታነሳበታለች፡፡

 

“ያልገሩትን ፈረስ” በውስጡ አካቶ ከያዛቸው ባለታሪኮች መሀከል አንደኛው ዋና አብራሪ ካፒቴን ያሬድ ጌታቸው ነው። በጊዜው አውሮፕላኑ የወደቀው በአፍንጫው ስለነበረ ከአሰቃቂነቱ የተነሳ አስክሬኑን እንኳን ለማግኘት አልተቻለም። በዚህ ልባቸው በሀዘን ተደቁሶ በእንባ ምሬት የከረሙት የያሬድ ወላጅ አባት፤ በአንድ ወቅት የተናገሯቸው ጉዳዮችን በማካተት ደራሲዋ፤ ብዙ ግለ ታሪካዊ ጉዳዮቹንም አስፍራበታለች። “…26ኛ ዓመቱ ለመድረስ ሦስት ወራት ብቻ ነበር የቀሩት። ድሬዳዋ ከተማ፤ ለገሀሬ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነበር ተወልዶ ያደገው። ድሬዳዋ ላይ የሚታደገው በፍቅርና በደስታ ነው። ቀትር ላይ በዛፍ ጥላ ስር፤ ምሽት ላይ ደግሞ በጎዳና ላይ ሽርሽር… ፍልቅልቁ አህመድ ኑር መሀመድ የዚህ ዘግናኛ አደጋ ሰለባ ነው…” በማለት ትገልጸዋለች። በተመሳሳይ መልኩ፤ በሀገራችን በደረሱ የአውሮፕን አደጋዎች ለልብ ስብራት የተዳረጉ ብዙ ቤተሰቦችን ፈልጋ አስፈልጋ፤ ብዙ ጉዳዮችን ቆፍራና መርምራ ከመጽሀፏ ላይ አስቀምጣቸዋለች።

መጽሀፉን በተመለከተ ብዙ የጥበብ ባለሙያዎች ሙያዊ ዳሰሳቸውን አቅርበውበታል። በተባ ብዕራቸው የምናውቃቸው ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ “ለኢትዮጵያ የስነ ጽሁፍ እምርታ ግዙፍ አሻራውን ለማስቀመጥ የሚችል መጽሀፍ ነው። በግሩም ቃላት፤ ድንቅ የሆኑ ማኅበራዊ እሴቶቻችን እያስመለከተን በሌላ በኩል ደግሞ የነብስን ፍትህ የተጠማና ሁሉንም ጉዳዮች እንድናውቅ የሚያደርግ ነው” ነው በማለት፤ በመጽሀፉ ውስጥ… እንዲህ ቢሆን ኖሮ የተሻለ ነበር ያሏቸውንም ጉዳዮች አንስተዋል። ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ነበር። “በደም የተጻፈ የደም ዶሴ ነው፤ በእንባ ተጽፎ በእንባ የሚነበብ። መጽሀፉ ግኡዝ አይደለም፤ በየምዕራፉና በየዐረፍተ ነገሩ ውስጥ የብዙ ነብሶች ጥያቄና ሙግት አለ። ብዙ ዘመናትን የሚያስጉዘን ባህልና ታሪክ አለው። በዘርና በሀይማኖት…በምንም ነገር የማይገታ ፍቅር አለው። ፋሲካ ሙሉ እናመሰግንሻለን!…” በማለት ነበር የገለጸው፡፡

እኛም በጥቂት ምልከታ እንዲህ እንቃኘው። “ያልገሩትን ፈረስ” የ157 ንጹሀን ዜጎች ሀውልት የቆመበት መጽሀፍ ነው። በመጽሀፉ ውስጥ ደራሲዋ አንድ የአጻጻፍ ስልትን ለመጠቀም ትሞክራለች፤ ይሄውም የሰዎችን ማንነት በጥያቄ በመጀመር አንባቢው ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ታደርግበታለች። ለምሳሌ ደራሲዋ በየመሀሉ አብዝታ “ታሜ ማነው?” በማለት ትጠይቃለች። ከጥያቄዎቹ አንደኛው ለታምራት ወላጅ እናት የቀረበ ነበር። ታዲያ ዘጠኝ ወር በሆዷ ተሸክማ፤ ወልዳ፤ አጥብታ፤ ብዙ ከፍላበት ላሳደገችው እናቱ ድንገት፤ “ታሜ ማነው? “ ተብላ ስትጠየቅ በእንደዚያ አይነት መጥፎ ስሜት ውስጥ ላለች እናት ቀርቶ ሌላውም የሚከብድ ነው። ጸሀፊዋ ግን በመጽሀፏ ይህን ትጠይቃለች፤ ስታሰፍረውም እንዲህ ነው፤ “…ገና በልጅነቱ ለጫማው መጥረጊያ ቀለምና ብሩሽ ገዝቶ፤ ጫማውን ፏ! አድርጎ ሲጠርግ እንደነበር ታውቃለችና፤ “ልጄ በዚያ በለጋ እድሜው እንኳን ሽቅርቅር ነበር…” ትላለች እናቴ ታሜ ማነው ብለው ቢጠይቋት ጊዜ” ትለዋለች። እናት፤ የምትሳሳለትን ልጇን ለመግለጽ የሚሆን የቃላት ኃይል አልነበራትምና ነው። ከመጽሀፉ አቀራረብ ባለፈ፤ በውስጡ የያዘው ታሪክ፤ ከሀገራችን የትዝታ ማህደር ውስጥ ሊፋቅ የማይችል፤ እንደ ሀገር ወሳኝ የሆነውን ጉዳይ በብዕር ቋጥሮ በመያዝ፤ በዚህ አይነቱ ይዘትም የመጀመሪያው መጽሀፍ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ ለመጽሀፉም ሆነ ለስነ ጽሁፉ አንድ አዲስ የከፍታ ግብአት ይሆናል።

በመጽሀፉ ውስጥ፤ በቀጥታ ተደራሲ የተደረጉት አካላት ቁጥራቸው እጅግ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ እራሳቸውን ፍለጋ ወደ መጽሀፉ አልፎም ወደ ስነ ጽሁፉ የሚመጡ ብዙዎች ይሆናሉ። መጽሀፉ በውስጡ የያዛቸው ጭብጦች፤ የግለሰቦቹን ያለፈ ሕይወት ማውሳትና መዘከር ብቻ አይደለም። ከዚህ መጽሀፍ ገጾች፤ የምናገኘው የታሪክ ጭብጦ ከኛው የሕይወት ጓዳ የተቀደና የቅርባችን የሆነ ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን። እንደ አንድ አንባቢ፤ የስሜት ባህር ውስጥ መስጠማችን የማይቀር ነው። ወይ ትዝታን አሊያም ትውስታን እየፈጠረብን አዕምሯችንን ፈገግ ማሰኘቱም አለ። በፊት ከምናውቀው በበለጠ፤ አሁን ከጸሀፊው ጋር አብረን ይበልጥ እንራቀቃለን። ለአንድ መጽሀፍ የታላቅነት የመጀመሪያ፤ የታሪኩ ፍኖተ ብርሃን አንዱ ነው። በውስጡ የያዘው ታሪክና ይዘት በማንበብ ጎዳና ላይ ላለው ሁሉ የመንገድ ስንቁን የሚያቀብል እንዲሁም ብዙኀኑን የሚያካትት መሆን ሲችልም ጭምር ነው። ሁሉም ማኅበራዊ ጉዳዮቻችንን፤ ባልተሸራረፈና ባልተበረዘ መልኩ እንደነበረው ቁጭ ያለበት በመሆኑ የማኅበረሰባችን ነጸብራቅ የሆነ መጽሀፍ ነው፡፡

“ያልገሩትን ፈረስ” ከቤተሰብ እስከ ሀገር፤ ከትላንት እስከ ዛሬ፤ ከጥልቅ ሀሴት እስከ መሪር ሀዘን፤ ከጾታዊ ፍቅር እስከ ቤተሰብና የሀገር ፍቅር፤ አንዱን እያነሳ ሌላውን እየጣለ፤ አንዴ ፈገግ ሌላ ጊዜም ፊታችንን ቅጭም እያስደረገ፤ እየሳቀቀንም እያለቀስንም የምናነበው መጽሀፍ ነው። ደራሲዋ ፋሲካ ሙሉ እንዳለችውም “…ምንም እንኳን የማንበብ ባህላችን የሞተ ቢሆንም ይህንን ብዙ እንባና ደም የፈሰሰበትን መጽሀፍ ግን አንብቡት”

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን መጋቢት   5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You