የድምፅ ብክለት መፍትሔ ሊያገኝ ይሆን?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት ከአዲስ አበባ ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ውይይት አድርገው ነበር፡፡ በውይይቱ ላይ ከተናገሩት አንዲት ነገር ቀልቤን ገዛችው፡፡ ለዓመታት ብሶቴን ስገልጽ የቆየሁበት ጉዳይ ነበር፡፡ በዚህ ጋዜጣ ላይ እንኳን በተደጋጋሚ ትዝብቴን ጽፌያለሁ፡፡ ጓደኞቼ እስከሚታዘቡኝ ድረስ ስለድምፅ ብክለት በተደጋጋሚ አማርራለሁ፡፡ ካፌ ወይም ሆቴል ስንመርጥ ከአገልግሎቱ ጥራት ይልቅ የፀጥታው ጉዳይ ያሳስበኛል፡፡ በሆነ አጋጣሚ አንድ ጩኸት የሌለበት ቤት ካወቅኩ ሁለት ታክሲ ይዤ ሁሉ ልሄድ እችላለሁ፡፡

የድምፅ ብክለት ነገር ያን ያህል አጀንዳ ሆኖ ሲወራበት አይሰማም፤ ዳሩ ግን አደገኛ ችግር ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማን ገጽታም የሚያበላሽ ነው፡፡ አጣዳፊ ሕመም ስላልሆነ ልብ አይባልም እንጂ የጤና ጠንቅ ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ከቤት ወጣ ከተባለ በየትኛውም አካባቢ ብዙ አይነት ጩኸት ያጋጥማል፡፡

ለዚህ ለጩኸት ባለኝ የመረረ ብሶት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለድምፅ ጩኸት አደገኛነት ሲያወሩ ሰማሁ። የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ያሉ የድምፅ ከፍታዎች ለከተማዋም ለሰው ልጆች ጤናም ያላቸውን ስጋት ሲናገሩ፤ ችግሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ ከታወቀ መፍትሔ ይደረግለት ይሆን? ብየ ጓጓሁ፡፡

ሁሉም ማለት ይቻላል አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ የድምፅ ብክለቶች በኋላቀርነትና በመሐይምነት የሚከሰቱ ናቸው። ከፊቱ ያሉ ተሽከርካሪዎች የትራፊክ መብራት ይዟቸው እያየ ያለምንም ማቋረጥ ጡሩንባውን የሚያንባርቅ አሽከርካሪ ብዙ ነው፡፡ በተለይም እንደ አውቶብስ ያሉ ትልልቅ ተሽከርካሪዎች ድምፃቸው እንዴት እንደሚረብሽ

ማንም ያውቀዋል፡፡ ‹‹ሃይገር›› የሚባለው ተሽከርካሪ ‹‹ክላክስ›› ካደረገ ለደቂቃዎች ጆሯችን ይደነዝዛል፡፡

‹‹ክላክስ›› አያድርጉ ማለት አይደለም፡፡ የሚያናድደው ያለምንም ምክንያት ማድረጋቸው ነው፡፡ በእግረኛ መንገድ ላይ ለሚሄድ ሰው ሁሉ ሊያንባርቁ ይችላሉ፡፡ ጩኸታቸው እንዴት እንደሚሰቀጥጥ! አንዳንዶቹ የቤት ውስጥ ኑሯቸው ትዝ ሲላቸው ሁሉ ብስጭታቸውን በክላክስ የሚገልጹ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ዝም ብሎ ወፈፍ የሚያደርጋቸው ነገር አለ፡፡ አንድ ገጠመኝ ልናገር፡፡

አራት ኪሎ ከንብ ባንክ ሕንጻ ፊት ለፊት ያሉት ጁስ ቤቶች አጠገብ ነው፡፡ አንድ የቤት መኪና የያዘ ሰው ዳር አስይዞ ቆሟል፡፡ ቆሞ ግን በክላክስ አካባቢውን ያናውጣል፡፡ ሰዎች ‹‹ምን ሆኖ ነው?›› በሚል ስሜት ዞር እያሉ ያዩታል፡፡ በረንዳ ላይ የተቀመጡት ደግሞ ‹‹ምናባቱ ነው!›› እያሉ ቆጣ እያሉ እንደገና ወደ ጨዋታቸው ይመለሳሉ፡፡ በዚህ መሐል አንዲት የጁስ ቤቱ አስተናጋጅ ወጣች፡፡ ለካ በክላክስ አስተናጋጅ እየጠራ ነበር፡፡ ለዚያውም ቶሎ ሰምታ ባለመምጣቷ ለመቆጣት ሲሞክር ነበር፡፡

እስኪ አስቡት! ይህ ምን አይነት መሐይምነት ነው? አስፋልት ላይ ሆኖ አስተናጋጅ በክላክስ መጣራት ምን አይነት አራዳነት መሆኑ ነው? ያለማቋረጥ ሲጮህ በሚውል ክላክስ እሷን እየተጣራ መሆኑን በምን ታውቃለች? አካባቢው ተሽከርካሪ የማይኖርበት ቢሆን ብርቅ ስለሚሆን ዞር ሊባል ይችላል፡፡ መሐል አራት ኪሎ የእሱ ክላክስ ምን አይነት ምሥጢራዊ አስማት ኖሮት ነው ካፌ ውስጥ ያለ አስተናጋጅ የሚያስወጣ?

አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች ክላክስ የሚያደርጉት ያለምንም አስፈላጊነት ነው፡፡ አንዳንዶቹ በእግረኛ መንገድ ላይ ለሚሄድ ሰው ክላክስ ያደርጋሉ፣ አብዛኞቹ ግን መሄጃ አጥቶ ለቆመ ተሽከርካሪ ነው ክላክስ የሚያደርጉት፡፡ ከፊት ያለው ተሽከርካሪ የቆመው መሄድ ጠልቶ አይደለም፤ መሄድ ስላልቻለ ነው፡፡ ከኋላው እንኳን ክላክስ መድፍ እና ታንክ ቢተኮስ መብረር አይችልም! ይህ መሆኑ እየታወቀ ግን ያለምንም ማቋረጥ አካባቢውን እስከሚያናውጥ ድረስ ያስጮሃሉ፡፡

ሌላኛው አደገኛ ጩኸት ደግሞ የሞንታርቦ ነገር ነው። በተለይ የበዓል ሰሞን ልብ ብላችሁ ከሆነ ከውስጡ የሚወጣውን ድምፅ ለመስማት እስከሚያስቸግር ድረስ ያስጮሁታል፡፡ እስከመጨረሻው በመለቀቁ ምክንያት ምን ቃል እየተነገረ እንደሆነ አይሰማም፡፡ ስንጥርጥርጥር የሚል ድምፅ ነው የሚሰማው፡፡ በጎዳና ላይ እያለፉ ሁለትና ሦስት ፌርማታ አልፈው ሁሉ ይረብሻል፡፡

ይሄው የሞንታርቦ ጩኸት አንዳንድ ግሮሰሪዎችና ምግብ ቤቶች ውስጥ ይገኛል፡፡ ገና በማለዳው ጆሮ የሚበጥስ ዘፈን ይከፈታል፡፡ በዚያን ሰዓት ማንን ያዝናናል ብለው እንደሚያስቡ አይታወቅም፡፡ ለመንፈሳዊ ጽሞና የሚከፈት መዝሙር ራሱ የሚረብሽ ይሆናል፡፡ መዝሙር የሚከፈተው ለመንፈሳዊ ጽሞና ነው፡፡ ዳሩ ግን ማታ ለዘፈን በከፈቱት ሞንታርቦ ጠዋት ደግሞ መዝሙር ይከፍቱበታል፡፡ ሲጀመር ሃይማኖታዊ የምስጋና መዝሙር ስካር እና ዝሙት ሲካሄድበት ያደረ ቦታ ላይ ባይከፈት ጥሩ ነበር፡፡ ፈጣሪን ማመስገን ጊዜና ቦታ አይመርጥም ከተባለ ግን ውስጥ ለገቡ ሰዎች ሊሰማ በሚችል መጠን እንጂ አካባቢውን በሚያጥለቀልቅ ድምፅ መሆን የለበትም፡፡

ሙዚቃ፤ ለመደሰት ከሆነ ለሰስ ባለ ድምፅ ሲሰማ ነው ማጣጣም የሚቻለው፡፡ ለመጨፈር ከሆነ ደግሞ በማለዳ የሚጨፍር የለም! ታዲያ ገና በማለዳው የጆሮ ታምቡር የሚበጥስ ሙዚቃ የሚከፍቱት ለማን ይሆን?

እንዲህ የሚደረገው አብዛኞቹ በኋላቀር አመለካከት ውስጥ ስላሉ ነው፡፡ ቀደም ሲል በነበረው ዘመን ሙዚቃ ብርቅ ነበር፡፡ ብርቅ ያደረገው ሙዚቃ የሚሰማባቸው አማራጮች (ቴፕ፣ ቴሌቪዥን፣ ጂ ፓስ… የመሳሰሉት) ስላልነበሩ ነው፡፡ በሁሉ ሰው ዘንድ ተደራሽ አልነበረም። በዚያን ጊዜ የገጠር ከተማ ውስጥ ያሉ ጠጅ ቤቶችና ጠላ ቤቶች ሙዚቃ የሚከፍቱት ደንበኛ ለመሳብ ነበር። ሙዚቃ ለመስማት ብሎ የሚገባ ሰው ይኖራል፡፡ ይህ ቢያንስ ከአሥራ ምናምን ዓመታት በፊት በገጠር ከተሞች የነበረ ነው፡፡

ዛሬ ላይ (ለዚያውም አዲስ አበባ ውስጥ) ሙዚቃ የደንበኛ መሳቢያ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል? ግድለም! ሙዚቃ የጊዜና የቦታ ገደብ ስለሌለው በስልክ ከመስማት በትልቅ ስፒከር መስማት ያስደስታል፡፡ ያ የሚሆነው ግን ሙዚቃውን ማጣጣም በሚቻልበት የድምፅ መጠን ሲሆን እንጂ መሰማማት እስከሚከለክል ድረስ በማስጮህ አይደለም፡፡

ሌላው እና በድፍረት የማይነገረው ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት ነገር ነው፡፡ አብዛኞቹ አማኞች ነገሩን የሚያዩት ‹‹እምነታችን ተነካ›› በሚል ስሜት ነው፡፡ እኔ የምከተለው ሃይማኖት ሌሎች ሰዎችን የሚረብሽ መሆን የለበትም፡፡ ሰዎች ያለመረበሽ ሰዋዊ መብት አላቸው፡፡ ‹‹…ተቀበል!›› እያሉ በሞንታርቦ የሚደረግ የኃይል ስብከት፣ በድምፅ ማጉያ የሚደረግ ‹‹የ…. ማሰሪያ›› የሚል የማጭበርበሪያ ልመና፤ ሊከለከሉ የሚገባቸው ናቸው፡፡ የየሃይማኖቱ ተቋማት እነዚህን ነገሮች ሊያስቆሙ ይገባል፡፡ በጥቂት አጭበርባሪዎችና አላዋቂዎች ምክንያት የየሃይማኖቱ ስም በወቀሳ መነሳት የለበትም! ‹‹ኤጭ! እነዚህ ደግሞ ጀመሩ!›› እየተባለ የእምነቱን ስም በምሬት የሚያስነሳ መሆን የለበትም!

በአጠቃላይ የእምነት ተቋማትን ጨምሮ፣ ተሽከርካሪዎች እና ንግድ ቤቶች የሚለቁትን አካባቢን የሚረብሽ የድምፅ ልቀት ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You