አንዳንድ ጥንቃቄዎች ከስጋት ይመነጫሉ። ሆኖም ስጋት ባደረበት አካል የሚወሰደው ጥንቃቄ ትክክል ላይሆን አሊያም ሌላኛውን አካል ሊጎዳ ይችላል። እርግጥ ነው ሰውን በእይታ ብቻ መገመት አይቻልም፤ አድራጎቱን እስኪያዩም ደህናውን ከመጥፎው መለየት አዳጋች ነው። በዚህ ስጋት መነሻነትም የሚከተሉት መፍትሄዎች እፎይታን ቢያስገኙም ዳሩ በሌላኛው አካል ደግሞ የቅሬታ ምንጭ ይሆኑ ይሆናል።
ከሰሞኑ ከወደ ፔሩ የተሰማውም ይህንን መሰል ጉዳይ ነው። ዜናውን ያሰራጨው ኦዲቲ ሴንትራል የተሰኘው ድረገጽም አንድ ሰው እግሩ ፊት ለፊቱ ከተቀመጠው ጠረጴዛ ጋር በሰንሰለት ታስሮ የሚያሳይ ፎቶ ተያይዟል። ይህን ሲሰሙ ምናልባትም የታሪኩ ባለቤት የሆነው በፎቶው ላይ የሚታየው ሰው እስረኛ አሊያም ወንጀል የሰራ ሰው ሊመስልዎ ይችላል። ነገር ግን ይህ ሰው በችግር ምክንያት ሃገሩን ትቶ ወደ ሌላ ሃገር የተሰደደ ምስኪን ግለሰብ መሆኑን ይሰማሉ።
ነገሩ እንዲህ ነው፤ በቬንዙዌላ ባለው ወቅታዊ የፖለቲካና ማህበራዊ ቀውስ በርካቶች ተሰደው ብራዚልን፣ ፔሩን እና ኮሎምቢያን መጠጊያቸው አድርገዋል። ታዲያ ከእነዚህ ስደተኞች መካከል የሆነውና ፔሩን የተጠጋው ላ ፓቲላ (ለደህንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረ) ግለሰብ፤ እህል ሊቀማምስ ከአንድ ምግብ ቤት ጎራ ይላል።
ጥቂት ቆይቶ ግን ባለ ምግብ ቤቶቹ ከጠረጴዛው ጋር የተያያዘውን ሰንሰለት ከታፋው አዋደው በቁልፍ ይከረችሙበታል። ሁኔታው ያስፈራውና ያሳዘነው ምስኪን ስደተኛም ነገሩን በፎቶ በማስቀረት ሃገሩ ላለ አንድ ጋዜጠኛ ይልከዋል።
ሉዊስ ማርቲኔዝ የተባለው ጋዜጠኛም በፔሩ የሚገኙ ምግብ ቤቶች ስደተኞች ተመግበው ሳይከፍሉ ይሄዱ ይሆናል በሚል ስጋት እግር ከጠረጴዛ (እግር ከወርች ነበር እኛ የምናውቀው) ማሰር ጀምረዋል ሲል በትዊተር ገጹ ይለጥፋል። ከቆይታ በኃላ የባለ ታሪኩን ፎቶ ያጠፋው ቢሆንም በርካቶች ግን ነገሩ ስለገረማቸው ፎቶውን አስቀርተው መነጋገሪያ አድርገውታል።
ባለታሪኩ ፓቲላ ስለ ሆነው ነገር ሲያብራራም፤ አጋጣሚው የሆነው የውጪ ሃገር ሰዎችን ከመጥላትና አሳንሶ ከማየት የተነሳ እንደሆነ ነው። በዚሁ ምክንያትም የምግብ ቤቱ ባለቤት ግለሰቡ የተመገበበትን ሂሳብ እስኪከፍል መንቀሳቀስ እንዳይችል ማሰርን ምርጫው እንዳደረገም ገልጿል። ፓቲላም ነገሩን በፎቶ ካስቀረና የምግብ ቤቱን ስም ከያዘ በኃላ ሳይበላ መውጣቱንም ጋዜጣኛው ገልጿል።
ጥንቃቄን ስጋት ይወልደው ይሆናል፤ ነገር ግን እንደ እኛ የተቸገረን መርዳት ከፔሩ ዜጎች እሩቅ ሳይሆን አይቀርም። ለመገልገል ምግብ ቤት የሄደ ሰውስ ከትዕዛዙ አስቀድሞ ሰንሰለት ሲቀርብለት ራሱን ደምበኛ ወይስ እስረኛ ብሎ ይጠራ ይሆን?
አዲስ ዘመን ሰኔ3/2011
ብርሃን ፈይሳ