የዛሬ ሳምንት የሸኘነው ሰኞ ዛሬም ተመልሷል፤ የሳምንቱ ማክሰኞም ነገ ሊመለስ ቀጠሮ ይዟል። ከአስር ወራት በፊት የሸኘው ክረምትም ወራቱን ሲያካልል ቆይቶ እነሆ በሰኔ «ግም» ብሏል። ማታ የተረከብነውን ጽልመት ንጋት ላይ ለጸሃይ ብናስረክብም ደግሞ ሰዓታትን ቆይቶ ዳግም ከተፍ ይላል።
እድሜም እንዲሁ ነው፤ በደካማ አካላት ህይወት ይጀመራል። ጉርምስናና ጥንካሬውም ጥቂት ዓመታትን ቢያስቆጥር ነው። ጉልምስናው እርጅናውን እየጎተተ አምጥቶ በድካም ያሳርፈዋል። ህይወት ዙረት ናት ይባላል፤ ዳሩ መሬቷም ክብ አይደለች? አዙሪቱ ሞት ከወሰደው በቀር የሄደውን መልሶ ማምጣት ሃቁ ነው። «ዞሮ ዞሮ ከቤት፤ ኖሮ ኖሮ ከመሬት» ያሉት አበውም ይህንኑ ተገንዝበው ነው።
እኔ የምለው ግን ሳይንስ የነገረን የዓለማችን መሽከርከር በጸባያችን ላይም ተጽእኖ ያሳድር ይሆን እንዴ? «ተውነው» ያልነውን እየመላለስን፤ «ተግባባን» ያልነውን እያፈረስን፣ የረሳነውን እያስታወስን፣ የተረዳነውን እየዘነጋን፣… እንዴት እንዘልቀው ይሆን?
በልጅነቴ የሰማሁትን አንድ ቀልድ ላካፍላችሁ፤ በአንድ የአእምሮ ህሙማን ማእከል የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ህመምተኞቹ ተሽሏቸው እንደሁ ለማጣራት ይነሳሉ። ከዚያም ቴሌቪዥን ከሚመለከቱበት ክፍል አቧራ ያለባቸውን ወንበሮች ደርድረው ሲያበቁ፤ ህሙማኑን አንዳንድ ወረቀት እየሰጡ እንዲታደሙ ይጋብዟቸዋል።
የጤና ባለሙያዎቹ ሲመለሱም ሁሉም አቧራማው ወንበር ላይ ተቀምጠው ቴሌቪዥን ሲመለከቱ ያገኟቸዋል። ከመካከላቸው አንዱ ግን ወረቀቱን ከአቧራው ላይ አንጥፎ ነበር የተቀመጠው። ባዩት ነገርም በመደሰትና ለውጥ እንዳለው በማመን፤ «ለምን ወረቀቱን ከወንበሩ ላይ አነጠፍክ?» ሲሉ ይጠይቁታል። እርሱም «ከፊት ለፊቴ የተቀመጠው ሰው ስለከለለኝ ከፍ እንዲያደርገኝ ነው» ሲል ነበር የመለሰላቸው።
ከሁሉ ይበልጥ ተስፋ ቢጣልበትም የታየው ግን ተቃራኒውን ነው። እኛም ያው ሆነናል፤ የገነባነውን መልሰን እናፈርሳለን፣ ያስተካከልነውን እናበላሻለን፣ ብንሄድም እንመለሳለን፣ ያወገዝነውን እናከብራለን፣ የሰቀልነውን ደግሞ እናወርዳለን፣ አልፈን አናልፍም፤ መልሰን ከዚያው ነን።
እንዲህ ለማለት ምን አነሳሳሽ አትሉኝም? ተግባራችን ነው። ከሰሞኑ ከአዲስ አበባ አንዱ ስፍራ በእግር ጉዞ ላይ ሳለሁ፤ አንድ ወጣት ተጠግቶኝ «ዶላር ነው፤ ምንዛሬ?» እያለ ይከተለኝ ጀመር። ከወራት በፊት በዘመቻ ይህ የጥቁር ገበያ የገንዘብ ምንዛሬ እንዲቀር መደረጉን አስታውሳለሁ። እንዲያውም ይህንን ህገወጥ ተግባር የሚያከናውኑ ሱቆችም መታሸጋቸው የአንድ ወቅት ዜና ነበር። ከቆይታ በኋላ ግን ዳግም አንሰራርቷል ለማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም ወጣቱን ጥቂት አለፍ እንዳልኩ ሌላኛውም በተመሳሳይ «ምንዛሬ?» ብሎኛላ።
ስደትም ሌላኛው አዙሪት ነው። «ስደት ይብቃ» የሚል መፈክር ይዘን ነበር ቅርብ ጊዜ፤ ስለ ስደት መጥፎነትም ብዙ ተሰብከን በብዙ ኮንነናል። አሁን ደግሞ ዳግም ማሻሻያ ተደርጎበት በጋዜጣ እና ሌሎች መንገዶች በገንዘብ እያስተዋወቁና እየደለሉ ወደ ስደት ለማጋዝ በአዲስ መልክ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
ምን ይሄ ብቻ፤ ሌላም አለ። ከወራት በፊት ከአዲስ አበባ ምድር የጎዳና ተዳዳሪነትን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እናስወግዳለን ተብሎ በከተማዋ ሲደረግ የነበረው ሽር ጉድ የጉድ ነበር። ከተመረጡ ክፍለ ከተሞችም የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደ ማሰልጠኛና ማገገሚያ የመውሰዱ ተግባር ተጀመረ። ለጊዜው የተመረጡት ክፍለ ከተሞች ፀዱ። አሁንስ? ያው የአዙሪታችን ጉዳይ ሆነና “ፀዱ” የተባሉት ክፍለ-ከተሞች ተመልሰው እዛው ገብተዋል።
ለአንድ ሰሞን ታትረን ብንሰራም ድካማችን ቅርብ ነው። ላንደግመው ምለን ተገዝተን የተውነውን ስንፍና፣ መጥፎ እሳቤ፣ መከፋፈል፣ መጠላለፍ እና መሰል ነገሮች ውለን ስናድር እርግፍ አድርገን እንተዋቸዋለን። ግለታችን ንፋስ ሲነካው ወዲያው ቀዝቅዞ ወደ ነበርንበት ይመልሰናል።
ሌሎችም አሉ፤ ትናንት ጥያቄ አንስተው እንደተመለሰላቸው ዘንግተው ዳግም መሰል ጥያቄ ያነሱ። ከአንድ የሙያ ዘርፍ ለተነሳ ጥያቄ የተሰጠ ምላሽ፤ መሰል ጥያቄ ላለው ሌላ ሙያም እንደሚያገለግል እየታወቀ መልሶ ለጥየቃ መነሳትን ምን ይሏል?
ከስፖርቱ መድረክም አንድ ምሳሌ ላንሳላችሁ፤ እግር ኳሳችንና ደጋፊዎቹን። ከስታዲየሞቻችን እስከ ጨዋታ ሜዳዎች፤ መሰዳደቡ፣ ለጠብ መፈላለጉ አልፎም ተርፎ ድብድብና ሁከቱ ጠንክሮ ነበር በአንድ ወቅት። በመንግስታዊ አካላትም ምክክር፣ ተግሳጽ እና ቅጣት ሲተገበሩም ጥቂት መሻሻል ታየ። ኧረ እንዲያውም «ስፖርታዊ ጨዋነት ቀንሷል» ተብሎ ነበር። ግን አፍታም አልቆየም፤ መልሶ አገረሸና ጭራሽ «ጨዋታውም ይቅር» ተባለ።
የህይወትን አዙሪት መጋፋት አይቻል ይሆናል፤ ይኼኛው አዙሪት ግን ከድክመታችን ይመነጫል። በየደረስንበት እየተማማልን መልሰን እዚያው ከሆንን እርምጃችን ሁሉ «ባለህበት እርገጥ» ኑሯችንም ውል አልባ መሆኑን እያየን ነው። ግን አዙሪቱ ነው መሰል፤ ከጥፋታችን አልተማርንም።
አዲስ ዘመን ሰኔ3/2011
ብርሃን ፈይሳ