ሳውዲ አረቢያ ባሳለፍናቸው ሳምንታት ሶስት ተከታታይ ስብሰባዎችን አዘጋጅታለች። እነሱም የባህረ ሰላጤ፣ የአረብና የኢስላም አገራት ስብሰባዎች ናቸው። ነገር ግን ሶስቱም ስብሰባዎች በዋነኛ አጀንዳነት ኢራንን ማግለል ላይ ያተኮረ ዓላማ ነበራቸው። የተቀሩት አጀንዳዎች በአካባቢው ስላለው የፀጥታ ችግር በተለይ በየመን፣ በሊቢያ፣ በሶሪያና በፍልስጤም አገራት ያለው ችግር ላይ ነው። ነገር ግን የፀጥታ ችግር በሳውዲና በአረብ ኢምሬት መካከል ያለው ግጭት እንዳይባባስ ለማድረግ ሰፊ ትኩረት አልተሰጠውም።
በስብሰባው መጠናቀቂያ ላይ ሳውዲ በኢራን ላይ የሚደረገው ጫና በወረቀት ላይ የሰፈረ እንዲሆን ዲፕሎማቲክ ስራ ሰርታለች። ለባህረ ሰላጤና ለአረብ አገራት ስብሰባ ኢራን በአረብ አገራ ላይ ያልተፈለገ ጫና እየፈጠረች እንደምትገኝ የሚያሳይ ሪፖርት ተልኮላቸዋል።
በስብሰባዎቹ ማጠቃለያ የእስልምና ኮርፖሬሽን ድርጅት ባወጣው መግለጫ ኢራንን ለማግለል ፍላጎት እንደሌላቸው ገልፀው፤ ነገር ግን በሳውዲና በአረብ ኢምሬት የነዳጅ ማስተላለፊያ ላይ ጥቃት በመድረሱ ተመሳሳይ የሆነ ጥቃት እነሱም ምላሽ መስጠት እንደሚችሉ ገልጿል። በኢራን ላይ ሳውዲ እያደረገችው ያለው ዲፕሎማሲ በምን አይነት መንገድ የባህረ ሰላጤ አገራትና መካከለኛው ምስራቅ ክፍልን እንዴት እንደሚጎዳ በመቀጠል መመልከት ይቻላል።
የሳውዲ ስኬት
እንደ አንዳንድ አረብ አገራት ጥምረት የተደረገው ስብሰባ የሳውዲ ባለስልጣናት የቀድሞ ክብራቸውና በአረብና በኢስላም ዓለም ውስጥ ሃይላቸው እንዲመለስ አድርጓል። በውይይቶቹ ወቅት ብዙ ክርክር አስነስቶ የነበረው ኳታር ጋር ያለው መጠላላትና የጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ ነበር።
ነገር ግን ሳውዲ የባህረ ሰላጤና የአረብ አገራትን ትኩረት በኢራን ላይ እንዲሆን በማድረግ ውጤታማ ስራ ሰርታለች። የሳውዲው ንጉስ ሳልማህ በወቅቱ እንዳሉት፤ ኢራን ለአስርት ዓመታት ሽብርተኞችን በመደገፍ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር በማድረግ ጫና ለመፍጠር እንቅስቃሴ አድርጋለች።
ንጉስ ያነበቡት ሃሳብ በቀጥታ ከምዕራባውያን የተቀዳ ቢሆንም ሳውዲ አጠቃላይ አረብ አገራት ኢራን ላይ እንዲያድሙ አድርጎላታል። ሰብሰባውም ሳውዲ ቀድሞ የነበራትን ተሰሚነትና ተቀባይነት መልሶላታል። ይህ ሁኔታ ሳውዲን በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ተቀባይነቷን ይበልጥ ካሳደገላት ኢራን በአካባቢው ያላት ተቀባይነት ይቀንስባታል። ከስብሰባው በኋላ ሳውዲ ያላትን ክልል እያሰፋች ትገኛለች። ሳውዲ ለእራሷ የምትፈልጋቸውን አጀንዳዎች ቅድሚያ በማሰጠት የምትፈልጋቸውን ነገሮች አሳክታለች።
በውይይቱ ወቅት ለባህረሰላጤና ለአረብ አገራት ሳውዲ የመጨረሻ የሆነ ሃሳብና ክርክር እንዲደረግ በማድረግ ውሳኔ እንዲተላለፍ አድርጋለች። እንደ ኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሀመድ ቢን አብዱራህማን አል ታሃኒ ገለፃ፤ በሁሉም ሃሳቦች ላይ አገራቸው በልዩነት ወጥታለች። ኢራቅ በበኩሏ በስብሰባው መጨረሻ የተወሰነውን ውሳኔ ተቃውማለች።
ሶሪያ ግን በስብሰባው የመካፈል እድል አልገጠማትም። አሁን ሳውዲ ያለችበት ሁኔታ ሁሉንም አረብ አገራት ይወክላል ወይም አይወክልም ማለት አይቻልም። በአሁኑ ወቅት ሳውዲ አረቢያ፣ አረብ ኢምሬትና ግብፅ በአረብ ሊግ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው አገራት ናቸው። ሌሎች ስልጣኖች ባይኗሯቸውም በባህረሰላጤ ትብብር ካውንስል ውስጥ ተመሳሳይ ስልጣን አሏቸው።
ሶስቱም አገራት በስተመጨረሻ ተፋጠዋል። የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በስብሰባው ወቅት እንዳሉት፤ የአረብ አገራት እራሳቸውን ለመከላከል ያስቀመጡትን ዘዴ በድጋሚ የሚታደስበት ሰዓት ነው። ነገር ግን የአልሲሲ ንግግር ዳግም ሳውዲ የአረብ አገራን በድጋሚ እንደምትመራ ወይስ በኢራን ላይ ጦርነት እንደሚከፈት ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም።
የአረብ አገራት አንድ አለመሆን
ሳውዲ ቅሬታ እያቀረበች የምትገኘው የአረብ ሊግም ሆነ የኢስላሚክ ካውንስል በኢራን ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ፍላጎት ስለሌላቸው ነው። ስለ ባህረ ሰላጤ አገራት ችግር በቀረበ ፅሁፍ ላይ ኢራን ስሟ አልተጠቀሰም ነበር። በባህረ ሰላጤ እና አረብ አገራት ስብሰባ ሳውዲ ነጥላ ኢራን እንድትብጠለጠል ብታደርግም የምትፈልገውን ነገር ማሳካት አላስቻላትም።
በስብሰባው የባህረ ሰላጤና አረብ ሊግ በጣም የተከፋፈሉና ከቀድሞ የበለጠ ተዳክመው ታይተዋል። ለዚህ ደግሞ ሳውዲ የተወሰነ ሚና የተጫወተች ሲሆን በተለይ የራሷን አጀንዳ በመጫን አገራቱ እርስ በርስ እንዳይደጋገፉ አድርጋለች። በዚህ ምክንያት ሳውዲ የመጨረሻ መግለጫውን በራሷ መንገድ በማዘጋጀት ብታቀርብም የፈለገችውን ያክል ተቀባይነት አላገኘችም።
አረብ አገራት ቀደም ብሎ የራሳቸው የሆነ የአመራር ዘዴዎች ነበራቸው። ነገር ግን የባህረ ሰላጤው ጦርነትና የአረብ ፀደይ አብዛኛዎቹን አገር አዳክሟቸዋል። በዚህ ምክንያት አረብ አገራት ለስልጣን ይልቅ ሰብዓዊ እርዳታዎች ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል። ሳውዲ፣ኢምሬትና ግብፅ ስለ ኢራን ወይም ስለ ቱርክ እንዲሁም በሙስሊም ወንድማማች ማህበር ውስጥ ስለሚኖር ዴሞክራሲ አይጨነቁም። በዋናነት የእነሱ ትኩረት በአረብ አገራት ውስጥ ስለሚኖረው ሰላምና መረጋጋት ብቻ ነው።
በዚህ ሁኔታ ግን ኢራን በየመንና በሶሪያ ጣልቃ በመግባት በባህረ ሰላጤ ጦርነት ከፍታለች የሚል ክስ በአካባቢውና በዓለም አገራት ቀርቦባታል። በተመሳሳይ ሁኔታ ደግሞ በፍልስጤምና በእስራኤል መካከል ሰላም ለማምጣት ምን መደረግ እንዳለበት አማራጭ ሃሳቦችም ቀርበዋል። እነሱን ለማሳመን ምንም ስልጣን ማሳየት እና ምንም ዓይነት ስልት ማስቀመጥ አያስፈልግም።
ሳውዲ አረቢያ የመጨረሻውን የመግባቢያ ፅሁፍ ሁሉንም ተሰብሳቢ አሳምኖ ነበር። ነገር ግን የመጨረሻ ውጤቱ ከህዝብ ግንኙነት ወሬነት የዘለለ አይደለም። ይህ ደግሞ የኃይል ሚዛንን አይቀይርም ወይም በምድር ላይ የሚለውጠው ነገር አይኖርም። በተለይም ግብፅ ፕሬዚዳንት አል-ሲሲ በንግግራቸው ውስጥ ኢራንን ከመጥቀስ ተቆጥበዋል። ይህም የሚያሳየው ግብፅ በኢራን ላይ ጦርነት እንዲከፈት ፍላጎት እንደሌላት ነው።
በመጥፋት ላይ ያለ ስትራቴጂ
ለማንኛውም ሳውዲ አረቢያ ከስብሰባው ጀርባ የራሷን አጀንዳ ለማራመድ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች። ከላይ በተዘረዘሩት ነገሮች ሲታይ ሳውዲ ተሳክቶላታል። አጠቃላይ ሲታይ ግን ሳውዲ ያልሆነ ስትራቴጂ ተከትላለች። የሳውዲ ዋናው ጉዳይ ኢራን በባህረሰላጤው ግጭት እጇ ስላለበት በቀጣይ በአካባቢው ተቀባይነት እንዳይኖራት ማድረግ ነው። የአረብ መሪዎች በኢራን ላይ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጡ እና በአረቡ ዓለም ውስጥ የማይናወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር ቢሞክሩም አሜሪካ ኢራንን እንድትወነጅል ማድረግ ግን መፍትሔ አይደለም። ምናልባትም የአረብ አገራት ትልቁ ችግር ይህ ሊሆን ይችላል።
በእርግጥ ሳውዲ አረቢያ የኢራን ችግርን ወደ ዋሽንግተን ማምጣቱ ለክልሉ አስከፊ ይሆናል። በሳውዲ የተዘጋጀው ስብሰባ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ የሆነ ጥቅም ያስገኝላቸዋል። ምክንያቱም ከኢራን ጋር ያለውን ውዝግብ በማሳደግ ለአገራቸው ወይም ለግል ጥቅም በማዋል ለቀጣይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
የአረብ አገራት ፈጣን ምላሽ ኢራን በአካባቢው ለሚኖራት ተቀባይነት ትልቅ እገዛ አለው። በዚህም በድርድር ጥንካሬዋን ልትመልስ ትችላለች። ነገር ግን ትክክለኛ የሆነ አንድነት ያስፈልጋቸዋል።
በተጨማሪም የአረቡ ዓለም በተለይም በጦር ግጭቶች የሚያጋጥሙትን ትልቅ ፈተናዎች መቋቋም ያስፈልገዋል። ነገር ግን ሳውዲ እና የእርሷ የበታች አጋሮች የችግሩ አካል እንጂ መፍትሔ እንደማይሆኑ አረጋግጠዋል። በአሁኑ ወቅት በየመን፣ በሊቢያ እንዲሁም በሱዳን ውስጥ አዲስ ጦርነት ጀምረዋል።
እንደ እውነቱ ከሆነ የሳውዲ መንግስት ፍላጎቶቹን ለመጠበቅ እና ለማስፋፋት ከሚያስፈልገው ሁሉ ጋር ለመተባበር አልፎ ተርፎም በጋለ ስሜት ዝግጁ ሆኖ ተገኝቷል። ይህ ማለት ሰዎችን ማሳደድ፣ ባለስልጣናትን ማስፈራራት፣ የአረብ አገራት መሪዎችን በገንዘብ መደለል እና ከውጭ ሃይሎች ጋር መተባበር በተለይ ከአሜሪካ እና እስራኤል ጋር በመሆን ኢራንን፣ ፍልስጤምንና አረብ አገራትን እስከማጥቃት ይደርሳል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2011
መርድ ክፍሉ