ዳግመኛ የተፃፈ ወርቃማ ታሪክ

ውልደቷ እና እድገቷ አዲስ አበባ ነው። ከንግድ ሥራ ኮሌጅ የአካውንቲንግ ምሩቅ ናት። ወደ ትዳር ዓለም ከገባች በኋላ ግን በትምህት መግፋት አልቻለችም። ከባለቤቷ ጋር በመለያየቷ ልጆቿን ብቻዋን ነበር የምታሳድገው። በአካውንታንነት በአንድ ድርጅት ውስጥ ትሠራ የነበረ ሲሆን፤ የሚከፈላት ደመወዝ ከልጆቿ የትምህርት ቤት ክፍያ አያልፍም። የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ምርጫዋ ስደት ሆነ። ልጆቿንም ለእህቷ እና ለእናቷ በአደራ ሰጥታ ወደ ደቡብ አፍሪካ አቀናች።

ይሁንና በሄደች በስምንተኛ ወር ልጇ ሻሎም መታመሟ ተነገራት። እናትና እህት ‹‹እኛ እናስታምማታለን አንቺ እዛው ቆዪ›› ቢሏትም የልጇ ሕመም እየተባባሰ ሄደ። እናት ወደ ሀገሯ መምጣት እንዳለባት ተነገራት። ወደ ሀገሯ በሠላም ብትገባም የልጇ ሕመም ግን ሠላም ነሳት። ልጇ የካንሰር ታማሚ ብትሆንም እንደምትድን በጽኑ ታምን ነበር። ግን አልሆነላትም። ልጇ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየቻቸው።

በልጇ ሞት ተፈተነች። የሽንፈት ስሜት እየተሰማት ቢሆንም ‹‹አልተሸነፍኩም›› በማለት ራሷን ለማበርታት ሞከረች። በሰው ፊት ጠንካራ መስላ ብትታይም ነገሩ ግን ተቃራኒ ሆነ። እንቅልፍ ከዓይኗ ጠፋ። በድባቴ ተሰቃየች። ለራሷም ‹‹ልጄ አልሞተችም›› በማለት ካለችበት ነገር ለመውጣት ራሷን ማበርታት ጀመረች። በድጋሚ ወደ ደቡብ አፍሪካ ብታቀናም የእርሷ ሕይወት ለብዙ ሴቶች ትምህርት ይሆናል ‹‹እነርሱን መርዳት አለብኝ›› ብላ የምትሠራውን ሥራ በመተው እንዲሁም ያለፈችበትን ህመም ማባከን አልፈለገችምና ዳግም ወደ ሀገሯ ተመለሰች። ይህች ጠንካራ ሴት ፌቨን ጋሻው ትባላለች።

ፌቨን ያለፈችባቸውን የሕይወት ውጣ ውረዶች

ለብዙዎች ለማስተማር ‹‹የንጉሱ ሴት ልጅ ወርቃማ መንገዶች›› የተሠኘ መጽሐፍ ለንባብ አበቃች። የመጀመሪው መጽሐፏ ሰዎችን በግል እና በጋራ ተሰባስበው የምታስተምርበት አጋጣሚ ስታገኝ ያለፈችበትን መንገድ ከመንገር በሻገር ለብዙዎች እንዲደርስ በማሰብ በመጽሐፍ መልክ አዘጋጅታ እንዲጠቀሙበት እና እንዲማማሩበት አድርጋለች። በመጽሐፉ አብዛኛው ክፍል የራሷን ታሪክ የሚዳስስ ሲሆን፤ እስከ አራተኛ ዕትም ደርሶላት አማዞንን ጨምሮ በበርካታ መደብሮች ላይ ለመገኘት በቅቷል።

በመቀጠልም ‹‹የንጉሱ ሴት ልጆች የልማት፣የማብቃት እና የበጎ አድራጎት ድርጅት መመሥረትም ቻለች። ድርጅቱ ከመመሥረቱ በፊትም ቢሆን ሱሰኛ የሆኑ ወጣቶችን ታስተምር የነበረችው ብርቱዋ ሴት ፤ ድርጅቱ ከተቋቋመ በኋላም በአራት ዘርፎች ሴቶች ስልጠና እንዲያገኙ፣ የማማከር አገልግሎት፣ የበጎ አድራጎት እና የሚዲያ ሥራ መሥራት ጀመረች።

የመሠረተችው ድርጅት በስልጠና በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጪ በክልል ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች በመሄድ ስልጠና ይሰጣል። በብዙ ውጣ ውረድ የሚያልፉ ሴቶችን ደግሞ የማማከር ሥራ ይሠራል። በበጎ አድራጎት ሥራ ደግሞ ‹‹ልብሴን ለእህቴ›› የሚል ዘመቻ በመክፈት አልባሳትን ከአዲስ አበባ ከሚገኙ ሴቶች በመሰብሰብ ‹‹ማንም ሴት ልጅ በልብሷ ምክንያት ከማሕበራዊ ሕይወቷ አትገለልም›› በማለት ከሁለት ሺ በላይ ሴቶች ድጋፍ እንዲያገኙ አድርጋለች።

ፌቨን በድጋሚ ትዳር መመሥረቷን ተከትሎ ‹‹ጎጆ መውጫ›› በሚል ዘመቻ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በማረሚያ ቤቶች፣ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላሉ ሴት ተማሪዎች እስከ ሁለት ዓመት የሚያገለግል የንጽህና መጠበቂያዎችን በአዲስ አበባ እና በክልሎች ድጋፍ ተደርጓል። በሚዲያው ዘርፍም ቢሆን በዩቲዩብ እና በማሕበራዊ ትስስር ገጾቿ ላይ ለሴቶች የሚጠቅሙ ሃሳቦች ይንሸራሸርበታል። በቅርቡም በራዲዮ እና በቴሌቪዥን ሴቶችን የሚያበረታታ ርዕሰ ጉዳይ በመቅረጽ ፕሮግራሙን ለመጀመር ዝግጅቷን አጠናቃለች።

አንዳንድ ወላጆች ሴት ልጆቻቸው በሱስ ውስጥ እንዳሉ አያውቁም። ብዙዎቹ ግን በድባቴ እና በሱስ ሕይወት ውስጥ እየተዘፈቁ ይገኛሉ።ራሳቸውን ‹‹ሱሰኛ ነን›› ብለው እንዳያጋልጡ ማሕበረሰቡ ያሸማቅቃቸዋል።ፌቨን በሱስ ሕይወት ያሳለፈች ሴት እንደመሆኗ በሱሰኝነት እና ድባቴ ላይ እየሠራችም ትገኛለች። ከዚህ ጋር ተያይዞም በዚህ ዓመት ለሴቶች ብቻ የሚሆን ከሱስ ማገገሚያ ቦታ ለማዘጋጀት እቅድ እንዳላት ስትናገር ትደመጣለች።

ፌቨን በአንድ ቀን ውሳኔ ከሱስ ለመውጣት ችላለች። ደግሞም በሂደት ያቆመችባቸው ጊዜያት ነበሩ። በገጠማት ተደራራቢ ፈተናዎች ለመደበቅ እንዲሁም አራዳ ለመባል የገባችበት ሱስ ለመግባቱ እንደቀለላት መውጫው ጠፍቶባትም ያውቃል። ዋናው ነገር ለመተው መወሰን እንደሆነ ትናገራለች። በመንፈሳዊም ይሁን ሕክምናውን ተከታትሎ መላቀቅ እንደሚቻል ታምናለች። ዋናው ግን ያንን ሕይወት መጥላት አለበት። ያን ጊዜ የሕክምና ባለሙያም ይሁን እግዚአብሔር ይረዳዋል ትላለች። መንፈሳዊ ልምምዱም ቢሆን ወሳኝነት አለው ባይ ናት።

በአብዛኛው ለእርሷ ከሱስ ሕይወት ለመውጣት መንፈሳዊ ሕይወቷ በጣም አግዟታል። የቀደመው ውሎዋን መሸሽ እና በፊት የነበራትን ልምዶች መቀየሯ ወደ ኋላ እንዳታይ አድርጓታል። ምርጫዎቿ መንፈሳዊ ነገርን መለማመድ መንፈሳዊ የሆኑ ነገሮችን መስማት እና የፓስተሮቿ (መንፈሳዊ መምህሮቿ) ተከታታይነት ያለው እገዛ ቀድሞውም ቢሆን የጠላችውን ሱሷን እርግፍ አድርጋ እንድትተው በሚገባ የረዷት መሆኑን ትገልፃለች።

ከሱስ ለመውጣት ሁሉንም ውሳኔ መጠቀም ይችላል። ዋናው የተሻለ ሕይወት መኖሩ ነው። መንፈሳዊ ቦታ ብቻ ካልመጡ ወይም ወደ ሕክምና ካልሄዱ መዳን አይችሉም አይባልም። ዋናው ምርጫ ውሳኔ እና በውሳኔ መጽናት ነው። በሱስ ውስጥ ያለ ሰው ‹‹በምን መንገድ ነው መውጣት የምችለው? ብሎ ማሰብ ግን ይኖርበታል ስትልም ትመክራለች።

የሱስ ሕይወት ጊዜን፣ ገንዘብን፣ ዕድሜን፣ ቤተሰብን … ያሳጣል። ብዙዎች ወደ ሱስ የሚገቡት በአቻ ጓደኞቻቸው ጉትጎታ እና ግፊት ነው። የፌቨንም ከዚህ የተለየ አይደለም። የነቃች፣አሪፍ የተባለች እና አራዳ የሆነች መስሏት ገባችበት። ሱስ ብዙ ነገሮችን አሳጥቷታል። ከቤተሰብ ጋር ያላትን ግንኙነት አሻክሮባታል፤ ሰዎች እምነትና ክብር እንደማታገኝበት በሚገባ ተምራበታለች። በዚህ ሕይወት ውስጥ ያለች ሴት ደግሞ ለቁምነገር፣ ለትዳር እና ለኃላፊነት አትታጭም። በአጠቃላይ ማንነትን ያሳጣል። ተስፋን ያስቆርጣል። በሰዎች ዘንድ የተተወች አድጓታል። ‹‹በአጭሩ የሱስ ሕይወት በከበባ ተጀምሮ በብቸኝነት የሚጠናቀቅ ሕይወት ነው›› ስትል ትደመጣለች።

ዛሬ ፌቨን ለመልካም ነገር ብቻ ነው ወደ ፊት የምታመለክተው። ‹‹ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለምን? እስከ ምን›› በሚል ርዕስ ሁለተኛ መጽሓፏን ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ ናት። አሁን አሁን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› የሚለው አባባል ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ፍንተው ብሎ ይታያል። ብዙዎችም በፈለጉበት መንገድ ተፅዕኖ ሲፈጥሩ አስተውላለች። ከዚህ ጋር ተያይዞም በማሕበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ምን እንደሆነ በተለያየ አቅጣጫ እንድታይ እድል እንደፈጠረላት ታምናለች። ብዙዎች ይህንን በአግባቡ መንገድ እየተጠቀሙበት እንዳልሆነ በተደጋጋሚ በመመልከቷ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ላይ አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን ኃላፊነት መሆኑን ብዙዎች አልተረዱትም የሚል እምነት አላት። የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች በተዛባ መንገድ እንዳይረዱት እና እንደ አራያ እንዳይወስዱት ለመታደግ እንዲሁም ለማሳወቅ መጽሐፉን ለመጻፍ በቅታለች።

በተጨማሪም ለምንድነው ተጽዕኖ የምንፈ ጥረው? እንዴት ነው መፍጠር ያለብን? በጎ ተጽዕኖ ፈጣሪነትስ ምን ያስፈልገዋል? ፈተናዎቹስ ምንድናቸው? የሚሉትን ሁሉ በዝርዝር በማካተት በጎ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ቀጣይነት እንዲኖረው ምን መደረግ እንዳለበት ጭምር የሚዳስስ ነው። ብዙዎች የራሳቸውን እውነት ጥለው የተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ሕይወት ነው የሚያነሱት። እነዚህ ሰዎች ኃላፊነት እንዲሰማቸው ምክክር እንዲደረግበት ቀነ ቀጠሮ ይዛለች።

በቀጣይም ብዙ እቅዶች አሏት። ተማሪዎች ከአቻ ግፊት እና ለራሳቸው ከሚሰጡት ግምት አንፃር በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለማሰልጠን በዝግጅት ላይ ናት። እንዲሁም ሴቶች ራሳቸውን የሚችሉበት የትምህርት እና የሥራ እድል እንዲያገኙ ለማመቻቸት ጥረት እያደረገች ትገኛለች። የመጡበትን የሕይወት ውጣ ውረድ ወደ ራዕይ ቀይረው የሚሄዱ ሴቶች በማፍራት ለሴቶች ምሳሌ የሚሆኑ ሴቶችን ለማፍራት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራች ትገኛለች።

የንጉሱ ልጆች ድጋፍ በሚገኘው ድጋፍ ከማህበረሰቡ ለማህበረሰቡ እየደረሰ ይገኛል። የመጀመሪየ መጽሐፏ ገቢ የድርጅቱን ወጪ እንድትሸፍን ረድቷታል። ከዚህ በኋላም ቢሆን የተለያዩ ሁነቶችን እና ፕሮጀክቶችን በመቅጽ ይሠራል።

ፌቨን ከሱስ እና ድባቴ ሕይወት ተላቃ ለብዙዎች በመድረሷ የደስተኝነት፣ የኩራት እና የአሸናፊነት መንፈስ እንድትላበስ አስችሏታል። ከሁሉም ከሁሉም ግን በየቀኑ የሚመጡላትን ግብረ መልሶች ስታይ የሚገጥሟትን ፈተናዎች በቀላሉ እንድታልፍ አቅም ፈጥሮላታል። በከባድ የሕይወት ፈተና ውስጥ ያሉ ወጣቶች ራሳቸው ላይ መጥፎ እርምጃ ለመውሰድ አስበው የእርሷን ታሪክ ሰምተው መተዋቸውን ሲነግሯት ደግሞ እንኳንም ወደዚህ በጎ ሥራ ገባሁ እንድትል አድርጓታል።

ሕይወት ይቀጥላል። የአንድ ሰው ታሪክ ለሌላው መማሪያ እና መጽናኛ ይሆናል። ከዚህ ቀደም በተማረችበት ትሠራ የነበረችው ፌቨን ልምዷን፣ ጊዜዋን እና እውቀቷን ለንጉሡ ሴት ልጆች ድርጅት አሳልፋ ሰጥታለች። እንደ ሴት ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው በብዙ ፈተና ያሳለፈችው ፌቨን ትናንት ከልጃቸው ጋር እንዳትታይ የሚፈልጉ ሰዎች ዛሬ ግን የልጃቸውን ሕይወት እንድትታደግላቸው ይመርጧታል። ታሪክን እንደገና እንደሚፃፍ ያመነች እና በተግባር ያሳየችው ጠንካራዋ ሴት ትናንታችን፤ ነጋችንን መያዝ እንደሌለበት እና የትናንት መጥፎ ታሪክ ባሪያ እንዳንሆን ደማቅ ታሪክን እንደገና መጻፍ እንደሚቻል ብርቱዋ ሴት ምሳሌ ሆናለች።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You