የጠፋብንና የራቀንን ነገር እራሳችን ውስጥ የመፈለጉ ልምድ ስለሌለን ራሳችንን መመርመሩን ትተን ወደ ሌላው አሻግረን እንመለከታለን፤ ልማድ ይሆን! ብቻ ራስን ፍለጋ ልንመልስ የማንችለውን ብዙ ጥያቄ እንጠይቃለን። በእርግጥ ራሳችን ጋር መልስ ጠፍቶ አይደለም፤ እንደውም ከራሳችን በላይ መልስና መፍትሄውን የሚያውቀው ከቶም የለም። ታድያ ለራሳችን ጥያቄ መልስ ካላገኘን ደስታ አልባ ሲያልፍም ለጭንቀት መዳረጋችን አይቀሬ ነው።
ጥያቄ፤ ደስታችንን የሚነጥቀን ማን ነው? እኔ የራሳችን ደስታ ነጣቂዎቹ እኛው እራሳችን ነን ባይ ነኝ። የደስታችን መራቅም ሆነ መቅረብ ምክንያቶች እኛው ነን። እንዴት? አላችሁኝ አይደል?። ጥሩነት የራቀው ሰው የተሰጠውን በደስታ ተቀብሎ እሱን ከማጣጣም ይልቅ የሌለውን መመኘት፤ የማያገኘውን መናፈቅ ያዘወትራል። ራሱን ከሌላው ጋር እያነጻፀረ ያለውን ንቆ የሌለውን እያሰበ ሚዛን ያጎድላል። የሚኖርበትን መውደድ ትቶ እንዲኖረው የሚፈልገውን እያሰበ ሁሌ ይቦዝናል፤ የሚኖረውን ኑሮ ጣዕም ያጣበታል። ያኔ ደስታ ከራሱ እልም ብሎ ይጠፋል።
ወዳጄ…አታማርር! ያለህን ነገር ተቀብለህ የተሰጠህን በልኩ ተጠቀም። ራስህን ደስተኛ አድርግ፤ ለማታውቀው ነገ ለመኖር ዛሬህን አትግደል። ደግሞ‘ኮ ነገ ለመገኘትህ እርግጠኛ አይደለህም። ይህን ስልህ ግን ተስፋ አታርግ ማለቴ አይደለም። ዛሬህን አሳልፈህ ለማታውቀው ነገ አትስጥ እንጂ። ዛሬን በወጉ እየኖርክ በደስታ እያሳለፍክ በጥሩ መንፈስ የተሻለ ነገ ፍጠር። በልክህ ኑር!
ልቀጥል! ሰዎችን በድለህ በአቋራጭ ያልተገባን አታግበስብስ። እስካሁን የተጠቀምክበት ብቻ ነው ያንተ። ለመሰብሰብ ያቀድከው አይደለም፤ እንኳንስ ያልያዝከው የያዝከውንም በወጉ ማጣጣምህን ማንም አያውቅም። ይልቅ ለነገሮች ያለህን አመለካከት በመቀየር በእጅ ላይ ባለችው ዛሬ ላይ ሀሴት አድረገህ እለፍ!
ሰዎች መናጢ ደሀ የሚል ስም ቢሰጡህ አያሳስብህ፤ በዚህ ዓለም በነዋይ ታውረው ነው። አስበው! አንተ ግን ከሁሉ የላቀ ነገር በእጅህ አለ። በአለም ላይ ያለ ሀብት ሊሰጥህ ጤናህን አሳልፈህ ትሰጥ ነበር? እመነኝ! የዚህን ያህል ሀብታም ነህ ወዳጄ! ተወዳዳሪ የሌለህ። ያለህ ብዙ ነው፤ ጎደለ ከሚሉህ ከምትለውም በላይ። ደስታን ማግኘት ከፈለግህ አንተነትህ ፈጽሞ በሌላው ሚዛን አትስፈር። የተሰጠህን ተቀበልና የራስህን ኑሮ ኑር። ሰው በድህነቱ ንፁህ ህሊናውን ይዞ ሊሰፈር የማይችል ደስታን ይጎናፀፋል።
ለሰዎች የምንሰጠው ክብር፣ ፍቅርና በጎ ምግባር ሌላኛው የደስታችን ምንጭ ነው። ልብህን በፍቅር ሞልተህ፣ ቀናነትን ተላመድና የኑሮን ጣዕም ማጣጣም ጀምር። ከራስህ የሰረቅከውን ደስታ ወደራስህ አስመልስ። ሰዎችን በእኩል ማየት ካልጀመርክ ስቃይ ውስጥ ነህ። ልብህ ውስጥ ጥላቻ ካለ ምንም ብሩህ ነገር መመልከት አያስችልህም፤ ጽልመት ነው። ጽልመት ደግሞ ምንም ተስፋ የለውምና ይጎመዝዛል። ያለ ተስፋ ህይወት ይቀፋል። ተስፋ ካጣህ እንግዲህ ምኑን ተኖረ?
ገጥሞህ አያውቅም? ከውጪ ስታየው ውብ ያልከው ሁሉን ያሟላ መኖሪያ ቪላ ወይም ዘመንኛ ቤት ውስጡ ፍቅርና ሰላም አጥቶ በጥላቻ የጠቆረ። ሰዎች በአግራሞት ፓ! ያሉለት ውስጡ ባዶ ከሆነ ምን ያደርጋል፤ ስትቀርበው የሚቀል። እናም በስዕብናህ ክበድ፣ የዛኔ አቤት እንዴት ደምቀህ እንደምትታይ። በጭለማ ውስጥ የምትንቦጎቦግ ብርሀን፤ ለሁሉም ጎልተህ የምትታይ ነህ። ይህን ካላደረክ ግን ደስታህን ከራስህ ላይ ሰርቀሀል። የደስታህ ሌባ አንተው ነህ።
ስለ ራስህ ጤነኛ አመለካከት ይኑርህ፤ አንተ ሁሉ ያለህ ነህ። ለዐይናችን ቆንጆ ነው ብለን ያስለመድነውን አይደል ቆንጆ የምንለው። ቁንጅና እኮ በህሊናችን የተሳለ ሃሳብ ነው። ለዚያ እኮ ነው ቁንጅና የሚለያይብን፤ በሁላችን ልቦና በተለያየ መልኩ የተሳለ ስዕል የተቀረጸ ምስል ስለሆነ። ለሁሉም የሚጎላ ውበት ለሁሉም በአንድነት የሚያስደንቅ እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭን መልካም ሀሳብና ምግባር ነው።
ራስህን ከማንም ጋር አታነጻፅር ምክንያቱም አንተ ማለት አንተ ነህ። ምድር ላይ ተወዳዳሪ የሌለህ፤ ከማንም ከምንም ጋር የማትወዳደር። ማንም የሚበልጥህ የለም። ሰዎች በሚሉት ቁንጅና የተበለጥክ ከመሰለህ ተሳስተሀል። ባይሆን ለሁሉም ውብ ሆኖ የሚታይ ጸባይና ጥሩ ስብዕናን ተላበስ ያኔ ሁሉንም ታስከነዳለህ።
ቂምና ጥላቻ ልብን ያጠቁራል። የጠቆረ ልብ ደግሞ ለባለቤቱ ደስታን ሊያጎናጽፍ አይችልም። ከማቄም ይልቅ ክፋትን በፍቅር መልስ። አንድ ቦታ ለመድረስ አልመህ መንገዱን በእግር ስታቋርጥ በመኪና ጎማው ውሃ የረጨብህን ባለ ጊዜ አትጋፈጠው። እሱ መኪና ውስጥ አንተ ደግሞ መሬት ላይ ነህ። ከመኪናው መውረዱ ስለማይቀር ታገሰው። ፈጽሞ አትስደበው ባይሆን በትዕግስትህ አስደምመው፤ በዝምታህ ግረፈው፤ በመልካምነት ብለጠው።
የሚረግጠውን ማየት ስለተወ ብዙ አይሄድም፤ ይደናቀፋል። አንተ ቤትህ ተመልሰህ ልብስህን አጽድተህ መንገድህን ቀይረህ ጉዞህን ቀይር። በቃ ትኖራለህ! እሱ ወድቆ ካየኸው ግን አትለፈው። አንስተህ ደግፈህ በፍቅር አክመው። ትደሰታለህ ለዚያውም ዘለቄታዊ ደስታ። ሰውን በፍቅር ማስተማር ምንኛ ትልቅነት መሰለህ።
እባክህን ሰዎች ሞኝ እስኪሉህ ድረስ በጎ ሁን። ለሰው ብለህ ራሰህን ስጥ፤ ለፍቅር ብለህ መስዋዕት ሁን። ስለ ፍቅር ብለህ ሁሌም ተንበርከክ። ፍቅርን መሸከም ካቃተህ እንኳን ውደቅ። ምክንያም የወደቅከው በፍቅር ነውና መልሶ ፍቅር ያነሳሀል። ለራስህ ብለህ ሰዎችን ብትጥል ፍቅርን ከገፋህ ግን ትወድቃለህ። ለዚያውም ክፉኛ አወዳደቅ፤ እንዳትነሳ ሆነህ።
ከጥላቻ የራቀ ንጹህ ልብ ለመታደልና ከጭንቀት ነጻ የሆነ ህይወት ለመምራት ሁሌም ለሰዎች በጎ መስራት ትልቅ መፍትሄ ነው። ጭንቀት ውስጥ የሚከተን ለነገሮች ያለን እሳቤ በተሳሳተ መልኩ መመልከታችን ነው። ምንም ነገር ያለምንም ምክንያት እንደማይፈጠር ለራሳችን መንገሩና ራሳችንን ማሳመኑ ይቸግረናል።
ወዳጄ! ደስታህን ከራስህ ጋር ማቆየት ትፈልጋለህ? እንቅልፍ የሚነሳህ የሰዎች ሀቅ ከማጉደልና እና በደል ከመፈፀም ሁሌም ተጠንቀቅ። ምግባርና ስራህ በጎ ከሆነ ባትበላ ርሀቡ አይቀፈድድህም፤ባትለብስ የሰው ፍቅር ትሞቃለህ። የትም ጋደም ብትል ለሽሽ ብለህ የሚያስቀና እንቅልፍ ትተኛለህ። ሰዎች ብዙ ጊዜ ስግብግብ የሚሆኑት ፈፅሞ ቢያገኙም በማይጠቀሙበት አግኝተውም በማይደሰቱበት መሻታቸው ላይ ነው።
ስግብግብ ሰው ተመልከት ይሰበስባል፣ ላይ በላይ ደራርቦ ከምሮ ከልክ በላይ ያደልባል። እድሜውን ሙሉ ያለ እረፍት የሱ ያልሆነን የማይገባውን የሌሎችን እየነጠቀ ሀብት ያከማችና በመጨረሻ እራሱ በሰራው ክፉ ተግባር ሰላሙን ያጣል። በላቡ ሰርቶ በተገቢው መንገድ ስላላገኘው ሁሌም ሰዎችን በጥርጣሬ ያያል፥ ማህበራዊ ህይወቱ ይናጋል፣ ቀድሞ ደህነቱን ይሰጠው የነበረ ነፃነት እስኪናፍቅ ድረስ ያገኘው ሀብቱ ያንገሸግሸዋል።
ወደ ኃላ እንዳይመለስ የሰራው ሴራ እንዳይነሳ አድርጎ እንደሚጥለው ስለሚያውቅ ራሱን እንዲጠላ ኑሮው እንዲጠየፍ ያደርገዋል። በወንጀል ላይ ወንጀል እሱን ለመሸፈን ደግሞ ሌላ እያለ የማይወጣው አዘቅት ውስጥ ይገባል። ተጠያቂ ባይሆንና ባያውቁበት እንኳን በህሊና እስር ይማቅቃል። የሰው ልጆችን በድሎ ሰዎች ረግጦ ከፍታ ላይ የደረሰ ከፍ ከፍ ይልና እንዳይተርፍ ሆኖ ይፈጠፈጣል። አቤት አወዳደቁ! ኳ! የዛኔ አጥንቱን መልቀም እንኳን ያዳግታል። ወዳጄ ደስታህ ከራስህ የምታርቀውም የምታቀርበው አንተ ነህ። ሰው ወደህ፣ ሰውን አክብረህ እና አፍቅረህ፤ ራስህን ለሰው ደስታ ሰውተህ ደስታህን አስመልስ። ሰላም ተመኘውልህ አቦ!
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2011
ተገኝ ብሩ