25 ዓመታት የተሻገረው ጥምረት- ላፎንቴኖች

“ላፎንቴኖች” ኢትዮጵያውያን አብሮ ከመብላት ባሻገር አብረው መሥራት እንደሚችሉ በተግባር ያሳዩ የሁለት ጥንድ ድምፃውያን የጋራ መጠሪያ ነው። በዛሬው የዝነኞች ገጽ ወትሮው በተለየ ሁለት ዝነኞችን የማቅረባችን ምክንያትም በትናንትናው ዕለት የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቅ ዐሻራ ካሳረፉ ከያኒያን መካከል የሚጠቀሱት የላፎንቴኖች 25ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓል በማሪዮት ሆቴል በታላቅ ኮንሰርት መከበሩን በማስመልከት ነው።

የላፎንቴኖች ትውውቅ 25 ዓመታትንም ይሻገራል። በወቅቱ “ሮያል ፓላስ በተሰኘ የምሽት ክበብ ሲሠሩ የተጠነሰሰው ወዳጅነት እስካሁን ዘልቋል። የሀገራችን አበው ነገርን ከስሩ ውሃን ከምንጩ ይላሉና በመጀመሪያ የቡድኑን አባላት የተናጠል ጉዞ ልናይ ወደድን።

ብርሃኑ ተዘራ ከአዲስ አበባ ካዛንቺስ፤ በተለይም ለገብርኤል ቤተክርስቲያን ቀረብ ካለ ቦታ የተገኘ ድምፃዊ ነው። አባት ቢሉ አያት የቤተክርስቲያን አገልጋይ ናቸው። ቤተሰቦቹ በስለት ያገኙት የስስት ልጃቸው ነውና የገብርኤል አገልጋይ እንዲሆን ተወስኖም ነበር። እሱም ይህን የቤተሰቦቹን ምኞት የሚፈጽም ልጅ ይመስል ነበር። ሰባተኛ ክፍል እስኪደርስ ድረስ ከትምህርቱ ጎን ለጎን የቤተክርስቲያን አገልጋይ ነበር።

ሰባተኛ ክፍል ሲደርስ ግን ሙዚቃ ጠልፋው ቀበሌ ውስጥ የሚገኝ የታዳጊ ቡድንን ተቀላቀለ። በአቅራቢያው በሚገኘው ቀበሌ 26፤ ቀጥሎም ከፍተኛ 15 ኪነት ቡድን እያለ የሙዚቃ ሕይወቱ ቀጠለ። የደርግ መንግሥት ከሥልጣን መነሳቱና ለተወሰነ ጊዜ የኪነት እንቅስቃሴ መቋረጡን ተከትሎ እሱም ከሙዚቃ ጋር የተለያየ መስሎ ነበር። ያኔ የምሽት ክበቦች የሙዚቃ መድረኩን መቆጣጠር ጀመሩ። ብርሃኑም በ1986 ዓ.ም ሰፈሩን ሳይለቅ ካዛንቺስ በሚገኝ የራሷ ሥም የሌላት ትንሽ ቤት ሙዚቃን መሥራት ጀመረ።

ቤቱ ትንሽ በመሆኑ ምንም ሥያሜ ባይኖረውም አጠገቡ “ላፎንቴን” የተሰኘ መዋእለ ህጻናት ስለነበር እንደምልክት ያገለግል ጀመር። በሂደት የቤቱ ሥም “ላፎንቴን” በሚል በሁሉም ዘንድ ታወቀ።

ብርሃኑ በወቅቱ የተለያዩ ድምጻውያንን ዘፈን ከመዝፈኑም ባሻገር በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የታዳሚን ቀልብ በሙዚቃ ወዳጆችንም ሆነ በሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ጊዜ አልፈጀበትም። ለዚህም ይመስላል በ1987 ዓ.ም ያየህይራድ አላምረው “ሮያል ፓላስ” የተሰኘ ቤት ለመክፈት ሲያስብ ካሰባቸው የቤቱ አድማቂ ድምጻውያን መካከል አንዱ እንዲሆን ያጨው።

ሌላው የሮያል ፓላስ ድምቀት እንዲሆን የታጨው ከአዲስ አበባ (መርካቶ) የተገኘው ድምጻዊ ታደለ ሮባ ነው። በመርካቶ ሠባተኛ አካባቢ የተወለደው ታደለ ከሙዚቃ እኩል ሊባል በሚችል መልኩ ለኳስ ለየት ያለ ፍቅር ነበረው። የእሱ የመኖሪያ አካባቢ በሆነው ከፍተኛ 25 ትልቅ የኪነጥበብ እንቅስቃሴ ነበር።

የኪነት እንቅስቃሴ ሊቋረጥ በተቃረበበት አካባቢ የቀበሌ 12 ታዳጊ ኪነት አባል በመሆን ቡድኑን በተወዛዋዥነት ተቀላቅሏል። በትምህርት ቤትም “ዘ ቲ በርድስ የሚሰኝ ግሩፕ መስርተው ይንቀሳቀሱ ነበር።

ታደለ በወቅቱ የእውቁን አሜሪካዊ ድምጻዊ የማይክል ጃክሰንን ከጸጉር አበጣጠር እስከ አለባበስ ለማስመሰል ስለሚጥርና የሱን ዳንሶች ይደንስ ስለነበር ቅጽል ሥሙ “ማይክል” ነበር። በዚህ መሃልም ቢሆን ኳስ ጨዋታው አልቀረም። ኳስ ተጋጥመው የእሱ ቡድን ተጋጣሚውን ሲያሸንፍ ዋና አስጨፋሪ ነበር። ካልሆነም “ማን ሞኝ አለ” ያለ ይመስላል፤ ላሸነፏቸው ተቃራኒ ቡድን በክፍያ የድል ዜማ አውራጅ ይሆናል። ይሄ የኳስ ፍቅሩ አሁንም አልተለየው። ከሀገር ውስጥ የቡና፣ ከውጭ ክለቦች የእንግሊዙ አርሰናል ደጋፊ ነው።

የድል ዜማ ሲያወርድም ሆነ በማንኛውም ጊዜ የታደለ ድምጸ መረዋነት በሰፈር ውስጥ የታወቀ ነው። የታደለን የማዜም ብቃት የሚያውቅና ድምጻዊ ኃይልዬ ታደሰን የሚያውቅ ሰው በወቅቱ ኃይልዬ ይሰራበት ወደነበረው ቦሌ (ኦሎምፒያ) ይገኝ የነበረው “ማራቶን ክለብ” ይወስደዋል። ያን ምሽት በቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በናይት ክለብ የመዝፈን እድልን አገኘ። እዛ ሲዘፍን ያየው ሰው አራት ኪሎ የሚገኘው “ፋሲካ ክለብ” እንዲዘፍን ጋበዘው። በተመሳሳይ ኒያላ ሆቴልም እንዲዘፍን ተጠራ።

ኒያላ ሆቴል በክፍያ የሠራበት የመጀመሪያ ቤት ነው። ኒያላ እየሠራ የሰፈሩ ልጆች የነበሩት ድምጻዊ አለማየሁ ሂርጶና ፒያኒስት ጸጋቸው በወቅቱ የተሻለ የነበረው አሮሰ ሆቴል ባለቤት ጎበዝ ልጅ እንዳለ በመንገር ይዘውት ሄዱ። እዛም የተሻለ እየሠራ ከቆየ በኋላ በያየህይራድ የተቋቋመውን ሮያል ፓላስ እንዲያደምቁ ከተመረጡት አንዱ በመሆኑ ቤቱን ተቀላቀለ።

ያየህይራድ አላምረው ድምጻዊ ታደለ ሮባን ይሠራበት ከነበረው አሮሰ ሆቴል፤ ድምጻዊ ብርሃኑ ተዘራን ላፎንቴን፤ ወይም “ትንሿ ቤት” በመባል ከምትታወቀው ቤት ሌሎችንም ድምጻውያን አሰባስቦ በከፈተው ሮያል ፓላስ በጋራ ሠበሰባቸው።

በወቅቱ በቤቱ ከእነሱ በተጨማሪ ድምጻዊ አበበ ተካ፣ ሂሩት (ሳንቡቃ)፣ ኪቦርዲስት ጸጋቸውና ሌሎችም ነበሩ። የታደለና የብርሃኑ ትውውቅ እንደማንኛውም ሙዚቃን በአንድ የምሽት ክበብ እንደሚሠሩ ሰዎች ነበር። በሂደት መቀራረባቸው ጠነከረ፤ ያኔ ጥብቅ ወዳጅነት መሠረቱ።

በሂደትም የራሳቸውን አድናቂ መፍጠር ቻሉ። አድናቆቱ አድናቆት ብቻ ሆኖ አልቀረም። “ለምን የራሳችሁን ቤት አትከፍቱም፤ የራሳችሁን ቤት ክፈቱ” እያሉ የሚመክሩም የሚያደፋፍሩም አድናቂዎች ተፈጠሩ። ይህንን ሃሳብ በውስጣቸው በሚያውጠነጥኑበት ወቅት ኪቦርዲስታቸው የነበረው ጸጋቸው “ሙን ላይት” የሚባል ቤት ሄዶ ሙዚቀኞቹ ሙዚቃን፤ ምግብ ቤቱ ምግብና መጠጥን እንዲያቀርቡና ገቢውን እኩል እንዲካፈሉ ሃሳብ አቀረበላቸው። በሃሳቡ እነብርሃኑምም ሆነ የሙን ላይት ባለቤቶች ተስማሙ። ታዲያ ቤቱ በነበረው ሥም ከሚቀጥል፣ ለምን ብርሃኑ በታወቀበት “ላፎንቴን” አይጠራም በሚል ሃሳብ የክለቡ ሥያሜ “ላፎንቴን” ሆነ።

ታደለና ብርሃኑ በክለቡ ቆየት ያሉ ዘፈኖችን በመዝፈን ይበልጥ ተፈላጊ ሆኑ። ያኔ ታዲያ የተለያየ አለባበስ ከመከተል ተነስተው አንድ አይነት የአለባበስ ስታይል መከተል ብሎም በሀገራችን ባልተለመደ መልኩ በጠባቂ (ጋርድ) መንቀሳቀስ ጀመሩ። ከምሽት ክለቦች በተጨማሪም የኤግዚቢሽን አድማቂም ሆነው ነበር።

በእነዚህ መድረኮች በሚያዜሟቸው ቆየት ያሉ ዘፈኖች ተወዳጅነትን አግኝተዋል። ያኔ ታዲያ በምሽት ክለቦችም ሆነ በኤግዚቢሽን ማእከል የሚጫወቷቸው ዜማዎች የቆዩ ከመሆናቸው አንጻር አይገኙምና “ለምን በካሴት አታወጧቸውም?” የሚል አስተያየት በረከተ።

በ1988 ዓ.ም ፈላጊማ ካለ በማለት ይመስላል “ተው አምላኬ” ሲሉ የሰየሙትን የመጀመሪያ አልበማቸውን ከሚጫወቷቸው ቆየት ያሉ ዜማዎች መሃል በመምረጥ አወጡ። አልበም ከማውጣታቸው አስቀድሞ በርካታ አድናቂዎችን ማፍራት ችለው ነበር። ለዚህም ይመስላል የመጀመሪያ አልበማቸውን ሲያወጡ በኤግዚቢሽን ማእከል “ተደናቂነትን ያተረፉት ላፎንቴኖች” የሚለው ሀረግ የአልበማቸው ማስታወቂያ የሆነው።

ላፎንቴኖች ሁሌ የተለየ ነገር ማድረግ መለያቸው ነው። “እንድች እንድች” የተሰኘው ሁለተኛ አልበማቸው ሲወጣ የአልበሙ ፖስተር ላይ ከታደለና ከብርሃኑ መሃል ድንክ ውሻ ነበረች። ሦስተኛ አልበማቸው ሲወጣ እውነተኛ አንበሳ ማካተት ቢሳናቸው ፖስተሩ ላይ በኤዲቲንግ አንበሳ አስገብተዋል። ላፎንቴኖች በሚለብሱት የተለየ ተመሳሳይ ልብስ እንዲሁም በሚያደርጓቸው ተለቅ ያሉ ጫማዎች፣ በሚያደርጓቸው መነጽሮች፣ በሚይዟቸው ከዘራዎች ብቻ በሁሉ ነገራቸው የተለዩና አርቲስት መሆናቸውንና ለመድረክ ያላቸውን ክብር የሚያስታውቅ ነው።

“እንድች እንድች” የተሰኘውና በ1991 ዓ.ም ያወጡት ሁለተኛ አልበማቸው ላፎንቴን የሚለውን ሥም ከብዙሃኑ ጋር ያስተዋወቀ አልበማቸው ነው። የአልበሙን መውጣት ተከትሎ በአሜሪካና በአውሮፓ የሚገኙ በርካታ ሀገራት በመዘዋወር ሥራቸውን የማቅረብ እድል ተፈጥሮላቸዋል። የአልበሙ መጠሪያ የሆነው “እንድች እንድች” እስካሁንም ተወዳጅ ሙዚቃቸው ነው።

እንድች እንድች

ሰላም ውለን ካደርን

ሆነን ጤና

በቃ ከዚህ ሌላ

ምናለና

ምስጋና ይድረሰው

ላምላካችን

ፍቅር ይስጠን

ጤና ይስጠን

ለሁላችን

እንጫወት እንደሰት

ሕይወት ያልፋል እንደዘበት

ተጫወቱ ተደሰቱ

ሕይወት ያልፋል እንደዋዛ

በየለቱ

“እጅ አንሰጥም” የተሰኘው ሦስተኛ አልበማቸው ላይ እጅ አንሰጥም፣ እናት ኢትዮጵያ (ባዴ ባዴሳ) የሀገሬ ሰው፣ መለየትሽ ክፉ፣ ናፈቅኋት ድሬን፣ ኧረ እንዴት፣ ልጅነቴ፣ ባባሁልሽ፣ ሠላሜ፣ አቤቱ ድንቡሼ፣ የሚሉትና ሌሎችም ሙዚቃዎች ተካተዋል።

ከኔም ከሱጋር ሆነሽ

ሁሌ አንድ ላይ ሆነሽ

የምትኖሪው ኑሮ

እቱ እንደምን ደስ አለሽ

አንዱን ለግልሽ ይዘሽ

መኖሩ ይሻልሻል

ከዚም ከዛም ማለት ግን

ኋላ አንችን ይጎዳሻል ….

ማየት መልካም

ሁሉን እይው

ግን በትዳር

ቀልዱን ተይ

ዘፈናቸው እያዋዛ ጥሩ መልእክት የሚያስተላልፍና ተወዳጅ ሥራቸው ከሆኑት ውስጥ ተጠቃሽ ነው። አራተኛ አልበማቸው የሆነው ባቡሬ (ጓደኛ) እሱም ከቀደሞዎቹ የበለጠ ተወዳጅ ሆኖላቸዋል። በአልበሙ ላይ ጓደኝነት ሲሉ፡-

ለታደለውማ

ብርሃን ነው ጓደኛ

ካገናኘም አይቀር

አምላክ መርጦ

ልክ እንደኛ

ጓደኛ

ሲሉ በሥማቸው ስለጓደኝነታቸው አዚመዋል። ላፎንቴኖች እድል ላላገኙ ታዳጊ ድምጻውያን እድል በመስጠት የሚያህላቸው የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። አብሮ በመሥራት ያምናሉ፤ በርካታ እድል ያላገኙ ታዳጊዎችን በብቃታቸው በመተማመን እድል በመስጠት አብረው ሠርተዋል። ለአብነትም ቴዲ አፍሮ፣ ጆኒ ራጋ፣ ዘሪቱ ከበደ፣ ሳንፎርድ፣ ትእግስት በቀለ፣ ማሚላና ኪቺኒ፣ ቶክቻው በሙዚቃው ዓለም ከመታወቃቸው በፊት አብረዋቸው ከሠሩት መሃል ተጠቃሽ ናቸው።

ቆየት ባሉት ጊዜያት ተለያይተዋል፣ ግሩፑ ፈርሷል የሚል ወሬ በተደጋጋሚ ሲሰማ ቢቆይም፤ እነሱ ግን የ20ኛ ዓመት በዓላቸውን ብርሃኑ መኖሪያውን አድርጎ በነበረበት፤ በርካታ ባልደረቦቻቸውና አድናቂዎቻቸው በተገኙበት አሜሪካ ማክበራቸው ይታወሳል።

ጓደኝነታቸውን ሲገልጹ “ከጓደኝነት አልፈናል” ይላሉ። ከጓደኝነትም በላይ የልጆቻቸው ክርስትና አባት ሆነዋል። ብርሃኑ 25 ዓመት በጓደኝነት ለመዝለቃቸው ሚስጥሩን ሲናገር “መቻቻል” እና “በጎደለ ሞላ” ይለዋል። ለጓደኝነታቸው መዝለቅ አንዱ የጎደለውን አንደኛው እየሞላ መቆየታቸው መሆኑን ይናገራል።

ከሁለቱ ብርሃኑ ተዘራ ሠዓት በማክበር ሲታወቅ፤ ታደለ ሮባ ደግሞ የለበሷቸውን ልብስና ጫማዎች፣ ፎቶዎች፤ እንዲሁም ሽልማቶች አደራጅቶ በማስቀመጥ ይታወቃል። የወፍጮ ቤት ባለቤት ከሆነው አድናቂያቸው መድረክ ላይ እየዘፈኑ በሁለት አህያ ተጭኖ በነፍስ ወከፍ የመጣላቸው መቶ ኪሎ ጤፍ የማይረሱት ሽልማታቸው ነው። እነሱም መድረኩ ላይ ጤፉን ተደግፈው ዘፈናቸውን አቅርበዋል። ላፎንቴኖች በአብዛኛው በጋራ ቢሠሩም ሲያስፈልግ በተናጠልና ከሌሎች ጋርም በመዋሀድ ይሠራሉ። በዚህ ሂደትም ሁለቱም የግል አልበም አውጥተዋል።

በግላቸው ከሌሎች ጋር በመዋሀድ ከሠሩትና ከተወደዱ የነጠላ ዜማዎቻቸው መካከል ብርሃኑ “ያምቡሌ” ን ከቶክቻው ጋር፣ “አምበሳው አገሳ”ን ከማዲንጎ አፈወርቅ ጋር፣ ከማሚላና ኪቺሊ ጋር “ኤሌ ኤሌ ያባ”ን በጋራ ሠርቷል። በተመሳሳይ ታደለ ሮባ አማርኛና አፋርኛ ቅልቅል የሆነውን “አጋፒዮ” የተሰኘ ዘፈን የአፋርኛ ድምጻዊ ከሆነው ሁሴን ጋር አበርክቷል። “ባቲና ብሉዝ” የተሰኘ ዘፈኑን ከፋንታ በላይ ጋር አቀንቅኗል። ታደለ ሮባ ከድምጻዊነቱም ባሻገር “የብርሃን ፊርማ” ፊልም ላይ በተዋናይነት ተሳትፏል። ከድምጻዊነቱም ባሻገር “ላላ ፕሮዳክሽን” ን በማቋቋም የተለያዩ ድምጻውያንን አልበም ፕሮዲውስ ያደርጋል፤ አልባሳትንም ለገበያ ያቀርባል።

ላፎንቴኖች በግል ቢሠሩም እርስ በእርስ መደጋገፋቸውና ተመልሰው በጋራ መሥራታቸው አይቀርም። ለዚህም በተወደደው በብርሃኑ ተዘራ ነጠላ ዜማ “ያምቡሌ” ሥያሜ የጋራ ቤት በመክፈት ሲሠሩ መቆየታቸው አንዱ ማሳያ ነው። አንዱ ለብቻው ወይም ከሌሎች ጋር በመጣመር ለሠራው ሥራ የመጀመሪያው ደጋፊ የቡድኑ አባል ነው። ላፎንቴኖች በአርቲስቶች ዘንድ ለአርቲስቶች መገናኘት ምክንያት ናቸው ይባላል። እነሱ ካሉ በርካቶች ይሰበሰባሉ፤ ሳቅ ጨዋታው ይደራል። እንዲሁም፣ በአርቲስቶች ኀዘን ወቅት ተገኝቶ ለማጽናናትም ሆነ በደስታ ጊዜ ለማድመቅ የሚቀድማቸው የለም።

ትናንት፣ የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በማሪዮት ሆቴል በርካታ አንጋፋ ድምጻውያን በተገኙበት 25ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓላቸውን በኮንሰርት አክብረዋል። በመድረኩ ከላፎንቴኖችም በተጨማሪ በርካታ አንጋፋ ድምጻውያን ሥራቸውን አቅርበዋል። ላፎንቴኖች ከሁለቱ ጥምረት ባሻገር ከሌሎች ድምጻውያን ጋርም በጋራ በማቀንቀን ይታወቃሉ። እነዚህ አብረዋቸው ያቀነቀኑ ድምጻውያን መድረኩ ላይ አብረዋቸው አዚመዋል። በቀጣይ ከኮንሰርቱ ባሻገር የላፎንቴኖችን የ25 ዓመታት ጉዞ የሚያሳይ መጽሐፍ የማሳተምና ፊልም የማሠራት እቅድ አላቸው።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን  የካቲት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You