ብዙ ሥራ የሚጠብቀው የቆዳ ኢንዱስትሪ

ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ ስለመሆኗ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ታዲያ ከአፍሪካ ቀዳሚ በሆነችበት የቀንድ ከብት ሃብቷ እምብዛም ተጠቃሚ ስትሆን አይስተዋልም፡፡ በተለይም ከቀንድ ከብቶቿ የምታገኘውን ቆዳ በአግባቡ ጥቅም ላይ አይውልም። አሁን ላይ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ፋይዳ ያለው የቆዳ ኢንዱስትሪ ውለታው የተዘነጋ ይመስላል፡፡ ለዚህም በየጥጋጥጉ የሚጣለው ቆዳ ምስክር ሆኖ ይታያል፡፡

በቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በሚስተዋሉ ውስብስብ ችግሮች ምክንያት ቆዳ ለኢንዱስትሪዎች በአግባቡና ጥራቱን በጠበቀ መንገድ መድረስ አለመቻሉ የዘርፉ ዋነኛ ማነቆ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በጥራት ከማዘጋጀት ጀምሮ በተለያዩ ችግሮች እየተፈተነ ያለው የቆዳ ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ በማምጣት የአገር ኢኮኖሚን መደገፍ የሚችል ዘርፍ ቢሆንም በተጋረጠበት ውስብስብ ችግሮች ምክንያት ኢንዱስትሪዎች ቆዳን ከውጭ እስከማስገባት የደረሱበት ጊዜ ስለመኖሩ ይነገራል፡፡

የኢትዮጵያ ቆዳ ጥራት ያለው፣ በዓለም የታወቀና ተፈላጊ ቢሆንም፤ አሁን ባለው ሁኔታ ዘርፉ በእጅጉ ተቀዛቅዟል፡፡ ይህም መንግሥትን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላትን እንዲሁም የአገርን ኢኮኖሚ በብርቱ እየጎዳ ነው፡፡ የቆዳ ኢንዱስትሪው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያጋጠመውን ችግር መፍታት እንዲችልም በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸው ይታወሳል። መንግሥትን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጡ እየተጠየቀ ባለበት በዚህ ጊዜም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች የቆዳ ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ነው የተገለጸው።

የዝግጅት ክፍላችንም በቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ዋነኛ ማነቆ የሆኑ ችግሮች ምን እንደሆኑ፤ መፍትሄዎቹ፤ እንዲሁም በቀጣይ ዘርፉን ለማነቃቃት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በተመለከተ በግብርና ሚኒስቴር የስጋ፣ ቆዳና ሌጦ ዘርፍ ኃላፊ ከሆኑት አቶ አስመላሽ በርሄ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

አቶ አስመላሽ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከዳልጋ ከብቶች ማለትም ከፍየልና ከበግ 31 ነጥብ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ጥሬ ቆዳና ሌጦ ምርት ታገኛለች፡፡ ከዚህ ውስጥም 19 ሚሊዮን ያህሉ ቆዳና ሌጦ አገልግሎት ላይ አይውSet featured imageልም፡፡ ይህ ምርት ወደ ገበያ መግባት ባለመቻሉም በአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ 19 ሚሊዮን ያህሉ ቆዳና ሌጦ አገልግሎት ላይ ቢውል ለሀገሪቱ ከሚያስገኘው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በተጨማሪ የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን ለዜጎች መፍጠር ያስችላል፡፡

ነገር ግን ዜጎች ለቆዳ ኢንዱስትሪው ባላቸው የግንዛቤ ማነስ የተነሳ አገሪቷ ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም። የቆዳ ኢንዱስትሪ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ አንጻር ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱ ቆዳ በየቱቦውና በየመንገዱ ተጥሎ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በአሁን ወቅትም የዘርፉን ችግር በመቅረፍ ሀገሪቷ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።

‹‹በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመፈተሽ ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል›› ያሉት አቶ አስመላሽ፤ በተለይም ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የዘር ችግሮችን በመለየት የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ ወደ ሥራ ከተገባ ለችግሩ መፍትሔ እንደሚመጣ ነው ያመላከቱት፡፡

ለዘርፉ ዕድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የመፍትሔ አቅጣጫ ለመስጠት በፌዴራል ደረጃ እየተሠራ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አስመላሽ፤ ከንግድና ኢንዱስትሪ እንዲሁም ከግብርና ሚኒስቴር የጥናት ቡድን ተዋቅሮ ከጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢና ከሌዘር አምራቾች ማኅበራት ጋር ጥናት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በጥናቱም እንደ ሀገር በሥራ ላይ ከነበሩ ሰባት ሺህ የጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢ ማኅበራት መካከልም አንድ ሺህ ማኅበራት በዘርፉ ባሉ ችግሮች ምክንያት ከገበያ መውጣታቸው ተመላክቷል ነው ያሉት፡፡ ማኅበራቱን ወደ ቀድሞ ሥራቸው በመመለስ ዘርፉን ማነቃቃት የሚያስችሉ ጅምር ተግባራት መኖሩንም ጠቁመዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የግብርና ሚኒስቴር ዘርፉን መደገፍና ማልማት የሚጠበቅበት ሲሆን፤ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም በበኩሉ የገበያ ስርዓቱን በማሻሻል ረገድ የድርሻቸውን ይወጣል ያሉት አቶ አስመላሽ፤ ምርቱን ተቀብሎ ለውጭ ገበያ የማቅረብ፣ የፋብሪካዎችን አቅም የመገንባት፣ የፖሊስ ማሻሻያ እንዲደረግ ግፊት መፍጠርና ሌሎች ስልታዊ ጉዳዮችን ቀርጾ የኤክስፖርት አቅምን የማሳደግ ድርሻ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መሆኑን ነው ያስረዱት ::

በተለይም ገበያው በግብይት ስርዓት መመራት እንዳለበትና ለዘርፉ አስፈላጊ የሆኑ አዋጆችና መመሪያዎች ወደመሬት ወርደው ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸው ሲያስረዱ፤ ‹‹ገበያው ለሁሉም ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ተደራሽ መሆን ሲችል የተሻለ ምርት ያለው የተሻለ ዋጋ ያገኛል›› ነው ያሉት፡፡

ዘርፉ እየተነቃቃ በሚሄድበት ወቅት ሀገሪቷ በዓለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ ድርሻ ይኖራታል ያሉት አቶ አስመላሽ፤ አቅራቢዎችም የተሻለ ቆዳ የማምረት ፍላጎታቸው እንደሚጨምርና በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ተዋናዮችም አስፈላጊውን ጥረት በማድረግ የምርቱ ጥራት እየተሻሻለ የሚሄድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የግንዛቤ ማስጨበጫና የማስተዋወቅ ሥራ ከመሥራት ባሻገር ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊወጣ ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በቆዳና ሌጦ ምርትና ግብይት ላይ ጥናት ያደረጉት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ረሂማ ሙሰማ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ቆዳና ሌጦ ምርቶች የራሳቸው መለያ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ቆዳ በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊ ቢሆንም ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የምርት መጠን እየቀነሰ መምጣቱን ነው የተናገሩት፡፡ ይህም ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የገቢ መጠን ማግኘት እንዳትችል አድርጓታልም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ከዓለም አምስተኛ ከአፍሪካ የመጀመሪያውን ደረጃ ብትይዝም በአሁን ወቅት ቆዳ በየአካባቢው እንደ አልባሌ ነገር እየተጣለ ይገኛል በማለት የገለጹት ተመራማሪዋ፤ ጥናቱ በዋናነት የተከናወነው በቆዳው ዘርፍ የሚስተዋሉ የችግሮች መነሻ ምክንያታቸውን ለመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማመላከት እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቆዳና ሌጦ 80 በመቶው ከአርሶ አደሩ አካባቢ የሚመጣ ሲሆን የተቀረው 20 በመቶው ብቻ በከተማ በሚገኙ ቄራዎች የሚቀርብ በመሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጥሬ ቆዳ ሌጦ ምርት እየቀነሰ እንደሚገኝ ተመራማሪዋ አስረድተዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የቆዳ ፋብሪካዎች 60 በመቶ ያህሉን ቆዳ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ቢሆንም ጥራቱን የጠበቀ የቆዳ አቅርቦት ማግኘት አልቻሉም፡፡ ይህም በሥራቸው ላይ እንቅፋት እየፈጠረ በመሆኑ ቅሬታ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም ይህን በሚገባ የሚያስተሳስር ሥራ መሰራት ያስፈልጋል፡፡ በተለይም አንድ አንድ የመንግሥት ፖሊሲዎች የቆዳ አቅርቦት ጥራት እንዲቀንስ ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከሌሎች ሀገራት አንጻር ሲታይ የኢትዮጵያ ቆዳና ሌጦ ምርት እየቀነሰ መሆኑ በኢኮኖሚው ላይ ጫና አሳድሯል፡፡ ይሁንና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ ከተቻለና ሀገሪቱ ያላትን በቂ ሀብትና የሰው ኃይል በአግባቡ መጠቀም ከቻለች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ ትችላለች፡፡ ከዚህ አንጻር ዘርፉ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ቀደም ባሉ ጊዜያት ለዘርፉ የተሻለ ትኩረት ይሰጥ እንደነበር ያነሱት ዶክተር ረሂማ፤ በአሁን ወቅት ለዘርፉ ያለው አመለካከት አናሳ መሆን፣ ባህላዊ የዕርድ ስርዓት፣ ለሀገር ውስጥ የቆዳ ምርቶች የዜጎች ፍላጎት ማነስ፣ ግልጽ የገበያ ትስስር አለመኖርና ሌሎች በዘርፋ ላይ የሚታዩ ውስንነቶች ስለመኖራቸው አመላክተዋል፡፡

የምርት ጥራት ችግሮችን መፍታት፣ በዘርፉ ለሚገኙ ባለሙያዎች በቂ ስልጠና መስጠት፣ የገበያ ስርዓቱን ማሻሻልና ማዘመን፣ ለዘርፉ ተቋማት አስፈላጊ ድጋፎችን መስጠት፣ ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን በየወቅቱ በመፈተሽ መፍትሔ መስጠት አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በቆዳ ኢንዱስትሪው ከ30 ዓመታት በላይ የሰሩት አቶ ከበደ አህመድ በበኩላቸው፤ የቆዳና ሌጦ ዘርፍ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ወቅት የስጋ ቦርድ በባለቤትነት ይዞ ይሠራበት እንደነበር አስታውሰው፤ ቀጥሎም የጥሬ ቆዳና ሌጦ ልማት ድርጅት እንዲሁም የቆዳና ጫማ ኮርፖሬሽን የሚባሉ ተቋማት በባለቤትነት መርተውታል፡፡ እነዚህ ተቋማት በወቅቱ ዘርፉን መቀየር ቢችሉም ተቋማቱ መቀጠል ሳይችሉ ቀርተው ከፈረሱበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን እነሱን ሊተካ የሚችልና ሙሉ ቁመና ያለው ተቋም አልተፈጠረም፡፡ በዚህ የተነሳ ዘርፉ ሊዳከም ችሏል፡፡

ስለዚህ ጥሬ ቆዳና ሌጦ በየቦታው የሚወድቅበትን ምክንያት በመለየት ችግሩን መፍታት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ከበደ፤ በተለይም በቆዳ አሰባሰብና ጥራት ላይ የሚሰራ አካል እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ይህን ማድረግ ሲቻል ቆዳ በአግባቡና በጥራት መሰብሰብ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም በዓመት ከ40 ሚሊዮን በላይ ጥሬ ቆዳና ሌጦ መሰብሰብ እየተቻለ ነገር ግን ከ50 በመቶ በታች እየተሰበሰበ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም በዘርፉ ያሉ ተቋማትና የሚመለከታቸው አካላት በመዳከማቸው ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም በዘርፉ ተሰማርተው ከነበሩና 15 ከሚደርሱ የቆዳ ፋብሪካዎች መካከል አብዛኞቹ ችግሩን መቋቋም አቅቷቸው ከገበያው መውጣታቸው የዘርፉን ችግር አመላካች ነው፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ከውጭ የመጡ ኢንቨስተሮች እሴት በመጨመርና የቴክኖሎጂ ሽግግር በመፍጠር የተሻለ ምርት ያመርታሉ ተብሎ ሲጠበቅ ከኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ያልተሻለ ቴክኖሎጂ በማምጣት ያልተገባ ውድድር ውስጥ ገብተዋል፡፡ በተጨማሪም ከሌሎች ሀገራት ቆዳ እያመጡ በመጠቀማቸው የኢትዮጵያ ብራንድ እየወደቀ መጥቷል፡፡ ነገር ግን የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ሊዳብር የሚችለው በራሱ ባለሀብት፣ ባለሙያና ሠራተኛ መሥራት ሲችል መሆኑን ገልጸው፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ያላቸውን ክፍተት በመሙላት ዘርፉን ማሻሻል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም እንደ ወታደር ጫማዎች፣ ቦርሳና ሌሎችም ምርቶች ከውጭ የሚገቡ የነበረ ቢሆንም በአሁን ወቅት ምርቶቹን በሀገር ውስጥ ለመተካት ጥረቶች መደረጉን በበጎ ያነሱት አቶ ከበደ፤ ይህም ቀጣይነት እንዲኖረውና የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ የሚችለው በጥሬ ቆዳ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ሲቻል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

እንደ ባት ጄንዩን ጎት ስኪን፣ ሰላሌ ሽፕ ስኪን፣ አቢሲንያ ሄር ሽፕ ስኪንና ሌሎችም የኢትዮጵያ ቆዳ ብራንድ በመሆን በዓለም ገበያዎች ይታወቃሉ፡፡ ይህን ዕድል በመጠቀም ከጥሬ ቆዳ አሰባሰብ ጀምሮ እስከ ምርት ድረስ በጥራት ለመሥራት ዘርፉ ባለቤት ሊኖረው ይገባል፡፡ ለዚህም ቀድሞ ከነበረው ልምድ በመውሰድ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድና በሌሎች ቦታዎች ተበታትኖ ያለውን የቆዳና ሌጦ ዘርፍ ወደ አንድ ማምጣት ጠቃሚ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች ማኅበር ጸሀፊ አቶ መስፍን ለገሰ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ከ30 በላይ የቆዳ ፋብሪካዎች አሉ ቢባልም በስራ ላይ ያሉት ከስድስት የማይበልጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ቆዳ በየመንገዱና ቱቦ ውስጥ ተጥሎ እየባከነ እንዳለም ያነሳሉ።

እንደ አቶ መስፍን ገለጻ፤ በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁ ማኅበራት የቆዳ እጥረት እንዳለባቸው በተለያዩ ጊዜያት ያነሳሉ፡፡ ነገር ግን ባላቸው አቅም ምርቶችን አምርተው ለገበያ እያቀረቡ ሲሆን፤ ለውጭም ሆነ ለሀገር ውስጥ ሳይባል ጥራት ያለው ምርት ለገበያ ከቀረበ ምርቱ ተፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከንግድ፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከግብርና ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ቡድን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውሮ በሰራው ጥናት ቄራዎች ቆዳን በየበሩ ጥለው እንደሚሄዱ መረዳት መቻሉን አንስተው፤ በቀላሉ ቢታይ ኬንያ፣ ሱዳንና ሌሎች ሀገራት ተመርቶ የሚሄደው የኢትዮጵያ ምርት እጅጉን ተፈላጊ በመሆኑ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር ሆኖ በመስራት የኢትዮጵያ ብራንድ እንዳይበላሽ መጠበቅ አስፈላጊ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን  የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You