ሉዓላዊነትን የገነባው የሰማዕታቱ አፅም

የየካቲት ወር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተለይም በታሪክና ፖለቲካ ጉልህ ሚና ያለው ወር ነው። ከእነዚህ የየካቲት ወር ጉልህ ታሪካዊ ክስተቶች የካቲት 12 የሰማዕታት ቀን እና ዓድዋ በደማቁ የሚታወሱ ናቸው። ዓድዋን በቀኑ ስንደርስ እናስታውሰዋለን።

ለዛሬው ከ87 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ስለተከሰተው የሰማዕታት መታሰቢያና መነሻ ሰበቦቹን እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን እናስታውስ።

ከ49 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት ያህል ከመሩት የኢህአዴግ ግንባር ድርጅቶች አንዱ እና ግንባር ቀደሙ የሆነው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ተመሠረተ።

ከ12 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም በኢትዮጵያ ባህልና ወግ ውስጥ በአደባባይ የማይደፈሩ ወሲባዊ ቃላትን በመጠቀም የሚታወቀው ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር አረፈ። ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ወሲባዊ ቃላትን በመጠቀም ስሙ ተደጋግሞ ይነሳ እንጂ ማኅበራዊና ታሪካዊ ጉዳዮችንም የጻፈ ደራሲ ነው። በግል ሕይወቱ ለየት ያለ ፍልስፍና የሚከተለው ስብሃት ገብረእግዚአብሔር በአስቂኝ ፍልስፍናዊ መልሶቹም ይታወቃል።

ከ28 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 14 ቀን 1988 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፓርላማ ደርግ መጋቢት 28 ቀን እንዲከበር አድርጎት የነበረውን የአርበኞች ቀን በመሻር ሚያዝያ 27 ቀን እንዲከበር ወሰነ።

ከ100 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 16 ቀን 1916 ዓ.ም ኢትዮጵያዊው የመጀመሪያው አፍሪካዊ ‹‹የንግድ ጄት›› አብራሪ የሆኑት ኢትዮጵያዊው ካፒቴን ዓለማየሁ አበበ ተወለዱ።

ከ88 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 16 ቀን 1928 ዓ.ም ደራሲ፣ የሥነ ጽሑፍ መምሕር፣ ገጣሚ እና የተውኔት ጠቢብ ዳኛቸው ወርቁ ተወለደ።

ከ87 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት፤ ከየካቲት 12 ጭፍጨፋ 4 ቀናት በኋላ፣ የካቲት 16 ቀን 1929 ዓ.ም ፀረ ፋሺስት አርበኞቹ እና ሀገር አስተዳዳሪዎቹ የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ አማቾች ራስ ደስታ ዳምጠው እና ደጃዝማች በየነ መርዕድ በፋሺስት ኢጣሊያና በባንዳ ወታደሮች ተገደሉ።

በዚሁ ወደ የካቲት 12 ሰማዕታት ታሪክ እንሂድ።

በ1888 ዓ.ም በዓድዋ ላይ ዓለም አቀፍ ውርደትን የተከናነበው ጣሊያን ለ40 ዓመታት ያህል ያኔ የደረሰበት ሽንፈት ሲያንገበግበው ከኖረ በኋላ በ1928 ዓ.ም በቀሉን ሊወጣ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ መጣ።

እነሆ ከ87 ዓመታት በፊት የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም እንዲህ ሆነ። ከጣሊያን ንጉሣዊ ቤተሰቦች አንድ ልዑል ልጅ በመወለዱ በኢትዮጵያ ድል ያለ ድግስ ተዘጋጅቶ እንዲከበር በጀኔራል ግራዚያኒ ትዕዛዝ ተላለፈ። ዝግጅቱም በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት (በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ቅጥር ግቢ ውስጥ የፋሽስቱ ባለሥልጣናት እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ሁሉ እንዲገኙ ተደረገ።

በዚህ ዝግጅት ላይ ትልቅ የደስታ ስጦታ መዘጋጀቱን አብርሃም ደቦጭ ሰማ። ውሳኔውንም ለበጅሮንድ ለጥይበሉ ገብሬ፣ ለብላታ ዳዲ፣ ለቀኝ አዝማች ወልደዮሐንስ፣ ለደጅ አዝማች ወልደ አማኑኤል እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጓደኞቹ ተናገረ። ጥሪው ከተደረገበት ቦታ ማንም ሰው መሄድ እንደሌለበትም አስታወቃቸው። ዳሩ ግን የፋሽስቱ እንዲህ በሀገራቸው ላይ ደጋሽ እና ጋባዥ መሆን ያላንገበገባቸው ሆድ አደሮች ‹‹ዞር በል ወዲያ›› ብለውት ለመሄድ ወሰኑ። አብርሃምም ለቅርብ ጓደኛው ለሞገስ አስገዶም ከነገረው በኋላ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መከሩ። በዚች ታሪከኛ ቀን የካቲት 12 ከማንም ቀድመው ዝግጅቱ ላይ መገኘት እንዳለባቸውም ወሰኑ።

ከመሄዳቸው በፊትም እንዲህ አደረጉ። በአብርሃም ደቦጭ ቤት ውስጥ የጣሊያንን ባንዲራ በሳንቃ ወለል ላይ አንጥፈው ሚስማር ገደገዱበት። የጣሊያን ፋሽስት ጉዱን አላየ! እዚያ ሽር ጉድ ይላል። አብርሃም እና ሞገስም የልባቸውን በልባቸው ይዘው ወደ ዝግጅቱ ገቡ።

ግራዚያኒም በአዳራሹ እየፈነጠዘ ብሉልኝ ጠጡልኝ ይል ጀመር። አዳራሹ ውስጥ ታድመው ዝግጅቱን ከሚያደምቁ አድር ባዮች ውስጥ ግን፤ የድግሱ ምግብ እሬት እሬት ያላቸው፣ አዳራሹ የፋሽስት ሶላቶ መራገጫ መሆኑ ያንገበገባቸው የሀገር ነፃነት የናፈቃቸው ሁለት ወጣቶች ነበሩ። ሞገስ አስገዶም እና አብርሃም ደቦጭ። ገዳይ ቢያረፋፍድ ሟች ይገሰግሳል እንደሚባለው፤ ግራዚያኒ ከሚገባው በላይ ቅጡን አጣ። በአዳራሹ የታደመውን ሰው እየዞረ ለተወለደው ልጅ ስም እንዲያወጡ ጠየቀ። አድር ባይ ባንዳ ሁሉ ያስደስታል ያለውን ስም ያወጣ ጀመር። አሁን የአብርሃምና የሞገስ ትዕግስት አልቋል። ለማንም የፋሽስት ዲቃላ ማነው ስም የሚያወጣ ተባባሉ። በቃ አሁን ጉድ ሊፈላ ነው! በኪሳቸው ደብቀውት የነበረውን ቦንብ መዥረጥ፣መዥረጥ አደረጉት። ግራዚያኒ ላይ ተወረወረ። ቆስሎም ወደቀ። ለአሸሸ ገዳሜ የታሰበው አዳራሽ ‹‹ዋይ! ዋይ!›› ተባለበት።

የጣሊያን ፋሽስቶች በእልህ እና በብስጭት ከሰላሳ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን በግፍ ጨፈጨፉ። አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶምም ወደ ሱዳን እየሄዱ ሳሉ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተገደሉ። ከዚያ በኋላ እንግዲህ የኢትዮጵያ ቆራጥ አርበኞች ጣሊያንን ከሀገር ለማስወጣት ሴት ወንድ ሳይሉ በዱር በገደሉ መዋጋት ጀመሩ። እነ ሸዋረገድ ገድሌ እና ከበደች ሥዩም ከሴት አርበኞች የሚጠቀሱ ናቸው።

የሞገስ አስገዶምና የአብርሃም ደቦጭ ቁርጠኛ ውሳኔ ብዙ ጀግኖችን ለትግል አነሳሳ። በኋላም ለእናት ሀገራቸው ቆርጠው በተነሱ አርበኞች ትግል የጣሊያን ፋሽስት ጓዙን ጠቅልሎ ከኢትዮጵያ ወጣ። እነዚህ ጀግኖች አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው እነሆ ኢትዮጵያን ብቸኛ አፍሪካዊት ነፃ ሀገር አስብለዋታል።

ጣሊያኖች ደጋግመው የሞከሩት ሙከራ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ከሽፏል። ጣሊያን በ1879 ዓ.ም ዶጋሌ ላይ፣ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ደግሞ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ዓድዋ ላይ ሽንፈትን አስተናግዳለች። ይህ ሁሉ የኢትዮጵያ ድል ነው። በመጨረሻም በየካቲት 12 ሰማዕታት ምክንያት የኢትዮጵያ አርበኞች ዳግም የሀገራቸውን ነፃነት አስጠበቁ። ለዚህም መታሰቢያ ከአምስት ኪሎ ከፍ ብሎ ስድስት ኪሎ ሳይደርስ የሚገኘው የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት ተገነባ።

በጭፍጨፋው ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎችን ለመዘከር የካቲት 12 በብሔራዊ ደረጃ እንዲዘከር በ1934 ዓ.ም ታወጀ። በ1951 ዓ.ም ደግሞ አሁን የምናየው እና 28 ሜትር ርዝመት እንዳለው የሚነገረው የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት እንዲቆም ተደርጓል።

የነገሩን ሥረ መነሻ ካየነው ከዓድዋ በፊትም ቆየት ያለ ነው። አውሮፓውያን የአፍሪካ ሀገራትን ለመቀራመትና የቅኝ ግዛት ለማድረግ ዓይናቸውን ወደ አፍሪካ ያማተሩበት የታሪክ ምዕራፍ ነበር። በወቅቱ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት በአውሮፓውያን እጅ ሲወድቁ፣ ኢትዮጵያን ለመውረር ቀይ ባሕርን ያቋረጠችው ጣሊያን ግን ሳይሳካላት ቀርቷል። በነጮቹ የእርስ በርስ ተባባሪነት ተደጋጋሚ ሴራ ቢሞክሩም ኢትዮጵያ ላይ ግን ሊሠራ አልቻለም።

ይህ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲከሽፍ ቆይቶ በ1888 ዓድዋ ላይ የኢትዮጵያን ገናናነት ከፍ አድርጎ ያሳየው ታላቁ የዓድዋ ድል ተመዘገበ። በጦርነቱም፤ የጣሊያንን ጦር የገጠመው የኢትዮጵያ ሠራዊት ጣሊያንን በማሸነፍ ድል ማስመዝገቡ፣ ድሉ የዓለም ጥቁር ድል ሲባል ጣሊያን የሽንፈት ካባ ተከናንባ የኢትዮጵያን ምድር ለቃ ወጣች።

በዚህ በዓድዋ ሽንፈት ቂም የያዘችው ጣሊያን ከ40 አመታት የሰፊ ዝግጅት በኋላ ተመልሳ በመምጣት ኢትዮጵያን በመውረር ብዙ ኢትዮጵያውያንን ለመስዋዕትነት በመዳረጓ የካቲት 12 የዚያ መስዋዕትነት መታሰቢያ ሆነ። የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንደሚሉት፤ ጣሊያን ለ40 ዓመታት ያህል ከፍተኛ ዝግጅት ስታደርግ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ግን ከፍተኛ መዘናጋት ነበር። በሕዝቦቿ ጀግንነትና አይበገሬነት ድል ማድረግ ተቻለ እንጂ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የነበረው ሁኔታ የታሰበበት አልነበረም።

በተለይም ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ ህልፈት በኋላ የነበረውን የኢትዮጵያ ታሪክ ካየነው ደግሞ እንደ ሰገሌ ዓይነት የእርስ በርስ ጦርነቶችና ሽኩቻዎች የነበሩበት ነው። አልጋ ወራሹ ተፈሪ መኮንን ንጉሠ ነገሥት እስከሚሆኑ ድረስ የነበሩ ሁኔታዎችም ወጣ ገባ ያሉ ነበሩ። ይፋዊው የጣሊያን ወረራ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ መንበረ ሥልጣናቸውን ካረጋጉ በኋላ መሆኑ ግን የተሻለ ሳያደርገው አይቀርም፤ ምክንያቱም ንጉሡ ብዙ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራታቸው ይነገርላቸዋል።

ይፋዊው የጣሊያን ወረራ በተመጀመረ ጊዜ ደግሞ የዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations) የተመሠረተበት ነበር፤ ኢትዮጵያ ለዚሁ ማኅበር ወረራው ተገቢ አይደለም በማለት በንጉሷ በኩል አቤት ብትልም አጋርነት ካሳዩ ጥቂት ሀገራት ውጪ ሰሚ አላገኘችም ነበር።

ይሁንና የዓለም መንግሥታት ማኅበር (league of nations) ከተመሠረተ ከዓመታት በኋላ ጣሊያን በድጋሚ ኢትዮጵያን ለመውረር ጦርነት ጀመረች። በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥትና አርበኞች ሀገርን ላለማስደፈር ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል።

ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የጣሊያንን ድርጊት አዲስ ለተቋቋመው የመንግሥታት ማኅበር ለማመልከት ወደ ውጭ ሀገራት ቢሄዱም ሕግና ሉዓላዊነት በወቅቱ ትኩረት ሊሰጣቸው ስላልቻለ ኢትዮጵያውያን የነፃነት ተጋድሏቸውን አጠናክረው ቀጠሉ ማለት ነው። ስለዚህ የየካቲት 12 ሰማዕታት ጀግኖች እልቂት የዓለም ኢፍትሐዊነትና አድሎ የፈጠረው ጭምር ነው። ምንም እንኳን ኢትዮጵያውያን በጀግንነታቸው ቢኮሩበትም የዓለምን ኢፍትሐዊነት ግን ሲመሰክር ይኖራል።

ለአፍሪካ ሀገራት ቅኝ ግዛት መነሻ የነበረውን የበርሊን ጉባኤ በጥቂቱ እናስታውሰው። ፖርቱጋል በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር 1884 በፖርቱጋል ጥያቄ መሠረት የጀርመን ቻንስለር ኦቶ ቮን ቢስማርክ ዋናውን የምዕራባዊ ሀገሮች ዓለም አቀፋዊ ስብሰባ በመሰብሰብ ጥያቄዎችን በማደራጀት በአፍሪካ ሀገሮች ቁጥጥር ላይ ተወያዩ።

የበርሊን ኮንፈረንስ በተከፈተበት ጊዜ አሥራ አራት ሀገሮች በአምባሳደሮች ተገኝተዋል። በወቅቱ የተወከሉት ሀገሮች ኦስትሪያ ሃንጋሪ፣ ቤልጂየም፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ታላቋ ብሪታንያ፣ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድ፣ ፖርቱጋል፣ ሩሲያ፣ ስፔን፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ ቱርክ እና ዩናይትድ ስቴትስ ነበሩ። ከኅዳር 1884 ጀምሮ ለሦስት ወራት በተካሄደው ውይይት በአውሮፓውያን ታላላቅ ኃይሎች መካከል የስብሰባዎች ስብስብ ነበር። በድርድሩ ውስጥ የተሳተፉት ሀገራት ዋና ዓላማ የአፍሪካን ቅኝ ግዛት ለማስፈፀም ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ነበር።

ከአስራ አራቱ ሀገራት መካከል ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ታላቋ ብሪታንያ እና ፖርቹጋል በወቅቱ የቅኝ ግዛት አፍሪካን ተቆጣጠሩት።

በጉባኤው ጊዜ በአፍሪካ የባሕር ዳርቻዎች የሚገኙት የአውሮፓ ኃያላን ሀገሮች ብቻ ነበሩ። በበርሊን ጉባኤ ላይ የአውሮፓ የቅኝ ግዛት ኃይሎች የአፍሪካን አህጉራት ለመቆጣጠር እየተዋጉ ሁሉ ነበር። ቢሆንም ግን ከመዋጋታቸው ይልቅ ስምምነታቸው በልጦ አፍሪካን ተከፋፍለው ቅኝ ገዝተዋል። የአውሮፓ ቅኝ ገዥ ሀገራትና የአፍሪካ ቅኝ ተገዢ ሀገራት የሚከተሉት ነበሩ።

ታላቋ ብሪታኒያ የኬፕ ኤይ ካይሮን ቅኝ ግዛቶች ለማግኘት የግብፅ፣ የታላቋ ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ (የብሪቲሽ ምሥራቅ አፍሪካ)፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዛምቢያ፣ ዚምባብዌ (ሩዴያ)፣ ቦትስዋና፣ ብሪታኒያ ናይጄሪያና ጋና (ጎልድኮስት) ገዝታለች።

ፈረንሳይ በአብዛኛው ምዕራብ አፍሪካን፣ ከሞሪታኒያ እስከ ቻድ (ፈረንሣዊ ምዕራብ አፍሪካ) እንዲሁም ጋቦንና ኮንጎ ሪፖብሊክ (ፈረንሳይ ኢኳቶሪያል አፍሪካ) ወስዳለች።

ቤልጂየም እና ንጉሥ ሌኦፖል ዲሞክራቲክ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ (ቤልጂየ ኮንጎ) ተቆጣጠሩት።

ፖርቱጋል በምሥራቅና በምዕራብ ሞዛምቢክ ሞዛምቢክን ወሰደች። የጣሊያን ይዞታዎች ደግሞ ሶማሊያ (ጣሊያን ሶማሊላንድ) እና የኢትዮጵያ ክፍል ነበሩ።

ጀርመን በናሚቢያ (ጀርመን ደቡብ ምዕራብ አፍሪካ) እና ታንዛኒያ (ጀርመን የምሥራቅ አፍሪካ) አግኝታለች።

የአንዳንድ አፍሪካ ሀገራት ስሞች በቅኝ ገዥዎቻቸው ስያሜ የወጡ ናቸው። ቅኝ ገዢዎቹ የያዙትን ቦታ የራሳቸውን ሀገር መነሻ ስም ያደርጉታል። በተለይ እንግሊዞች ‹‹ብሪቲሽ…›› እያሉ ይሰይማሉ።

ይህ ሁሉ አፍሪካን የመቀራመት ዘመቻ ነው እንግዲህ ኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ የከሸፈባቸው። ምንም እንኳን የሠሩት ሥራ ዛሬ ድረስ ያበለሻሸው ነገር ቢኖርም፤ ኢትዮጵያ ግን በራሷ ማንነት ብቻ የምትታወቅ የጀግና ሀገር እንዲትሆን አድርጓታል። ይህ የሆነው ደግሞ እንደ የካቲት 12 ዓይነት የሰማዕታት ዋጋ ተከፍሎበት ነው።

ክብር ለጀግኖች ሰማዕታት!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን  የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You