ትኩረት የሚሻው የሴት ተማሪዎች ንጽህና መጠበቂያ ጉዳይ

ማህሌት መኮንን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ናት፡፡ ማህሌት በአንዲት ሴት ላይ የደረሰን አንድ ታሪክ ልታጫውተን ፈቀደች፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- አንዲት ዕድሜዋ ከ14 ዓመት የማይዘል የቤት ሠራተኛ ታዳጊ በምትሠራበት ቤት ውስጥ ቡና እያፈላች ነበር፡፡ ይህች ታዳጊ ከተቀመጠችበት ስትነሳ ልብሷ እና የተቀመጠችበት ወንበር የወር አበባ ደም ነክቶታል፡፡ በቤቱ ውስጥ ከማህሌትና ከታዳጊዋ የቤት ሠራተኛ ውጪ ያሉት ወንዶች ብቻ ነበሩ፡፡ ወንዶቹ ይህን ሲመለከቱ ታዳጊዋን ‹‹አይዞሽ›› ከማለት ይልቅ ተጠየፏት፡፡ ይህን ያስተዋለችው ማህሌት ግን ሞዴስ ገዝታ አጠቃቀሙን ለታዳጊዋ አስረድታ እንዳትረበሽ ብትነግራትም፤ ታዳጊዋ ለረዥም ሰዓት በድንጋጤ እና በሃፍረት ውስጥ ነበረች። ማህሌት ከዚህ የተገነዘበችው ታዳጊዋ ባደገችበት አካባቢ ስለወር አበባ ጉዳይ ማንሳት እንደ ነውር እንደሚቆጠር ነው።

ማህሌት አብረዋት በሚማሩ ሴቶች ላይ ሳይቀር የወር አበባ መደናገጥና ፍርሀት ሲፈጥር እንደታዘበች ትናገራለች። ከዚያም አልፎ ገና ለገና ደም ይነካብኛል፣ ሞዴስ ቶሎ ቶሎ እንዳልቀይር ደግሞ ያልቅብኛል የሚል ስጋት አድሮባቸው እንቅስቃሴያቸው የተገደበ መሆኑንም ተረድታለች፡፡ ያምሆኖ በአንፃራዊነት በከተሞች አካባቢ ያለው አመለካከት የተሻለ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ይሁን እንጂ ይህን የግንዛቤ ክፍተት ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልፃለች።

የወር አበባ ሲመጣ ሴቶች ከሚያስተናግዱት ህመም በተጨማሪ ‹‹ለሞዴስ መግዣ ብር ከማን ልጠይቅ?›› ብለው የሚጨነቁ ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ችግር በከተሞች አካባቢ አለን ብሎ ለማሰብ የሚከብደው አይጠፋም፡፡ ችግሩ በስፋት እንዳለም የተረዳው ብዙ አይደለም፡፡ ሴቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከትምህርት ቤት ይቀራሉ፡፡ መቅረታቸው ስለሚያማቸው ብቻ አይደለም። የንጽህና መጠበቂያ እንደልብ ስለማያገኙ ልብሳቸው ደም እንዳይነካ በመፍራት እንጂ፡፡

የሥነልቦና ተማሪዋ ማህሌት በዚህ ጉዳይ ላይ ቁጭቷን ስትገልፅ፣ ‹‹በጤና ተቋም ውስጥ ኮንዶም በነፃ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን ሞዴስ (ፓድ) በየሱቁ ይሸጣል፤ ይህ በፍፁም ትክክል አይደለም፡፡ ጉዳዩ በደንብ ሊጤን ይገባል፡፡ የወር አበባ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ያለጊዜው ማስቆም አይቻልም ስለዚህ በነፃ መታደል አለበት›› በማለት ትናገራለች፡፡

ወይዘሮ ሀናን አህመድ የሀንስ ዊዝ ኬር መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ናት፡፡ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበረችበት ወቅት የደረሰባትን ነገር በማስታወስ መሰል ታሪኳን አጋርታለች። ወይዘሮ ሀናን በትምህርት ቤት ክፍል ውስጥ እያለች ልብሷ በወር አበባ ደም ተበላሸ፡፡ ሹራቧን ወገቧ ላይ አሥራ ሌሎች እንዳያዩባት ሸፈነችው፡፡ ወደ ቤቷ መሄድን ናፈቀች፡፡ ተሸማቀቀች፡፡ በሀፍረት የሌሎችን ዓይን ላለማየት ‹‹አሞኛል›› በሚል ሰበብ ለሳምንት ከትምህርት ገበታዋ ትቀራለች። በቂ ግንዛቤ ስላልነበራት ብዙ ከባድ ጊዜዎች አሳልፋለች። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለችም ቢሆን አንድ ፓድ ለምን ያህል ጊዜ መጠቀም እንደሚቻል ግንዛቤው ስላልነበራት ለኢንፌክሽን ተጋለጠለች፡፡ እነዚህ ነገሮች ተደማምረው ወደ ትዳር ዓለም ስትገባ ተደጋጋሚ ውርጃ አጋጠማት። በሀኪሞች መውለድ እንደማትችል ተነግሯታል። እርሷ የደረሰባት ችግር እርሷ ላይ ብቻ እንዲቀር ዛሬ ላይ ታሪኳን በማጋራት ግንዛቤ በመስጠት እየሠራች ነው። ደግሞም ታጥቦ ዳግም ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን እያመረተች ትገኛለች፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ሀንስ ዊዝ ኬር ከዳሸን ባንክ ጋር በመሆን ‹‹ማንኛዋም ሴት በንጽህና መጠበቂያ ምርት እጥረት ከትምህርት ገበታዋ መቅረት የለባትም›› በሚል ሃሳብ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መልሶ መጠቀም የሚቻል እንዲሁም ከ12 ወራት እስከ 18 ወራት ድረስ የሚያገለግል የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን በዩኒቨርሲቲ ለሚማሩ አንድ መቶ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ለሁለት ሺ ሴት ተማሪዎች ድጋፍ ተደርጓል፡፡

እንደ ወይዘሮ ሀናን ማብራሪያ፣ ‹‹የታብብ የንጽህና መጠበቂያ እንቅስቃሴ›› ከተማው ላይ ከፍተኛ ትምህርት  ተቋማት ያሉ ተማሪዎችን ለመርዳት ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሚማሩ አብዛኞቹ ተማሪዎች ከክፍለ ሀገር የመጡ ናቸው፡፡ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢ ባለው የሰላም መደፍረስ ቤተሰብ ገንዘብ ለመላክ ይቸገራል። ቢያንስ የፓድ ሃሳባቸውን ለማቅለል ድጋፍ ማድረግ አስፈልጓል። በተጨማሪም ጭንቀታቸውን በማቃለል ትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚግዝ ነው፡፡

የንጽህና መጠበቂያ እጦት በከተማ ደረጃ አለ ብሎ ማሰብ ከባድ ቢመስልም ችግሩን ለማወቅ ወደ ትምህርት ቤቶች ሄዶ መጠየቅ ብቻ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ መረዳት ይቻላል የምትለው ወይዘሮ ሀናን፤ ነገር ግን ችግሩ ብዙ አልተነገረም ብላ ታምናለች፡፡ ጉዳዩ አሳፋሪ እንዳልሆነ እና ተፈጥሯዊ እንደሆነ ለማስረዳት ብዙ መሠራት አለበትም ትላለች፡፡ በቀጣይም የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ ታራሚ ቤት ላሉ ሴቶች ድጋፍ ለማድረግ ተሰናድታለች፡፡ ከዚህ ባሻገር ወደ ትምህርት ቤቶች፣ ተፈናቃዮች፣ የሃይማኖት ተቋማት (ሴት ገዳማውያን) በማቅናት ድጋፍ ለማድረግ እና ለመድረስ እንደምታሠራ ቃል ገብታለች፡፡

እንደ ጀማሪ ድርጅት እስከዛሬ ለ10 ሺ ሴቶች ድጋፍ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ ድርጅቱ ከሚያገኘው ትርፍ አንድ በመቶ በጎዳና ላይ ለሚገኙ ሴቶች የሚያደርስ መሆኑን የጠቆመችው ወይዘሮ ሀናን፣ መንግሥት ከንጽህና መጠበቂያ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ተመልክቶ ቢሠራበት መልካም ነው የሚል ሃሳብ አላት፡፡ አንዲት ሴት ትምህርት ቤት ስትገባ የትምህርት ቁሳቁሶች እንደሚያስፈልጓት ሁሉ የንጽህና መጠበቂም ያስፈልጋታል፡፡ ዋናው ቁምነገሩ ሴቷ እንድትበቃ ማድረግ ነውና ድጋፍ ማድረግ ቢቻል ብዙ ሴቶች ጋር መድረስ ይቻላል በማለትም ሃሳቧን አካፍላለች።

ዶክተር ሰውዓለም ፀጋ በአዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነልቦና የትምህርት ክፍል መምህርት ናቸው። በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው የሥርዓተ ጾታ እና ኤችአይቪ መከላከል ዳይሬክተርም ናቸው፡፡ የወር አበባ ጉዳዩ በቀጥታ ሴቶችን የሚመለከት ቢሆንም ወንዶችንም ያገባቸዋል የሚሉት ዶክተር ሰውዓለም፣ ‹‹የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ የብዙ ነገር እጦት አለበት፣ ለጥናት ሲባል የእንቅልፍ እጦት አለበት፡፡ የገንዘብ እንዲሁም ከሰዎች የመገናኘት (የሶሻል ወርክ ኔትዎርክ) እጦት አለበት ብለን ብንናገር ማጋነን አይደለም፤ የንህጽና መጠበቂያ ቁሳቁስ እጦት ደግሞ ሴት ተማሪዎችን የሚፈትን ነገር ነው›› ይላሉ። በአሁኑ ወቅት ዋጋው እየተወደደ መሆኑን በመግለፅም ተማሪዎችም ለመግዛት ሲቸገሩ እንደሚመለከቱ ይናገራሉ። ስለዚህም መልሶ መጠቀም የሚቻል የንፅህና መጠበቂያ ለሴት ተማሪዎች መሰጠቱን አመስግነዋል፡፡

በዳሸን ባንክ ሴት ሰፖርቲንግ አክተር ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ወይዘሮ እስከዳር አሊ ስለ ድጋፉ ሲናገሩ፤ ባንኩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የተለያዩ ተግባራትን እያደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ከሀንስ ዊዝ ኬር ጋር በመተባበር ለአንድ ሺ ሴት ተማሪዎች በደሴ፣ ኮምቦልቻና ወልዲያ ከተማ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። በተመሳሳይ በመቀሌ እና አክሱም ለሚገኙ አንድ ሺ ሴቶች ድጋፍ ማድረጉን ያስታውሳሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግምታዊ ዋጋው አንድ ሚሊዮን የሚሆን የንፅህና መጠበቂያ ግብአቶችን ለሁለት ሺ ሴት ተማሪዎች ድጋፍ ማድረጉን በመግለጽም፤ ድጋፉ ቀጣይነት እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን የካቲት 14/2016

 

Recommended For You