በልዕለ ሐያሏ አሜሪካ በቴክሳስ ግዛት አንዲት የሁለተኛ ደረጃ መምህርት ህገወጥ ስደተኛ ተማሪ ዎች ከትምህርት ቤት እንዲባረሩ የዶናልድ ትራም ፕን እርዳታ በትዊተር ገጿ መጠየቋን ተከትሎ፤ ትምህርት ቤቱ በምላሹ መምህሯን ከስራ አሰናብቷታል።
ቢቢሲ በድረገጹ እንዳስነበበው ጆርጂያ ክላርክ የተባለችው ይህችው መምህርት በትዊተር ገጿ ባሰፈረቸው መልዕክት “ትምህርት ቤቱ ከሜክሲኮ በመጡ ህገወጥ ስደተኞች ተሞልቷል። ትምህርት ቤቱ ይህንን የሚያጣራ ሰው ሊመድብ ይገባል፤ ተማሪዎቹም ሊባረሩ ይገባል” ማለቷን ተከትሎ፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችና የመብት ተሟጋቾች ትምህርት ቤቱ ኮንትራቷን እንዲያቋርጥ መጠየቃቸውን ተከትሎ የትምህርት ቤቱ ቦርድ እንድትባረር ወስኗል።
በቴክሳስ ግዛት የሚገኝው ይህ ፎርት ወርዝ የተሰኘው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተዳደር በመምህሯ ላይ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ፤ አንድ የስደተኞች መብት ተሟጋች ቡድን መምህሯ “ትምህርት ቤቶቹን ወደ መጠረዢያ ቦታነት የመቀየር ፍላጎት እንዳላት” ገልፆ፤ የትምህርት ቤቱ ቦርድ በወሰደው አፋጣኝ እርምጃም ምስጋናውን አቅርቧል።
“ፎርት ወርዝ ከ86ሺ ተማሪዎች በላይ የሚማሩበት ነው፤ ዋናው አላማችንም ማንኛውም ተማሪ መድልዎና መገለል ሳይገጥመው ተከብሮ የሚማርበት ቦታን መፍጠር ነው” በማለት የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ስለ ውሳኔው ያስታወቀ ሲሆን፤ የትምህርት ቤቱን ውሳኔ የተቃወሙም አልታጡም። ለአብነት ፎርት ወርዝ ሪፐብሊካን የተባለ የሴቶች ማህበር መምህርቷን ደግፎ የትምህርት ቤቱ ውሳኔ ህገ መንግስቱ የሰጣትን የመናገር ነፃነት የጣሰ ነው ብሏል።
የአሜሪካ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በበኩሉ በምንም ሁኔታ ላይ ያሉ ስደተኞች በህዝብ ትምህርት ቤቶች ላይ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብለው እንዲያስተምሩ የደነገገ ሲሆን፤ ትምህርት ቤቶችም የስደተኛ ወላጆችን ስለ ህጋዊነታቸው መጠየቅ አይችሉም። ህጋዊ ባይሆኑ እንኳን ሪፖርት ማድርግ አይችሉም ብሏል።
መምህርቷ ይግባኝ ለመጠየቅ አስራ አምስት ቀናት ያላት ሲሆን፤ መምህርቷ በትዊተር ገጿ ላይ የፃፈችው መልዕክት በይፋ የሚታይ እንዳልመ ሰላትም ለትምህርት ቤቱ አስተዳደር ገልጻለች።
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2011
ሶሎሞን በየነ