በሱዳን ባለፉት ወራት በዳቦ የዋጋ ጭማሬ የተቀሰቀሰው የተቃውሞ ሰልፍ እስከ መፈንቅለ መንግስት የዘለቀ ሲሆን፤ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዘው የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር መሪ ስልጣናቸውን ለሲቪል አስተዳደር አስረክቡ በሚል የሲቪል አስተዳደር በሚፈልጉ ዜጎች ከፍተኛ ተቃውሞ እየደረሰባቸው ይገኛል።
በዚህም በአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች የሲቪል አስተዳደር የሚፈልጉ ዜጎች ለተቃውሞ ሰልፍ በሚወጡበት ወቅት አገሪቱን በማስተዳደር ላይ ከሚገኝው ወታደራዊ መንግስት ጋር ፍጥጫው ቀጥሏል።
የወታደራዊ መንግስቱን ተግባር የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት የአለም መንግስታትና መላው የአለም አገራት ድርጊቱን እያወገዙ ቢገኙም፤ ወታደራዊ መንግስቱ እስከ ሁለት አመት ከመንበሬ ፍንክች አልልም የሚል ምላሽ በመስጠቱ፤ የሲቪል አስተዳደር በሚፈልጉ ዜጎችና በወታደራዊ መንግስቱ መካከል ፍጥጫው ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ወታደራዊ መንግስቱም በሰላማዊ መንገድ ድምጻቸውን ለማሰማት ለሰልፍ አደባባይ የወጡ ንጹሀን የአገሪቱን ዜጎች እየቀጠፈ ይገኛል።
ቢቢሲ በድረገጹ እንዳስነበበው፤ ከተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ጋር ግንኙነት ያለው የሐኪሞች ቡድን እንዳሳወቀው የሟቾቹ ቁጥር 100 መድረሱን ተናግሯል። ብድኑም ሟቾቹ የተገደሉት በዋና ከተማዋ ካርቱም በተቃውሞ ሰልፍ ላይ እያሉ
ነው ብሎ ነበር። እንዲሁም በካርቱም የ40 ሰዎች አስከሬን ከናይል ወንዝ ውስጥ መውጣቱን ብድኑ ጨምሮ ገልፀዋል።
የሱዳን ባለስልጣናት በልዩ ኃይሉ 100 ሰላማዊ ሰልፈኞች ተገደሉ የሚለውን በማስተባበል የሞቱት 46 ብቻ ናቸው ማለታቸውን ቢቢሲ በድረገጹ ይዞት የወጣ ሲሆን፤ የአገሪቱ ባለስልጣናት መጀመሪያ አካባቢ ዝምታን የመረጡ ቢሆንም የጤና ሚኒስትሩ የሟቾቹ ቁጥር 46 ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የሱዳን የተቃዋሚና ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ከሐገሪቱ ወታደራዊ ምክር ቤት የቀረበለትን የእንነጋገር ጥሪ ወደ ጎን በማለት ተቃዋሚዎች ላይማንገላታት፣ እስርና ግድያ እየተካሄደ መነጋገር እንደማይፈልግ አስታውቋል።
በካርቱም የሚኖሩ ዜጎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የሰቀቀን ኑሮ እየኖሩ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፤ የወታደራዊ ምክር ቤቱ ምክትል ኃላፊ ሞሐመድ ሐምዳን ተቃዋሚ ሰልፈኞቹን ለማስቆም ኃይል መጠቀማቸውን አስተባብለዋል። እርሳቸውም አክለው ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ድብቅ አጀንዳ ባላቸው ኃይሎችና በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች አላማቸው ተነጥቋል ብለዋል።
“ቀውስ እንዲፈጠር አንፈቅድም፤ ከአቋማችንም ፈቀቅ አንልም፤ በሐገሪቱ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን መስራት አለብን” ያሉ ሲሆን የወታደራዊ ምክር ቤቱ ምክትል ኃላፊ ሞሐመድ ሐምዳን፤ በአንጻሩ ከካርቱም የሚወጡ በርካታ ዘገባዎች እንደሚገልፁት የአገሪቱ ልዩ ኃይል ዜጎች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ የከተማዋን ጎዳናዎች በመቆጣጠር ሲንቀሳቀስ ያገኟቸውን ንፁኃን ዜጎችን እያንገላታ ነው ተብሏል።
ሱዳን የሲቪል አስተዳደር በሚፈልጉ ዜጎች የተቃውሞ ሰልፍ አማካኝነት ለ30 ኣመት አገሪቱን የመሩት ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሺር ከሰልጣን ከወረዱ በኋላ አገሪቷ እየተመራች የምትገኘው በወታደራዊ ምክር ቤት ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ጃንጃዊድ ሚሊሺያ ተብሎ ይታወቅ የነበረው ይህ ልዩ ኃይል እ.ኤ.አ በ2003 በነበረው የዳርፉር ግጭት ላይ ተሳትፎ ነበር በሚል ክስ ሲቀርብበት መቆየቱ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2011
ሶሎሞን በየነ