አዲስ ዘመን ድሮ

አንጋፋውን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አንባቢያን የእውነት ጠይቀውበታል፤ እየተማሩም አስተምረውበታልና ሁሌም ከአንባቢያን ሃሳብና ጥያቄዎች ላይ ለትውስታ ማቅረባች ከግርምትና ከመዝናኛነት ባሻገር ባለፈው ትውልድና በዛሬው መካከል ያሉትን ልዩነቶችም ጭምር የሚያሳይ ነው:: ቆየት ካሉ የመረጃ ማህደሮች መካከልም ለዛሬ በሦስት ብር ጉቦ 60 ብር የተቀጣው ቪቼንሶ፤ የመጠጥ ሱሰኛ የሆነው ሰካራሙ ውሻ ለራስ ምታቱ አስፕሮ ይውጣል..እና ሌሎችም አካተን አቅርበናል::

ሦስት ብር ጉቦ ሰጥቶ ስድሳ ብር ተቀጣ

ቪቼንሶ ሎምባርዲያ የተባለ የ19 ዓመት ወጣት ለወታደር ኃይሉ ሀብቴ የትራፊክ ፖሊስ ባልደረባ ሦስት ብር ጉቦ በመስጠቱ ተከሶ 60 ብር ተቀጥቷል::

የ29 ዓመቱ ወጣት የትራፊክ ፖሊስ ስለሁኔታው ሲያጫውተን “…የካቲት 23 ቀን እኔ ሲኒማ ኢትዮጵያ አጠገብ ቆሜያለሁ፤ ሰውየው ከምሽቱ 3 ሰዓት ገደማ ይሆናል:: በሴይቼንቶ መኪና ረጅም መብራት እያበራ መጣ:: እንደተለመደው ፊሽካዬን ነፋሁ፤አቆመ:: በረጅም መብራት ይነዳሉና ጥፋተኛ ኖት አልኩት:: ታዲያስ? አለኝ:: የመንጃ ፈቃድዎን ያሳዩኝ አልኩት:: አልሰጥም አለ፤ ስምዎሳ? አልኩት፤ አልነግርም አለኝ:: እንግዲያውስ በመኪናዋ ቁጥር የፍርድ ቤት መጥሪያ ይቀበሉኝ አልኩት::

ስማኝ አለኝ፤ ቪንቼሶ ሎምባርዲያ እኔ አሥመራ በነበርኩበት ጊዜ፤ የአዲስ አበባ ፖሊሶች በገንዘብ እየተደለሉ ይለቃሉ ብለውኛልና የምትፈልገው ስለገባኝ እንካ ሦስት ብር አለኝ:: ወዲያው በአጠገቤ የነበሩትን አንድ የፖሊስና አንድ የወህኒ ቤት ዘበኛ ምስክር ቆጠርኩ::

ልጁ እኮ ገንዘብም የለውም፤ 60 ብር ቢፈረድበት፤ ከአባቴ ዘንድ ለምኜ ላምጣ ብሎ በፍርድ ቤት ትእዛዝ አብሬው ካባቱ ቤት ሔደን ነው ገንዘቡን ያመጣነው:: መንጃ ፈቃድማ ባይኖረው ስንት በተቀጣ ነበር” እያለ አጫወተን::

ቪቼንሶ ሎምባረዲያ አዲስ አበባ አንደኛ ወረዳ ፍ/ቤት ቀርቦ ጥፋቱን ስላመነ፤ የካቲት 29 ቀን 60 ብር መቀጫ ተፈርዶበት ከፍሏል::

(አዲስ ዘመን መጋቢት 4 ቀን 1957ዓ.ም)

5 ሴቶች ገደል ተንዶባቸው ሞቱ

በየረር ከረዩ አውራጃ ግዛት በሉሜ ወረዳ በቆቃ ም/ ወረዳ ግዛት ልዩ ስሙ መልመሌ ከተባለው ቀበሌ 5 ሴቶች በገደል ውስጥ ከሚገኝ ኩሬ ውሃ ሲቀዱ ገደሉ ስለተናደባቸው አምስቱም ሴቶች ሞተዋል::

አደጋው እንደተሰማ የየረር ከረዩ አውራጃ ገዥ፤ አቶ ደምስ ባንጃውና የአውራጃው ፖሊስ አዛዥ ኮሎኔል ኪዳኔ ወልድ ጊዮርጊስ፤ አደጋው ስፍራ ደርሰው ሁኔታውን ተመልክተዋል:: የሟቾቹ አስክሬን እስካሁን በመፈለግ ላይ ነው::

(አዲስ ዘመን የካቲት 13 ቀን 1957ዓ.ም)

አውቶማቲክ የጫማ መወልወያ አዲስ አበባ መጣ

ጫማ በኤሌክትሪክ የሚወለውሉ መሣሪያዎች በቅርቡ አዲስ አበባ ገብተው ሥራቸውን ጀምረዋል:: ለጊዜው የመጡት መሳሪያዎች ሁለት ሲሆኑ ያስመጧቸው አቶ አበበ የሚባሉ የሞዝቮልድ ኩባንያ ባልደረባ ናቸው:: ጫማ መወልወያዎቹ መሣሪያዎች ራሳቸው ቀለም፤ ብሩሽና መወልወያ ያላቸው አውቶማቲክ ናቸው::

(አዲስ ዘመን ጥር 10 ቀን 1957ዓ.ም)

ውሻው እየሰከረ አስፕሮ ይውጣል

ከለንደን፤ የቢራ ሱስ የጠነከረበት ውሻ በቅርቡ ወደ አልኮል መዛወሩን አንድ የእንስሳት ጤና አዋቂ በሰጠው ዜና ለመረዳት ተችሏል::

“ፓትሲ” በመጠጥ ኃይል ይሁን አይታወቅም ዓይኖቹ በደንበኛው አይገለጡም:: ዓይኑን ሲገልጥ በእንቅልፍ ላይ ያለ ይመስላል:: በቀን የሚወስደው መጠጥ ከአራት ፓይንት በላይ ነው:: ጠጪነቱንም ለማስወገድ በቀን የሚወስደው የመጠጥ ብዛት እንዲቀነስ ተድርጎ ነበር:: ግን ሱሰኛነቱ እየባሰበት ሔዷል::

ይህ ውሻ መጠጥ የለመደበትን ጊዜ በትክክል የሚያውቅ ሰው የለም:: ፓትሲ በሌሊት እየተነሣ ድርጎውን በሚያገኝበት መጠጥ ቤት ደጃፍ የመከፈቻው ሰዓት አልደርስ እያለው በየቀኑ ከዚያች ሥፍራ ቆሞ ሲጠባበቅ ይታያል::

የፓትሲ ባለቤት እንደገለጠው ከሆነ፤ ፓትሲ የመጠጥ ሱስ በጣም ስለሚጠነክርበት ጠዋት ጠዋት ራሱን ያመዋል:: ስለዚህ ለራስ ሕመም በየቀኑ ሁለት ሁለት አስፕሪን ይወስዳል ብሏል::

ፓትሲ በመጠጥ ቤቱ እየዞረ የቢራ ድርጎውን እንዲያገኝ ይጮሃል:: ግን አብዝተው እንዳይሰጡት የመጠጥ ቤት ባለቤቶች ተጠይቀዋል::

(አዲስ ዘመን መስከረም 4 ቀን 1957ዓ.ም)

ጥያቄ አለኝ

ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ

*ከአምስቱ የፋንታ ቆርኪዎች አራቱን አግኝቼ ቲ ጎደለችኝ:: ይቺን ቆርኪ ከሌላ ወስጄ ወይም ገዝቼ ባቀርብ ራዲዮኑን ማግኘት አልችልም?

ኃይሌ ፍታዊ(ከአሥመራ)

-መቻል ትችላለህ:: ግን እስካሁን እሷን ያገኘ ሰው የለምና ከየት ታገኛለህ?

*ሀብታሞች የዕድር ገንዘብ ሳይከፍሉ ሲቀሩ የሚጠይቃቸው የለም:: እኔ ግን ደሀ በመሆኔ የእድር አልከፈልክም ብለው ከዕድር አስወጡኝ:: ለምን እንዲህ ያደርጋሉ?

ኃይሉ ተፈራ(ከሂርና)

-ተው ሌላ ጉዳይ ይኖር ይሆናል:: ከሌለ እናንተ የሂርና ሰዎች እባካችሁ እንዲህ አታድርጉ:: ባይሆን የዛሬውን ማሩትና ዳግመኛ አይለምደውም:: አንተም ዓመልህን አሳምረህ የእድርህን ገንዘብ እየከፈልክ ኑር::

*እነዚህ ወፍ ሳይንጫጫ እየመጡ የሚጮሁት ላሊበላ የሚባሉት ሌሊት እየተነሡ ካልጮሁ ይቆመጣሉ ይባላል:: ይህ ነገር እስከምንድረስ እውነት ነው?

ሻለቃ አበራ ታቦር

-እስከመጨረሻው ድረስ ውሸት ነው::

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 4 1961ዓ.ም)

*ስለ ፍቅር ይጠይቁሃል:: የእውነትም የፍቅር ምርኮኞች ከሆኑ ይኸ ሁሉ የወንድና የሴት ጋለሞታ ለምን በዛ?

ስንታየሁ መሰንበት(ከማዘጋጃ ቤት)

-መቼም የፍቅር ዓይነቱ ብዙ ስለሆነ የኔዎቹ ጠያቂዎች የሚይዛቸው እያስወደደ የሚያለያየው ነው:: በዚሁ ላይ እባካችሁ ሰዎች የተዋደድነው ተጠፋፋን የሚለውን ጥያቄያችሁን ተውኝ:: እናንተ የምትተዋወቁት ያልተገናኛችሁ እኔ የት ብዬ እንዳገኝላችሁ ነው?

(አዲስ ዘመን የካቲት 4 ቀን 1962ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን የካቲት 5/2016

 

 

Recommended For You