ሱዳን በከፍተኛ አብዮታዊ ነውጥ ውስጥ ትገኛለች፡፡ አምባገነኑ ጀነራል አልበሽር በከባድ ሕዝባዊ ተቃውሞና ሰልፍ ከስልጣኑ ተገዶ ለቋል። ለሽግግሩ ወታደራዊ ምክር ቤት ወደ መንበረ ስልጣን መምጣት በር ቢከፍትም ዛሬም የሱዳን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ የለየለት አልሆነም፡፡ ወደየት እያመራች ነው? የሚለው ጥያቄ በሀገር ውስጥና በውጭ ጭምር አነጋጋሪና አከራካሪ ሆኗል፡፡
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ዶ/ር መሀሙድ አሱሌማን ደራሲ አምደኛና ብሎገር ነው፡፡ ወቅታዊውን የሱዳን ሁኔታ በጥልቀት ፈትሾታል፡፡ ስጋትና ተስፋ በአቻነት ተፋጠው ቆመዋል ሲል ሱዳን ከውስጥም ከውጭም ሰቅዞ ይዟታል ሲል ያስነበበውን ፅሑፍ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡
በሱዳኑ አብዮት አልበሽር ከስልጣን ከለቀቀ ከሀሙስ ሚያዝያ 19 (አፕሪል 11፣ 2019) ጀምሮ ስድስተኛ ሳምንታችን ላይ ገብተናል፡፡ አሁንም ከወታደራዊው የሽግግር ጁንታ መንግሥት ጋር ድርድሩ ዘግይቷል፡፡ ግልጽነት በጎደለው ድብቅ አጀንዳ በጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሀንና በምክትላቸው መሀመድ ሀምዳን ዳጎሎ አካ ሀሚዳቲ የሚመራው መንግሥት የቀድሞዎቹን ወንጀለኛ መሪዎችና ስርዓቱንም በመከላከል መልሶ እንዲያንሰራራ ለማድረግ ሩጫ መያዙን ዶ/ር መሀሙድ ይገልጻል፡፡
የሱዳን አብዮት ከተጀመረ ወዲህ ወደስልጣን የመጣው የወታደራዊው ሽግግር መንግሥት እስከ አሁን ምንም ዓይነት ትርጉም ያለው የለውጥ ምልክት አላሳየም፡፡ የሱዳንን ሕዝብ አብዮታዊ ተነሳሽነት ለማጥፋት፤የቀድሞውን በሙስናና ብልሹ አሠራር የተዘፈቀውን ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶችና ምልክቶች ይታያሉ።
የአልበሽር ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ በደቡብ ሱዳንና በመላው ሱዳን የዘር እልቂትን ተግባራዊ ያደረገ፤ የሱዳንና የደቡብ ሱዳንን ሕዝብ ከእናት ምድራቸው 1 ሺህ ስኩዌር ማይልስ የለየ ነው፡፡
ከታኅሣሥ እአአ 19 2018 ጀምሮ የኦማር አል በሽር መንግሥት የ30 ዓመታት የአገዛዝ ስርዓት እጅግ ከፍተኛና ከባድ የሆነ የሕዝብ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ ከ200 ሰዎች በላይ ተገድለዋል፡፡ መንግሥት በመስከረሙ የ2013 (እኤአ) አመጽ የሞቱት 85 ሰዎች ናቸው ይላል፡፡ ቀደም ሲል አመጽና ተቃውሞው በካርቱም ብቻ የተወሰነ ነበር። የታኅሣሥ 2018 የሱዳን ሕዝብ አመጽና አድማ በመላው ሀገሪቷ እያስገመገመ ተቀጣጠለ፡፡
ከኤልጌኔይ እስከ ሱዳን ወደብ፤ ከኒያላ እስከ ጥንታዊቷ ሀልፋ ከዚያም ተሻግሮ ሁሉንም የታላቁን ዳርፉር ግዛቶች ኮርዶፋን፤ ማዕከላዊ ገዚራ ፤ ራቅ ያሉትን የሰሜንና የምሥራቅ አካባቢዎችን ይዞ እስከ ካርቱም በመዝለቅ አጥለቀለቀው፡፡ የሱዳን ምድር በአብዮታዊ ማዕበል ተናጠች፡፡ ከዚህ በላይ ዝርዝር መጨመር አያስፈልግም ይላል ዶ/ር መሀሙድ፡፡
ወሳኝ የሆነው የታኅሣሥ 19/2018 (እኤአ) ሕዝባዊ አመጽና ተቃውሞ መገንፈሉን ተከትሎ በበርካታ የሱዳን ከተሞች ታላላቅ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሄዱ፡፡ የሕዝቡ ተቃውሞ እየተቀጣጠለ እየጋመ የሄደበት መሰረታዊ ምክንያቶች ነበሩት፡፡ የገበያ ዋጋ መናርና የኑሮ ውድነት፡፡ በሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ውስጥ የኢኮኖሚው ሁኔታ ማሽቆልቆል፡፡
ዜጎች በባንክ ውስጥ ገንዘብ ካለመኖሩ የተነሳ ከራሳቸው ባንክ አካውንት ገንዘባቸውን ማግኘት አለመቻላቸው ቆስቋሽና ገፊ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ መንግሥት ለደረሰበት የኢኮኖሚ ኪሳራና ዝቅጠት ጉልህ ማሳያና ማረጋገጫ ነው፡፡ የሀገሪቱ ገንዘብ ከሌሎች የውጭ ገንዘቦች በተለይ ከአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነጻጸር የምንዛሪ ደረጃው በከፍተኛ ደረጃ ወርዷል፡፡ በየቦታው የተካሄዱት ብርቱ የተቃውሞ ሰልፎች መሪ ጥያቄ አስቸኳይ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ይደረግ የሚል የነበረ ቢሆንም እስከ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ከስልጣን ይውረድ ድረስ መሸጋገሩን ዶ/ር መሀሙድ በጽሑፉ ያስረዳል፡፡
ኦማር አልበሽርና የሚመራው መንግሥት ስልጣን እንዲለቅ የሚጠይቀው ሕዝባዊ ተቃውሞ በኤልደማዚን በታኅሣሥ 13/2018 ነው የተጀ መረው፡፡ በሰሜን አትባራ ከተማ የነበረው ተቃውሞ ግን የተለየ ነበር፡፡
ይህች ከተማ ለክብሯ ሲባል የብረትና የእሳት ከተማ ተብላ ትጠራለች፡፡ የባቡሮች መጠገኛ ስለሆነች፡፡ ባቡሮችና የሠራተኛ ማሕበራት በሱዳን የሰሜኑ ክፍል ስለሚገኙ በታኅሣሥ 19/2018 (እ.ኤ.አ) የሕዝቡ ተቃውሞ ገንፍሎ በመውጣቱ የስርዓቱን የናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ ሕንፃ በእሳት አጋዩት፡፡ የተቃውሞው ንቅናቄ እምብርት በመሆን እውቅና አገኙ፡፡
ከዚያን ዕለት ጀምሮ ሕዝባዊ ተቃውሞና አመጹ ልክ እንደ ሰደድ እሳት በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ 30 ከፍተኛና አነስተኛ ከተሞች ተዛመተ። ተቀጣጠለ፡፡ የአልበሽር መንግሥት ሕዝባዊ አመጽና ተቃውሞውን ለማፈንና ለመድፈቅ ኃይል በመጠቀም በእውነተኛ ፤በላስቲክ ጥይትና በአስለቃሽ ጋዝ ለማፈን ብርቱ ጥረት አደረገ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች አመጹ ከተጀመረ ወዲህ ከ40 በላይ ሰዎች ተገድለዋል፤ ከየካቲት 7/2019 ጀምሮ ከ1000 በላይ ሰዎች ታስረዋል፡፡ ለቁጥር የሚያታክቱ ቆስለዋል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ይህንኑ መረጃ ሻባካ ድረገጽ መግለጹን ዶ/ር መሀመድ በጽሑፉ አካተዋል፡፡
የታኅሣሥ 19/2018 የሱዳን ሕዝባዊ አብዮት ለአምስት ወራት ተኩል የቀጠለ ነበር፡፡ እጅግ ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሎበታል፡፡ የዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ቆስለዋል፡፡ ደም ፈሷል፡፡ በእርግጥም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰማእቶች በሀገራቸው ለውጥ ለማምጣት ሲሉ ወድቀዋል፡፡
በጀነራል አብደል ፋታህ አልቡርሀንና በምክትላቸው በቀድሞው የጃንጃዊድ ሚሊሺያ መሪ ጀነራል ሀሜዲቲ በሚመራው የሽግግሩ ወታደራዊ ምክር ቤት ውስጥ በሚገኙ የቀድሞው ስርዓት ርዝራዦች የተነሳ የሕዝቡና የወጣቱ ጥያቄዎች ምላሽ አለማግኘታውን ሕዝቡ በጸጋ ይቀበለዋል ብለን አናስብም ይላሉ ዶ/ር መሀሙድ፡፡
‹‹እኛ የምንጠይቀው የሽግግሩ ወታደራዊ ጁንታ የጊዜውን (የሁኔታውን) ውስብስብነት ተረድቶ ስልጣኑን በሲቪል ለሚመራ መንግሥት እንዲያስረክብ በዚህም ሀገሪቱን ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያዘጋጅ ነው፡፡ እኛ እንደ ሱዳን ሕዝቦች አብዮተኞችና ፖለቲካዊ ድርጅቶች በቀጣዩ ፕሮግራም ላይ መስማማት አለብን፡፡ ይህንንም ሙሉ በሙሉ በከፍተኛ ደረጃ ተግባራዊ እናደርጋለን›› ይላሉ ጸሐፊው፡፡
ታሪክን በማጣቀስ ረገድ የአሁኑ አብዮት በጥቅምት 21/1964 (እኤአ) እና በሚያዝያ 1985 (እኤአ) ከተካሄዱት አብዮቶች የላቀና የበለጠ ትርጉም ያለው ነው፡፡ በቅርቡ ተቃውሞው ከሱዳን አልፎ በመላው ዓለም በሚገኙ የሱዳን ዲያስፖራ አባላት ውስጥ በመስፋፋት በለንደን፤ በዱብሊን፤ በፓሪስ፤ በዋሽንግተን ዲሲ፤ በካይሮ፤ ተካሂዷል፡፡
በግልና በሕዝብ ስብስብ በሱዳን ውስጥ በተካሄደው የሕዝብ አመጽና ተቃውሞ ለተጎዱ፤ ለሞቱ፤ ለታሰሩ የገቢ ማሰባሰብ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በዋነኛነት ብዙዎች የሱዳን ዲያስፖራዎች የእነሱን ሚና የሚመለከቱት በሱዳን ውስጥ ያለውን ድምፅ የማጉላትና ይህም እንዴት አድርጎ መቀጠል እንዳለበት ነው ሲል ሻባካ ድረገጽ ማስፈሩን ዶ/ር መሀሙድ በጽሑፋቸው ይገልጻሉ፡፡
በሱዳን ጉዳይ የተለየ ትኩረት ሰጥተው ከሚከታተሉት ውስጥ ዋሽንግተን ዲሲ እና ከሞስኮ ብላድሚር ፑቲን እንዲሁም ዓለም አቀፉ የሙስሊም ብራዘር ሁድ ንቅናቄ አንጃዎች፤ የቱርኩን ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን እና ኳታርን የመሳሰሉት ይገኙበታል ብለዋል ጸሐፊው፡፡
ሁለቱ የሽግግሩ ወታደራዊ ምክርቤት መሪ ጀነራሎች ‹‹እኛው ሀገሪቱን መምራት አለብን›› የሚል ውሳኔ ላይ ሳይደርሱ አይቀሩም የሚሉ አሉ። በእርግጥም ወቅታዊው የሱዳን ሁኔታ ውስብስብ ነው፡፡ ሁለት ነገሮች ብቻ በመካከላቸው አሉ፡፡ ሦስተኛ መንገድ የለም። ወይ የሲቪል መንግሥት ወይንም እስከወዲያኛው አብዮት ብቻ መሆኑን ጸሐፊው አስምረውበታል፡፡
በሱዳኑ የሽግግሩ ወታደራዊ ምክር ቤት ውስጥ ስላሉ ሁኔታዎች ሌሎች ጭምጭምታዎችም ይሰማሉ፡፡ ጀነራል ያሴር አልአታ ከፖለቲካ ኮሚቴው ስልጣናቸው ተነስተዋል፡፡ በምትካቸው ካባሺ ኦፊሴላዊ ቃል አቀባይና የፖለቲካ ኮሚቴው ሊቀመንበር ሆነዋል፡፡ በዚህም ታቅዶ የነበረው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተጨናግፏል። ጀነራል ሙስጠፋ ሞሀመድ ሙስጠፋ የቀድሞው የወታደራዊ ደህንነት ዳይሬክተር እንዲሁም የሽግግሩ ወታደራዊ ምክርቤት አባል የደህንነትና መከላከያ ኮሚቴው ሊቀመንበር ስልጣናቸውን ለቀዋል።
ዶ/ር አይሻ አል ባስሪ የቀድሞዋ የተባበሩት መንግሥታትና የዩኤን አሚድ ቃል አቀባይ የነበሩ ሲሆን በሱዳን ሕዝብ ላይ የሚሠራውን ሴራ ስለደረሱበት ከዩ ኤን አሚድ በወር ከ20 ሺህ ዶላር በላይ የሚያገኙበትን ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡ በዚህ የሽግግሩ ወታደራዊ ምክር ቤት ሴራ ፊት የሱዳን ሕዝብ ምርጫ የሲቪሉ አልገዛም ባይነትና እምቢተኝነት እንዲሁም ሀገር አቀፍ የሥራ ማቆም አድማ መጥራት ብቻ መሆኑን ምሁራን ይናገራሉ፡፡
ወታደራዊው ጁንታ ስልጣኑን ለሲቪል መንግሥት ወይም ለፖለቲካ ፓርቲዎች የመስጠቱን ሃሳብ ውድቅ አድርጎታል፡፡ ከሳኡዲ አረቢያና ከአረብ ኢምሬት ጋር ያለውን ቁርኝት አጠናክሮአል። ጀነራል ሙሀመድ ሀምዳን ሀምዲቲ ለሳኡዲ አረቢያ ታማኝነቱንና ታዛዥነቱን በስጦታ አበርቷል፡፡ አብዱል ፈታህ አልቡርሀን ደግሞ ሌላውን አብዱልፈታህ ለማግኘት ወደካይሮ ሩጫውን ጀምሯል፡፡
ሀምዲቲ እና አል ቡርሀን እንዲሁም ሳላህ ጎሽ ሱዳንን ለሙስሊም ብራዘር ሁድ አሳልፈው በመስጠት የወደቀና የተዋረደ መንግሥት ሊያደርጓት ጥድፊያ ይዘዋል፡፡ የሱዳን ሕዝብ ሀገሩ በወንጀለኞችና በቅጥረኛ ነፍሰገዳዮች ስር እንድትወድቅ አያደርግም፤በዝምታም አይመለከትም የሚሉ ሃሳቦች ገዝፈዋል፡፡ የሆነ ሆኖ ግን አሁንም ሱዳን በመስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2011
ወንድወሰን መኮንን